Translate

Friday, October 24, 2014

የቴሌ “አገልግሎት” መስተጓጎል ከሳምንት በላይ አስቆጠረ

"ችግሩ ሙሉ በሙሉ ተቀርፏል" የቴሌኮም ዳይሬክተር

eth telecom

ኢትዮ ቴሌኮም ከ1.6 ቢሊዮን ዶላር የማስፋፊያ ፕሮጀክት ውስጥ የአዲስ አበባ ከተማ የሞባይል ማስፋፊያ መጠናቀቁ ቢገለጽም፣ አገልግሎቱ አሁንም በሞባይል አገልግሎት ላይ የሚታየውን ችግር ሊቀርፍ ባለመቻሉ፣ በተለይ ሰሞኑን ከአገልግሎት ጥራት ጋር በተያያዘ ደንበኞች ምሬታቸውን እየገለጹ ነው፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም በበኩሉ ችግሩ የተከሰተው በተወሰኑ ቦታዎች እንደነበረና በአሁኑ ወቅት ግን ሙሉ ለሙሉ ተቀርፏል ይላል፡፡
በተለይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የከተማዋ የሞባይል ስልክ ተጠቃሚዎች፣ የሞባይል መቆራረጥና የጥሪ መስተጓጎል ከሳምንት በላይ ያስቆጠረ ቢሆንም ባለፉት አምስት ቀናት ግን ችግሩ ይበልጥ መባባሱን አመልክተዋል፡፡

ካለፈው ዓርብ ማምሻውን ጀምሮ በሞባይል ስልኮች ለመጠቀም ከፍተኛ ችግር እንዳጋጠማቸው ጠቅሰዋል፡፡ የሞባይል ጥሪ ቅዳሜና እሑድም ተባብሶ መቀጠሉን ደንበኞች በምሬት ገልጸዋል፡፡ ከጥሪ አገልግሎትም በተጨማሪ በአጭር ጽሑፍ መልዕክትና የሒሳብ መጠየቂያና የቅድመ ክፍያ ካርዶችን ለመሙላት እንኳን አዳጋች ሆኖ ነበር፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አብዱራሂም አህመድ  ሰሞኑን የባሰበትን የሞባይል አገልግሎት መስተጓጎልና መቆራረጥ አምነው፣ ‹‹በአሁኑ ጊዜ ችግሩ ሙሉ በሙሉ ተቀርፏል፤›› በማለት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በተለይ በአራዳ ክፍለ ከተማ አካባቢ የኃይል መቆራረጥ በማጋጠሙ ኦሲኤስ (OCS) የተባለው ኃይል አስተላላፊ ሥራ በማቋረጡ ችግሩ ተፈጥሯል ብለዋል፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ ችግሩ የተስተዋለው የቅድመ ክፍያ አገልግሎት የሚሰጡ (Prepaid) የሞባይል መስመሮች ላይ ነበር፡፡
አቶ አብዱራሂም ይህንን ቢሉም፣ ጥቅምት 11 ቀን 2007 ዓ.ም. ከማለዳ ጀምሮ የጥሪ ችግሩ በሞባይል ስልኮች ላይና በመደበኛ የስልክ አገልግሎቶች ላይ ተስተውሏል፡፡ በተመሳሳይም ችግሩ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በዱከም፣ በቢሾፍቱና በአጎራባች ከተሞች ጭምር መከሰቱን ደንበኞች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
‹‹ኢትዮ ቴሌኮም የሞባይል የማስፋፊያ ሥራዎችን አጠናቅቄያለሁ፤ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን ቀርፌዋለሁ ባለ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ችግሩ በድጋሚ ተከስቷል፡፡ አሁን ደግሞ እንደሚታየው ላለፉት አምስት ቀናት ያህል ጭራሽ ኔትወርኩ ሞቷል፡፡ ወይ አንድ ፊቱኑ ሞባይል የሚባለውን ነገር ቢተውት ይሻላል፤›› ሲል ከቦሌ ወደ መገናኛ በሚጓዝ ታክሲ ላይ ሪፖርተር ያነጋገርነው ተሳፋሪ ገልጿል፡፡
ባለፈው ዓመት መጨረሻ ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ተከናውኗል ያለውን የሞባይል ማስፋፊያ ሥራ ሙሉ ለሙሉ በቻይናው ሁዋዌ ኩባንያ አማካይነት ማከናወኑንና የነበሩት የአገልግሎት ችግሮች መቀረፋቸውን ኢትዮ ቴሌኮም መግለጹ ይታወሳል፡፡ ከመደበኛው የሞባይል ማስፋፊያ በተጨማሪ ‹‹3G›› እና ‹‹4G›› የተባሉት አገልግሎቶች መጠናቀቃቸውንና ለተጠቃሚዎች ዝግጁ መሆናቸውም ጨምሮ አስታውቆ ነበር፡፡ የ‹‹3G›› አገልግሎት የተጀመረ ቢሆንም እስካሁን የ‹‹4G›› አገልግሎት ግን አልተጀመረም፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ከቻይናዎቹ ሁዋዌ እና ዜድቲኢ ኩባንያዎች የ1.6 ቢሊዮን ዶላር የማስፋፊያ ፕሮጀክት ከአንድ ዓመት በፊት ተፈራርሟል፡፡ እስካሁን ግን በስምምነቱ መሠረት የአዲስ አበባው ፕሮጀክት ቢጀመርም፣ መላ አገሪቱን የሚያዳርሰው ግን አለመጀመሩ ይታወቃል፡፡
ሁለቱ የቻይና ኩባንያዎች እያንዳንቸው የ800 ሚሊዮን ዶላር ሥራ የተረከቡ ሲሆን፣ ዜድቲኢ የአዲስ አበባው ፕሮጀክት ሙሉ በመሉ ለተቀናቃኙ ዜድቲኢ መሰጠቱ እንዳላስደሰተው እየተነገረ ነው፡፡ ረዥም ጊዜ የወሰደ ተጨማሪ ውይይት ከመንግሥት ጋር እያደረገ እንደነበር በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወሳል፡፡ በዜድቲኢ ሥራ አለመጀመርና በአዲስ አበባ ተጠናቋል በተባለው ፕሮጀክት በመንግሥትና በኢትዮ ቴሌኮም ላይ የሕዝብ ጥያቄ እየተነሳ ነው፡፡
ባለፈው ዓመት ፓርላማው ጭምር በኢትዮ ቴሌኮም ላይ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ሲነሱበት መቆየቱም ይታወሳል፡፡ በተለይም ከመደበኛ ስብሰባዎች በተጨማሪ የመሠረተ ልማት፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የድርጅቱን ኃላፊዎች በተደጋጋሚ በመጥራት ማብራሪያ መጠየቁና ማሳሰቢያም መስጠቱ ይታወሳል፡፡
አቶ አብዱራሂም አህመድ፣ በተደጋጋሚ ወደ ሕዝብ በመውጣት ድርጅቱን በሚመለከት በሕዝብ የሚነሱ ጥያቄዎችን ምላሽ ለመስጠት በመገናኛ ብዙኃን ብቅ ማለታቸው የተለመደ ቢሆንም፣ ነገር ግን ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ አንዱአለም አድማሴንና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ቀርበው ያለውን ሁኔታ አለማስረዳታቸው የድርጅቱን አጠቃላይ አሠራር ግልጽ እንዳይሆን ተፅዕኖ ማድረጉንና በድርጅቱ አቅም ላይም ብዥታን እየፈጠረ መሆኑን የሚገልጹ አስተያየት ሰጪዎች አሉ፡፡
ሊጠናቀቅ አንድ ዓመት ብቻ በቀረው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን መጨረሻ በአገር አቀፍ ደረጃ የሞባይል ተጠቃሚዎችን ቁጥር 59 ሚሊዮን ለማድረስ የታቀደ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የተጠቃሚዎች ቁጥር 29 ሚሊዮን መድረሱን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ (ምንጭ: ሪፖርተር)

No comments:

Post a Comment