Translate

Monday, December 29, 2014

አንድነት ትብብሩ ውስጥ ለመግባት ያስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች ሊሟሉ ይችላሉን?

እያስፔድ ተስፋዬ
Eyasped Tesfaye Semyawi party member
እያስፔድ ተስፋዬ (የሰማያዊ ፓርቲ አባል)
የፓርቲዎች መተባበር እና ጋራ መቆም እጅግ በጣም አስፈላጊ እና አንገብጋቢ የሆነበት ጊዜ ላይ ደርሰናል ብዬ አምናለሁ፡፡ ፓርቲዎች በጋራ መስራታቸው ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ከሰሞኑ በትብብር በተሰሩት ስራዎች ያስተዋልነው እና ምስክርነት የማያሻው ጉዳይ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ በአሁኑ ወቅት የተሻለ አቅም አላቸው የሚባሉት ሰማያዊ፣ አንድነት እና መኢአድ ተባብረው መስራት አለባቸው፡፡ ተነጣጥሎ መስራት የትግሉን እድሜ ከማራዘም ውጪ ምንም ፋይዳ የለውምና፡፡
አንዳንዶች በሰማያዊ እና በአንድነት መካከል ሰፊ የትግል ስትራቴጂ ልዩነት ስላላቸው አንድ ላይ መስራት ይከብዳቸዋል የሚል አስተያየት አላቸው፡፡ በመሬት ላይ ያለው ሀቅ ግን በትግል ስትራቴጂያቸው ላይ የጎላ ልዩነት የሌላቸው መሆኑ ነው፡፡ ነገሮችን በተግባር የማቀዳደም ካልሆነ በስተቀር አንድነትም ሆነ ሰማያዊ ምርጫው ነፃ እንዲሆን መታገላቸው የማይቀር ነው፡፡ እንደውም መድረክም ሳይቀር በፖለቲካ ምህዳሩ ላይ መስተካከል አለባቸው ብሎ የሚያምንባቸውን ቅድመ ሁናቴዎች ማስቀመጡን ገልጧል፡፡


ይህ ከሆነ ታዲያ ለምን በትብብር አንድ ላይ አይሰሩም?
ለመተባበር የአንድነት ቅድመሁናቴዎች ምንድንናቸው?
የአንድነት አመራሮች ከተለያዩ ሚዲያዎች ጋር ካደረጉት ቃለምልልስ እንዲሁም ከአንዳንዶቹ ጋር በግል ካደረኩት ውይይት እንደተረዳሁት ከሆነ አንድነት ፓርቲ ወደ ትብብሩ ለመግባት ሁለት ቅድመሁናቴዎችን አስቀምጧል
1ኛው፡- ትብብሩ ምርጫውን ብቻ ግብ አድርጎ የተመሰረተ የአጭር ግዜ ግብ ብቻ ያለው ሳይሆን ዘላቂ የሆነ የመጨረሻ ግቡም በመግባባት ላይ የተመሰረተ የውህደት ግብ መሆን አለበት የሚል እና
2ኛው፡- የትብብሩ አባል ፓርቲዎች ለትብብሩ ስልጣናቸውን ቆርሰው መስጠት የሚችሉበት እና ትብብሩ ፓርቲዎቹን በአንድ ላይ አስተባብሮ መምራት የሚችልበት መሆን አለበት የሚል ነው፡፡ (ከተሳሳትኩ አንድነቶች አርሙኝ)
እንግዲህ በአንድነት በኩል የተቀመጡት ነጥቦች እንዚህ ከሆኑ ቀጣዩ ጥያቄ የሚሆነው ትብብሩ እንዚህን ቅድመሁናቴዎች ሊያሟላ አይችልም ወይ የሚለው ነው፡፡
በእኔ እይታ ትብብሩ ቅድመሁናቴዎቹን ሊያሟላ ይችላል፤ ይገባልም፡፡ በአሁኑ ወቅት ወደ ውህደት መሄድ ከህግም አንፃር የሚቻል አይደለም ነገር ግን ከምርጫው በኋላ እስከመዋሀድ ለሚደርስ ግብ ለመስራት ከአሁኑ ተስማምቶ፤ አሁን ግን በትብብር እየሰሩ ለመሄድ የሚቸግር ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ ከዚህ ባለፈ ደግሞ የትብብሩ አባል ፓርቲዎች ስልጣናቸውን ለትብብሩ ቆርሰው መስጠታቸው ህብረታቸውን ያጠናክረው ይሆናል እንጂ ምንም ክፋት የለውም፡፡ ፓርቲዎቹ ለትብብሩ ስልጣናቸውን እየቆረሱ መስጠታቸው እንድ ፓርቲ እኔ ያልኩት ብቻ ካልተሰራ ወይም ካልሆነ በሚል በሚያመጣው ሀሳብ የፓርቲዎቹ ግንኙነት እንዳይሻክር ለማድረግ ጠቃሚ መንገድ ነው፡፡ ከዚህም ባለፈ ደግሞ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙትን የፓርቲዎቹን መዋቅሮች በአንድነት እና በማሰናሰል ለማሰራት በር የሚከፍት ነው፡፡
የትብብሩ አመራሮች እና የአንድነት አመራሮች የህዝብን ጥያቄ እና ፍላጎት አድምጣችሁ በቅርቡ አንዳች የምስራች ታሰሙናላችሁ ብዬ እጠብቃለሁ፡፡ ቸር ያሰማን፡፡

No comments:

Post a Comment