Translate

Wednesday, November 18, 2015

“15 ሚሊዮን ህዝብ መደበቅ ሰማይን በመዳፍ ለመሸሸግ እንደ መሞከር ይቆጠራል” (በውቀቱ ስዩም)

Ethiopian author and poet, Bewketu Seyoumባገራችን ኣብዛኛው ዜጋ ለቀን ጉርስና ላመት ልብስ ሲታገል የሚኖር ነው፡፡ ጌቶች ደግሞ ኣማርጠው ይበላሉ፡፡ ኣማርጠው ይለብሳሉ፤በለስ ሲቀናቸው ደግሞ የሃያ ኣምስት ሚሊዮን ብር ቪላ ይቀልሳሉ፡፡ እንዲያም ሆኖ ደግሞ መከበርና መደነቅ ይፈልጋሉ፡፡ ሰው ምንም በስጋው ቢመቸው በሌላው ተመዝኖ እንደቀለለ ሲሰማው ደስተኛ ኣይሆንም፡፡ ስለዚህ ጌቶች ያስንቀናል ብለው የሚያስቡትን ነገር በሙሉ ጠምድው ይይዙታል፡፡ ይዋጉታል፡፡ ኢትዮጵያ- ጌቶች ለኩራታቸው፤ ዜጎች ለራታቸው የሚታገሉባት መድረክ ናት፡፡
ብዙ ጊዜ ረሀብ ሲከሰት ጌቶች ራብተኛውን ሁሉ ሰብስበው ጎተራ ውስጥ ሊደብቁት ይቃጣቸዋል፡፡ የድሆች የተራቆተ ሰውነት የገጠጠ ኣጥንት፤ የጌቶችን የመከበር ፍላጎት ያከሽፈዋል፡፡ ባንድ ወቅት በቦሌ መዳኒያለም ዳርቻ ስራመድ ኣካባቢው ኣለወትሮው በለማኞች ኣለመሞላቱን ታዝቤ ተገረምሁ፡፡ያዲሳባ ኣስተዳደር ፤ ለማኞችን“ በጥቃቅንና ኣነስተኛ ” ኣደራጅቶ ያሳለፈላቸው መስሎኝ ነበር፡፡ እንደተሳሳትሁ ለመረዳት ጥቂት ደቂቃ በቦታው መቆም ነበረብኝ፡፡ ኣንዲት ተመጽዋች ሴት ልጇን ይዛ ከቅጽሩ ስር ለመቀመጥ ስታነጥፍ ፖሊስ በቆረጣ ገብቶ “ዞር በይ ነግሬሻለሁ” እያለ ሲያዋክባት ተመለከትሁ ፡፡ የደነገጠ ልጇን እየጎተተች ተወገደች፡፡ ከዚያ ወዲያ ከኣቡነ ጳውሎስ ሃውልት በቀር ባካባቢው ደፍሮ የቆመ ኣልነበረም፡ ፡ ወደ ቤቴ ከመሄዴ በፊት ያቡኑን ወፍራም ሀውልት ዞር ብየ ሾፍኩት፡፡ እጁን እንደ ራሱ ሀይሉ ሙርጥ ገትሮ ከፊትለፊት ያለውን “ሬድዋን ህንጻ” ሲባርክ ነበር፡፡
“ገጽታ ግንባታ?”
በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን የፍርድ ምኒስተር የነበሩት ኣፈንጉስ ነሲቡ የሌባ ብዛት ቢያስቸግራቸው ኣንድ መላ መቱ፡፡ ሲሰርቅ የተገኘ ወሮበላ ግንባሩ ላይ በጋለ ስለት ምልክት እንዲደረግበት ደነገጉ፡፡ ታድያ ሌቦች የዋዛ ስላልነበሩ ሻሽ በመጠምጠም የግንባራቸውን ጠባሳ ሊሰውሩት ሞክረዋል፡፡ በጊዜው ደግሞ ሻሽ መጠምጠም ካክሱም ዘመነ መንግስት ጀምሮ የወረደ የነገስታቱና የመሳፍንቱ ወግ ነበር፡፡ ጮሌ ሌቦች ውርደታቸውን ከመሸፈን ኣልፈው የንጉስ ገጽታ ተላብሰው ብቅ ኣሉ፡፡
በዘመናችን የተራቡ ዜጎችን መደበቅ እንደ ገጽታ ግንባታ የሚቆጥሩ ሰዎችን ከባለሻሽ ሌቦች ለይቼ ኣላያቸውም፡፡
በነገራችን ላይ፤ ብርቱካን ኣሊ ግለሂስ ያደረገችበትን ዘገባ ካየሁ በኋላ ለጊዜው ለመናደድ እንኳ ቸግሮኝ ነበር፡፡ ዘገባውን የሠራው ጋዜጠኛ እንዲህ ኣይነቱን ካንድ ድንጋይ የተጠረበ ደደብነት ተሸክሞ የመኖር ችሎታው በጣም ኣስደነቀኝ፡፡ በዚህ በሰላቢው ቀን ይቅርና፤ በደህናው ቀን እንኳ የባላገሩን ራብና መከራ ከጉያው የበቀልን ልጆቹ እናውቀዋለን ፡፡ ኣስራ ኣምስት ሚሊዮን ህዝብ መደበቅ ሰማይን በመዳፍ ለመሸሸግ እንደ መሞከር ይቆጠራል፡፡ መመፍትሄው በተቸገሩ ሰዎች ጫማ ቆሞ ነገሮችን መመልከት ነው፡፡ ለነገሩ ችግርን ያልቀመሰ ሰው ለችግረኛ መራራት እንዴት ይቻለዋል?
ኣብን ተውትና ፤ንገሩት ለወልድ
ተገርፏል ተሰቅሏል ፤ እሱ ያውቃል ፍርድ
እንዲል ባላገር፡፡

No comments:

Post a Comment