Translate

Wednesday, August 31, 2016

አገዛዙ በዐማራ ሕዝብ ላይ ይፋ ጦርነት አውጇል፤ በባሕር ዳር የሰባታሚት ማረሚያ ቤት ዐማሮች በጅምላ ተቀብረዋል


ዐማራ ዛሬ (ነሃሴ 25 ቀን 2008 ዓ.ም) 
Muluken Tesfaw #AmharaResistance
አገዛዙ በዐማራ ሕዝብ ላይ ይፋ ጦርነት አውጇል፤ በባሕር ዳር የሰባታሚት ማረሚያ ቤት ዐማሮች በጅምላ ተቀብረዋል
• የአብራጂራ ሕዝብ የመከላከያ ታንክ ላይ ሰንደቅ ዓላማ ተከለ 
• የዐማራ ተጋድሎ ከእለት ወደ እለት እየጨመረ ሒዷል፤ የጋይንት፣ የቋሪትና ግምጃ ቤት አካባቢዎች ከጠላት ቀጣና የጸዱ ናቸው 
• የትግሬ መከላከያ ሠራዊት በወገራ አውራጃ ሕጻናትና አቅመ ደካሞች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ፈጽሟል
• የደባርቅ፣ የመተማ፣ ሸኽዲና ሽንፋ ከተሞች በቃጠሎ ታፍነው ውለዋል
• በቡሬ ትንሳኤ ሆቴል ግቢ 2 አስከሬን ተደብቆ ተገኘ
• በወንበርማ ሽንዲ ወረዳ የዐማራ ተጋድሎ ሁለተኛ ቀኑን አስቆጥሯል
• በእጅባራ ሕዝብና መከላከያ ተፋጠዋል

ባሕር ዳር
ከወደ ባሕር ዳር ያገኘነው መረጃ አስደንጋጭ ነው፡፡ የትግራይ መንግሥት የጅምላ ጭፍጨፋ በዐማራው ሕዝብ ላይ በይፋ ማወጁን ተከትሎ ትናንት ብዙ ቁጥር ያላቸው ዐማሮች ተሰውተዋል፡፡ የባሕር ዳር፣ ጢስ ዓባይ፣ መሸንቲና መራዊ ከተሞች ከፍተኛ እልቂት ከደረሰባቸው ቀዳሚዎቹ ሆናዋል፡፡ 
ትናንት በነበረው የዐማራ ተጋድሎ የሰባታሚትና የጢስ ዓባይ ገበሬዎች በገፍ ታፍነው ታስረው የነበሩ ወጣቶችን ማስለቀቃቸው የታወቀ ቢሆንም ቁጥራቸው ያልታወቁ ወጣቶችን ግን ከማምለጣቸው በፊት በጥይት ተጨፍጭፈዋል፡፡ አንድም የተገደለ ዐማራ አስከሬን ወደ ሆስፒታል ያልተወሰደ ሲሆን የሟቾች ቁጥር አገዛዙን ያሳጣል በሚል የትግሬ መከላከያ ሠራዊትና ፖሊስ በጅምላ በማረሚያ ቤቱ ግቢ ውስጥ መቅበራቸውን ነው የዐይን ምስክሮች የገለጹት፡፡ ትናንት ከተሰውት ዐማሮች የሁለት የጢስ ዓባይና የሰባታሚት ገበሬዎች አስከሬን ብቻ ነው የወጣው ተብሏል፡፡ የሁለቱን አስከሬን ለማውጣት የገቡ የዓይን እማኞች እንደሚሉት በጣም ብዛት ያላቸው ዐማሮች አስከሬን መመልከታቸውን እና ሁሉም እዚያ ግቢ እንደተቀበሩም እንደሚያውቁ አክለው ተናግረዋል፡፡ የፈለገ ሕይወት ሆስፒታል የሚሠሩ ባለሙያዎችን የተባለውን ያክል አስከሬን በእነርሱ በኩል ማለፍ አለማለፉን የጠየቅን ሲሆን አሁን አሁን የተገደለውን ሰው ሁሉ ወደ እኛ ሳያመጡ ማፈን የተለመደ እንደሆነ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ 
በመራዊ ከተማ የጦር ጀቶች ዝቅ ብለው ሲበሩ እንደዋሉም ለማወቅ ችለናል፡፡
አብራጂራ/ ሶሮቃ/ እርጎየ፤ የአብራ ጂራ ዐማራ ታሪክ ሰርቷል፡፡ የሆነው እንዲህ ነው፡፡ ከሦስት ቀናት በፊት ወጣቶች በዐማራው ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን በደል እስኪቆም የአርማጭሆን እና የጠገዴን ዐማሮች ቀሰቀሱ፡፡ የአብራ ጂራና የእርጎየ ከተማ ሕዝብ በአንድነት ተነሳ፡፡ የንግድ ተቋማትና የመንግሥት ሥራ እንዲቆም ወጣቶች ጠየቁ፡፡ አንዳንድ ወያኔዎች አንዘጋም ብለው አንገራገሩ፡፡ እንርሱን ከቤት እያስወጡ የወያኔ ንብረት የሆነ ሁሉ በአንድነት በእሳት ወደመ፡፡ የትግሬ ጦር ሁለት ታንክ ይዞ መጣ፡፡ የአርማጭሆ አርበኛ ሕዝብ ግን ፊት ለፊት ገጠመው፡፡ የትግሬ ጦር ብሬኑንና ታንኩን እየተወ ፈረጠጠ፡፡ የመከላከያ ሠራዊት ታንክ ላይ የአርማጭሆ ወጣቶች የአባቶቻችን ሰንደቅ ዓላማ አውለበለቧት፡፡ እስካሁን ድረስ የአርማጭሆ አካባቢ በሕዝብ ሥር ነው፡፡ 
የእርጎየ ከተማም የአብራ ጂራን ሕዝብ ሞዴል ተከትላለች፡፡ ዛሬ የወያኔዎችን ንብረት አንድ ባንድ ለቅማ አቃጥላለች፡፡ 
ምሽቱን ከኹመራ 5 ኦራል የትግሬ ጦር ወደ አብደራፊ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የሰማን ሲሆን ሦረቃዎች ኬላውን ጥርቅም አድርገው ዘግተውታል፡፡
መተማ/ ገንዳውኃ/፤ የመተማ ወረዳ ዛሬ በቃጠሎ ታፍኖ ውሏል፡፡ የመተማ ዮሃንስ፣ የገንዳውሃ (ሸኽዲ)ና የሽንፋ ከተማዎች የአገዛዙ የቅርብ አገልጋይ የሆኑ ግለሰቦች ቤትና ንብረት ሙሉ በሙሉ ወድሟል፡፡ መተማ ዮሃንስ 2 ዐማሮች የተሰው ሲሆን ሕዝቡም የሞቱን ሰዎች አስከሬን በመያዝ በቁጣ የበለጠ ገንፍሎ ወጥቷል፡፡ ከመተማ ዮሃንስ አስተያየታቸውን የሰጡን ግለሰብ ‹‹መተማ ዮሃንስ ዛሬ በድርቡሽ ዘመን ስጥቃጠል የነበረውን ጊዜ ሳትመስል አልቀረም›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ 
የትግሬ መከላከያ ሠራዊት በሕዝብ ላይ እየተኮሰ ሲሆን ዐማሮችም በመደራጀት ራሳቸውን እየተከላከሉ ነው፡፡
ወገራ/ደባርቅ፤ በወገራና ደባርቅ አካባቢዎች የትግሬ መንግሥት ይፋ ጦርነት አውጇል፡፡ በአምባ ጊወርጊስና አካባቢው ሕጻናት እና ታዳጊ ወጣቶች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት አገዛዙ ፈጽሟል፡፡ አንድ እማኝ እንደገለጹልን ከሆነ በጎንደር ዩንቨርሲቲ ሆስፒታል ብቻ የስድስት ሕጻናት አስከሬን ተከማችቷል፤ ከ20 የሚበልጡ ታዳጊዎች ደግሞ በሞት አፋፍ ላይ ናቸው ብለዋል፡፡
በደባርቅ ከተማ የአገዛዙ ቅጥረኞችና ወያኔዎች ቤትና ንብረት ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ሲወድም ውሏል፡፡ የደባርቅ ከተማ ቃጠሎ ተከዜ ማዶ ድረስ ሊታይ እንደሚችልም አስተያየታቸውን የሰጡን ሰዎች ገልጸዋል፡፡ በደባርቅና በጃናሞራ መካከል ያለው የሰሜን ተራሮች አካባቢ ከወያኔዎች አገዛዝ እስካሁን እንደነጻ ነው፡፡
ነፋስ መውጫ/ጋይንት፤ የጋይንት ዐማሮች ከጨጭሆ በኩል የሚመጣውን መንገድ እንደዘጉ ነው፡፡ ዛሬ ላይ የጎብጎብ ወጣቶች ነፋስ መውጫ በመሄድ የመንገድ መዝጋቱን ሥራ አግዘዋል፡፡ ወታደሮች ወደ ጋይንት መጥተዋል የተባለ ቢሆንም ከተማዋን ግን አልፈው እንዳልሄዱ በቦታው ያናገርናቸው ሰዎች ገልጸዋል፡፡ የጋይንት ከተማ አንድም ካቢኔ የለባትም፡፡ 
የአገር ሽማግሌዎችና የጎበዝ አለቆች የጸጥታ ሥራውንና ሰላማቸውን በራሳቸው እያስከበሩ ነው፡፡ 
በስማዳ ወረዳ ከ4 የሚበልጡ ቅጥረኛ ባንዳዎች መገደላቸውን የሰማን ቢሆንም የመገናኛ መስመሮች በመዘጋታቸው ማረጋገጥ አልቻልንም፡፡ ምዕራብ በለሳ ምንም ዓይነት መገናኛ ዘዴ ባለመኖሩ በምን ሁኔታ ላይ ሕዝቡ እንደሰነበተ የታወቀ ነገር የለም፡፡
ደብረ ታቦር/ ጋሳይ፤ የጋሳይ ከተማ የጎበዝ አለቆች ከተማዋንና አካባቢውን ማስተዳደር ከጀመሩ ቀናትን አስቆጥረዋል፡፡ ማንም በሞክሸዎች ሰፍር የሚያልፍ የለም፡፡ የደብረ ታቦር ከተማ ሕዝብ ደግሞ ከቤት ከተደበቀ ሦስተኛ ቀኑን ይዟል፡፡ በቤት ውስጥ አድማው ሊጎዱ የሚችሉ ሰዎችን ሕብረተሰቡ እየተንከባከበ እንደሚገኝ ለማወቅ ችለናል፡፡ 
አንድ አስተያየት ሰጪ የቤት ውስጥ አድማው ሰው እርስ በእርሱ እንዲተጋገዝና እንዲቀራረብ በር ከፍቶለታል ብለውናል፡፡
ቻግኒ/ እንጅባራ፤ የእንጅባራ አገው ዐማራ ሕዝብ ከትግሬ መከላከያና ፖሊስ ጋር ተፋጦ እንደሚገኝ ለማወቅ ችለናል፡፡ የጅባራን ከተማና የአዊ ዞንን የሚያስተዳድሩ ካቢኔዎች ሙሉ በሙሉ ከከተማ ወጥተው የገቡበት አይታወቅም፡፡ ወጣቶችን ለማሳር የሚሞክሩ የትግሬ መከላከያዎችም ተባረዋል፡፡ ሕዝቡ ተነቃንቆ ከወጣ ሦስተኛ ቀኑን ያስቆጠረ ሲሆን የግምጃ ቤትን ሞዴል በመከተል የጎበዝ አለቃ ለመምረጥ ማቀዳቸውን ገልጸዋል፡፡ የእንጅባራ ሕዝብ የደጀን፣ ሉማሜ፣ አወበል፣ ማርቆስ ሕዝብ መንገድ በመዝጋት የሚመጣውን መከላከያ እንዲያስቆም ጠይቀዋል፡፡ 
በሌላ በኩል የቻግኒን ሕዝብና የትግሬ መከላከያና ፖሊስ ኃይል ባለመመጣጠኑ ብዙ አገው ዐማሮች መታሰራቸውን ሰምተናል፡፡ ይህ ዜና በሚጠናቀርበት ሰአት ከ40 በላይ ሰዎች መታሰራቸውን የሰማን ሲሆን በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ የከተማዋ ነዋሪወች ከተማዋን ለቀው ወጥተዋል፡፡ የቻግኒ ሕዝብም የአገዛዙ ንብረት የሆኑ ቤቶችንና የንግድ ተቋማትን አቃጥለዋል፡፡
አንክሻ ጓጉሳ/ግምጃ ቤት፤ በአንክሻ ጓጉሳ ወረዳ የግምጃቤት፣ የአዘናና የእሁዲት ከተሞች በጎበዝ አለቆች መተዳደር ከጀመሩ ቀናትን አስቆጥረዋል፡፡ ማንም ወደ እነርሱ መግባት አይችልም፤ ሕብረተሰቡም የራሱን ሰላም በራሱ እያስጠበቀ ነው፡፡ የወያኔ መንፈስ ከተባረረ ሰንብቷል፡፡ 
ፈረስ ቤት፤ የደጋ ዳሞት ዐማራ ለተጋድሎ ከወጣ ቀናትን አስቆጥሯል፡፡ ትናንት ነሃሴ 24 ቀን 2008 ዓ/ም ቅዳሜ ገበያ 4፡00 አካባቢ እንደገና የተነሳው የዐማራ ተጋድሎ የወያኔ ባንዲራዎችን በማቃጠል ሰንደቅ ዓላማችን በሁሉም ሴክተር መሥሪያ ቤቶች እየሄደ ቀይሯል፡፡ በዚሁ ሁሉ መካከል 2 ዐማሮች ተሰውተውብናል፡፡ 3 ሰዎች ደግሞ በፈረስ ቤት ጤና ጣቢያ ሕክምና እየተደረገላቸው ሲሆን ሁለት ደግሞ ደብረ ማርቆስ ሆስፒታል ሕክምና ላይ መሆናቸውን ሰምተናል፡፡ የፈረስ ቤት ካቢኔ አንድም በከተማዋ እንደማይታይ ለማወቅ ችለናል፡፡
ደንበጫ፤ የደንበጫና የጨረቃ ሕዝብ ተጋድሎ ከጀመረ አምስተኛ ቀኑን አስቆጥሯል፡፡ እስካሁን ድረስ ምንም ሥራ የሌለ ሲሆን ከፍተኛ የትግሬ ጦር መሥፈሩን ከቦታው አረጋግጠናል፡፡
ቡሬ
በቡሬ ከተማ ባለቤትነቱ የሕወሓቱ ቀንደኛ አባልና ሰላይ የሆነ ትንሳኤ የሚባለው ሆቴል ግቢ ውስጥ ሁለት ዐማሮች ተገድለውና ሸንኮራ አገዳ ቅጠል በላያቸው ላይ ተደርጎ ተገኘ፡፡ ይህ አስደንጋጭ ሁኔታ የሕወሓት ሰዎች ንብረት በሆኑ በዐማራው አካባቢ በተመሳሳይ መልኩ ሊፈጸም እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ የቡሬ ከተማ ሕዝብ እካሁን ተጋድሎ ላይ ነው፡፡ 
ሽንዲ/ ወንበርማ፤ በወንበርማ ወረዳ ወያኔዎች ከዐማራው ላይ ይፋ ጦርነት እያካሄዱ ነው፡፡ እስካሁን ሦስት ወንድሞቻችን ተሰውተዋል፡፡ የወንበርማ (ሽንዲ) ሕዝብ ለሁለት ተከታታይ ቀናት አደባባይ በመውጣት ከአገዛዙ ጋር እየተጋደለ ነው፡፡ ወደ ወለጋ የሚወስዱና የሚያመጡ መንገዶች ሁሉ ዝግ ናቸው፡፡
ማሳሰቢያ፤ በሁሉም አካባቢ ያላችሁ ዐማሮች መረጃ በማቅረብ ትተባበሩን ዘንድ ልናሳስብ እንወዳለን፡፡ 
ይህ ሁሉ የመጨረሻው መጀመሪያ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment