Translate

Saturday, August 13, 2016

ስለ ወያኔ መውደቅ ሳስብ(ሄኖክ የሺጥላ)

ስለ ወያኔ መውደቅ ሳስብ ፥ አይኖቼ በደስታ እንባ ይሞላሉ ። እንባውን የፈጠረው ይቺን ቀን ማየት ያልቻሉትን ብዙዎች ስለማስብ ነው ። ዛሬ ጎንደር ላይም ሆነ ኦሮሚያ ላይ የተነሳው ትግል ፥ ባንድም ይሁን በሌላ መልኩ የዛሬው ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት አእላፋት ህይወታቸውን ገብረውበታል ። እልፎች ታስረዋል ፥ ህልቆዎች ከስራ ፥ ከሃገር ተባረዋል ፥ ቆጥረን የማንጨርሳቸው ሊህቃኖች ተንገላተዋል ፥ ታድርደዋል ። ህፃናቶች ተገለዋል ፥ እናቶች ፀጉራቸውን ተላጭተው አሸባሪ ተብለው ታስረዋል ። ብዙዎች በርሃ ወርደዋል ፥ እጅግ ብዙዎች ሞተውለታል ፥ ብዙዎችም ሞተውበታል!

የዛሬው ቀን ላይ ለመድረስ ወደድንም ጠላንም ፥ አመንንም አላመንንም አስራት ወልደየስ ህይወቱን ዋጋ ከፍሎበታል ፥ አሰፋ ማሩ ሞቶለታል ፥ እስክንድር ነጋ ታስሮለታል ፥ ቴዲ አፍሮ ያለ በደሉ እና ያለ ወንጀሉ ታስሮለታል ። የዛሬው እምቢታ 25 አመት የተጠነሰሰ ፥ ብንሸነፍም ተምረን የተሸነፍንበት ፥ ብንወድቅም ደግመን መነሳት መቻላችንን ያሳየንበት ትግል ነው ።
የዛሬው ትግል እነ ታማኝ በየነ ሃያ ምናምን አመት ያለ ማቋረጥ የጮኹለት ትግል ነው ፥ እነ ሙልጌታ ሎሌ ያለመታከት የፃፉለት ቀን ነው ፥ እነ ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን ያለ እረፍት ህዝብን ያስተማሩበት እና ያነቁበት ትግል ውጤት ነው !
የዛሬው ትግል ባንድ ሌሊት የመጣ ፥ ባንድ ሰው ሃሳብ የተፀነሰ እና የተወለደ ትግል አይደለም ። ይህ ትግል ማንነቱን የተቀማው የወልቃይት አማራና ፥ መሬቱን ለውጭ ባለሃብት አሳልፎ እንዲሰጥ የተገደደው ጋንቤላ በየፊናቸው ባነሱት ጥያቄ ድሆ ድሆ የለውጥ ጫፍ ላይ የደረሰ ትግል ነው ።
ለዚህ ትግል እነ በፍቃዱ ዘሃይሉ ታስረውለታል ፥ እነ አቤል ዋበላ ተገርፈውለታል ፥ እነ አበበ ቀስቶ ጥፍራቸው ተነቅሎ ደማቸው እያፈሰሱ « ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ » በማለት ቆራጥነታቸውን አሳይተውበታል ፥ እነ አንዷለም አራጌ ተሰቃይተውለታል ፥ እነ ርዮት አለሙ በህመም የሞት እና የህይወትን ምጥ አሳልፈውበታል ፥ እነ በቀለ ገርባ ራሳቸውን ስተው ወድቀውለታል ፥ እነ ካፒቴን ተሾመ ተንኮሉ በጨለማ ቤት ተጥለው እናታቸውን እስር ቤት በራፍ ላይ በበሽታ ተነጥቀውበታል ፥ እነ ሳሙኤል አወቀ ሞተውለታል ፥ እነ ህፃኑ ነብዩ ባያውቁትም የበኩላቸውን አስተዋፆ አበርክተው አልፈዋል ፥ እነ አንዳርጋቸው ፅጌ በርሃ ለበርሃ ተንከራተውለታል ፥ እነ ብርሃኑ ነጋ ህይወታቸውን ጥለው ተሰደውለታል ። እነ መስፍን ወልደማሪያ በመጦሪያ ዘመናቸው ፥ በተራ መሃይም ጦንጤ እየተመናጨቁ ተንገላተውለታል ፥ እነ ታዬ ወልደሰማያት ክቡር የሆነ ትግልን ።፥ መራር የሆነ መካራን አሳልፈውበታል ፥ እነ ፕሮፈሰር አልማሪያም ያለ መታከት በብዕራቸው የተባ ትግላቸውን አካሂደውለታል!
አዎ የዛሬው ቀን ፥ የብዙ እምቢታዎች ጥንስስ ነው ። የብዙ መገፋቶች እና መከፋቶች ውጤት ነው ! ዛሬ ብቻውን አልመጣም ! ዛሬ ላይ የደረስነው ከ አምስት ሚሊዮን በላይ አማራ በኢንቁፍቱ ፥ በበደኖ ፥ በጉራፈርዳ እና ወዘተ ገብረን ነው ። ህዝብ እንደ ጅረት ደሙን አፍስሶ ነው ። ዘር ጠፍቶ ነው ። ዛሬ ላይ የደረስነው እነ የኔ ሰው ገብሬ ራሳቸውን በእሳት አቃጥለው ነው ፥ በፓለቲካ አመለካከታቸው የታሰሩት « ሽንታም አማራ!» አየተባሉ የሚደርስብቸውን ግፍ ተቋቁመው ባልበገርም ባይነት በታገሉት የቁርጥ ቀን የአማራ ልጆች ደም ነው ! ዛሬ ላይ የደረስነው በኦሮሚያ በሺዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ልጆችን ገብረን ነው ። ይቺ ቀን ፥ ልጆቿን በራብ ተነጥቃ ፥ « አይ ታመው ነው የሞቱት » ብላ እንድታስተባብል የተደረገችውን የብርቱካን አሊን የእናት ሲቃ ና ያልተለቀሰ የሃዘን እንባ ተሸክመን ነው ። ዛሬ ለመድረስ ሺዎች በፍትህ እጦት ተሰቃይተዋል ፥ እልፎች ሙስና እና ዘረኝነት በፈጠረው ረሃብ ሞተዋል! ዛሬ ብቻውን የመጣ ቀን አይደለም ! ዛሬ ላይ ቆመን የነገን ድል ስናስብ ፥ ሃውልት የምናቆምላቸው ፥ ከቆምነው እኛ በጀግንነት ብቻ ሳይሆን በቁጥርም ይልቃሉ ! የዛሬው ቀን የብዙ ጀግኖች ትግል እና ደም ውጤት ነው ።
በዚህ ትግል ውስጥ ያመንናቸው ክደውናል ፥ ወዳጅ ያልናቸው አሳልፈው ሰጥተውናል ፥ ትናንት ከኛ ጋ ቆመው የነበሩት ዛሬ በሌላ ጎን ሆነው በአንድ አይነት ጉሮሮ ሲያቀነቅኑ እና ሲቀኙ ሰምተናል ። ተሰብረን ግን አልቀረንም ። ወድቀንም አልቀረንም ። ኢትዮጵያዊያኖች ነንና ድጋሚ ተነስተናል ። ድጋሚ!
ውዴ ተመስገን ደሳለኝ « የፈራ ይመለስ !» ብሎ ነበር። አዎ የፈራ ይመለስ!
በመጨረሻም ስማችሁን ሳልጠቅስ ያለፍኩት ወገኖቼ ፥ ሁሌም በልቦናዬ እና በህሊናዬ ውስጥ ትኖራላችሁ ፥ አላችሁም!
ድል ለሰፊው ህዝብ !

No comments:

Post a Comment