Translate

Wednesday, August 7, 2013

በፀረ-ሽብር አዋጁ ፓርቲዎች ሊከራከሩ ነው ! ኢህአዴግ፣ መድረክ፣ አንድነት፣ ሰማያዊ ፓርቲዎች ይሳተፋሉ

በዘሪሁን ሙሉጌታ
ከፀደቀ አራት ዓመታት በላይ በማወዛገብ ላይ ያለው የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 ላይ ፓርቲዎች በመጪው ቅዳሜ ክርክር ሊያደርጉ ነው። የክርክር መድረኩን ያዘጋጀው የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ነው።
ተቋሙ በፀረ-ሽብር አዋጁ ላይ እንዲከራከሩ ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ መድረክ አንድነትና ሰማያዊ ፓርቲዎች እንዲሳተፉ ጋብዟል። መኢአድ ግን ለጊዜው ምክንያቱ ባልታወቀ መንገድ በክርክር መድረኩ አለመጋበዙን የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ አበባው መሐሪ ለሰንደቅ ጋዜጣ ገልፀዋል። ባለፈው አርብ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት ፓርቲዎቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ክርክር መድረክ እንዲመጡ በደብዳቤ ጥያቄ ቢያቀርብም፤ አንድነት ፓርቲ በቂ ጊዜ ይሰጠን በማለቱ ትናንት ይደረጋል የተባለው ክርክር ወደ ቅዳሜ እንዲተላለፍ መደረጉን የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሦ ጊዳዳ ተናግረዋል።
መድረክ በክርክር መድረኩ ለመሳተፍ ተወካይ መመደቡን የግንባሩ ሊቀመንበር አቶ ጥላሁን እንዳሻው የገለፁ ሲሆን፤ እስካሁን በክርክር መድረኮች ተጋብዞ የማያውቀው ሰማያዊ ፓርቲ በክርክር መድረኩ ተጋብዟል። ፓርቲውም በሊቀመንበሩ በኢንጂነር ይልቃል ጌትነት እንደሚወከል ታውቋል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሽመልስ ከማል ከፓርቲዎቹ ጋር ስለሚደረገው ክርክር ከሰንደቅ ጋዜጣ ተጠይቀው “ክርክርና ድርድር የተለያየ ነው። መንግስትም ሆነ ኢህአዴግ በፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ለመከራከር ቅድመ ሁኔታ አስቀምጦ አያውቅም። በዚህ መነሻ ጣቢያው በራሱ ተነሳሽነት ወቅታዊና አንገብጋቢ ጉዳዮችን በመለየት የማወያየት ተግባሩን እየተወጣ ነው” ብለዋል።
በፀረ-ሽብር ሕጉ ላይ የሚካሄደውን ክርክርን ተከትሎ “መንግስት የፀረ-ሽብር አዋጁን ሊያሻሽል ነው” እየተባለ የሚነገረውን አስተያየት ከእውነት የራቀ ነው ሲሉ አቶ ሽመልስ አስተባብለዋል።
 
- ሰንደቅ ጋዜጣ 

No comments:

Post a Comment