Translate

Sunday, June 8, 2014

እየራበንም ቢሆን በምግብ እራሳችንን ችለናል – ኃ/ማሪያም ደሳለኝ

(ግንቦት7 ዜና) – ወያኔ ስልጣን በያዘባቸዉ አመታት በተለይም ባለፉት አስር አመታት የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ በድርብ አኃዝ አደገ፤ ኢትዮጵያ በ2015 ዓም መካከለኛ ገቢ ካላቸዉ አገሮች ተርታ ትሰለፋለች፤ በኤሌክትሪክ ኃይል እራሳችንን ችለን ለጎረቤት አገሮች እንተርፋለን፤ በቅርቡ ደግሞ በምግብ ምርት እራሳችንን ቻልን የሚሉ በአይን የማይታዩና በእጅ የማይዳሰሱ የ”ላም አለኝ በሰማይ” ክምሮች እየከመረ የኢትዮጵያን ህዝብ ለመደለል ሞክሯል። የአገሩ ኤኮኖሚ በእጥፍ አደግ ሲባል ችግርና መከራዉ በሦስት እጥፍ የጨመረበት የኢትዮጵያ ህዝብ ግን እንኳን መካከለኛ ገቢ ካላቸዉ አገሮች ተርታ ሊሰለፍ ከሦስቱ ዕለታዊ ምግቦች አንዱን በቅጡ መብላት ተስኖት መብራት በሳምንት አንድ ቀን ብቻ እያገኘ “ጽድቁ ቀርቶብኝ በወጉ በኮነንከኝ” እያለ ጨለማ ቤት ዉስጥ ቁጭ ብሎ የመከራ ዘመን መቁጠር ጀምሯል።

Ethiopian PM Hailemariam Desalegn on Al Jazeera
የኢትዮጵያ ህዝብ እንመራሀለን ከሚሉት የወያኔ መሪዎች እጅ እጅ ብሎ የሰለቸዉ ነገር ቢኖር እንደሰዉ በእግሩ ቆሞ የሚሄደዉ ዉሸታቸዉና ቅጥፈታቸዉ ነዉ። የወያኔ መሪዎችና እዉነት አንድ ላይ ታይተዉ ስለማያዉቁ ህዝብ አይኑ እያየ የሆነዉን ነገር አልሆነም ወይም ጭራሽ ያልተሞከረዉን ነገር ሆነ ብለዉ ሲዋሹ ለአፋቸዉም ለሰብዕናቸዉም አይሳሱም። ለምሳሌ ሠላማዉ ዜጎችን በጅምላ ገድለዉ ብርድልብስ ጠቅልለዉ እየቀበሩ ማንንም አልገደልንም፤ መብቱን የጠየቀ ሰላማዊ ሰልፈኛ በጥይት እየጨፈጨፉ – ባንክ ተዘረፈ፤ መሬታችንን ለምነዉ ለሱዳን እየሰጡ – የተሰጠ መሬት የለም፤ አኝዋክን ከመሬቱ አፈናቅለዉ መሬቱን ለባዕዳንና ለቤተሰቦቻቸዉ በርካሽ እየቸበቸቡ ኢትዮጵያ ዉስጥ የመሬት ቅርሚያ የለም እያሉ የዋሿቸዉ ግዙፍ ዉሸቶች ከብዙዎቹ ቂቶቹ ናቸዉ።

ከአስራ ሰባት አመት የጫካ ዉስጥ ቆይታ በኋላ አዲስ አበባ የገቡት ዋና ዋናዎቹ ወያኔዎችም ሆኑ እነሱ መለምለዉ ያሰለጠኗቸዉ ምስለኔዎች የተካኑበት አንድ ትልቅ ነገር ቢኖር ዉሸት መደርደርና ከበስተኋላዉ ምንም ትርጉም የሌለዉ ቁጥር እየደመሩ የኢትዮጵያን ህዝብና አለም አቀፉን ማህበረሰብ ማታለል ነዉ። አዎ! የወያኔ መሪዎች ከምንም ነገር በላይ ቁጥር ይወዳሉ። የሚናገሯቸዉ ቁጥሮች እነሱን የሚጠቅሙ ከሆነ ለጥጠዉ ለጥጠዉ ሰማይ ያደርሷቸዋል፤ የቁጥሮቹ ማነስ የሚጠቅማቸዉ መስሎ ከታያቸዉ ደግሞ ይጠቅሙናል ብለዉ ባሰቡት ልክ ያሳንሷቸዋል። ለምሳሌ አለም አቀፍ ዕርዳታ ሰጪ አገሮችና ተቋማት 6 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ህዝብ ተርቧልና አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ያስፈልገዋል ብለዉ ሲያስጠነቅቁ . . . . ወያኔ ደግሞ የለም የተራበዉ ህዝብ ከአንድ ሚሊዮን ያነሰ ነዉ ይላል። ለወያኔ ትልቁ ቁም ነገር የኢትዮጵያ ህዝብ የረሃብ አደጋ ላይ መዉደቁ ሳይሆን እራሱን ሞቶ ከተቀበረ ስርዐት ጋር ማወዳደርና የተሻለ መስሎ መቅረብ ብቻ ነዉ።
ወያኔ እንደሚናገረዉ እዉነትም የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ በድርብ አኃዝ አድጎ ቢሆንና በዚህ እድገት ዉስጥ የኢትዮጵያ ህዝብ ችግርና መከራ ያንን ያክል ተቀርፎ ቢሆን ኖሮ ወያኔን እንኳን መጣህልን ብሎ ከማመስገን በቀር አይንህን ላፈር ብሎ የሚቃወመዉ ቀርቶ አፉን ሞልቶ የሚያማዉም ዜጋ አይኖርም ነበር፡፡ ድፍን የኢትዮጵያ ህዝብ የመርገም ቀን ብሎ የሚጠራዉ ግንቦት ሃያም እንደዛሬዉ በግድ ሳይሆን እንደ የካቲት ሃያ ሦስትና እንደ ሚያዝያ ሃያ ሰባት የኢትዮጵያ ህዝብ በቀበሌ ተገድዶ ሳይሆን በራሱ ተነሳስቶ ደስ ብሎት የሚያከብረዉ በዐል ይሆን ነበር። ሀቁ ግን ወያኔ ኤኮኖሚዉ በድርብ አኃዝ አደገ በተባለ ቁጥር የኢትዮጵያ ህዝብ ችግርና መከራ በሦስት እጥፍ ያድጋል፤ የኤሌክትሪክ ኃይል አምርተን ለጎረቤት አገሮች ልንሸጥ ነዉ በተባለ ቁጥር ኢትዮጵያ ዉስጥ የመብራት አገልግሎት እንደ ምግብ ራሺን በሳምንት አንዴ ለዚያዉም ለተወሰኑ ሰዐታት ታይቶ የሚጠፋ የህልም እንጄራ ሆኗል።
አገራችን ኢትዮጵያ እንደ ፈረንጆቹ የዘመን አቆጣጠር በ2015 መካከለኛ ገቢ ካላቸዉ አገሮች ጎን ትሰለፋለች ተብሎ የተነገረንን የሞኞች ተስፋማ አንዱኑ አለመስማቱ ይሻለን ነበር። በ2102 ዓም በአለማችን ከፍተኛ ገቢ አላቸዉ ከተባሉት አገሮች ዉስጥ አንዷ ፖላንድ ነበረች፤ የፖላንድ ህዝብ በ2012 ዓም የነፍስ ወከፍ ገቢ $ 12660 በ2012 ሲሆን ፖላንድ ከፍተኛ ገቢ ካላቸዉ አገሮች የመጨረሻዋ ነበረች። በዚሁ በ2012 ዓም መካከለኛ ገቢ ካላቸዉ አገሮች አንዷ አልባኒያ ስትሆን በ2012 ዓም የአልባኒያ ህዝብ የነፍስ ወከፍ ገቢ $4030 ነበር፤ አልባኒያ መካከለኛ ገቢ ካላቸዉ አገሮች ዉስጥ የመጨረሻዋ ናት። በ2012 ዓም የኢትዮጵያ ህዝብ የነፍስ ወከፍ ገቢ $380 ነበር። ይህንን እጅግ በጣም ዝቅተኛ የሆነ ገቢ ነዉ “የማይነጋ መስሏት ምን እንዲሉ” በ2015 ዓም $4000 ይደርሳል ብለዉ መለስ ዜናዊና ሱፊያን አህመድ የዛሬ አምስት አመት የነገሩን። ዛሬ የፈረንጆቹ 2015 ሊገባ የቀረዉ ስድስት ወር ብቻ ነዉ። የኢትዮጵያ ህዝብ የነፍስ ወከፍ ገቢ እንኳን 4000 ዶላር ሊደርስ ለዘመናት ከሰነበተበት ደሃ ከሚባሉ አገሮች ጋርም ሲወዳደር ዝቅተኛ ከተባለበት ደረጃ እንደ ግመል ሽንት ወደ ኋላ እንጂ ወደፊት ሲራመድ አይታይም።
እስከ ሐምሌ 2004 ዓም ድረስ ከላይ በጠቀስናቸዉ የዉሸት ክምሮች ህዝብንና አገርን ሲያታልል የከረመዉ ዘረኛዉ መለስ ዜናዊ ነበር። በእርግጥ መለስ ዜናዊ ላይመለስ ተሰናብቶን ሄዷል፤ ሆኖም እሱን ተካ የተባለዉ ሰዉ መለስ በአምሳያዉ የፈጠረዉ ሰዉ ስለሆነ ጌታዉ በአደራ መልክ ጥሎለት የሄደዉን ተልዕኮ በመፈጸም ላይ ይገኛል። ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ጥርስ የሌለዉን ስልጣን ተሸክሞ በሰራባቸዉ ባለፉት ሁለት አመታት ለሱዳን መንግስት ሽልማት ሆኖ በቀረበዉ መሬት ጉዳይ፤ በሰላማዊ ሰልፍ ጥያቄ፤ በዕድገትና ትራንስፎርሜሺን ጉዳይና በሌሎችም ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ያደረጋቸዉ ንግግሮችና የሰጣቸዉ አስተያየቶች በሙሉ እንደ ካርቦን ኮፒ ከጌታዉ ከመለስ ዜናዊ የተቀዱ ንግግሮች ናቸዉ። መለስ ዜናዊ ሞቶም ኢትዮጵያን እየገዛ ነዉ የሚባለዉ እንደነ ኃ/ማሪያም አይነቶቹን በቁማቸዉ የሞቱ ሰዎች ተክቶ ስለሄደ ነዉ።
ኃ/ማሪያም ደሳለኝ በቅርቡ እሱን እራሱን ጨምሮ ድፍን የኢትዮጵያ ህዝብ ግዞት ዉስጥ የገባበትን ግንቦት ሃያ ቀንን የድልና የነጻነት ቀን ነዉ ብሎ ሲናገር ተደምጧል። ግንቦት ሃያ ኢትዮጵያ ዉስጥ የዘረኝነት፤ የጎጠኝነት፤ የሙሰኝነትና የአፈና መሰረት የተጣለበትን ቀን ነዉ፤ ኃ/ማሪያም ይህንን ቀን የኢትዮጵያ ዳግማዊ ትንሳኤ ቀን ነዉ ማለቱ የሚያሳየን ግለሰቡ ከኢትዮጵያና ከታሪኳ ጋር አለመተዋወቁንና እሱም የአገሩን የኢትዮጵያን ታሪክ የሚመለከተዉ እንደ ጌቶቹ በቁጥር ወስኖ መሆኑን ነዉ። ግንቦት ሃያ የኢትዮጵያ ህዝብ ሁለት እጆቹን በሰንሰለት አስሮ ከያዘዉ ስርዐት እጆቹና እግሮቹ ወደ ታሰሩበት ስርዐት የተዘዋወረበት ዳግማዊ የባርነት ቀን ነዉ። በእርግጥ ግንቦት 1983 ሰዉ በላዉ የደርግ ስርዐት የተደመሰሰበት ቀን ነዉ፤ ግን ግንቦት ሃያን የዳግም ነጻነት ቀን የሚያሰኘዉ የደርግ መደምሰስ ብቻ ሳይሆን ከደርግ መደምሰስ ጋር የኢትዮጵያ ህዝብ ከታሰረበት ሰንሰለት ተላቅቆ ቢሆን ነበር። በተግበር የተመለከትነዉ ግን ግንቦት ሃያ የኢትዮጵያ ዳግማዊ ባርነት ቀን መሆኑን ነዉ።
ኃ/ማሪያም ደሳለኝ በዚህ ግንቦት ሃያ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ነዉ በሚለዉ አስጸያፊ ንግግሩ ብቻ አልተወሰነም . . . እንደዚህም ብሎ ነበር። በሁለት አስርተ አመታት ዉስጥ 250 ሚሊዮን ኩንታል በማምረት በአገር አቀፍ ደረጃ በምግብ እራሳችንን ችለናል፤ በአለም ህብረተሰብ ዘንድ በረሃብና በድርቅ ትታወቅ የነበረቸዉ አገራችን በሁለት አስርተ አመታት ትግል በምግብ እራሳችንን ችለናል ብሎ በሙሉ አፉ ተናግሯል።
አገራችን ኢትዮጵያ በምግብ እራሷን ስትችል ተጠቃሚዎቹ ዝናብና ዳመና ፊታቸዉን ባዞሩብን ቁጥር የእርዳታ ለጋሾችን እጅ የሚመለከቱት ወገኖቻችን ናቸዉና አገራችን ኢትዮጵያ በምግብ እራሷን ቻለች ሲባል የማይደሰት ኢትዮጵያዊ ያለ አይመስለንም፤ የዛሬዉ ጉዳያችን ኢትዮጵያ እንዴት በአጭር ግዜ ዉስጥ በምግብ እራሷች ቻለች ሚለዉ ጥያቄ ጋር አይደለም። ኢትየጵያ ሰርቶ የሚያሰራና እንዲሁም እድገቷንና ብልጽግናዋን የሚመኝ መሪ አለመኖሩ ነዉ እንጂ ሃያ አመት እንኳን በምግብ እራስን ለመቻል ለሌሎችም ብዙ ነገሮች የሚበቃ ረጂም ግዜ ነዉ። የዛሬዉ ጥያቄያችን እዉነትም አገራችን ኢትዮጵያ በምግብ እራሷን ቻለች ወይ፤ ወይም ኢትዮጵያ ካሁን በኋላ የምግብ እርዳታ አያስፈልጋትም ወይ የሚል ነዉ። ለመሆኑ ኢትዮጵያ ዉስጥ በገሃድ የሚታየዉ እዉነታና የኃ/ማሪያም ደሳለኝ በምግብ እራሳችንን ችለናል ብሎ የተናገረዉ ንግግር አብረዉ ጎን ለጎን ይሄዳሉ?
መለስ ዜናዊ ከሃያ ሁለት አመታት በፊት የኢትዮጵያ ህዝብ በአጭር ግዜ ዉስጥ በቀን ሦስቴ የመብላት ዋስትናዉ ይረጋገጣል ብሎ ነበር። ዛሬ ከሃያ ሁለት አመታት በኋላ ከ40 በመቶ በላይ ኢትዮጵያዉያን እንኳን በቀን ሦስት ግዜ ምግብ ሊበሉ አንዱንም ጠግበዉ የሚበሉት የታደሉ ናቸዉ። መለስ ዜናዊን የተካዉ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ የጌታዉን ትምህርት ተከትሎ ኢትዮጵያ በምግብ እራሷን ችላለች ብሎ ይናገር እንጂ እሱ እራሱ ከሚመራቸዉ ካቢኔዎች አንዱ ከሆነዉ ከግብርና ሚኒስቴር በቅርብ የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተዉ በ2006 በጀት አመት ብቻ 2.2 ሚሊዮን ኢትዮጵያዉያን ከፍተኛ የምግብ ችግር ዉስጥ እንደሚወድቁ ተናግሯል፤ ልብ በሉ ወያኔ እንደዚህ አይነቱን እሱን የሚያጋልጥ ቁጥር ማሳነስ እንጂ እዉነቱን መናገር አይወድም። ኢትዮጵያ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ እንደተናገረዉ እዉነትም በምግብ እራሷን ችላ ቢሆን ኖሮ በዉሸት ከተካነዉ የኃ/ማሪያም አፍ ይልቅ ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚገኙ የእህል ገበያዎች በግልጽ በነገሩን ነበር። ከኢትዮጵያ በየግዜዉ የሚወጡት የገበያ መረጃዎች ቁልጭ አድርገዉ የሚያሳዩን የምግብ ዋጋ በየቀኑ እያሻቀበ ሲሄድ ነዉ። የአገራችን የምግብ አቅርቦት በጨመረ ቁጥር ዋጋዉ ይቀንሳል እንጂ አይጨምርም ፤ወይም ሌላ ሁሉ ቢቀር የምግብ ምርት መጨመር ገበያዉን ያረጋጋዋል እንጂ የአንድ ኩንታል ጤፍ ዋጋ ኡኡ በሚያሰኝ መልኩ 2000 ብር አይደርስም ነበር።
በቅርቡ የአለም ባንክ፤ ለጋሽ አገሮችና የወያኔ አገዛዝ በጋራ ያወጡት ሰነድ በያዝነዉ አመት 2.7 ሚሊዮን ኢትዮጵያዉያን አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ካልተደረገላቸዉ ህይወታቸዉ አደጋ ላይ አንደሚወድቅ ይናገራል። ይህ የጋራ ሪፖርት ኢትዮጵያ እንደ ፈረንጆቹ ዘመን አቆጣጠር በ2013 ብዛት ያለዉ የምግብ ምርት አምርቻለሁ ብትልም የተመረተዉ 231ሚሊዮን ኩንታል አገሪቱን መቀለብ እንደማይችልና አገሪቱ በያዝነዉ የፈረንጆቹ አመት 388635 ሜትሪክ ቶን የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋት በግልጽ አስቀምጧል።ኃ/ማሪያም ደሳለኝ አስተምሮት ያለፈዉ ጌታዉ በቀን ሦስቴ እንበላለን ብሎ አንደዋሸን እሱም ረሃብ እየቆነደደን በምግብ እራሳችንን ችለናል ብሎ ቢዋሽ ብዙ አይገርመንም። ሆኖም አንድ የሚገርምም የሚያሳዝንም ነገር አለ፤ እሱም ኃ/ማሪያም በምግብ እራሳችንን ችለናል ብሎ የሚነግረን በጎን ከአለም ባንክና ከለጋሽ አገሮች ጋር የምግብ ዕርዳታ ለሚያስፈልገዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ዕርዳታዉ የሚገኝበትን መንገድ እየተደራደረ ነዉ። በምግብ እራሱን የቻለ አገር የአንድ አመት ዝናብ ስለተጓጎለ ብቻ ጓዙን ጠቅልሎ ዕርዳታ ልመና የለጋሽ አገሮችን በር አያንኳኳም።
ለመሆኑ ለምንድነዉ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ በእጁ የልመና ስልቻዉን ይዞ በአፉ በምግብ እራሳችንን ችለናል እያለ የኢትዮጵያን ህዝብ የሚደልለዉ? ኢትዮጵያ በወያኔ ዘመን በምግብ እራሷን ቻለች ብሎ ወያኔን ለመካብና የወያኔን መልካምነት ለመናገር አስቦ ከሆነ ተሳስቷል። ወያኔ የአገራችንን መሬት በቁጥጥሩ ስር አድርጎ እህል አምራቹን ገበሬ ከመሬቱ እያባረረና መሬቱን ለባዕዳን እየቸበቸበ ኢትዮጵያ በምግብ እራሷን የምትችልበት ሁኔታ ሊፈጠር አይችልም። ደግሞም በምግብ እራሳችንን የምንችለዉ ወያኔ አምርቶ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ አምርቶ ነዉ። የአገራችን የኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና የሚረጋገጠዉ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ በምግብ ምርት እራሳችንን ችለናል ብሎ ስለተናገረ ሳይሆን የምግብ ዋስትናችን የሚረጋገጠዉ ወያኔ የኢትዮጵያን ገበሬ የመሬት ባለቤትነት መብትና የኤኮኖሚ ነጻነት ሙሉ ለሙሉ ሲያከብር ብቻ ነዉ። ወያኔ ኢትዮጵያ ዉስጥ መሬት በግል ይዞታ ስር የሚሆነዉ በኢህአዴግ መቃብር ላይ ነዉ ብሎ በገዛ አፉ እንደተናገረ ኢትየጵያ በምግብ እራሷን የምትችለዉ ኢህአዴግ ሞቶ ሲቀበር ብቻ ነዉ።
ኢትዮጵያ የአገር ሀላፊነት የሚሰማዉና ህዝብ ወድዶ የሚረጠዉ መንግስት ሲኖር በምግብ እራሷን መቻል ብቻ ሳይሆን ታላቅ ፤ ኃያልና ጎረቤቶቿን የምታክብር ጎረቤቷቿም የሚያከብሯት አገር ትሆናለች፤ ያኔ በምግብ እራሳችንን መቻላችንና ታላቅ አገር መሆናችን እኛ ወይም የእኛ መሪዎች የሚናገሩት ሳይሆን ሌሎች ሳይወዱ በግድ የሚናገሩት ሀቅ ይሆናል። እንዲህ አይነቱ የኢትዮጵያ ህዝብ ለዘመናት የናፈቀዉ ግዜና ዘመን እንዳዉ ስለተመኘነዉ ብቻ ከተፍ አይልም። እንዲህ አይነቱ ሰላም፤ ዕድገት፤ ነጻነት፤ እኩልነትና ፍትህ የሰፈነበት ዘመን እዉን ለማድረግ ወያኔን ማስወገድና ዘረኛ ስርዐቱን መቅበር የግድ ይላል። የወያኔ መወገድ ደግሞ የአንዳንዳችንን የህይወት፤ የአንዳንዳችንን የገንዘብ፤ የአንዳንዳችንን የግዜና የግዜና የእዉቀት፤ የአንዳንዳችንን ደግሞ ሁሉን አቀፍ መስዋዕትነት ይጠይቃል። ስለዚህ የዚህ እያንዳንዳችን የዚህ ትግል ጥሪ ቤታችንን ሲያንኳኳ አቤት ብለን ለእናት ኢትዮጵያ ለመድረስ በተጠንቀቅ እንቁም።

No comments:

Post a Comment