Translate

Sunday, March 22, 2015

ሰማያዊ ፓርቲ ስለ ወጣት ታጋዮቹ መታሰር ምንም አለማለቱ እያነጋገረ ነው

እየሩሳሌም ተስፋው፣ በርሃኑ ተክለያሬድ እና ፍቅረማርያም አስማማው የተባሉት ታዋቂና ወጣት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ወያኔ የፖለቲካ እስረኞችን በሚያጉርበትና ስቃይ በሚፈጽምበት ማዕከላዊ እስር ቤት እንደሚገኙ ታውቋል።Semayawi party youth arrested
ወጣቶቹ በማዕከላዊ እስር ቤት መሆናቸው በይፋ ከመታወቁ በፊት ጓደኞቻቸው እና ቤተሰቦቻቸው የት እንዳሉ ሳያውቁ ሰንብተዋል።
ወጣቶቹ የት እንዳሉ ባልታወቀበት ሰዓት አንዳንድ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ከወጣቶቹ መሰወር ጋር በተየያያዘ በፌስቡክ ላይ የሚያውቋቸውን እነርሱ የአርበኞች ግንቦት 7 አባላት ወይንም ደጋፊዎች ያሏቸውን ግለሰቦች ሲወቅሱ ከርመዋል።
እንደ ሰማያዊ ፓርቲ አባላት ወቀሳ ከሆነ ኢሳት በማዕከላዊ ታስረው ስለሚገኙት የሰማያዊ ፓርቲ ወጣቶች “ወጣቶቹ አርበኞች ግንቦት 7ን ለመቀላቀል ሲንቀሳቀሱ ታሰሩ” ብሎ መዘገብ ነበረበት ይላሉ።
ኢሳት በዚህ ጉዳይ ላይ ይፋዊ መልስ ባይሰጥም የኢሳት ባልደረባ የሆነው ጋዜጠኛ ደረጀ ሃብተወልድ የሚከተለውን ብሏል፣
ይድረስ ለሰማያዊዎች!
ከሁሉም በቅድሚያ የሰማያዊ ልጆች ተይዘው ታስረዋል በመባሉ የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን እገልጻለሁ።
በመጀመሪያ የማዝነው እነዚያ የሚያሣሱ ወጣቶች በክፉዎች መዳፍ ስር በመግባታቸው ሲሆን፤ ሁለተኛው ምክንያቴ ደግሞ ገዥው ፓርቲ ይህን ጉዳይ ሰበብ አድርጎ በፓርቲያችሁ እንቅስቃሴ ላይ እንቅፋት ሊፈጥርባችሁ ይችል ይሆናል የሚል ስጋት ስላደረብኝ ነው።(ምንም የአንድን አባል ፍላጎትና ውሳኔ መቆጣጠር ባትችሉም)
ይህ እንዳለ ሆኖ “ተይዘዋል” የተባሉትን ልጆች አስመልክቶ በፌስቡክ ላይ እየተሰራጬ ያለው ጽሁፍ ግራ አጋብቶኛል።
-አንዱ ግራ ያጋባኝ ነገር አንዳንድ ሰዎች ጉዳዩን ከኢሳት ጋር ሲያያይዙት በማዬቴ ነው።
-ሁለተኛው ነገር ልጆቹ ለፖሊስ ምን ብለው ቃላቸውን እንደሰጡ ባልታወቀበት ሁኔታ በጉዳዩ ላይ በእርግጠኝነት መጻፍ ፤ በልጆቹ ላይ ለመመስከር ከመቸኮል በምን ይለያል? ምናለ ጥቂት ትእግስት ቢኖር? የሚል ነው።
እሽ እናንትስ የሆነ ነገር ብትሉ ስጋታችሁን እረዳለሁ። አንዳንድ ሰዎችም ከቅንነት በመነሳት ቁጣቸውንና ንዴታቸውን መግለጻቸው የሚጠበቅ ነው። ሁላችንም ብንሆን የምናደርገው ነው።
በሌላ በኩል ግን እንደነ ግርማ ዐይነቶቹ የፓርቲ ሽኩቻና ቂም ያለባቸው የሌሎች ድርጅት ሰዎች ይችን ምክንያት አድርገው ቂማቸውንና ጥላቻቸውን ለመወጣት ሲሉ፣ ለልጆቹ ቅንጣት ታህል ባለማሰብ፣ ያለምንም መረጃ( በዘፈቀደ ) እንደመጣላቸው ጉዳዩን ሲያራግቡት ማዬት በጣም ያሳዝናል።
በጥያቄ ላጠቃልል፦
ኢሳቶች ምን አጠፋን? እስኪ ከላይ ከጠቀስኩት ውጪ የኢሳት ስህተት የምትሏቸውን አንድ፣ሁለት ብላችሁ ጠቁሙንና በስብሰባችን በግልጽ እንነጋገርባቸው።እንወያይባቸው።
ኢሳት ስህተት ሠርቶ ከተገኘ፤ በበኩሌ በአደባባይ ይቅርታ ለመጠየቅ ዝግጁ ነኝ።በአደባባይ ይቅርታ መጠየቅ ቀላል አይደለም። ኃላፊነትን መውሰድ፣እዳን መሸከም… ማለት ነው።
ከስሜት ውጪ ሰከን ብለን እንነጋገር።
ይህ በዚህ እንዳለ ወጣቶቹ በማዕከላዊ እስር ቤት መሆናቸው ከታወቀ በኋላ ደግሞ ኢሳት የሚከተለውን ዜና አሰራጭቷል፣
መጋቢት ፱(ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-3 የሰማያዊ ፓርቲ አባላት መታሰራቸውን ለኢሳት የደረሰው መረጃ አመለከተ።
ወጣት ብርሃኑ ተክለያሬድ፣ ወጣት ፍቅረማርያም አስማማውና እየሩሳሌም ተስፋው ካለፉት 2 ሳምንታት ጀምሮ በማእከላዊ እስር ቤት ውስጥ እንደሚገኙ ኢሳት አረጋግጧል።
ወጣቶቹ በምን ምክንያት እንደታሰሩ ለማወቅ አልተቻለም። መንግስትም እስካሁን የሰጠው ይፋ መግለጫ የለም። በሌላ በኩል ደግሞ የፓርቲው ሊ/መንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ወደ ሰሜን አሜሪካ በማቅናት በመጪው ግንቦት በሚካሄደው ምርጫ ውስጥለሚሳተፉ የሰማያዊ ፓርቲ እጩዎች ገንዘብ እንደሚያሰባስቡ የአንድነት የሰሜን አሜሪካ ድጋፍ ማህበርና የሰማያዊፓርቲ ሰሜን አሜሪካ ድጋፍ ማህበር በጋራ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ኢ/ር ይልቃል በኢትዮጵያ የምርጫ ሂደት ምን ይመስላል፣ ምርጫው ውስጥ መቆየት ያለው ፋይዳ፣ የሰማያዊ ፓርቲ አጠቃላይ ገፅታና እንቅስቃሴ ምን ይመስላል፣ በሚሉት ጥያቄዎች ላይ ውይይት እንደሚያደርጉ ኮሚቴው ገልጿል፡፡
የፓርቲውን የሰላማዊ ትግል ስትራቴጂዎች በውጭ ሀገር ለሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ማስረዳትና በነዚህ ጉዳዮች እንዲሁም ባጠቃላይ የአገራችን ወቅታዊ ሁኔታዎች ዙሪያ ከኢትዮጵያዊያን ጋር ዉይይት ማኪያሄድም የዝግጅቱ አንድ አካል መሆኑም በመግለጫው ተጠቅሷል።
እየሩሳሌም ተስፋው፣ በርሃኑ ተክለያሬድ እና ፍቅረማርያም አስማማው በማዕከላዊ እስር ቤት ናቸው፣ ለምንና እንዴት ለእስር እንደበቁ ከፓርቲያቸው ሰማያዊም ይሁን ካሰሯቸው ወያኔዎች ምንም የተሰማ ነገር የለም። በተለይም ሰማያዊ ፓርቲ አባላቱ ሲታሰሩ ጉዳዩን ተከታትሎ ስለ ታሳሪዎቹ ሁኔታ ለህዝብና ለቤተሰቦቻቸው መግለጽ ያለበት ይመስለናል።

No comments:

Post a Comment