Translate

Thursday, October 30, 2014

ሰበር ዜና – ‹‹አቦይ ስብሐት ጎበዝ ነኽ አለኝ›› ያሉት ፓትርያርኩ የማኅበራትን ተጠሪነትና የገንዘብ እንቅስቃሴ በሚመለከተው የሕጉ ረቂቅ ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ተፋጠው ዋሉ

  • ፓትርያርኩ የማኅበራት ገንዘብ ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ገቢ ኾኖ በማእከል ካልተመራ በሚል ከማኅበራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ጋራ የሚቃረን ግትር አቋም ይዘው ውለዋል፡፡
  • አቋማቸው ተቀባይነት ካላገኘ ስብሰባውን ለመምራት እንደሚቸገሩ በመግለጽ ምልአተ ጉባኤን ለማስገደድ ያደረጉት ሙከራ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ጽኑ አቋም ሳቢያ አልተሳካላቸውም፡፡
  • ጉዳዩ ‹‹ከአዲስ አበባ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች ጋራ ብዙ የሠራኹበትና የደከምኩበት ነው፤ በቀላሉ የምተወው አይደለም›› በሚል ከአክራሪነት ጋራ የተገናኘ ጽሑፍ ሲያነቡ ውለዋል፡፡
  • ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ‹አቦይ› ስብሐት ተናገረኝ እንዳሉት፣ ‹‹አንተ ጎበዝ ነኽ፤ ጽናት አለኽ፤ እንዲኽ ዐይነት ፓትርያርክ አይተን አናውቅም፡፡››
ከተጀመረ ስድስተኛ ቀኑን ያስቆጠረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የመጀመሪያ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ በዛሬ፣ ጥቅምት ፲፯ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ሙሉ ቀን ውሎው፣ የ፲፱፻፺፩ ዓ.ም. ሕገ ቤተ ክርስቲያን ለማሻሻል በቀረበውና የልዩነት አቋም በተያዘባቸው የረቂቁ አንቀጾች ላይ ጠንካራ ውይይት ሲያደርግ አምሽቷል፡፡

የማሻሻያ ረቂቁ፣ ባለፈው ዓመት ግንቦት የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ኹለተኛ ዓመታዊ መደበኛ ስብስባ ወቅት አንቀጽ በአንቀጽ ከተወያየበት በኋላ ተጨማሪ እርማትና ማስተካከያ አድርጎ ለአኹኑ ምልአተ ጉባኤ እንዲያደርስ የሠየመው ስድስት አባላት ያሉት የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የሊቃውንትና የምሁራን ኮሚቴ ያቀረበው ነው፡፡
የማሻሻያ ረቂቁንና በኮሚቴው አባላት መካከል የልዩነት አቋም የተያዘበትን ቃለ ጉባኤ ባለፈው ቅዳሜ ከቀትር በፊት ውሎው የተናበበው ምልአተ ጉባኤው፣ ለዛሬ ባሳደረው መሠረት ነው ፓትርያርኩ በአንድ በኩል፣ መላው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በሌላ በኩል ፍጥጫ የተቀላቀለበት ውይይት ሲያካሒዱበት የዋሉት፡፡
የልዩነት አቋሞች የተያዘባቸው ነጥቦች፡-
  • የሊቃነ ጳጳሳትን ተጠሪነት(ዝውውር እና ምደባ)
  • የማኅበራትን ተጠሪነትና የገንዘብ እንቅሰቃሴ ማእከላዊነት
  • የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አመራር የተመለከቱት ይገኙበታል፡፡
ከስድስት የኮሚቴው አባላት መካከል በሦስቱም ነጥቦች ላይ የልዩነት አቋማቸውን በቃለ ጉባኤው ያስመዘገቡት የፓትርያርኩ ልዩ ጸሐፊ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ናቸው፡፡ ልዩ ጸሐፊው ከአምስቱ የኮሚቴው አባላት ተለይተው በያዙት አቋም÷ የሊቃነ ጳጳሳቱንና የማኅበራትን ተጠሪነት ለቅዱስ ሲኖዶሱ የሚያደርጉት የረቂቁ አንቀጾችለፓትርያርኩ ይኹን በሚል እንዲተኩ፤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትም የፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት እንደኾነና በሊቀ ጳጳስ ሳይኾን በፓትርያርኩ እንደሚመራ የሚገልጽ በረቂቁ ያልነበረ አንቀጽ በግልጽ እንዲቀመጥ ተከራክረዋል፡፡ ፓትርያርኩ አቡነ ማትያስም በዛሬው የምልአተ ጉባኤ ስብሰባ የያዙት አቋም ይኸው የልዩ ጸሐፊው ክርክር በሌላ መጽሔት የታየበት፤ ከልዩ ጸሐፊው ጋራም አንድና ያው እንደነበር ተገልጧል፡፡
የኮሚቴው አብላጫ ማለትም አምስቱም አባላት የተስማሙበትና ከርእሰ መንበሩ አቡነ ማትያስ በቀር በመላው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የተያዘው አቋም ደግሞ÷ ከፓትርያርኩ ጀምሮ እያንዳንዱ ሊቀ ጳጳስ፣ ጳጳስና ኤጲስ ቆጶስ ተጠሪነቱ ለቅዱስ ሲኖዶስ እንዲኾን፤ ሊቃነ ጳጳሳትንና ኤጲስ ቆጶሳትን በየሀገረ ስብከቱና በተለያዩ የሥራ ክፍሎች የመመደብ፣ በበቂ ምክንያት የማዘዋወር ሥልጣን የቅዱስ ሲኖዶስ እንደኾነ አጥብቆ የሚሟገት ነው፡፡
በሥራ ላይ የሚገኘው የ፲፱፻፺፩ ዓ.ም. ሕገ ቤተ ክርስቲያንም ይኹን ቀደም ሲል በጥቅምት ፲፱፻፹፬ ዓ.ም. እና በሚያዝያ ፲፱፻፹፰ ዓ.ም. ጸድቀው ያገለገሉት ሕገጋተ ቤተ ክርስቲያን በዚኽ ረገድ ልዩነት የማይታይባቸው ሲኾን ይኸውም ብፁዕ አቡነ ናትናኤል በዛሬው ስብሰባ እንደገለጹት÷ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የኾኑትን ሊቃነ ጳጳሳት የደረጃ እኩልነት፣ የመንፈሳዊ ተልእኮ ምደባና ብቃት፣ በቅዱስ ሲኖዶስ አባልነታቸው ሊያገኙት የሚገባውን ክብርና እምነት የሚያጠይቅ ድንጋጌ በመኾኑ ነው፡፡ ቀኖናው በእኛ ብቻ ሳይኾን በሌሎችም አኃት አብያተ ክርስቲያናት የሚሠራበት በመኾኑ በቤተ ክርስቲያናችንም ተጠብቆ ሊሠራበት እንደሚገባ ተገልጧል፡፡
ስለ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አመራር በሥራ ላይ በሚገኘው የ፲፱፻፺፩ ዓ.ም. ሕገ ቤተ ክርስቲያን÷‹‹እያንዳንዱ ሀገረ ስብከት ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጀምሮ በቅዱስ ሲኖዶስ በተሾመ ሊቀ ጳጳስ ወይም ጳጳስ ወይም ኤጲስ ቆጶስ ይመራል›› ተብሎ የተደነገገ ሲኾን ሕጉን መሠረት አድርጎ በ፲፱፻፺፩ ዓ.ም. ለሦስተኛ ጊዜ ተሻሽሎ የወጣው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ቃለ ዐዋዲ ደንብም ይህንኑ የሚያጸና ነው፡፡ የአሁኑ የማሻሻያ ረቂቅም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሀገሪቱ ርእሰ ከተማ ስለኾነና ከሌሎች አህጉረ ስብከት የሚለይባቸው ልዩ ኾኔታዎች እንዳሉና እነዚኽን ኹኔታዎች ከግምት ያስገባ የተለየ አወቃቀርና የፈሰስ አከፋፈል ሥርዐት እንደሚኖረው ቢያሰፍርም በአንቀጽ ፵፫ ንኡስ ቁጥር ፪‹‹ከአዲስ አበባ ጀምሮ እያንዳንዱ ሀገረ ስብከት በቅዱስ ሲኖዶስ በተሾመ ኤጲስ ቆጶስ ወይም ሊቀ ጳጳስ ይመራል›› ነው የሚለው፡፡
ከስድስቱ የኮሚቴው አባላት አምስቱ፣ በምልአተ ጉባኤውም መላው ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ይህንኑ የሊቀ ጳጳስ(ጳጳስ) አመራር የደገፉ ሲኾን ‹‹የፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት›› ተብሎ በግልጽ ካልተደነገገ በሚል የተለየ አቋም የያዙት ደግሞ ርእሰ መንበሩ አባ ማትያስ ከኮሚቴው አባላትም ልዩ ጸሐፊው ንቡረ እድ ኤልያስ ብቻ ናቸው፡፡
በፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ዋና ጸሐፊነታቸው የሀገረ ስብከቱን ገዳማትና አድባራት ቅጥር፣ ዕድገትና ዝውውር ወትሮም በተካኑበት የአማሳኞች ሰንሰለት የሚቆጣጠሩት ንቡረ እዱ፣ በፓትርያርኩ ዘንድ ስለምን ይህ አቋም እንዲያዝ እንዳደረጉ ግልጽ ነው – ልዩ ጸሐፊው ‹‹የልማት/ልማታዊ ጉብኝት›› በሚሉትና አጥቢያዎቹ ‹‹የኮቴ››እያሉ በሚሣለቁበት የዘረፋ አሠራር እግራቸው በረገጠው ደብር ኹሉ በትንሹ ከ25‚000 ያላነሰ ብር የሚቀበሉበትና የከበሩበት ነውና! አዲስ አበባን የተጧጧፈች የሙስና ገበያ አድርገው የአብያተ ክርስቲያናቱ ቅጽሮች ሳይቀሩ እየተሸነሸኑ ከአንድም የአራት ይዞታዎች ባለቤት የኾኑበት ነውና! በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያን ሀብትና ንብረት አላግባብ የሚዘረፍበት፣ ሕጋዊና መንፈሳዊ አስተዳደር እየተጓደለ ጎጠኝነትና አድልዎ፣ ሁከትና ብጥብጥ ነግሦበት የነበረው የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር አምሳል ናቸውና!
ማኅበራትን በተመለከተ የረቂቁ አንቀጽ ፯ ንኡስ አንቀጽ ፳፬÷ ‹‹በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መንፈሳዊ አገልግሎት ለማበርከት ለሚቋቋሙ ማኅበራት ዕውቅና ይሰጣል፤ የማኅበራቱን መተዳደርያ ደንብ መርምሮ ያጸድቃል፤ ያሻሽላል፤ አስፈላጊ ኾኖ ሲያገኘውም ማኅበራቱን ያግዳል፤ ይሰርዛል›› በማለት ሓላፊነቱንና ተግባሩን የሚሰጠው ለቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡ ይኸው አቋም በማሻሻያ ረቂቁ ላይ ተጨማሪ እርማትና ማስተካከያ አድርገው እንዲያቀርቡ ከተሠየሙት የኮሚቴው አባላት አምስቱ የተስማሙበት ሲኾን ከፓትርያርኩ በስተቀር መላው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትም አቋማቸውን ያሳረፉበት ነው፡፡
ይኹንና ‹‹የኮሚቴው አባላት ማኅበራት ለፓትርያርኩ ተጠሪ እንዲኾኑ 5 ለ1 በኾኑ ልዩነት ተስማምተዋል›› የሚል ከተነበበው ቃለ ጉባኤ የተለየና የተሳሳተ መረጃ ጭምር በንቡረ እዱ የተነገራቸው ርእሰ መንበሩ አቡነ ማትያስ በበኩላቸው፣ የማኅበራት ተጠሪነት ለፓትርያርኩ ይኹን ከማለት አልፈው የማኅበራት ጠቅላላ ገንዘብ ወደ መንበረ ፓትርያርኩ ገቢ ተደርጎ በበጀት እየተፈቀደ የሚያገለግሉበትን ማእከላዊ አሠራር በአቋም አክርረው አስተጋብተዋል፤ ‹‹አቋሜ ይኸው ነው፤ የምትቀበሉ ከኾነ ተቀበሉ›› በሚል ለውይይት በማይመች የስብሰባ አመራርም ምልአተ ጉባኤውን ሲያደክሙት ውለዋል፡፡
ለአገልግሎት በበጎ ፈቃድ የተሰባሰቡ የማኅበራት አባላት የገንዘብ አስተዋፅኦ ለመንበረ ፓትርያርኩ ገቢ እየተደረገ በማእከላዊነት ይንቀሳቀስ ማለት ከማኅበር ሕገ ተፈጥሮአንፃር የማያስኬድ መኾኑን የገለጹት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ፣ በአህጉረ ስብከትና በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ደረጃ እንኳ የሚጠየቀው ፈሰስ እንጂ ጠቅላላ ገንዘብ አለመኾኑን በመጥቀስ አስረድተዋቸዋል፤ ተገቢው አካሔድም በማኅበራት ምንነትና አስፈላጊነት ላይ መተማመን፣ የሚቋቋሙበትንና የሚያሠራቸውን ሕግ ማውጣት፣ ከተፈቀደው አገልግሎታቸው ጋራ በተገናኘ የገንዘብ አጠቃቀማቸውንና የንብረት አያያዛቸውን አግባብነትና ባለቤትነት በሚገባ ለማወቅና በጥብቅ ለመቆጣጠር የሚያስችል ሕግ መደንገግና አሠራሩን መዘርጋት መኾኑን ለፓትርያርኩ ለማስጨበጥም ሲጥሩ ውለዋል፡፡
ከቀትር በፊት በነበረው የስብሰባ ውሎ ‹‹አቋሜ ይኸው ነው፤ የምትቀበሉ ከኾነ ተቀበሉ›› ሲሉ ያረፈዱት ፓትርያርኩ ‹‹ይህንኑ አቋሜን የማትቀበሉ ከኾነ ስብሰባውን ለመምራት እቸገራለኹ›› በማለታቸው ምልአተ ጉባኤው የከረረውን ለማለዘብ የምሳ ዕረፍት አድርጎ ለመመለስ ተነሥቷል፡፡ ከቀትር በኋላ ስብሰባው ሲጀመር ‹‹ስብሰባውን ለመምራት እቸገራለኹ›› ያሉትን ቀይረው ‹‹አቋሜን ካልተቀበላችኹ ወደ ሌላው አጀንዳ እንቀጥል›› ቢሉም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ፣ አጀንዳው የብዙኃኑን አቋም ይዞ መቋጨት እንደሚገባው በማሳሰብ ምልአተ ጉባኤው በጉዳዩ ላይ ውይይቱን መቀጠል እንደሚፈልግ ገልጦላቸዋል፡፡ ማኅበራት ብለው ሲናገሩ ስለማኅበረ ቅዱሳን ማለታቸው ከኾነም የማኅበሩ መተዳደርያ ደንብ ረቂቅ በአጀንዳነት የተያዘ በመኾኑ ራሱን ችሎ በስፍራውና በጊዜው መነጋገር እንደሚገባ ሊያግባቧቸው ሞክረዋል፡፡
ፓትርያርክ አባ ማትያስ ግን ይባሳችኹ ብለው፣ በማኅበራት ዙሪያ የያዙት አቋም ከምልአተ ጉባኤው ስብሰባ በፊት ከአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችጋራ ብዙ ሲሠሩበትና ሲደክሙበት የሰነበቱበት መኾኑን በመግለጽ ‹‹ስንት የደከምኹበት ነው፤ በቀላሉ የምተወው አይደለም›› በማለት ፍርጥም ብለዋል፤ ከዚኽም አልፎ በልዩ ጸሐፊው ንቡረ እድ ኤልያስ እንደተረቀቀ የተዘገበውን ማኅበራትን ከአክራሪነትና አሸባሪነት ጋራ የሚያቆራኝ ጽሑፍ እያነበቡና ጠቅሰው እየተናገሩ ምልአተ ጉባኤውን በርእሰ መንበር ከሚመራ አባት በማይጠበቅ አኳኋን ለመረዳትም ለማስረዳትም የሚያዳግትና ሒደቱን ቅርቃር ውስጥ የሚከት አካሔድ በመከተላቸው የዕለቱ ውሎ ያለአንዳች ውሳኔ ለመቋጨት እንደበቃ ተገልጧል፡፡
በምልአተ ጉባኤው የዛሬው ውሎ፣ የልዩ ጸሐፊው የልዩነት ነጥቦች ሳይጨመሩና ሳይቀነሱ የፓትርያርኩም አቋሞች ኾነው መንጸባረቃቸው፣ አቡነ ማትያስ ሕገ ቤተ ክርስቲያኑንና የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤን ሥልጣንና ተግባር እየጣሱ ለፈጸሟቸው ስሕተቶች በቀጣይም ለሚይዟቸው አቋሞችና ለሚከተሉት አካሔዶች የክፋቱ ሥርና የመለካዊ ምክሩ መተላለፊያ ማን እንደኾነ በማያሻማ ኹኔታ ቁልጭ አድርጎ ለምልአተ ጉባኤው አባላት እንዳሳየ ታምኖበታል፡፡
የልዩ ጸሐፊው ንቡረ እድ ኤልያስ መለካዊ ግብር፣ ርእሰ መንበሩ የሚያስተጋቧቸው ፀረ – ቅዱስ ሲኖዶስና ፀረ – ሕገ ቤተ ክርስቲያን የክፋትና የተሳሳቱ አቋሞች ምንጭና መተላለፊያ በመኾን ብቻ የሚገለጽ አይደለም፡፡ ፓትርያርኩ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱና በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ከከፈቱት ዘመቻ በስተጀርባ አለ ተብሎ እንዲታሰብ የተፈለገውን ኃይል ለማሳሰብና የብፁዓን አባቶችን አቋም ያላላል የተባለ የሥነ ልቡና ጨዎት ዐይነት ነገርም አለበት፡፡
ይህንኑም ፓትርያርኩ ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ጆሮ እንዲደርስ አድርገው እንዳስወሩት፣ ሰሞኑን በአንድ ምሽት ከአቶ ስብሐት ነጋ ጋራ ራት አብረው ተመግበዋል፡፡ በዚኹ የራት መርሐ ግብር ታዲያ አቡነ ማትያስ ‹አቦይ› ስብሐት ተናገረኝ እንዳሉት፣ ‹‹አንተ ጎበዝ ነኽ፤ ጽናት አለኽ፤ እንዲኽ ዐይነት ፓትርያርክ አይተን አናውቅም፡፡››በርግጥ አቶ ስብሐት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱን ‹‹አይረቡም›› ብለው መዝለፋቸውን፤ ማኅበሩንም ‹‹የፖሊቲካ መድረክነት ይታይበታል›› ብለው መፈረጃቸውን ባለመዘንጋት የራሳቸው አቋምና ፍላጎት እንደሚኖራቸው ባንስተውም ይቺ የራት መርሐ ግብር ጨዎት መላ ግን ብዙዎችን ፈገግ ሳታሰኝ አልቀረችም፡፡
የኾነው ኹኖ በሕገ ቤተ ክርስቲያን አተረጓጎም፣ የሊቃነ ጳጳሳትን ተጠሪነት ከምደባቸውና ዝውውራቸው ጋራ እንዳያሻማ አድርጎ በግልጽ መደንገግ÷ የቅዱስ ሲኖዶሱን ልዕልና በፓትርያርኩ ዐምባገነናዊ አመራር ሰጪነት ለመተካት የታሰበውን አካሔድ በማምከን ሥልጣኑንና ተግባሩን ማስከበር መኾኑ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ዘንድ በቂ ግንዛቤ ተይዞበታል፤ በምልአተ ጉባኤው የአጀንዳ ማርቀቅና ማጽደቅ ወቅት እንደተነገረውም ‹‹የማኅበረ ቅዱሳን ጉዳይ የሕዝብ ጥያቄ ኾኗልና›› ማኅበረ ቅዱሳንንይኹን ሌሎች ማኅበራትን በሒደት አዳክሞ የሚያፈራርስ ሳይኾን ትክክለኛ ሚናቸውን የተገነዘበና በጥንካሬ ለማሠራት የሚያስችል ሕግና መተዳደርያ ደንብ እንደሚወጣተስፋ ይደረጋል፤ በመኾኑም የምልአተ ጉባኤው ስብሰባ ነገም ቀጥሎ ይውላል…..

No comments:

Post a Comment