Translate

Wednesday, October 29, 2014

ከሰማያዊ ፓርቲ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተሰጠ መግለጫ

ከሰማያዊ ፓርቲ
በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተሰጠ መግለጫ
ሰማያዊ ፓርቲ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ በሕብረተሰቡ ዘንድ የሚነሱ በርካታ መሰረታዊና ወቅታዊ ጥያቄዎችን ጥያቄዎቹ አድርጎ ሲንቀሳቀስ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ባለፉት ሁለት አመታት ውስጥም ፓርቲያችን በተለያየ መልኩ የተቻለውን ሁሉ በማድረግ እየታገለ በመንግስት ላይ ጫና ለማሳደርና ችግሮች መፍትሔ የሚያገኙበት አቅጣጫ ሲያመለክት ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ የሀገራችን አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ከግዜ ወደ ግዜ እየተባባሱና እየከፉ የመምጣታቸውን ያህል ገዢው ፓርቲ ቆም ብሎ ከማሰብ ይልቅ ወደ ማይወጣው አዘቅት ውስጥ ሀገሪቷን ጭምር እያንደረደራት ይገኛል፡፡ ይህም አልበቃ ብሎ ከዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት ፍፁም በማይጣጣም መለኩ ዜጎችን ለአንድ ሀሳብ ብቻ እንዲገዙ አስገዳጅ መንገዶችን ጭምር በመጠቀም አፋኛ መዋቅሩን በማናለብኝነት እያስፋፋ ይገኛል፡፡ ይህም አልበቃ ብሎ ለማናቸውም አስተዳደራዊም ይሁን ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ሀይልን በመጠቀም ለመደፍጠጥና ለማጥፋት ቆርጦ በመነሳት ፍፁም አምባገነንነቱን ገፍቶበት የበርካቶች ህይወት ተቀጥፏል፡፡
ለዚሁ እንደማሳያም:-

ካለፈው ዓመት የክረምት ወራት መጨረሻ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ዜጎች በተለያየ ዘርፍ በመከፋፈል የግዳጅ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡ በዚህ አስገዳጅ ስልጠናም የምርጫ ቅስቀሳ በሚመስል መልኩ ከህወሓት/ኢህአዴግ ውጪ አማራጭ እንደሌለ ከመስበክ ባለፈም ማናቸውም የተለየ ሀሳብ የሚያራምዱ የህብረተሰብ ክፍሎችን፣ ድርጅቶችንና ግለሰቦችን ፍፁም ስነ ምግባር በጎደለው መልኩ የጥላቻ ዘመቻ በማካሄድ የሃሳብ ልዩነትን የማስተናገድ ፍላጎቱ ሙሉ ለሙሉ የተዳፈነ መሆኑን አሳይቷል፡፡ ለዚህ ህገወጥ እንቅስቃሴ እና ዓላማም ወደ 1 ቢሊየን የሚጠጋ የህዝብ ሃብት ባክኗል፤ እየባከነም ይገኛል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ እነዚህን ስልጠናዎች እጅግ በቅርበት ሲከታተላቸው የቆየ ሲሆን ከጅማሬውም ተቃውሞውን በይፋ ማሰማቱ ይታወሳል፡፡
በሌላ በኩል የሕብረተሰብ የመረጃ ክፍተት ለመሙላት እና ካለበት የፖለቲካ ድብርት ለማውጣትና ለማነቃቃት ሕገ መንግስቱን መሰረት አድርገው ሃሳባቸውን በነፃነት የገለፁ ጋዜጠኞችና የህትመት ውጤቶቻቸው ከገበያ እንዲወጡ በማተሚያ ቤቶች በኩል አስተዳደራዊ ሴራ መስራቱ ሳያንስ ሕገ መንግስቱን በሚፃረር መልኩ በሕትመት ሚዲያዎቹ ባለቤቶች፣ አዘጋጆች፣ በጋዜጠኞቹና ሰራተኞቻቸው ላይ በማስፈራራት ስነ ልቦናዊ ጫና በማሳደር በርካቶች ለስደት ሲዳረጉ ጥቂቶች ደግሞ ለእስር ተዳርገዋል፡፡ ገዢው ፓርቲ ባንድ በኩል ሀሳቡን ለመጫን የግዳጅ ስልጠና እየሰጠ በሌላ በኩል ደግሞ የተለየ ሀሳብን እንዲሁም የህዝብ ብሶትን የሚያሰሙ ጋዜጠኞች ላይ የማሳደድ ዘመቻ መክፈቱ የስርዓቱን መበስበስ እና አፋኝ አምባገነንነትን ብቸኛ አማራጭ አድርጎ መቀጠል መምረጡን ግልጽ አመላካች ነው፡፡
ከላይ ከሰፈሩት ሁነቶች እጅግ የከፋውና እየተባባሰ የመጣው ሌላው ከፍተኛ አደጋ ያዘለ ችግር ደግሞ፤ አስተዳደራዊ እና ፖለቲካዊ ጥያቄ እያነሱ ያሉ የሕብረተሰብ ክፍሎችን በሀይል ለመገዛት ቆርጦ መነሳቱ ነው፡፡ ባሳለፍናቸው ሁለት ወራት ብቻ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ዜጎች በመንግስት ሀይሎች ተገድለዋል - ቆስለዋል - ተሰደዋል፡፡ በኦጋዴን መንግስትን የተቃወሙ ዜጎች ወደ ግጭት እንዲገቡ በሚገፋፋ መልኩ ጥያቄዎቻቸውን በመግፋት በርካታ ዜጎች በመንግስት ሀይሎች ህይወታቸው መቀጠፉ ሳያንስ ሬሳቸው እንኳን ክብር በሌለው ሁኔታ መሬት ለመሬት እየተጓተተ ባደባባይ ሰብአዊ መብት ሙሉ ለሙሉ ተጥሷል፡፡ በጋምቤላም በተመሰሳይ መልኩ የህወሓት ሰዎች መሬት በሕገ-ወጥ መንገድ መቀራመታቸውን የተቃወሙ ዜጎች ወደ ግጭት የተገፉበት እና በርካታ የሰው ህይወት የተቀጠፈበት ሁነት እጅግ አሳዛኝ እና መንግስት የተያያዘው መንገድ ወደ ከፋ ሁኔታ ሀገሪቷን እየወሰዳት ለመሆኑ ማረጋገጫ ነው፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ ከላይ የተዘረዘሩትንና ከዚህ ያልተጠቀሱትን በተለያየ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚፈፀሙትን በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና አስጊ ሁኔታዎች በቅርብ እየተከታተለ ይገኛል፡፡ በተደጋጋሚ እንደተገለፀውም አሁን ካለንበት ሀገራዊ አዘቅት እና አደጋ መውጫው መፍትሔ በቆራጥነት ሀገርን የማዳን ትግል ማካሄድ እንደሆነ ፓርቲያችን በሚገባ ይገነዘባል - ያምናል፡፡ በስልጠናዎቹ ወቅትም ተማሪዎች እና በርካታ የሕብረተሰብ ክፍሎች በብዛት ሲያነሱት የነበረውን ጥያቄና ስሞታም ከግንዛቤ በማሰገባት ጥያቄዎቹ ምላሽ የሚያገኙበትን የትግል አቅጣጫ በተጠናከረና በተጠና መልኩ አሳታፊ አድርጎ ከግብ ለማድረስ በሙሉ ቁርጠኝነት እና አቋም ላይ እንደሚገኝ ያረጋግጣል፡፡
በመሆኑም የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ ከግምት በማሰስገባት መላው የሀገሪቱ ህዝብ፣ በውጪ የምትኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ለሀገር ተቆርቋሪ ተቋማት እንዲሁም በገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ስር ሆናችሁ ለውጥን የምትሹ ወገኖች ሀገራችንን ወደ አደጋ እየወሰዳት ያለውን አፋኝ ስርዓት በቻላችሁት ሁሉ በመቃወምና ከስርዓቱ ጋር ባለመተባበር በብሔራዊ ደረጃ የሚደረገው ትግል አካል እንድትሆኑ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
ጥቅምት 18 2007
ሰማያዊ ፓርቲ
አዲስ አበባ

No comments:

Post a Comment