Translate

Monday, August 19, 2013

ቀዳማዊ ኃይለስላሴና አዲሱ የኢትዮጵያ ሞዴል

(ክፍል አንድ -በጃፋር ሐሰን)

hailes


1930ቹ ዓመታት ለመላው ዓለምና ለኢትዮጵያ አስቸጋሪ ጊዜያት ነበሩ፡፡ የሁለተኛው ዓለም ጦርነት እየተፋፋመ በመጣበት ጊዜ ኢትዮጵያም በእብሪተኞች ወራሪዎች ዓይን ውስጥ ገብታ እንደነበር በታሪክ ይታወቃል፡፡
ወዲያውም አገሪቱ በፋሽስት እጅ ውስጥ ወደቀች የብዙ ሰዎችም ደም ፈሰሰ፣ ለመናገር የሚዘገንኑ እጅግ ብዙ ግፎች በንፁሃን ዜጎች ላይ ተፈፀሙ፡፡ አገሪቱ በፋሽስት እጅ ውስጥ እንድትወድቅ ያደረጓት ምክንያቶች ምን ምን ነበሩ? እነዚያ ታሪካዊ ምክንያቶች ሊታወቁ ይችላሉ እንዴትስ እናውቃቸዋለን፣ ማወቅ ከተቻለ ከእነርሱስ ምን እንማራለን? ታዋቂው ታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ኤርሊችበSaudi Arabia and Ethiopia: Islam, Christianity and Politics Entwined ላይእንዳቀረበው ከሆነ፣ አገሪቱ በፋሽስት ጣሊያን እጅ ውስጥ እንድትሆን ያደረጓት የተለያዩ መሰረታዊ ምክንያቶች ነበሩ፡፡ የሙሶሊኒ ጦር፣ የጦር የበላይነቱን እንዲጨብጥ እናም ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን አገሪቱን በቁጥጥር ውስጥ ለማድረግ ያበቁት ዋና፣ ዋና መሰረታዊና ታሪካዊ እውነቶች በፕሮፌሰሩ መጽሐፉ ውስጥ ተጠቅሰዋል፡፡
በወቅቱ የፖለቲካና የሃይማኖት ፍጥጫዎች በተለይም (ፖለቲካዊ ሃይማኖት ከመንግስት ጋር የፈጠረው ፍጥጫ) በጉልህ ይታዩ ነበር፡፡ የቀዳማዊ ኃይለስላሴ መንግስት ለእነዚህ ፍጥጫዎች ወሳኝ እርምጃዎችና የፖሊሲ ለውጦችን ወስዶ ነበር፡፡ እነዚያን ወቅታዊ ፍጥጫዎችንና ፖለቲካዊ የፖሊሲ ለውጥ እርምጃዎች ማወቅ በአሁኑ ጊዜ እየሆነ ያለውን ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ እንቅስቃሴዎችን እንዴት መገምገም ቀጥሎም መደገፍ ወይንም መቃወም እንዳለብን መጠነኛ ጥቆማዎችን ይሰጠናል፡፡
ሙሶሊኒ፡ የእስልምና አዳኝ!
የፕሮፌሰር ኤርሊች ታሪካዊ የምርምር መጽሐፍ ፋሽስቱ ሙሶሊኒ እራሱን ያቀረበው እንዴት እንደነበር ከዚያም የተከተለውን ፖሊሲ በዝርዝር አቅርቧል፡፡ ታሪኩ በጣም የሚገርም ከመሆኑም በላይ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለዓለም ሁሉ የሚሆን የማንቂያ ደወል ይገኝበታል፡፡ ከታሪኩ እውነታ በመነሳት የቀዳማዊ ኃይለስላሴ መንግስት ከጦርነቱ በፊት የወሰደው የኢትዮጵያ ሞዴል ፖሊሲ ለውጥ አቅጣጫ፣ ጦርነቱ ካከተመ በኋላ የተወሰዱ እርምጃዎች ኢትዮጵያ ለዓለም የምታስተምረው ትልቅ ትምህርት እንዳላት ያሳያል፡፡ ያንን ታሪክ ማወቃችን የምንኩራራበት ሳይሆን ነቅተን ልንጠነቀቅለትና ልንጠብቀው የሚገባን እሴት እንዳለን የሚያሳይ ነው፡፡ ከዚያም “ተቀምጦ የሰቀሉት ቆሞ ለማውረድ ያስቸግራል” የሚለው የአባቶቻችን አባባል በእኛ ትውልድ፣ በእኛው በገዛ እጃችን እንዳይፈፀምና አገሪቱን አዘቅት ውስጥ ከመክተት ስህተት እንድንመለስ ይረዳናል፡፡ ፕሮፌሰር ኤርሊች የጻፈውን ታሪክ በተከታታይ ለማንበብ በተከታታይ ጠቅለል ባለ መልኩ ከሚያስነብበው ከ(አንሰሪን ኢስላምhttp://www.answeringislam.org/amargna/islaminethiopia/islamhistoryinethiopia_ch4.html) አማርኛ ገፅ ላይ ማንበብ ግሩም እይታን ይሰጣል፡፡
ፋሽስት ሙሶሊኒ አገሪቱን ሊወር ዝግጅቱን ባጠናቀቀበት ወቅት ንጉሱ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ የነበሩበትን ጭንቀት ማሰብ እራሱ ያስጨንቃል፡፡ ዘመናዊ ጦር የመዘዘ፤ ከጀርመኑ የናዚ እንቅስቃሴ ጋር የቅርብ የጦር ስምምነትና የርዕዮተ ዓለም ሐሳብ የሚጋራ፤ ከዚህም በላይ የታሪካዊውን የአድዋን ጦርነት ሽንፈት ለመበቀል የተገኘውን አጋጣሚ ከመጠቀም ወደኋላ የማይል ጨካኝ የጠላት ሰራዊት መጥቷል፡፡ ይህ ጠላት ድል ተመትቶ የሚመለሰው እንዴትና በምን መንገድ ነው? ምን ለማድረግስ ይቻላል? እንደዚህ ዓይነቶቹ ጥያቄዎች አገር ለመምራት የተቀመጠን የአገር ባለአደራ ማሳሰብ ብቻ ሳይሆን እንቅልፍን የሚነሱ ጉዳዮች ናቸው፡፡
የኢትዮጵያን መንግስት በከፍተኛ ችግር ውስጥ ከጣሉት መሰረታዊ ችግሮች አንዱ ሙሶሊኒ እራሱን ያቀረበበት አቀራረብ ነበር፡፡ እርሱ እራሱን ያቀረበው የእስላም አዳኝ – በተለይም በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ሙስሊሞች አዳኝ አድርጎ ነበር፡፡ ፕሮፌሰር ኤርሊች ትክክለኛ ጥናት ላይ በተመሰረተ እውነተኛ ታሪክ ግልፅ  ያደረጋቸው ነገሮች የተለያዩ ማስረጃዎችን (የቴሌግራም፣ የጋዜጦችና የተለያዩ ጽሑፎችን የኢትጵያን ጋዜጦችን እና ለስለላ የረቀቀ ስራ ተጠልፈው የተቀዱ የስልክና የቴሌግራም መልእክቶችን ሁሉ በመፈልፈል የተቀናበረ) በመያዝ ነው፡፡ በእርግጥም ፋሽስቱ ሙሶሊኒ እራሱን ያቀረበው በኢትዮጵያ ውስጥ የተጨቆነውን እስልምናን ለማዳን ማለትም “የኢትዮጵያ እስልምና አዳኝ” በማለት ነበር፡፡
“የኢትዮጵያ እስልምና አዳኝ” የሚለው የሙሶሊኒ ፅንሰ ሐሳብ ኢትዮጵያን የእስላም ጠላት አድርጎ በመሳል በረቀቀ መንገድና ቅንብር ለሌላው ዓለም በተለይም ለአካባቢው አረብ አገሮች በሚያሳምን ሁኔታ ቀርቦ ነበር፡፡ አቀራረቡም ከአሁኑ ጊዜ የዋሃቢስቶች እስልምናዊ እንቅስቃሴ በምንም ያልተለየ እና እንደሚከተለው ነበር፡ “ኢትዮጵያ የምትባለው አገር እስልምናን እና ሙስሊሞችን የምታሰቃይ ናት፤ ሙስሊሞችና እስልምና የአገሪቱ ዋና የጀርባ አጥንት ናቸው ነገር ግን ያለአግባብ ተጨቁነዋል፤ እስልምና በኢትዮጵያ ውስጥ ነፃነት ማግኘት አለበት ይህንንም ለማምጣት የምችለው እኔ ብቻ ነኝ የሚል ነበር፡፡” ይህ የሙሶሊኒ ሐሳብ በብዙ የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች በተለይም በሳውዲ አረቢያ መንግስት ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትን አገኘ፡፡ ተቀባይነትን ማግኘት ብቻ ሳይሆን ድጋፍንም ተቀዳጀ፡፡ በመልስ ለእስላም የአማርኛ ድረ ገፅ ላይ “የሙሶሊኒ ግመሎች” በሚል ርዕስ እንደቀረበው ሙሶሊኒ 12,000 ግመሎችን ከሳውዲ አረቢያ እንዲገዛ ተፈቀደለት፡፡ ከዚያም ከባድ የጦር መሳሪያዎችን በአገሪቱ ውስጥ በግመሎቹ በማጓጓዝ በጦርነቱ የበላይነትን ለማግኘት ቻለ፡፡ የዚህ የሙሶሊኒ የእስላም እርዳታ ጦርነት በሳውዲ አረቢያ ጋዜጦች መካከለኛውም ምስራቅ ሚዲያዎች በወቅቱ ጋዜጣ ብቻ በነበረው “በአልጀዚራ”ም ሳይቀር ከፍተኛ የድጋፍ እና የፕሮፓጋንዳ ሽፋን ተሰጠው፡፡
የፋሽስቱ ጣሊያን ጦርነት፣ የማን ጦርነት ነበር?
የሙሶሊኒን ፕሮፓጋንዳና የተካሄደውን ጦርነት የተፈፀመውን ግፍና የንፁሃን ዜጎች እልቂት ወደ ታሪክ ዞር በማለት አንድ ጊዜ ስንመለከት፤ እጅግ ብዙ ጥያቄዎች በአዕምሯችን ውስጥ ይፈጠራሉ፡፡ ከነዚህም መካከል፡ “የጣሊያን ጦርነት የማን እና የምን ጦርነት ነበር?” የሚለው ይገኝበታል፡፡ ከፕሮፌሰር ኤርሊች መጽሐፍ ውስጥ የቀረበው እውነተኛ፤ ገለልተኛና በብዙ ተጨባጭ የምርምር ማስረጃዎች የተደገፈው ታሪካዊ ጽሑፍ እንደሚያሳየው ከሆነ የሙሶሊኒ ጦርነት በኢትዮጵያ ላይ የተደረገ፡-
በአንደኛ ደረጃ፡- “የእስልምና ጦርነት” በተለይም
በሁለተኛ ደረጃ፡- ሳውዲ አረቢያ በእጅ አዙር ኢትዮጵያን የወጋችበት ጦርነት ነበረ ለማለት ሙሉ ለሙሉ ያስደፍራል፡፡ ከዚህም ባሻገር
በሦስተኛ ደረጃ፡- የአገሪቱ የዋሃቢዝም እንቅስቃሴ ደጋፊ ሙስሊሞች አገሪቱን የእስላም አገር ለማድረግ በማቀድ ከፋሽስት ጣሊያን እና ከሳውዲ አረቢያ ጋር በመሆን የተዋጉበት ጦርነት ነበርም ለማለት ያስደፍራል፡፡
ይህንን ሐሳብ በአሁኑ ጊዜ ያሉ አንዳንድ ታሪክን የሚያውቁ አገር ወዳድና በሰላም አብሮ ለመኖር የሚፈልጉ ሙስሊሞች ይስማሙበታል፡፡ በዚህ በኩል በኢትዮ ዛሬ ድረ ገፅ ላይ “ክርስትያኖች አብራችሁን ቁሙ” የሚል ማሳሰቢያ ባለው “የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጥሪ” በሚል ርዕስ የቀረበው ጽሑፍ አንዱ ነው፡፡ በዚያ ጽሑፍ ላይ ጸሐፊው ሰለሞን ተሰማ ጂ ተመሳሳይ እውነቶችን ለማንፀባረቅ ሙከራ አድርጓል፡፡ በመሆኑም ከ1933 ጀምሮ ዋሐቢስቶች መፍጨርጨር እንደጀመሩ ሳውዲ አረቢያም የዋሃቢዝምን እንቅስቃሴ ወደ ባሌና ወደ አሩሲ ውስጥ በበጎ አድራጎት ስም እንዳሰረፀች ጠቃቅሷል፡፡ መዘዘኛዎቹ ሳውዲዎች የጫሩት እሳት በአሁኑ ጊዜ ላለው ችግር ምክንያት እንደሆነም በጽሑፉ ጅማሬ መግቢያ ላይ ጸሐፊው አቅርቧል፡፡ http://www.ethiopiazare.com/articles-55/opinion/2845-ye-ethiopia-muslimoch-tiri-by-solomon-tessema-g
የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ምላሽ – አዲሱ ሞዴል
የሙሶሊኒ አካሄድ በከፍተኛ ሁኔታ ያሳሰባቸው ንጉሱ በዘመኑ ከነበሩት የመንግስት ባለስልጣኖች ጋር የፋሽስቱን እንቅስቃሴ ለመግታት የሚቻልባቸውን ስልቶች ቀይሰዋል፡፡ በመሆኑም በአስቸኳይ ሦስት ገፅታ ያለው እንቅስቃሴ ጀመሩ፣ ከሦስቱ ሁለተኛው ያተኮረው የኢትዮጵያ አስተዳደር ሞዴል ላይ ነበር፡፡ የሙስሊሙን ሕብረተሰብ በኢትዮጵያዊነቱ ስሜት ውስጥ እንዲኖርና አገሪቱ የሁላችንም አገር መሆኗን እንዴት እናሳውቀው? አገሪቱንስ ከጠላት አብረን እንዴት እንከላከላት? የሚሉትና የመሳሰሉት ጥያቄዎች ንጉሱን ቀዳማዊ ኃይለስላሴንና በጊዜው የነበሩትን አማካሪዎች ወደ አዲስ ኢትዮጵያዊ የአስተዳደር ሞዴል ቀረፃ ፅንሰ ሐሳብ አስገብቷቸው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ አዲስ የአስተዳደር ሞደሌ ቀረፃን አስፈላጊ ካደረጉት ምክንያቶች ውስጥ፡
  • የሙስሊሙ ማህበረሰብ በጣሊያን የውሸት  ፕሮፓጋንዳ እንዳይሳብና የገዛ አገሩን እንዳይወጋ፤ ከዚህም የተነሳ ታሪካዊ ጠባሳን በአገሪቱ ላይ እና በማህበረሰቡ ላይ እንዳይጥል፤
  • ጠላትን መመከትና ድልም ማድረግ የሚቻለው አብሮ በመተባበርና በአንድነት መሆኑን ለማሳሰብ፤
  • በአዲሱ የአስተዳደር ሞዴል ኢትዮጵያ የምትባለው አገር በአገሪቱ ውስጥ የሚኖሩት ሕዝቦች ሁሉ የጋራ አገር እንደሆነች፣ ሕዝቦችም ያለ ዘር ልዩነት ያለፆታ ልዩነት እንዲሁም ያለ ሃይማኖት ልዩነት የሚኖሩባት አገር እንደሆነች ለመግልፅ፤
  • በመሆኑም ኢትዮጵያ የምትባለው አገር የክርስትያን ሃይማኖትና የአንድ ጎሳ አገር ብቻ ተብላ በመጠራት ልትቀጥል እንደማትችል በይፋና በግልፅ ያስቀመጠ ፖሊሲ ነበር፡፡
የፋሽስቱ ጣሊያን እንቅስቃሴና ዝግጅት ተግባራዊ ሲሆን በዜጋው ላይ የሚያስከትለው ጉዳት አሳሳቢና ጊዜ የማይሰጠው ስለነበር፤ የኢትጵያን አዲስ አስተዳደራዊ ሞዴል ለማህበረ ሰቡ ለማስረዳትና በተለይም ሙስሊሞችን ለማቀፍ እራሳቸው ንጉሱ ከፍተኛ ጥረትና እንቅስቃሴ አደረጉ፡፡
ስለዚህም ግንቦት 22 ቀን 1935ዓም ንጉሱ በሐረር ከተማ ተገኝተው ለሐረር ሕዝብ በተለይም ለሙስሊሙ ማህበረሰብ ከዚህ አዲስ ሞዴል የተነሳ ኢትዮጵያ የክርስትያን አገር ብቻ ተብላ እንደማትጠራ፣ አገሪቱ የሁሉም ሃይማኖት የሁሉም ሕዝብ ዘር በእኩልነት የሚኖርባት አገር እንደምትሆን ተናገሩ፡፡ ለሁሉም ሃይማኖት የሕገ መንግስት እኩልነት እንደሚኖር ቃል ገቡ፡፡ ሙስሊሙን ማህበረ ሰብ በስጋት ውስጥ ያስቀመጠው ጭንቀት የሃይማኖት ጭቆና ይኖራል የሚለው ስለነበር፣ ሃይማኖት የግል ጉዳይ ሲሆን አገር ግን የጋራ ናት – የሚለው አጠቃላይ መርሆና አባባል እንዲሆንና በሁሉም ውስጥ እንዲሰርፅ ጥረት ተደረገ ከዚህም ጥረት የተነሳ በአገሪቱ በስፋት የሚታወቀው አባባል “አገር የጋራ ነው ሃይማኖት የግል ነው” የሚለው ይፋ ሆነ፡፡
ከዚያም የአዲስ ኢትዮጵያ ሞዴል ማስተዋወቅ በመቀጠልም ሙስሊሞችን ለማቀፍ በሚደረገው አዲስ ጥረት አካል በዳግማዊ ሚኒሊክ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር በነበረው ግብፃዊ ኮፕት አማካኝነት የአረብኛ ጋዜጣ እንዲታተም ፈቀዱ፡፡ በ1904 አፄ ሚኒሊክ ይገነባል በማለት ተስፋ የገቡትን የአንዋር መስጊድን እንዲገነባም ፈቀዱ፡፡
ኢትዮጵያ አዲስ የአስተዳደር ሞዴል የምትከተል መሆኗን ይፋ ያደረገው የዚያ እንቅስቃሴ ውጤት አካልም በመካከለኛው ምስራቅ ባሉ የአረብ አገሮች ሁሉ ውስጥ እንዲታወቅና ኢትዮጵያ አዲስ የአስተዳደር ሞዴል እንደቀረፀች የሚያስረዱና ዲፕሎማቲካዊ ድጋፍን የሚያሰባስቡ ልዑካንም ወደ መካከለኛው ምስራቅ አገሮች ተላኩ፡፡ ዓላማውም ፋሽስቱ ጣሊያን ያቀናበረውን በኢትዮጵያ “የእስልምና አዳኝ”  ተልእኮ ፕሮፓጋንዳውን ማክሸፍና የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ለፋሽስቱ ምንም ዓይነት ድጋፍ እንዳያደርጉ ለማሳሰብ ነበር፡፡
የአዲሱ የኢትዮጵያ ሞዴል ጥረት ውጤቶች፡
አዲሱ የኢትዮጵያ ሞዴልን በአገሪቱ ውስጥ ለማስተዋወቅ የተደረገው ጥረት በጥቂቶች ዘንድ ብቻ ተቀባይነትንና ድጋፍን ያገኘ ሲሆን፣ በአብዛኛው ድጋፍን ባለማግኘቱ የተፈራው የታሪክ ጠባሳ ተከስቷል፡፡ በአገሪቱ ውስጥ 70,000 የሙስሊም ወታደሮች ከጣሊያን ጎን ተሰልፈው ነበር ከእነዚህም መካከል 15,000 የሊቢያ ሙስሊሞች ወታደሮች በሐረር ከተማ በተጠባባቂነት ተመድበው በጦርነቱ ተሳትፈው ነበር፡፡ የአገሪቱ ሙስሊሞች የጣሊያን ታማኞች በመሆን በየቦታው ለስለላና ሌላውን ለመቆጣጠር ተመድበው ነበር፡፡ በጣሊያኖች ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ የተሰጠው የሳውዲ ሐጂ ጉዞ ተጓዦች ቁጥር እጅግ በጣም አድጎ ነበር፡፡ በመሆኑም በእስልምና አዳኙ በፋሽስት ጣሊያን ጦርነት መሰረት ኢትጵዮጵያ የእስላም አገር ትሆናለች የሚለው በተለይም የዋሃቢስት ሙስሊሞች ክፍል ተስፋ በጣም ግሎና ተጋግሎ ነበር፡፡
ወደ መካከለኛው ምስራቅ አገር የተላኩት ልዑካን የተደረገላቸው አቀባበል በጣም አሳፋሪና አሳዛኝም ነበር በተለይም በሳውዲ አረቢያ ዘንድ የነበረው ታሪክና ትውልድ የማይረሳው ትክክለኛ የጠላት ስራ የነበረ ሲሆን በመንግስት ልዑካኑ ላይ የደረሰው በደል እንዲሁም መንገላታት ከገለፃ በላይ እንደነበረ ከፕሮፌሰር ኤርሊች ትክክለኛ ማስረጃዊ ታሪክ ላይ ማንበብ ይቻላል፡፡ በአንፃሩ ሳውዲ አረቢያ የፋሽስቱ ጣሊያን ጦር ድል ማድረግ የሚቻልበትን ሁሉ ድጋፍ አድርጋለች ኢትዮጵያን አዋርዳለች፣ 12,000 ግመሎች ለጦር መሳሪያ አጓጓዥነት ለጣሊያን ሰራዊት አቅርባለች፡፡
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ምላሽ
የፋሽስቱ ሙሶሊኒ “የኢትዮጵያ እስልምና አዳኝ” አቀራረብ እንቅስቃሴ በውጭው ዓለም ከፍተኛ ድጋፍና ልዩ ልዩ የእርዳታ ቃል ኪዳን ስላስገኘለት ፋሽስቱ ሙሶሊኒ በጣም ተደስቶ ነበር፡፡ ከውጭው ድጋፍ በተጨማሪ የሚቀጥለው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች አቋምና ድጋፍን ማግኘት ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ምን ይላሉ? የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ሁለት ምላሽ ነበራቸው፡፡ አንደኛው በጣም የታወቁት የመርካቶ ነጋዴዎች ለንጉሱ ጥሪ የሰጡት ቀናነት ያለበት ምላሽ ሲሆን ግንቦት 30 1935 በታተመው ብርሃንና ሰላም ጋዜጣ ላይ መሐመድ አል ሳዲቅ የሰጠው መግለጫ ነው፡፡ ሌላው የአብዛኛዎቹ ምላሽ ግን ከሙሶሊኒ ጋር ቀጥታና ተዘዋዋሪ ትብብር ያደረገ ነበር፡፡
ፋሽስቱ ሙሶሊኒ የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን ልብ ማርኮ የጦርነቱ ተሳታፊዎችና የፋሽዝም ደጋፊዎች ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? የሚለውን በሚገባ አስጠንቶታል፡፡ ፋሽስቱ ጣሊያን ለዚህ እንዲመቸው ኢትዮጵያን “የምስራቅ አፍሪካ ኢጣሊያ” በማድረግ ወይንም የሚል ስያሜን በመስጠት ስድስት ቦታ ከፋፍሏት ነበር ማለትም፡
አንደኛ፡ ሶማሊያ ብዙውን ኦጋዴንን ያካተተ
ሁለተኛ፡ ሐረር
ሦስተኛ፡ ጋላ (ዖሮሞ) ሲዳማ ተብሎ በመጠራት
አራተኛ፡ ኤሪትሪያ ብዙውን ትግራይ በማካተት
አምስተኛ፡ ሸዋ
ስድስተኛ፡ አማራ ተብላ ነበር፡፡ ይህ ክፍፍልም የተደረገው በዘርና በሃይማኖት መስፈርት አማካኝነት እንደነበር የፕሮፌሰር ኤርሊች መጽሐፍ ያስረዳል፡፡ ሸዋና አማራው ከእነዚህ ውስጥ በጣም ትንሹ ክፍል ሲሆን እንደ ክፍለ ግዛት የታወቀውም በአማርኛና በክርስትያን ባህል መሰረት ነበር፡፡ የተቀሩት ከፊል እስላምና ከፊል ክርስትያን ከተባለችው ከኤርትራ በስተቀር እስልምና ዋናው ሃይማኖታቸውና ባህላቸው እንደሆነ ተደርጎ ተወስዶ ነበር፡፡Anwar-Mosque
የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን ድጋፍ ለማግኘት ውስጥ ውስጡን ከፍተኛ የፕሮፓጋንዳ ስራ ተሰርቷል፡፡ ፋሽስቱ ጣሊያን በረቀቀ መንገድ ባቀናበረው ሁኔታ በጣሊያን ሙሉ ድጋፍ ብዙ ሙስሊሞች ወደ መካ መዲና ሐጂ ማድረጋቸው፤ የሐጂዎቹም ቁጥር ከዓመት ወደ ዓመት ከፍተኛ እየሆነ መጣ፡፡ የሐጂው ዓላማዎችም አንደኛ ሐጂ የሚሄዱ ሙስሊሞች አክራሪ ሆነው የኢትዮጵያ ጥላቻ ኖሯቸው እንዲመለሱ፤ እንዲሁም ሁለተኛው ጣሊያን ያለውን ዕቅድ በውጭም በውስጥም በማስተዋወቅ ለጣሊያን ወረራ ቅድመ ሁኔታ እንዲያመቻቹ ነበር፡፡ የዚህም የመጨረሻ ግቡ በ”እስልምና አዳኙ” በሙሶሊኒ እርዳታ አገሪቱ የእስላም አገዛዝ የሚሰፍንባት አገር ወደ መሆን እንደትሄድ ነበር፡፡ ይህ እንዴት እውነት ሊሆን ይችላል? እነዚህ ሁሉ እውነት ሊሆኑ የሚችሉት የክርስትያኑ የቀዳማዊ ኃይለስላሴን መንግስት ለመጣል በሚደረገው ትግልና ጦርነት ሙስሊሞች በቀጥታና በተዘዋዋሪ ከተሰለፉ ብቻ ነበር፡፡ ስለዚህም ሙስሊሞች ከጣሊያን ጎን የሚሰለፉበትን ሁኔታ መሰረት መጣል አስፈላጊ ነበር፡፡ ይህ የሙሶሊኒ አቀራረብ ከአገሪቱ ሙስሊሞች ዘንድ ድጋፍ እንዲያገኝ፣ የአገሪቱ ሙስሊሞች እንዲተባበሩትና አገሪቱን በፍጥነት ለመቆጣጠር ምቹ ሁኔታን እንደሚከፍትለት ምንም ጥርጥር አልነበረውም፡፡
ይሁን እንጂ ይህ ጉዳይ ለኢትዮጵያ መንግስትና ለአዲሱ የአስተዳደር ሞዴል ፖሊሲ አስቸጋሪ ነበር፡፡ አስቸጋሪ ያደረገውም የአገሪቱን ሙስሊሞች አቋም በምንም መንገድ ለማወቅና በተደጋጋሚም እንደታየው ፍላጎታቸውንና ጥያቄያቸውን በምንም መንገድ ለማርካት የማይቻል ስለነበረ ነው፡፡ እዚህ ነጥብ ላይ አንባቢዎች ቆም ብለው ለምን? የሚል ጥያቄን እንዲጠይቁ እጋብዛለሁ፡፡ መልሱንም በአጭር አረፍተ ነገር በመደምደሚያዬ ላይ አስቀምጣለሁ፡፡ ከዚህ የሚቀጥልም ጥያቄ እንዲመከተለው መጠየቅ ይቻላል አሁንስ አሁን ባለው ሁኔታስ የሙስሊሞችን አቋምና ፍላጎት ማወቅ ይቻላልን? ለዚህም ጥያቄ አጭር መልስን በስተመጨረሻው እሰጥበታለሁ፡፡
ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ያቀረቡትን አዲስ “የኢትዮጵያ ሞዴል” ያልተቀበሉት ሙስሊሞች ምክንያታቸው ምን ነበር? ምክንያታቸው ግልፅ ነበር፡፡ የጣሊያን ወረራ ሙሶሊኒ እንዳስተጋባው ቅስቀሳና ፕሮፓጋንዳ ልዩ የሆነ የፖለቲካል እስላምን በአገሪቱ መስርቶ እስላም ኢትዮጵያን ለማየት ነበር፡፡ የቀዳማዊ ኃይለስላሴን የአዲስ ኢትዮጵያ ሞዴል የተቀበሉት ጥቂቶቹ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይም (ከዚህ በላይ በጠቀስኩት እትም) ሳይቀር ድጋፍም ጥሪም ቢያቀርቡም ሌሎች ግን ጣሊያን ሊያመጣ የሚችለውን ነፃነት ለመጠበቅና ኢትዮጵያን ከጣሊያን ጋር በመወገን ለመውጋት መረጡ፡፡
የኃይለስላሴን ጥሪ ያልተቀበሉት እነዚያ የዋሃቢዝም ተካታዮች ነበሩ፡፡ እነዚያ የፖለቲካዊ እስልምና አራማጆች ነበሩ፣ እነዚያ ኢትዮጵያ – ነጃሺ፣ ወይንም ነጃሺ – ኢትዮጵ የሚል የፈጠራ ታሪክ ተከታዮች ነበሩ፡፡ እነዚያ ናቸው እስልምና እምነት በኢትዮጵያ ውስጥ ሲረገጥ ሲጨቆን ኖሯል የሚሉት፤ እነዚያ ናቸው ኢትዮጵያ እንደ አንድ አገር ከእስልምና ጋር አብራ እንደማትኖር የሚያውጁት፡፡ የአሁኑ ጊዜ የዋሃቢዝም እንቅስቃሴ ስር የሰደደው በዚያ አመለካከትና የፖለቲካ እስልምና የረጅም ጊዜ እቅድ ላይ ተመስርቶ ነው፡፡
አዲሱ ሞዴል ከፋሽስት ጣሊያን ወረራ በኋላ፡
ከፋሽስት ጣሊያን ወረራ በኋላ የነበረው የኃይለስላሴ መንግስት በጦርነቱ ዋዜማ ለሙስሊሞችና ለመላው የአገሪቱ ሕዝብ የገባቸውን ቃል ኪዳኖች በከፊል ፈፅሟቸዋል፡፡ አገሪቱ በአብዛኛው ሁሉን ሃይማኖት አቀፍ ሆና ነበር፤ ሆናለችም፡፡ በሚኒሊክ ቃል የተገባውና በፋሽስቱ የተጀመረው የአንዋር መስጊድ ግንባታም ተጠናቀቀ፡፡ በንጉሱ ፈቃድ ቁርአን ወደ አማርኛ እንዲተረጎምና እንዲታተም ተደረገ፡፡ በተለያዩ ጊዜዎችም የመስጊድ ግንባታዎች እየተፈቀዱ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የመስጊዶች ግንባታም ቀጠለ፡፡ በመሆኑም ሙስሊሞች ድሮ ከግራኝ መሐመድ ጋር ትብብር እንዳደረጉት ሁሉ ከጣሊያንም ጋር ትብብር በማድረግ አገሪቱን ቢያደሙምና ቢዋጉም መሪዎቻችን ልባቸውን በማስፋት አብሮ ለመኖር፤ በሃይማኖት ልዩነት እንዳይኖር፣ የበቀልም እርምጃ እንዳይወሰድ የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት አድርገዋል፡፡
በቀዳማዊ ኃይለስላሴ የተነደፈው አዲስ የኢትዮጵያ ሞዴል በየተወሰነ ደረጃ በደርግ ዘመንና አሁንም በኢሕአዴግ መንግስት ዘመን በመንፀባረቅ በተለይም ለሙስሊሞች ከፍተኛ ድጋፍ ሆኖላቸው እንደቆየ ምንም ጥያቄ የሌለው ነገር ነው፡፡
በተደጋጋሚ በተለያዩ ጽሑፎች ላይ እንደሚታዩት ከሆነ ለሙስሊሙ ማህበረሰብ ኃይለስላሴም፣ የደርግም መንግስት የአሁኑም ኢሕአዴግ መንግስት የቻሉትን ያህል መልካምን ለማድረግ ጥረዋል፡፡ የሆኖ ሆኖ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የምንታዘበው ነገር ቢኖር የማንኛውም የመንግስት (የቀዳማዊ ኃይለስላሴ፣ የደርግ እና የኢሕአዴግ) ድጋፍና መልካም እርምጃ የሙስሊሞችን ፍላጎት አርክቶ ጥያቄያቸውን የመለሰበት ጊዜ አልነበረም፡፡ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጥያቄ ምን ነበር? አሁንስ ምንድነው? ወደፊትስ ምን ይሆናል? አሁንም አንባቢ ቆም ብሎ እንዲጠይቅ እጋብዝና በመደምደሚያዬ ላይ በአጭር አረፍተ ነገር መልሱን እሰጣለሁ፡፡ በመቀጠልም በክፍል ሁለት ላይ የሙሰሊሞች ጥያቄ ምክንያቱ ምን እንደሆነና የቀዳማዊ ኃይለስላሴም ሆነ ቀጥሎ የመጡት ተከታታይ መንግስታት ፖሊሲዎች ለምን እንዳልሰሩና ወደፊትም የሚሰጡ ማናቸውም በጎ አስተያየቶችና ፖሊሲዎች ለምን እንደማይሰሩ ስረ መሰረታዊ ምክንያትን አቀርባለሁ፡፡
እንደሚታወቀው ሁሉ የጣሊያን ወረራ ከአምስት ዓመታት በኋላ ከሸፈ፣ የእስልምናም ተስፋ አብሮ ተዳፈነ፡፡ የቀዳማዊ ኃይለስላሴ አዲስ የአስተዳደር ፖሊሲ ግን እጁን እንደዘረጋ ቢሆንም ከሙስሊሞች ዘንድ ተቀባይነት አልነበረውም፡፡
በጣሊያን መንግስት ድጋፍ መሰረት ወደ መካ ይደረግ የነበረው ሐጂ መጠን እጀግ በጣም ከፍ ያለ እንደነበረ ቀጠለ፡፡ ብዙዎቹ የሐጂ ተጓዦች በምፅዋ ከደረሱ በኋላ ፀረ ኃይለስላሴ ቅስቀሳ እንዲያደርጉና ኢትዮጵያ በእስልምና ላይ የምትፈፅመውን ግፍ እንዲናገሩ ስልጠና ይሰጣቸው እንደነበረና ሲመለሱ ደግሞ በጣም አክራሪዎችና የኢትጵያ መንግስት ጥላቻ ይዘው እንደነበረ ነው፡፡
ፕሮፌሰር ኤርሊች በመጽሐፉ ላይ እንዳቀረበው ጣሊያን ድል ተደርጎ እንደወጣ በመጋቢት 27 1941 የሐረር ከተማ ነፃ ወጣች፡፡ ዋናው የዋሃቢዝም አራማጅ ሼክ ዩሱፍ አብድ አልራሃማን ወደ ሐረር ተመልሶ የዋሃቢዝም እንቅስቃሴን ማቀጣጠልና ሐረርን ለመገንጠል ከፍተኛ ጥረቱን ቀጠለ፡፡ የሙስሊም መሪዎችን በመሰብሰብ ሐረርን ነፃ በማውጣት ለመራው የብሪቲሽ ኮሎኔል ዳላስ የስምምነት ፍርማ በማቅረብ የመገንጠል ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡ እንግሊዞቹ ይህንን ጥያቄ እንዳልተቀበሉት መጽሐፉ ያስረዳል፡፡ ይሁን እንጂ የተቋቋመው የዋሃቢዝም እንቅስቃሴ ወጣቱን በአክራሪነት በማሰልጠን ለወደፊቱ የነፃነት ትግል የማዘጋጀት ስራውን ውስጥ ውስጡን ቀጥሎ ነበር፡፡ የኃይለስላሴ መንግስት ለዓለም ትምህርት በሚሰጥ መልኩ ሁኔታውን ተቆጣጥሮት አገሪቱ በሰላም ተረጋግታ እንድትቆይ አድርጎ ነበር፡፡ እንዴት የሚለውን በክፍል ሁለት እንመለከተዋለን፡፡
የነበረው  ከመንግስት ፖሊሲዎችና ቀናነት የተሞላባቸው እምርጃዎች ባሻገር የአገሪቱ ሕዝብ በሙስሊሞች እና በእስልምና ላይ ያለው አመለካከት ሊጠቀስ ይገባዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብና እስልምና
የአገሪቱ ሕዝብ እስልምናን እንደ አንድ እምነት ሙስሊሞችን ደግሞ እንደ ማንኛውም የሰው ልጅ በማየት ማህበራዊ ግንኙነቱንና አንድነቱን አልቀነሰም ደግሞም አልለወጠም፡፡ በተለይም የኃይለስላሴውን “ሃይማኖት የግል አገር ግን የጋራ” የሚለውን እያንፀባረቀ መኖሩ የተመሰከረለት ነው፡፡ ብዙዎች ኢትዮጵያ የምትባለው አገር እስልምናና ሌሎች እምነቶች በሰላምና በእኩልነት ያለምንም ችግር ለመኖር እንደሚችሉ እንደምሳሌ የምትቆጠር አገር ናት ለሚሉት ሁሉ መነሻ ነው፡፡
በመሆኑም ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ማለቴም ሙስሊም ያልሆነው ከሙስሊም ጋር ለመጎበራት አብሮ ቡና ለመጠጣት እና በልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ ማህበራዊና ባህላዊ መሰባሰቦች ውስጥ አብሮ ለመሆን፣ በደስታም በሐዘንም ለመሳተፍ ጥያቄም ችግርም አልነበረበትም አሁንም የለውም ወደፊትም አይኖረውም፡፡
ይሁን እንጂ የሌላው ማለትም ሙስሊም ያልሆነው ማህበረሰብ የማንኛውም ዓይነት ክርስትያን እምነት ተከታይ፣ አማኝ ያልሆነው (ሴኩላሩ) ፖለቲከኛውና ምሁሩ እንዲሁም ጋዜጠኞችና የፖለቲካ አቀንቃኞች ሁሉ፣ የሙስሊሞችን ውስጣዊና ምስጢራዊ እንቅስቃሴ ያውቃሉ ማለት አይደለም፡፡ እንዲያውም በታሪክ የተከናወነውንና አሁንም ውስጥ ውስጡን የሚሆነውን በተመለከተ የኢትዮጵያ ሕዝብ ካለው ከፍተኛ የዋህነት የተነሳ ረስቶታል ማለት ይቻላል፡፡ ሆኖም በዋሃቢስቶች አማካኝነት ለተቀናበረው ሴራ ተጎጂ ወይንም ሰለባ መሆኛው ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡ አሁን በጣም ሳይዘገይ ይህ ጉዳይ ካልተነቃበት አገሪቱ ልክ እንደ የግብፅ የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያንና ሙስሊም ያልሆነው የግብፅ ሕዝብ እየደረሰበት ያለው ዓይነት የስቃይ ደረጃ በቅርብ እንደምትደርስ ጥያቄ የለውም፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ እስልምና እምነትን በተመለከተ የወሰደው ታሪካዊ ልበ ሰፊነት፣ የኃይለስላሴ መንግስት አዲስ የአስተዳደር ሞዴል፣ በአገር ደረጃ ሊያስመሰግነውና በዓለም አቀፍ ደረጃ የአረብ አገሮችን ጨምሮ ደግሞ ትልቅ ትምህርትን የሚሰጥ ነው፡፡
“ኢስላሞ ፋሽዝም” ያኔና አሁን
ፋሽስት ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ላይ አድርጎት የነበረው ጦርነት የማን ጦርነት ነበር በሚለው ርዕስ መጠነኛ እይታ ተሰጥቷል፡፡ በቅርቡ በለንደን ከተማ በሁለት የእስላም ወጣቶች የታረደውን የእንግሊዝ ወታደር በተመለከተ የእስላም ሊግ ተወካይ በቢቢሲ የቴሊቪዥን ቃለ መጠይቅ ላይ ግድያውን ተቃውሞ ሲናገር የተደመጠው የአሁኑ ጊዜ እንቅስቃሴ “ኢስላሞ ፋሽዝም” ነው በማለት ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በገሃድ የታየውም “ኢስላሞ ፋሺዝም” ነበር፡፡ ይህ “ኢስላሞ ፋሺዝም” ነው በእነ ጆሐር የአሜሪካ ስበሰባ መግለጫ መሰረታዊ ዕቅድ ውስጥ “ቀይ መሃረብ” ተብሎ የተገለጠው፣ ነጩን ዓይተናል፣ ብጫውንም ተመልክተናል፣ ቀጣዩንና ቀዩን ማለትም የንፁሃንን ደም አፍሳሹን የምናይበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም፡፡
እዚህ ነጥብ ላይ ነው ቀደም ብዬ በኋላ በትንሽ አረፍተ ነገር እመልሰዋለሁ ያልኩትን ጥያቄ የማነሳው፡፡ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ባለፉት የታሪክ ዘመናት በነበሩተ መንግስታት የቀረቡላቸውን እድሎች፣ የአስተዳደር ሞዴል ለውጦች፣ የሃይማኖት ነፃነት መብቶችና ስጦታቸዎች ለምን በደስታ አልተቀበሉትም?
የኢትዮጵያ ሙስሊም የዋሃቢዝም እንቅስቃሴ መሪዎችና ደጋፊዎቻቸው ምንድነው የሚያረካቸውና የሚያስደስታቸው? በእርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ሙስሊሞች የተነጠቁት ወይንም ያጡት የሃይማኖት ነፃነት ነውን? ከታሪክና አሁንም ካለው እውነታ ስንመከተው መልሱ ሌላ ነው፡፡ መልሱን እነርሱ ያውቁታል ለሌላው ኢትዮጵያዊ ግን ድብቅ የሆነ ቢሆንም እዚህ ላይ በአንድ አረፍተ ነገር አቀርበዋለሁ፡፡ እርሱም “ኢትዮጵያ በእስላም ፖለቲካ የምትመራ የእስላም አገር ማድረግ ብቻ ነው”፡፡
ወደዚህ የመደምደሚያ ሐሳብ እንዴት ሊደረስ ይቻላል? ውስጣዊ ምክንያቱ ምንድነው የቀዳማዊ ኃይለስላሴ አዲስ የኢትዮጵያ ሞዴል፤ የደርግም መንግስት ጥረት እና የኢሕአዴግም የብዙ ሺ መስጊዶች ግንባታ ፈቃድ፣ እጅግ በጣም ብዙ ትምህርት ሰጪ መቻቻሎች ስለምን የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን አላረኳቸውም? ጣሊያን ድል ተደርጎ ከወጣ በኋላ የቀዳማዊ ኃይለስላሴ መንግስት በተለይ በሐረር ላይ ወስዶት የነበረው እርምጃ ለአገሪቱና ለመላው ዓለም የሚሰጠው ትምህርት ምንድነው? የአሁኑ ጊዜ መሪዎችና የቀረው ዓለም ከዚያ የብልህ መሪዎች እርምጃ ምን ይማራሉ? ከጥቅል የአንድ አረፍተ ነገር የመደምደሚያ መልሱ ባሻገር የእስልምና እንቅስቃሴን የሚመራውን ምስጢራዊ ምክንያትና ጠቃሚ ነጥቦችን በክፍል ሁለት ላይ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡
ጸሐፊውን ለመንቀፍም ሆነ ለማበረታታት በ jafar.hasen@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

No comments:

Post a Comment