Translate

Friday, October 23, 2015

የቃሊቲ ማረሚያ ቤት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ እንደሌሉ ገለፀ (ነገረ ኢትዮጵያ)

• ‹‹የስርዓቱን ሽፍትነት ያመላክታል›› 3ኛ ተከሳሽ አቶ ደናሁን ቤዛ
• ‹‹የሚቀርብልን ምግብ ለእንሰሳትም መቅረብ የማይገባው ነው›› 2ኛ ተከሳሽ አቶ አሸናፊ አካሉ
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
Ato Andargachew Tsige, Ginbot 7በእነ ዘመነ ካሴ የክስ መዝገብ ከ2ኛ -5ኛ መዝገብ ለተከሰሱት አቶ አሸናፊ አካሉ (2ኛ ተከሳሽ)፣ አቶ ደናሁን ቤዛ (3ኛ ተከሳሽ)፣ አቶ ምንዳዬ ጥላሁን (4ኛ ተከሳሽ) እና አቶ አንሙት የኔዋስ (5ኛ ተከሳሽ) በመከላከያ ምስክርነት የተጠቀሱት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንደሌሉ ማረሚያ ቤቱ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛው ወንጀል ችሎት በላከው ደብዳቤ ገልፆአል፡፡ 19ኛ ወንጀል ችሎት ሀምሌ 29/2007 ዓ.ም የቃሊቲ ማረሚያ ቤት አቶ አንዳርጋቸውን ለምን እንዳላቀረበ እንዲያብራራ፣ እንዲሁም ለምስክርነት እንዲያቀርብ ለዛሬ ለጥቅምት 12/2008 ዓ.ም ለአራተኛ ጊዜ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበር ቢሆንም ማረሚያ ቤቱ አቶ አንዳርጋቸው ቃሊቲ እንደሌሉ በደብዳቤ አሳውቋል፡፡
ተከሳሾቹ ማረሚያ ቤቱ ሲያጉላላቸው ቆይቶ አሁን የለም ማለቱ ትክክል እንዳልሆነ የገለፁ ሲሆን 2ኛ ተከሳሽ አቶ አሸናፊ አካሉ ማረሚያ ቤቱ ምላሽ የሰጠው በአራተኛው ትዕዛዝ መሆኑን ጠቅሶ የፍርድ ሂደታቸውን ከሚገባው በላይ እያጓተተ እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ ገልፆአል፡፡ ‹‹መከላከል ከጀመርን አንድ አመት ከስድስት ወር ሆነ፡፡ በግዞት ነው ያለነው፡፡ የሚቀርብልን ምግብ ለእንሰሳትም መቅረብ የማይገባው ነው›› ያለው አቶ አሸናፊ የማረሚያ ቤቱን ምላሽ ‹‹ፌዝ ነው›› ብሎታል፡፡
3ኛ ተከሳሽ አቶ ደናሁን ቤዛ በበኩሉ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን በመከላከያ ምስክርነት ሲጠቅሱ አቃቤ ህግ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ የሞትና የእድሜ ልክ ፍርደኛ እንደሆኑ በመጠቆም ተቃውሞ አሰምቶ እንደነበር፣ የእድሜ ልክና የሞት ፍርደኛ ቃሊቲ እንደሚታሰር ገልፆ ማረሚያ ቤቱ አቶ አንዳርጋቸው እንደሌሉ መግለፁ ‹‹የስርዓቱን ሽፍትነት ያመላክታል›› ብሏል፡፡ ‹‹የእድሜ ልክ ወይንም የሞት ፍርደኛ የት ነው የሚታሰረው?›› ሲልም ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡
3ቱ ተከሳሾች የፀረ ሽብር ግብረ ኃይሉና ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ አንዳርጋቸውን እንደያዙ በቴሊቪዥን መግለፃቸውን አስታውሰው አሁንም ለሁለቱ አካላት ደብዳቤ እንደሚፅፉ ለፍርድ ቤቱ አሳውቀው የነበር ቢሆንም ከ6ኛ-9ኛ ያሉት ተከሳሾች ማረሚያ ቤቱ በፈጠረው ችግር የአቶ አንዳርጋቸውን ምስክርነት ለመስማት የፍርድ ሂደታቸው እየተጓተተባቸው በመሆኑ የአቶ አንዳርጋቸው ምስክርነት ቀርቶ ብይን እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
ሆኖም ግን 4ኛ ተከሳሽ አቶ ምንዳዬ ጥላሁን ‹‹ከአንዳርጋቸው ጋር ተገናኝተህ መመሪያ ተቀብለሃል ስለተባልኩ አቶ አንዳርጋቸው መጥቶ መመስከር አለበት›› ሲል አሁንም አቶ አንዳርጋቸው እንዲቀርቡለት ጥያቄውን አቅርቧል፡፡ ፍርድ ቤቱም 4ኛ ተከሳሽ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ እንዲቀርቡለት የሚያቀርበውን አቤቱታ ተመልክቶ ይገኙበታል ተብሎ ለታሰበው ተቋም ትዕዛዝ ለመስጠት ለጥቅምት 23/2008 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

No comments:

Post a Comment