Translate

Tuesday, November 3, 2015

የታማኝ እዳ

እንግዳ ታደሰ – ኦስሎ
በቃል የምነት እዳ ሸክፎ ሸክሙን 
እንደ ሴባስቶፖል ሽቅብ ቁልቁለቱን
ሲወጣና ሲወርድ ቋጥኝ አቀበቱን 
እስቲ እንካፈለው የሃገር እዳውን ፡፡
Ethiopian activist Tamagne Beyene
እዳው በግል የናት አባት እዳ አይደለም ፡፡ የርሱ እዳ የዕምነቱ እዳ ነው ፡፡ ለሸክም የከበደ ፥ የሰው ፊት የሚያስገርፍ፥ ዕረፍት የሚነሳ ፥ ከወለዳቸውና ከሚወዳቸው ቤተሰቡ ለወራት የሚያቆራርጥ፣ እንደ አጼ ቴዎድሮስ መድፍ ሴባስቶፖል ሽቅብና ቁልቁል የሚያስሮጥ፣ ኢሳትን በግሩ ለማቆሞ የሚደረግ ትግል ፡፡

ይህ ሰው በህወሃት ቀንበር ሥር ተሸብቦ ድምጹ የታፈነውን የዘጠና ሚልዮን ህዝብ መከራና እዳ ብቻውን የተሸከመ እስኪመስል ከምድር ጫፍ ሰሜን ዋልታ ኖርዌይ ፣ እስከምድር ግርጌ ደቡብ አፍሪቃ ፥ ከዚያም አውስትራልያ ረጅም የጢያራ ጉዞ በማድረግ ኢሳት በባለቢሊዬኖሮቹ የህወሃት ቱጃሮችና ረዳት ከበርቴዎቻቸው እንዳይዘጋ የሰው ፊት እያሳቀቀው ምጽዋት ሲለምን ይታያል፡፡ በርግጥ ከጎኑ የቆሙ ቆራጥ ወገኖቹ ቢኖሩም ፣ ዳገቱን ሲያዘግም የብርታት ከዘራ የሚያቀብሉት ወገኖች ባይጠፉም፣ በዚያው አንጻር ደግሞ ምክንያት በሌለው ጥላቻ የሚጎንጡትም አልጠፉም ፡፡
ምናልባት ከአህጉር ፥ አህጉር ለርዳታ ሲዘዋወር ፣ የደላው የሚመስላቸው ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ ፡፡ አድካሚውንና እጅግም ሲበዛ ለበሽታ አሳልፎ የሚሰጠውን ረጅም ሰዓታት የአውሮፕላን ጉዞ ከግምት ውስጥ ያላስገቡ ተቺዎች የሚሰነዝሩት ባዶ አስተያየት እና የህወሃት ጭፍሮች ጥላቻም ጭምር እንደሆነ የታወቀ ነው ፡፡ የአባት ቅርብ ክትትልን የሚጠይቀውን ፥ በትምህርት ቤት ልጆች የሚሰጣቸውን የቤት ሥራና ከወላጆች ማግኘት የሚገባቸውን እርዳታን ፍቅር በአባት እምነት እዳ ምክንያት በቅርብ የሚያጡትን ልጆቹንም ማሰብ በተገባ ነበር ፡፡ ትልቁን የጋራ የቤተሰብ ኃላፊነት ታማኝ ለወራት የኢሳትን ዓላማ ለማሳካት ሲደክም ፣ እናትም ፥ አባትም ሆና በአሜሪካን አገር ኑሮና ፥ አስቸጋሪ የደህንነት ዋስትና በተመናመነባት አሜሪካ የምትንገላታውንም ውድ ባለቤቱንም ማሰብ ባስፈለገም ነበር ፡፡ በርግጥ ታማኝ ከህወሃት ሰዎችና ደጋፊዎቻቸው ይህን ነቀፋ ስለሚጠብቅ ብዙ የሚያሳስበው ጉዳይ አይደለም ፡፡ ይህ እዳ የታማኝ በየነ ፥ ይህ እዳ የሻምበል በላይነህ ፥ ይህ እዳ የአበበ ገላው ፥ ይህ እዳ የኤርምያስ ለገሰ ወዘተ እዳ ብቻ አይደለም ፡፡ ድምጹ የተሸበበት የዘጠና ሚልዮን ህዝብ እዳ ነው ፡፡
ኢትዮጵያ ከዘረኞችና ከባንዳዎች ነጻ ስትወጣ ፣ ሁሉም በነጻነት ወደ እናት ምድሩ ሲተም ፣ በእናት አገሩም ህይወቴና ሞቴ ከርሷ ይሁን ብሎ መኖር ሲጀምር ፣ ታማኝም እንደማንኛውም ዜጋ ነው አየሯን በነጻነት የሚስበው ፡፡ ለርሱ ለብቻው አየር አይጠለፍለትም ፡፡ ለርሱ አገሪቱ ለመጠጥ ከምታቀርበው የለገዳዲም ሆነ የገፈርሳ ውሃ ውጭ ልዩ የመጠጥ ውሃ ጅረት ለብቻው አትጠልፍለትም ፡፡ ይህ እንኳ እየተሰማ ያለው ፣ ከገዥዎቻችን መንደር ብቻ ነው ፡፡ ዛሬ ሰፈሬን በባለስልጣን ሰፈር ያድርገው እየተባለ እንደሚለመነው ፣ የህወሃት ባለስልጣኖች ካሉበት መንደር መብራትም ሆነ ዉሃ በፍጹም እንደማይጠፋ ስንቶቻችን ነን የምናውቀው ? ለሃጣን በመጣ መብራትና ዉሃ በአክባቢው ያሉ ሰዎች እየበራላቸውም እየጠጡም ነው ፡፡
በኪነ ጥበቡ ዓለም የሚገኘው ሃብት የተሻለ ነው ፡፡ ዓለምን በመዞር ከሆነ ኪነጥበቡም ያዞራል ፡፡ ብብት ሳይኮረኩሩ አስቆ ሃብት በመሃረብ ሊቋጠር ይችላል ፡፡ ለአገር ነጻነትና ትንሳኤ ኢሳትን በግሩ እናቁም ተብሎ ለልመና ሲወጣ ግን የሰው ፊት ይገርፋል ፡፡ ታማኝ ባለፈው ሳምንት ኦስሎ ውስጥ በተደረገው አኩሪ የኢሳት አምስተኛ ዓመት ክብረ በዓል ዕለት እርሱም ልክ እንደፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ፣ ከንግዲህ ህዝብ ሰብስቤ አዋጡ አልልም ፡፡ በጋራ ሽክሙን ብንካፈል ወደ ነጻነት ያደርሰናል ፡፡ አናዋጣም ግን የሚሉ ካሉ አይስጉ ! የቆረጡ ሃብታቸውን አሟጠው እስከመጨረሻው የሚረዱ ቆራጥ ዜጎች አሉ ሲል እድምተኛው ረጅም ደቂቃ በቆየ ጭብጨባ ነበር ድጋፉን ያሳየው ፡፡
ታማኝ በተገኘበት ሥፍራ የሚነቅፉትን የሃሳብ ድኩማኖች አንስቶ ሲተች አልተሰማም ፡፡ ይልቅስ ወደላኳቸው አለቆቻቸው ነው በተጨባጭና በማስረጃ ያሰማሯቸው ከለቀቁት ፊልም ተነስቶ ባገናዛቢ መልኩ ራሳቸውን ሲሞግታቸው የሚስተዋለው ፡፡ እንደመሰለኝ ታማኝ መለመን ደክሞታል ፡፡ ኢሳት የህዝብ ዓይንና ጆሮ ሆኖ እንዲቀጥል እዳው መሆን ያለበት ወደ ነጻነት ናፋቂው ህዝብ ትከሻ ባስተማማኝ መልኩ እንዲሸጋገር ነው ፡፡ከዚህ በተረፈ ወዳጃችን ታማኝ የሚፈራው ታላቁ እስክንድር እንዳለው ፣ በአንበሳ ፊት አውራሪነት የመጣን የበግ መንጋን ሠራዊት እንጂ፣ በጠቦት በግ ፊት አውራሪነት የመጣን የአንበሳን ሠራዊት አይደለም የሚፈራው፡፡
I am not afraid of an army of lions led by a sheep; I am afraid of an army of sheep led by a lion.

1 comment:

  1. Tamagn beyen Ewuneti Egezeyabiheri kekifu hulu yetebikihi minimi enekuni seraheni balagizehimi Ejigi betami Akebirihalehu , Betseloti hulemi Asebihalehu Betami ewedihalehu

    ReplyDelete