Translate

Sunday, June 1, 2014

የብርቱ – ካህን ፍሬዎች

አርአያ ጌታቸው

Birtukan Mideksa
የኢትዮጵያ ፖለቲካን በተለይ ከንጉሳዊ ስርዓት ውደቀት በኋላ የነበረው የፓርቲ ፖለቲካ እስከ 1997 ዓ.ም ያለውን መመልከት ብንችል፤ የሴት እህቶቻችን ምንመ እንኳ አልፎ አልፎ በፖለቲካው ውስጥ ተሳትፎ የነበራቸው ቢሆንም ይሄ ነው የሚባል ተጽዕኖ ፈጣሪዎች አልነበሩም፡፡ ሆኖም ከቅንጅት ውህደት መስከረም 1998 ዓ.ም የብርቱካን ወደ አመራርነት መምጣት በሴቶች የፖለቲካ ህይወት ላይ ትልቅ ተፅእኖ ፈጥሯል፡፡ ብርቱካን ከአንድ ዓመት ከ10 ወር እስር በኋላ ተፈትታ የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ሆና በመመረጥ በኢትዮጵያን ፖለቲካ ውስጥ የመጀመሪያዋ ሴት የፓርቲ መሪ በመሆን በታሪክ መዝገብ ውስጥ ራሷን አሰፈረች፡፡ ሆኖም ብርቱካን ከእድሜዋ ወጣትነት፣ በህግ ያለት እምነት እና ዕውቀት ሴት እና እናት ከመሆኗ ጋር ተደማምሮ በህብረተሰቡ ውስጥ የነበረውን የመሪ ጥማት በቀላሉ ልታሟላ እንደምትችል የተረዳው የወያኔ ስርዓት በ7 ወር የፓርቲ ሊቀመንበር እድሜዋ በዓጭሩ ለመቅጨት በማሰብ በድጋሚ ማንንም ሊያሳምን በማይችል ተልካሻ በሆነ ምክንያት ለእስር ዳረጋት ፡፡ ሆኖም ያልተረዱት ነገር ብርቱካን በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ሴቶችን ምንያህል ማርካ እንደነበረ ነው፡፡ ከነዚህም ውስጥ ዛሬ በእስር ላይ የምትገኘው ጀግናዋ ርዕዬት አለሙ አንዷ ነች፡፡

ርዕዬት ወደ ጋዜጠኝነት ሙያዋ ከመግባቷ በፊት ለአጭር ጊዜም ቢሆን እሷም የፖለቲካ ተስታፎ ነበራት፡፡ ርዕዬት ከመታሰሯ በፊት በተደጋጋሚ እንደገለጸችው ብርቱካንን ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘቻት በአንድ መጽሐፍ ምርቃት ላይ ሲሆን ከዛም ወደ እንድነት ቢሮ እንድትመጣ ጋብዛት በዛው አባል እንደሆነች እና የኢትዮጵያን ፖለቲካ በንቃት መከታተል እንደጀመረች መስክራለች፡፡ ብርቱካን በእስር ላይ በነበረችበትም ወቅት በተደጋጋሚ እስክትፈታ ድረስ ያለመቋረጥ ቃሊቲ በመላለስ ትጠይቃት እንደነበረ እኔም ምስክር ነኝ፡፡ በአንድ ወቅት በቅርብ ላገኘው ባልችልም “የብርቱካን ፍሬ” የሚል ግጥም ፅፋ እንደነበር አልዘነጋውም፡፡ ከብርቱካን መፈታትም በኋላ ርዕዮት በተለያዩ ጋዜጦች እና መፅሄቶች በምትጽፋቸው ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ትችቶች እና ዳሰሳዎች በዓጭር ጊዜ ውስጥ በብዙ ሰዎች “ይህቺ ልጅ የት ትደርስ ይሆን? በሚል ጉጉት መታየት ጀመረች፡፡ ወያኔ በአጭር መቅጨት ፖሊሲው ርዕዮት ፍጹም አስቂኝ እና አናዳጅ በሆነ ምክንያት አሰራት፡፡ አሁንም ያልተረዳው ርዕዮትም እንደብርቱካን ሁሉ በራካታ ሴቶችን ማራካ እንደነበረ ነው፡፡
የዞን ዘጠኝ ወጣት ጦማሪያን ስብስብ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙት በቤሩት በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወቷን ላጣቸው አለም ደቻሳ ሀዘናቸውን ለመግለጽ ለመጀመሪያ ጊዜ በማኅበራ ድረ ገፅ የሚተዋወቁ ሰዎች በመስቀል አደባባይ በመቀጣጠር የጣፍ ማብራት ስነስርዓት ባካሄዱበት ወቅት ነው፡፡ በእለቱ ከተገኙት ወጣቶች ውስጥ የተወሰኑት በመሰባሰብ እንዲሁ ከምንበተን በሚቀጥለው ምን ማድረግ እንዳለባቸው እየተነጋገሩ ባለበት ወቅት፤ የመጀመሪያ እንቅስቃሲያቸው ውስጥ ለብዙዎቹ ጦማሪያን እንደ ሞዴል የሚያይዋትን ርዕዮት ዓለሙን በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ሄዶ በመጠየቅ አጋርነታቸውን ማሳየት ነበር ፡፡
በዕለቱም ከርዕዮት ጋር ስለ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ሲያወሩ ውስጡ በስምንት ዞኖች የተከፋፈለ እንደሆን ትነግራቸዋለች፤ እነሱም ቃሊቲ ያሉት ብቻ ሳይሆኑ ሀገሪቷ እራሱ ወደ እስር ቤት እንደተቀየረች በመንገር “ከቃሊቲ ውጭ ያለነው እኛ ደግሞ ያለንበትን እስር ቤት ዞን ዘጠኝ ማለት ነው” በማለት ዞን ዘጠኝ የሚለውን ስያሜ እንደያዙ ከጣማሪያኑ አንደበት ለመስማት ችያለሁ፡፡ ከነዚህ ጦማርያን ውስጥም ያለማቋረጥና ያለመታከት የርዕዮትን ጉዳይ ትከታተል የነበረችው ማህሌት ፋንታሁን አንዷ ነበረች፡፡ ማህሌትም በማህበራዊ ድረ ገጽ ላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሀሳቧን ያለምንም ፍርሀት እና ይሉኝታ በመጻፍ ታዋቂ ለመሆን ችላለች፡፡ ነገር ግን ስርዓቱ ሀገሪቷ ላይ ሰው እንዳይበቅልባት ካለው ፅኑ አቋም በመነሳት ለነገ ተስፋ ይሆናሉ የሚላቸውን ወጣቶች እያደነ በየእስርቤቱ እያጎራቸው ይገኛል፡፡ ማህሌትም ከነዚህ ውስጥ አንዷ ሰለባ ሆናለች፡፡
ወያኔ ፍፁም ሊረዳው ያልቻለው ወይም ያልፈለገው ነገር ቢኖር የብርቱካን የርዕዮት እና የማህሌት እስር በርካታ ሴቶችን ይማርክ እና ያነቃቃ እንደሆን እንጂ ከትግል እንደማያርቅ የነዚህ ሶስት ጀግና ሴቶች ሰንሰለታዊ ጎዞ ከበቂ በላይ ማሳያ ነው፡፡
ጎልተው የወጡትን እነዚህ ሶስቱን እንስቶች ለማሳያነት አነሳሁ እንጂ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሴት እህቶቻችን መብቶቻቸውን ለማስከበር የከፈሉትን ዋጋ ዘንግቼው አይደለም፡፡ በተለይ ከማህሌት ፋንታሁን ጋር ለእስር የተዳረገችው ኤዶም እና ሁሌም የማደንቃቸው እና የማከብራቸው የሰማያዊ ፓርቲ ሴቶች “የጣይቱ ልጆች” ሌሎች የዘመናችንን ሴት እህቶቻችን አንጸባራቂ የትግል ታሪክ ግንባር ቀደም ተጠቃሾች ናቸው፡፡
ምንም እንኳ የቅንጅት ፓርቲ ደጋፊዎቹን እና አባላቱን አንገት ባስደፋ ሁኔታ ቢከስምም ብርቱ – ካህን እንዳለችው “ቅንጅት መንፈስ ነው” ያ በጊዜው የነበረው እና የዲሞክራሲ፣ የአንድነት፣ የፍቅር፣ የፍትህ እና የሰላም ጥማት እና ናፍቆት መንፈሱ ዛሬም አለ፡፡ ፓርቲው ይክሰም እንጂ መንፈሱ አለ ይኖራልም፡፡ የብርቱ – ካህን ፍሬዎችም መብቀላቸው እና ማደጋቸውን ይቀጥላሉ፡፡
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

No comments:

Post a Comment