Translate

Monday, June 23, 2014

የሶማሊው ክልል መሪ የመንግስት ደህንነቶች ሊገድሉዋቸው እንደሚችሉ በመጠቆም ጠባቂዎቻቸውን ቀየሩ

የሶማሊ ክልል መሪ አብዲ ሞሃመድ ኡመር የፌደራሉ መንግስት የደህንነት ሰዎች ሊገድሉኝ ይፈልጋሉ በማለት ቀድሞ ሲጠብቁዋቸው የነበሩ ጠባቂዎቻቸውን በመቀየር አካባቢው በታማኞቻቸው በአይነ ቁራኛ እንዲጠበቅ እያደረጉ ነው።

ካለፉት ሳምንታት ጀምሮ ወደ የፕሬዚዳንቱ ቢሮ ወደሚገኝበት አካባቢ የሚዘዋወሩ ሰዎች ልዩ ፍተሻ እየተደረገባቸው ነው።
አቶ አብዲ ባለፈው ሳምንት ከ9 ዞኖችና ከ68 ወረዳዎች የተውጣጡ 1 ሺ 500 የሚሆኑ ከመላው ኦጋዴን የተውጣጡ የአገር ሽማግሌዎችን ሰብስበው ማእከላዊውን አስተዳደር የሚተቹ ንግግሮችን ተናግረዋል።
የደህንነት ሃላፊው ጌታቸው አሰፋ በሙስና የተበለሻ “ሌባ ነው” ሲሉ የፈረጁት አቶ አብዲ፣ ለፓስፖርት ማውጫ በሚል ከኦጋዴን ተወላጆች ገንዘብ እንደሚቀበሉ ለተሰብሳቢው ተናግረዋል።
“አትፍሩ የኢህአዴግ የደህንነት ሃይል በሙሉ ከክልላችን ተጠራርጎና ተሰባብሮ እንዲወጣ አድርጌዋለሁ፣ በክልሉ ያለሁት እኔ ነኝ” በማለት የተናገሩት አቶ አብዲ፣ ማንኛውም የአገር ሽማግሌ የኢህአዴግን የደህንነት ሃይሎች  እንዳይተባበር ጥሪ አቅርበዋል።
“ኢትዮጵያውያን አይወዱንም፣ መሬታችን እንጅ እኛን አይፈልጉንም፣ እንደሁለተኛ ዜጋም ያዩናል” ያሉት አቶ አብዲ፣ ህገመንግስቱ እስከመገንጠል የሚደርስ መብት ያጎናጸፋቸው መሆኑን ለሽማግሌዎቹ አስረድተዋል።

በከፍተኛ ፍርሃት ውስጥ የሚገኙት ፕሬዚዳንቱ፣ የእጅ ስልካቸውን ከመቀየር ጀምሮ በግቢያቸው ውስጥ የሚካሄዱ ማንኛውንም አይነት እንቅስቃሴ  ክትትል እንዲደረግበት ትእዛዝ ሰጥተዋል። ለመንግስት ደህንነቶች ይሰራሉ ብለው የጠረጠሩዋቸውን ሰዎች ቢሮ ማዘጋታቸውም ታውቋል።
በጅጅጋ አንዳንድ አካባቢዎች በተለይ እርሳቸው ጫት በሚቅሙበት ቀበሌ 6 አካባቢ ከ11 ሰአት በሁዋላ የህዝቡ እንቅስቃሴ እንዲገታ የተደረገ ሲሆን፣ ወደ ከተማዋ የሚደረጉ ፍተሻዎችም ተጠናክረዋል።
በአቶ አብዲ እና በኢህአዴግ መካከል በተለይም በደህንነት ሹሙ ጌታቸው አሰፋ መካከል ልዩነት ተነስቶ እንደነበር ኢሳት መዘገቡ ይታወሳል። በቅርቡ አልሸባብ በክልሉ በመንግስት ታጣቂዎች ላይ የፈጸመው ጥቃት በሀወሃት ባለስልጣናትና በአቶ አብዲ መካከል ያለውን ልዩነት ሳያሰፋው እንዳልቀረ ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ወገኖች ገልጸዋል። አቶ አብዲ በከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንዲወድቁ ያደረጋቸውም የልዩነቱ መስፋት ሳይሆን አይቀርም።
በሌላ ዜና ደግሞ አቶ አብዲ የኦጋዴን ነጻ አውጭ ድርጅት ተዳክሟል በማለት በተናገሩ ማግስት፣ ከደገሃቡር 1 ኪሜ ርቀት ላይ ኦብነግ በወሰደው ጥቃት 7 ሰዎች ተገድለው 9 ቆስለዋል።
ክፉኛ ከቆሰሉት መካከል የደገሃቡር የጸጥታ ሃላፊ አቶ  አሻርና የአካባቢው የልዩ  ሚሊሺአ አዛዥ ሙሀመድ ዳይክ ይገኙበታል። ሁለቱም ሰዎች ሲታከሙበት ከነበረው ደገሃቡር ሆስፒታል ወደ ካራማራ ሆስፒታል እንዲወሰዱ ተደርጓል።
ከትናንት በስቲያ ፕሬዚዳንቱ 100 የሚሆኑ የልዩ ሚሊሺያ አባላቱን ወደ አካባቢው መላካቸው ታውቋል።

No comments:

Post a Comment