Translate

Thursday, December 25, 2014

ለሰብአዊነት ቅድሚያ የሰጠ ኢትዮጵያዊ! አብርሃ ደስታ – ከፍኖተ-ነፃነት

Abraha-Destaትግራይ ክልል ላይ የሚፈፀሙትን ጭቆናዎች ሳይታክት አጋልጧል። ዘረኝነትን ፣ አምባገነንነትን ፣ ሙሰኝነትን ፣ ኢ-ፍትሐዊነትን አውግዟል።ሰብአዊነትን በማስቀደም ሰውን በሰውነቱ የሚለካ ምርጥ ኢትዮጵያዊ ነው-አብርሃ ደስታ፡፡ አብርሃ ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የብዙ ሰዎችን ቀልብ ለመሳብ ከመቻሉም በላይ ፤ “ፌስቡክን” ከፌዝ-ቡክነት በመታደግ የተለያዩ ጠቃሚ መረጃዎችን ሲያቀብለን ነበር፡፡
በመግቢያችን ላይ በአጭሩ እንደተገለጸው ይህ ድንቅ ኢትዮጵያዊ ፣ የአሁኑ የፖለቲካ እስረኛ አብርሃ ደስታ በአንድ ወቅት ከፍኖተ-ነፃነት ባልደረባ ጋር ያደረገው ወግ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

በቀዳሚነት የቀረበለት ጥያቄ “በመጪው ምርጫ ተቃዋሚዎች የሚያሸንፉ ይመስልሀል? የሚል ነበር፡፡ የሠጠው ምላሽ
“በተቃውሞ ጎራ ውስጥ ያሉ ሀቀኛ ተቃዋሚዎች ምርጫን እንደ ግብ ማየት የለባቸውም፡፡ በምርጫ መሳተፍን እንደ መንገድ (means) እንጂ እንደ ውጤት (end) ሊወስዱት አይገባም፡፡ በምርጫ መሳተፍን የሚቀበሉ የምርጫ ፓርቲዎች የተናጠል ጉዞ የትም እንደማያደርስ ተገንዝበው አንድ ላይ መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የተናጠል ትግል ተጠቃሚ የሚያደርገው ገዢውን ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ ምርጫ 1992ትን ብንመለከት በዚህ ምርጫ ላይ ገዢው ፓርቲ በአንድ ምርጫ ጣቢያ ላይ በርካታ እጩዎች እንዲመዘገቡ በማድረግ ድምፅ እንዲከፋፈል ተግቶ ሰርቷል፡፡ በአንድ የምርጫ ጣቢያ ላይ ከ20 በመቶ በሚያንስ ድምፅ ብቻ ገዢው ፓርቲ ማሸነፉ ይታወሳል፡፡ ይህ ለምን ሊሆን ቻለ? የሚለውን ብንመለከት በአንድ የምርጫ ክልል ላይ በርካታ እጩዎችን አስርጎ በማስገባት የተቃዋሚዎች ድምፅ እንዲከፋፈል ስለተደረገ ነው፡፡ በወቅቱ ተቃዋሚዎችም በህብረት ከመታገል ይልቅ በተናጠል መታገልን መርጠው እንደነበር የሚዘነጋ አልነበረም፡፡ ከዚህ በመነሳት ነው የተናጠል ትግል አያዋጣም የትም አያደርስም የምልህ፡፡ ስለሆነም በመጪው ምርጫ ጠንካራ የሚባሉት ፓርቲዎች ቢቻል ውህደት ካልሆነም ግንባር ፈጥረው ከታገሉና ህዝቡ ጋር በደንብ ከተገናኙ ገዢውን ቡድን በምርጫ የማያሸንፉበት ሁኔታ አይታየኝም፡፡
ትልቁና አሳሳቢው ጉዳይ ገዢው ቡድን በምርጫው ሲሸነፍ ወይም እንደሚሸነፍ ሲያውቅ የሚወስደው እርምጃ ነው፡፡ በዚህ ሰዓት ላይ ኮሮጆን ከመገልበጥ አንስቶ እስከመግደል የሚዘልቅ እርምጃ ሊወስድ ይችላል፡፡ ስርዓቱ ጡንቻውን ማሳየት የጀመረ ጊዜ ህዝቡ እምቢተኝነቱን በተግባር ሊያሳይ ይገባል፡፡ ድምፁ ሲሰረቅ በዝምታ መመልከት አይኖርበትም፡፡ ለድምፁ መከበር ራሱ ዘብ ሆኖ መቆም ይኖርበታል፡፡ ህዝቡ ከራሱ ውጪ ለራሱ ድምፅ የሚቆምለት አንድም አካል እንደሌለ ተረድቶ ድምፁን ማስከበር ይጠበቅበታል፡፡ ህዝቡ ግዴታውን በዚህ መልክ ከተወጣና ሀቀኛ ተቃዋሚዎችም የተናጠል ትግሉን ትተው በህብረት ከታገሉ ይህን ስርዓት በምርጫ የማያስወግዱበት አንዳች ምክንያት የለም፡፡” የሚል ነበር፡፡
አብርሃ ፣ በምሳሌነት ያነሳውን የምርጫ 92ቱን ሁነት የቀድሞው የመንግስት ኮሚኒኬሽን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኤርሚያስ ለገሠ ፣ “የመለስ ትሩፋቶች ባለቤት አልባ ከተማ” በሚለው መፅሀፉ ላይ አንድን ወረዳ በምሳሌነት በማንሳት በወቅቱ ስለነበረው ሁነት እንዲህ ይተርክልናል፡፡
“በወረዳ 24 ለፓርላማ የቀረቡት የተቃዋሚ ፓርቲ እጩዎች ከአራት በላይ መሆናቸው እና የራሳቸው ደጋፊ ያላቸው መሆኑ በተጨማሪነት ጠቀመን፡፡ ኢዴፓን ወክሎ የቀረበው ክንፈሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ) በወጣቶች ፣ ክፍሌ ጥግነህ (የቅንጅት አመራር የነበረ) በምሁራንና ነጋዴው ማህበረሰብ ፣ የትግረ ወርጂው ሀጂ መሃመድ በሙስሊም ዘንድ ተቀባይነት ነበራቸው፡፡
የሰርቶ አደር ጋዜጣ አዘጋጅ የነበረው ታዲዮስ ታንቱ በቀድሞ ስርዓት ደጋፊዎችና ወታደሮች ድጋፍ አግኝቷል፡፡ ሌሎቹ የግል ተወዳዳሪ እጩዎች በእኛ የቀረቡ ሲሆን ኢህአዴግን መምረጥ በማይፈልገው አካባቢ ድምፅ እንዲሻሙ የተዘጋጁ ናቸው። በመሆኑም በአብላጫ ወንበር አሰራር መሰረት ከ84% በላይ ህዝብ ያልመረጠው የኢህአዴግ እጩ ወደ ፓርላማ ገባ፡፡ ከውጤቱ ማየት እንደሚቻለው አግባብተን ካስገባናቸው የግል እጩዎች አንዱ ራሱን ቢያገል ውጤቱ ግልብጥብጡ ይወጣ ነበር ፣ ኢህአዴግን የወከለው ሰው ፓርላማ አይገባም ነበር፡፡” (ገፅ 60-61)
ለአብርሃ ደስታ የቀረበለት ሁለተኛ ጥያቄ “ሀቀኛ የምትላቸው ተቃዋሚዎች ስትል ምን ለማለት ፈልገህ ነው? ሀቀኛ የምትላቸው ተቃዋሚዎችስ እነማን ናቸው?
አብርሃ ፣ ምላሹን እንደሚከተለው አስከተለ፡፡ “ሀቀኛ ስል እውነተኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለማለት ፈልጌ ነው፡፡ ምርጫ ሲደርስ ብቻ ከመሸጉበት ወጥተው አለን የማይሉና ተለጣፊ ያልሆኑ ፓርቲዎች ልልህ ፈልጌ ነው፡፡ ለምሳሌ እኔ ሀቀኛ ስል የምመድባቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች አረና ፣ ኦፌኮ ሰማያዊ ፣ አንድነትና መድረክን ነው፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች በተናጠል ሳይሆን በጋራ ሆነው ሀገር የማስተዳደር ብቃት አላቸው ብዬ እገምታለሁ፡፡ የራሳቸው ደንብና ፕሮግራም ያላቸውና አንድ ሰው እንዳሻው የማያሽከረክራቸው ፓርቲዎች ናቸው፡፡ በራሴ መመዘኛ እነዚህን ፓርቲዎች ሀቀኛ በማለት እመድባቸዋለሁ፡፡ በአንፃራዊነት ከሌሎች ፓርቲዎችም የሚሻሉና ጠንካራ ብዬ የምመድባቸው እነዚህ ከላይ በስም ያነሳሁልህን ፓርቲዎች ነው፡፡”
አሁን ባለው የፖለቲካ ምህዳር ምርጫ መሳተፍ አያዋጣም የሚሉ ወገኖች በስፋት አስተያየታቸውን ይሰነዝራሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች ምርጫውን አለመሳተፍ (boycott) እንደ መፍትሔ ያስቀምጣሉ፡፡ ለዚህም እንደምክንያት የሚያቀርቡት ነፃና ገለልተኛ የሆነ ምርጫ ቦርድ በሌለበት ፣ ስርዓቱ የፖሊስ ፣ መከላከያና ደህንነቱን በቁጥጥሩ ስር ባደረገበት ሁኔታ ምርጫ መሳተፍ ፋይዳ የለውም፡፡ ስለዚህም ምርጫውን አለመሳተፍና ገዢው ቡድን ብቻውን እንዲወዳደር ማድረግ የተሻለ ነው ይላሉ። “ምርጫን አለመሳተፍ (boycott) ማድረግ መፍትሔ አይሆንም” ይለናል፡፡
ወጣቱ የፖለቲካ እስረኛ አብርሃ ደስታ ግን “በሰላማዊ መንገድ የምታገል ፓርቲ ነኝ እስካልክ ድረስ በምርጫ የመሳተፍ ግዴታ ውስጥ ትወድቃለህ፡፡ በሰላማዊ መንገድ የሚታገል ፓርቲ ስልጣን የሚይዘው በምርጫ ነው። ስለሆነም በምርጫ መሳተፉ የሚጠበቅ ነው፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩ በጣም የጠበበ መሆኑ አያጠያይቅም። “የፖለቲካ ምህዳሩ ጠቧል” ብሎ ግን ምርጫን አለመሳተፍ ግብ ሊሆን አይገባም። ቅድም ስንነጋገር ሀቀኛ ብዬ ያነሳውልህ ፓርቲዎች ተባብረው እንኳ ምርጫውን ላለመሳተፍ ቢወስኑ ኢህአዴግ ግድ አይሰጠውም። ራሱ የፈለፈላቸውን ፓርቲዎች ወደ ምርጫ እንዲገቡ አድርጎ ማሸነፉን ማወጁ አይቀርም፡፡ ምርጫውን ቦይኮት ለማድረግ ቢታሰብ እንኳ ወቅቱን ማገናዘብ ያስፈልጋል፡፡ ለምርጫው የተወሰነ ጊዜ ሲቀረው ነባራዊ ሁኔታዎችን አገናዝቦ ራስን ከምርጫው ማግለል ይቻላል። ምርጫ ህዝቡ ጋር የምትደርስበት አንድ መንገድ እንደመሆኑ መጠን ህዝቡን ከቀሰቀስክ በኋላ ከምርጫው ራስን ማግለል ይቻላል፡፡ በግሌ ምርጫን ቦይኮት ማድረግን ግን አልደግፍም፡፡”
አንድ የሚከነክነኝ አከራካሪ ሀሳብ አለ፡፡ ይህ አከራካሪ ሀሳብ ጥቂት በማይባሉ ሰዎች ይነሳል፡፡ የትግራይ ህዝብ በስርዓቱ እንደተጠቀመ አድርጎ የማቅረብ ነገር በስፋት ይታያል፡፡ የትግራይ ህዝብንና ሕወሓትን አንድ አድርጎ የመመልከት ነገርም አለ። አብርሃ ፣ የትግራይ ህዝብና ሕወሓትን ለያይተን መመልከት እንዳለብን በተደጋጋሚ ገልጿል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ባነሳሁለት ጊዜ ተከታዩን ምላሹን ሰቶኛል፡፡
“የትግራይ ህዝብና ሕወሓት ሌላ ቢሆኑም የትግራይ ህዝብና ሕወሓትን የመቀላቀል ነገር በስፋት ይታያል። በትግራይ ምድር ስላለው ጭቆና በስፋት ፅፌያለሁ። የትግራይ ህዝብ በስርዓቱ እንዳልተጠቀማ ለማየት የአዲስ አበባ ጎዳናዎችን ብቻ መመልከት በቂ ይመስለኛል፡፡ አብዛኛው ለማኝ ከትግራይ ክልል እየፈለሰ ወደ አዲስ አበባ የሚመጣው በትግራይ ምድር መኖር አመቺ ስላልሆነለት እንጂ ልመናን መርጦ አይደለም፡፡ ሕወሓት ሁልጊዜም የትግራይ ህዝብን የሚያስፈራራበት አንዳች ካርድ አለችው፡፡ ይህቺ ካርድም እኔ ከሌለሁ ደርግ ተመልሶ ይመጣባችኋል የምትለው ናት፡፡ ተቃዋሚዎችን በጠቅላላ ፀረ-ትግራይ አድርጎ ይስልና ፕሮፖጋንዳውን ይረጫል፡፡ የትግራይ ህዝብ እንደ ሌላው ህዝብ ሁላ ሕወሓትን ይፀየፋል። ሕወሓት ምንም ያመጣለት ነገር እንደሌለ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ በስሙ እንደሚነገድበትም በሚገባ ተረድቷል፡፡
ስለሆነም ሕወሓትን ለማስወገድ በሚደረገው ትግል ላይ የበኩሉን ሚና መጫወት ይፈልጋል፡፡ በዚህ ትግል ላይ እንዲሳተፍ የሚያደርገው በሀገራችን የተንሰራፋው ጭቆና ነው፡፡ የትግራይ ህዝብን ጭቆና መቀበልና እውቅና በመስጠት ለችግሩ መፍትሔ ማበጀት ይቻላል ባይ ነኝ። ሌላው እዚህ ላይ ላነሳው የምፈልገው ጉዳይ የተቃዋሚ አመራሮች ስለትግራይ ህዝብ ሲያነሱ ወያኔ ባይሉ ይመረጣል ባይ ነኝ፡፡ ወያኔ ማለት እምቢ-ባይ ወይም አብዮተኛ ማለት ነው፡፡ የዛሬው ገዢዎቻችን ወያኔዎች አይደሉም፡፡ የትግራይ ህዝብ ግን ወያኔ ነው፡፡ የተቃውሞ ጎራ አመራሮች ወያኔ በማለት ቃሉን ሲጠቀሙ የትግራይ ህዝብን እያስከፉ እንዳሉ ሊገነዘቡ ይገባል ባይ ነኝ፡፡ ዛሬም ድረስ የትግራይ ህዝብ ወያኔ ነኝ ብሎ ያስባል፡፡ ወያኔ የሚለው ቃል ሕወሓትን ለመግለፅ መዋል የለበትም። ይህን ማድረግ ከተቻለ ለችግሮቹ በቀላሉ መፍትሔ ማበጀት ይቻላል ባይ ነኝ እላለሁ፡፡”
አብርሃ ፣ ሕወሓት በትግራይ ህዝብ ላይ የሚያደርሰውን ግፍና በደል ማጋለጡ ፣ ገዢዎቻችንን እንቅልፍ አሳጥቶ ስላሸበራቸው አስረውታል ፡፡ የዛሬው ፅሁፍ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በአንድ ወቅት ስለ አብርሃ ፣ ከጻፉት በመቆንጠር ቆይታችንን እንቋጫለን፡፡
“በእኔ ግምት ባለፉት ሀያ ሁለት ዓመታት ውስጥ ትግራይ እንደ አብርሃ ያለ ድንበር-ዘለል ፣ ጠልቆና አርቆ የሚያስብ ወጣት አፍርቶ አላየሁም ፤ ከትግራይነት አልፎ ፣ ከኢትዮጲያዊነት አልፎ በሰውነት ደረጃ ላይ የሚከበርና የሚያስከብር ወጣት ነው ፤ ስለዚህም በአብርሃ መጨቆንና መታፈን ትግራይ ብቻ ሳትሆን ኢትዮጵያም ትጎዳለች ፤ ይቺ ሀገር ሰው እንዳይበቅልባት የተደረገው እንዲህ በአምባገነኖች ጭካኔና በሕዝብ አስረካቢነት ነው። እግዚአብሔር አብርሃን ይጠብቀው! እኛንም ከለላ ለመሆን መንፈሳዊ ወኔውን ይስጠን፡፡”

No comments:

Post a Comment