Translate

Saturday, October 10, 2015

ነጻ አውጪ ግምባር አገዛዝ እንጂ መንግሥት አይመሠርትም

"ረሃቡ የገዥው ፓርቲ የፖሊሲ ውድቀት ነው!" ሰማያዊ ፓርቲ

tplf haile debretsion

ላለፉት 25 ዓመታት በነጻ አውጪ ግምባር ስም ኢትዮጵያን እየገዛ ያለው የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር “ኢህአዴግ” ብሎ በፈጠረው ስያሜ አገር በግፍ እየገዛ መሆኑ ሳያንስ በየአምስት አመቱ በሚያካሂደው “ምርጫ” የሚመሠርተው “መንግሥት” መፍትሔ ሊሰጥ እንደማይችል መድረክ አስታወቀ። ሰማያዊ ፓርቲ በበኩሉ በኢትዮጵያ ለተከሰተው ረሃብ የአገዛዙ ፓርቲ ተጠያቂ ነው ይላል።

የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ “ኢህአዴግ ያቋቋመው መንግስት መፍትሄ አይሰጥም ተባለ” በሚል ርዕስ ያወጣው ዜና ከዚህ እንደሚከተው ይነበባል:-
ኢትዮጵያ ውስጥ እየተስተዋለ ያለው ረሃብ የገዥው ፓርቲን ፖሊሲ ውድቀት ያሳያል ሲል ሰማያዊ ፓርቲ ከሰሰ፡፡
ኢህአዴግ ያቋቋመዉ አምባገነን መንግስት ለኢትዮጵያ መሰረታዊ ችግሮች መፍትሄ ሊሰጥ አይችልም ሲል ታቃዋሚዉ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ አስታወቀ።
የ2007ቱን የምርጫ ሂደት የተቹት አመራሮቹ ህግ ወጥ የሆነ ነገር እየተንከባለለ መጥቶ መንግሥት ምስረታ ላይ ደርሷል ብላል።
በተያያዘ ዜናም የፊታትን ቅዳሜና እሁድ በጠቅላይ ሚንስትር ደሳለኝ ኃይለማሪያም ሰብሳቢነት የሚካሄደው የእድገትና የለውጥ ሽግግር እቅድ ስብሰባ ላይ ቢጋበዙም የማይገኙ መሆናቸውን የተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እየገለጹ ነው።
መድረክ የሰጠዉን መግለጫ የተከታተለው እስክንድር ፍሬዉ ተከታዮን ዘግቧል። ለማዳመጥ እዚህ ላይ ይጫኑ።
ይህ በ እንዲህ እንዳለ የሰማያዊ ፓርቲ “ረሃቡ የገዥው ፓርቲ የፖሊሲ ውድቀት ነው!” በሚል ርዕስ የሚከተለውን መግለጫ ሰጥቶዋል:-
ገዥው ፓርቲ ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ህዝብ በቀን ሶሰት ጊዜ እንደሚመግብ ቃል ሲገባ ቆይቷል፡፡ በተለይ ባለፉት 10 አመታት ጀምሮ ኢኮኖሚውን በሁለት ዲጅት እያሳደገ እንደሚገኝ ልሳኑ ባደረጋቸው የመንግስት ብዙሃን መገናኛዎች በረሃብና በርዛት እየተሰቃየ ለሚገኘው ህዝብ መልሶ እየነገረ ይገኛል፡፡ ይሁንና ይህ ስርዓቱ ሀገሪቱን ወደመካከለኛ ገቢ ያደርሳል የሚለው እድገት ለጥቂት ጊዜያት በተከሰተና በተለመደ የዝናብ እጥረት የሚከሰትን ድርቅ እንኳ መቋቋም አቅቶት ዜጎቻችን በተደጋጋሚ የረሃብ ሰለባ ሲሆኑ ቆይተዋል፡፡
በተለይ በዚህ ወቅት በመላ ሀገሪቱ የተከሰተው አስደንጋጭ የረሃብ አደጋ ዜጎችን ለከፋ ስቃይና መከራ ዳርጓቸዋል፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከ7.5 ሚሊዮን በላይ ዜጎቻችን ለከፋ የረሃብ አደጋ ተጋልጠዋል፡፡ ከ40 ሺህ በላይ ህፃናት የረሃቡ ሰለባ ሆነዋል፡፡ ከግጦሽና ከውሃ እጥረት የተነሳ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የቤት እንሰሳት እየሞቱ ነው፡፡ ረሃቡ ባልጠናባቸው አካባቢዎች ሳይቀር አርሶ አደሩም ሆነ አርብቶ አደሩ ነፍሱን ለማዳን የእርሻ በሬዎቹን ሳይቀር ለገበያ እያቀረበ በርካሽ ዋጋ ለመሸጥ ተገዷል፡፡
ገዥው ፓርቲ ችግር ቢከሰት እንኳ በአደጋ ጊዜ ለዜጎች የሚበቃ እርዳታ አቀርባለሁ ሲል የነበረ ቢሆንም ለወገኖቻችን ግን የሚደርስላቸው አልተገኘም፡፡ ይባስ ብሎም ለዜጎች ዓለም አቀፍ ተቋማት እንዳይደርሱላቸው የተፈጠረው ረሃብ የራሱ የፖሊሲ ውድቀት መሆኑን የሚያውቀው ስርዓቱ የዜጎቻችን ስቃይና መከራ ሲሸፋፍን ከርሟል፡፡ ከአቅሙ በላይ ሲሆን ችግሩ እንደተከሰተ ቢገልፅም ለዜጎች ተገቢውን እርዳታ በሚያስገኝ መልኩ እርምጃ እየወሰደ አይደለም፡፡ በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ፣ በአፋር፣ በደቡብ፣ ትግራይ፣ በአማራ፣ በሶማሊና በሌሎቹም ክልሎች በተከሰተው ረሃብ ዜጎች ከፍተኛ ችግር ላይ ናቸው፡፡ ለተከሰተው የረሃብ አደጋ ተገቢው ትኩረት መነፈጉ ገዥው ፓርቲ እመራዋለሁ ለሚለው ህዝብ ደንታ ቢስነቱን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ረሃቡ፣ ርዛቱ፣ ድህነቱ፣ ስደቱ፣ ስራ አጥነቱ፣ የኑሮ ውድነቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዜጎችን በብርቱ እየተፈታተኑ በሚገኝበት ወቅት ገዥው ፓርቲና በስሩ ያሉ ድርጅቶች ተመሰረትንበት የሚሉትን ጊዜ ለወራት በቅንጦት በማክበት በብዙ ሚሊዮን ገንዘብ ከኢትዮጵያውያን ጉሮሮ ነጥቆ ድግስ ሲደግስና አሸሸ ገዳሜ ሲል በርካታ ኢትዮጵያውያንን አሳዝኗል፡፡
ለተከሰተው ረሃብ ኢህአዴግ ለይስሙላ ቆሜለታለሁ የሚለውን አርሶ አደርና አርብቶ አደርን ህይወት ለማሻሻል የረባ ስራ እንዳልሰራ ያረጋገጠ ነው፡፡ ግብርናው ኢኮኖሚውን ይመራል ቢልም እስካሁን ግን በየአመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የረሃብ ሰለባ እንደሆነ ቀጥለዋል፡፡ መሬት የመንግስት ነው በሚል ሽፋን አርሶ አደሩን ከቀየው እያፈናቀለ ለስርዓቱና ደጋፊዎችና ለባዕዳን መሬትን እየሸጠ አርሶ አደሩን ለረሃብ ተጋላጭ አድርጎታል፡፡ በስርዓቱ የፖሊሲ ውድቀት የተፈጠረውን አደጋ ለመሸፋፈን በሚያደርገው ጥረትም በርካታ ኢትዮጵያውያንን የችግሩ ሰለባ እየሆኑ ነው፡፡
ቢዘገይም ፓርቲያችን ሰማያዊ ገዥው ፓርቲ ለወገኖቻችን የሲቃ ድምፅ ጆሮ ዳባ ማለቱን አቁሞ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ እንጠይቃለን፡፡ በተለይ ስለ ችግሩ ለኢትዮጵያውያንና ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ስለ ረሃቡ በደንብ የሚያስረዳ ገለልተኛ አካል ተቋቁሞ ለዜጎቻችን መፍትሄ እንዲፈለግ እንጠይቃለን፡፡ ስርዓቱ ደካማና ኃላፊነት የጎደለው እንደመሆኑ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ኢትዮጵያውያንና የዓለም ማህረሰብ ከወገኖቻችን ጎን እንዲቆሙ ጥሪ እናቀርባለን፡፡ በዋናነት ግን ይህ የኢትዮጵያውያን መከራ የመነጨው ከገዥው ፓርቲ የተሳሳተ ፖሊሲ፣ የአፈፃፀም ብቃት ችግርና ለኢትዮጵያውያንም ባለው ግድየለሽነት መሆኑን ተገንዝበን ይህን ለችግሮቻችን ምንጭ የሆነ ስርዓት በቁጥርጠኝነት መታገል እንዳለብን ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
ድል የህዝብ ነው!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
መስከረም 27 ቀን /2008 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment