Translate

Friday, March 6, 2015

የአድዋ ድልን እያከበርን ለዛሬ ነፃነታች ቃል እንግባ!

pg7-logoመቶ አስራ ዘጠነኛውን የአድዋ ድል በዓል እየዘከርን እንገኛለን። እንደዛሬው ሁሉ ያኔም ቀደምቶቻችን በርካታ የውስጥና የውጭ ችግሮች ነበሩባቸው። እንደዛሬው ሁሉ ያኔም በመካከላቸው የሀሳብና የጥቅም ልዩነቶች ነበሩ። ያም ሆኖ ግን ቀደምቶቻችን በአገር ነፃነት ጉዳይ ላይ ሰፋ ያለ መግባባት ላይ መድረስ በመቻላቸው በዘመናዊ የጦር መሣሪያዎችና ድርጅት የተጠናከረውን የአውሮፓ ጦር በጥቁር የጦር አዛዦችና ተዋጊዎች መመከት ቻሉ። ከአድዋ በፊት አፍሪቃ በተለይም ኢትዮጵያ ውስጥ አውሮፓዊያን የተሸነፉባቸው ተናጠል አውደ ውጊያዎች ነበሩ፤ ጦርነትን ሲሸነፉ ግን አድዋ የመጀሪያው ነው። በዚህም ምክንያት ነው የአድዋ ድል የአፍሪቃውያን ከዚያም አልፎ የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ድል ተደርጎ የሚወሰደው።

ዛሬ ግን እኛ ያኔ የነበሩት አያትና ቅድመ አያቶቻችን እደረሱበት የመግባባት ደረጃ ላይ መድረስ ባለመቻላችን አገር በቀሉን ቅኝ ገዢ – ህወሓትን – ከኢትዮጵያዊያን ጫንቃ ላይ ማውረድ አቅቶን አገራችንና ሕዝቧን ከባዕድ በባሰ ሁኔታ እያዋረደ በመግዛት ላይ ይገኛል።
ያኔ ለሀገሩ፣ ለነፃነቱና ለክብሩ ቀናዒ የሆነው ኢትዮጵያዊ ራሱን ወታደር አድርጎ በየጎበዝ አለቃው አዝማችነት በጠላት ላይ ዘምቶ ድልን ተቀዳጅቷል። ዛሬ ግን ቁጥሩ ቀላል ያልሆነ የመከላከያ ሠራዊት አባል ለህወሓት አዛዦች ሎሌነት አድሮ የራሱን ወገን ይፈጃል። ያኔ በአገዛዙ ላይ ብሶት የነበረው እንኳን ሳይቀር ብሶቱን ችሎ ለሀገር ሉዓላውነትና ክብር ሲል ተዋድቋል። ዛሬ ግን ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑ ወገኖቻችን የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም ከብሶቶቻቸው በላይ አሻግረው መመልከት ተስኗቸዋል።
ዛሬ 119ኛውን የአድዋ ድል በዓል አያቶቻችንን በማድነቅ ብቻ ልናሳልፈው አይገባም። የአያቶቻችንን ገድል ስናከብር ዛሬ የምንገኝበትን ሁኔታ መመዘን ይገባናል። ራሳችንን ከእነሱ ጋር በማስተያየት እንደምን ያለን ውለታ መላሽ ያልሆንን የልጅ ልጆች መሆናችንን መመዘን እና ራሳችንን መውቀስ ይገባናል። የሚሳዝነው ዛሬ ራሱን ከሚወቅሰው በላይ አያቶቹን የሚወቅስ መብዛቱ ነው። እነሱ ችግሮችን ተሻግረው የምንኮራበትን ድል አቀዳጅተውን አልፈዋል። እኛ ግን እነሱ ያቆዩልንን ድል እንኳን ማስጠበቅ አልቻልንም። ከአድዋ ድል አንድ መቶ አስራ ዘጠኝ ዓመታት በኋላ አገራችንን ለህወሓት የአገር ውስጥ ቅኝ አገዛዝ ማስረከባችን ሊያመንና ሊያንገበግበን ሲገባ ድሮ ሊደረጉ ሲችሉ አልተደረጉም በምንላቸው ነገሮች ላይ እየተከራከርን ግዜያችንን እናጠፋለን።
አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ታላቁን የአድዋን ድል ለአጎናፀፉን ቀደምቶቻችን ያለንን ክብር መግለጽ ያለብን ዛሬ አገራችን ከህወሓት የአገር ውስጥ ቅኝ አገዛዝ ነፃ ለማውጣት በምንገባው ቃል ኪዳን ነው ብሎ ያምናል። አገራችንን በቅኝ ግዛትነት እያስገዛን የቀደምቶቻችንን ድል መዘከር ለእኛ ለልጆቻቸዉ የሚያሳፍር ተግባር ነው ብሎ ያምናል። አርበኞች ግንቦት 7 የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት አገር በቀል ቅኝ ገዥ በሆነው ሕወሓት እየተመራ የኢትዮጵያን ሕዝብ የማዳከሙን ተግባር በአስቸኳይ ማቆም ይኖርበታል ብሎ ያምናል። ስለሆነም የመከላከያ ሠራዊት አባላት ልባችሁንም ክንዳችሁንም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር አድርጉ። ቀደምት አባቶቻችን አድዋ ላይ ድል የነሱት ቅኝ ገዥ ዛሬ ቀለሙን ለውጦ “ህወሓት” ተሰኝቶ ያንተ አዛዥ ሆኗል። መሣሪያህን በህወሓት አዛዦችህ ላይ የምታዞርበት ወቅት አሁን ነው። ንቃ፤ ተነስ!
አገርን ለጠላት አስረክቦ በቀደምት ጀግኖች ታሪክ መኩራት አሳፋሪ ነው። አባቶቻችን በነፃነት ያቆዩልን አገር የህወሓት መፈንጫ ሆና ማየት የሚያሸማቅቅ ነው። የጀግኖች አያቶቻችን የልጅ ልጆች መሆናችንን የምናስመሰክረው አገራችንን ከህወሓት አገዛዝ ነፃ ስናወጣና የዜጎቿ መብቶች የተከበሩባት ፍትህና እኩልነት የሰፈኑባት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ስንመሠርት ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዚህ ታላቅ ዓላማ ይነሳ ሲል አርበኖች ግንቦት 7 ጥሪ ያስተላልፋል።
አርበኞች ግንቦት 7: የአድዋ ድልን እያከበርን ዛሬ ነፃነታችንን ለማስከር ለመታገል ቃል እንግባ ይላል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!

No comments:

Post a Comment