Translate

Saturday, January 25, 2014

ሱማሊያዊት ኢትዮጲያ(አሌክስ አብርሃም )

 ይሄውላችሁ ዛሬ ቤት ለቀኩ !! ምርጧን ቅዳሜ እቃ ከዛ ከዚህ በማንዘፋዘፍና ‹‹ቆምጨ›› ጋር በመነታረክ እንዳሳለፍኳት ስነግራችሁ በታላቅ ደስታ ነው ! ምክንያቱም ቅዳሜ ቀን ምንም ይፈጠር ምን ቅዳሜ መሆኑ በራሱ አንዳች የሰላም ስሜት አለውና …. ብለን ቅዳሜያችንን የነጀሱትን ነገራ ነገሮች ሁሉ አፉ ካልን በኋላ ስለነበረው ነገር ጨዋታችንን እንቀጥላለን ! (አሌክስ አብርሃም ነኝ ከአዲሱ ቤቴ ልበል እንዴ? )

ጓድ መንግስቱ ሃይለማሪያም ‹‹አንድነት ሃይል ነው ›› የሚል መፎክር እንደነበራቸው ‹ሰምቻለሁ› ብላችሁ ‹‹እድሜየ አልደረሰም በደርግ ጊዜ አልተወለድኩም ልትል ነው …ምናምን ›› ስለምትሉኝ የጓድ መንግስቱን መፎክር ባልሰማ አልፈን የቀድሞው ጠ/ሚንስትር ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ ‹‹መደራጀት ሃይል ነው ›› ያሉትን ንግግር ለዚህ ፅሁፍ እጠቀማለሁ ! እውነት ነው መደራጀት ሃይል ነው ! ዛሬ ነው የገባኝ እነዚህ ተደራጅተው በተለይ ኮንዶሚኒየም ቤቶች አካባቢ እቃ የሚያወጡና የሚያወርዱ ‹ቆምጨወች› እንዴት ሃያል ሁነዋል ጃል ? 

እኔኮ መንግስት ሌባና ሱሰኛ ጎረምሶችን እያደራጀ ህዝብ እንዲዘርፉ መላኩን አልሰማሁም ነበር ! እንግዲህ ያው ባለፈው አከራዮቸ ኪራይ ጨመሩብኝ ብየ ስነጫነጭባችሁ እነደነበር ታስታውሳላችሁ ብዙወቻችሁ ‹‹ አሌክ አይዞህ ሽ አመት አይኖር መዝረጥ አድርገህ ክፈላ ›› የሚል ምክራችሁን ስለላካችሁልኝ የአከራይ ተከራይ አምላክ የእናተን መጨረሻ ያሳየኝ ብየ እንባየን ወደሰማይ ረጭቸባችኋለሁ ! ቀልዱን እንተወውና አከራይ የፈለገውን ማስከፈል እንደሚችል ‹‹ነፃገባየው ›› ደንግጎለታል ! ሚስትህ በወለደች በሁለተኛው ቀን እንደአራስ ጠያቂ እቤትህ መጥቶ ‹‹ኪራይ ጨምር ካልሆነም ውልቅ ›› የሚልህን አከራይ ኧረ በህግ ልትለው አትችልም ‹መብቱ› ነዋ !



በእርግጥ በብስጭቴ ወቅት አከራዮቸን ስሳደብና ስረግም ያለምንም ስስትና ማፈግፈግ አብራችሁኝ ስትረግሙና ስድብ ስትረዱኝ ለነበራችሁ ሁሉ ግቢ ግቢ ቤት የመኪና ማቆሚያ ሁሉ ያለው ጀባ ብያለሁ …ምርቃቴ መሬት ጠብ አይል ሰማይ አይወጣ እንዲሁ በአየር ላይ የቆመ ነገር ነውና አሚን ብትሉም ባትሉም (‹‹ዛት ማች ›› አለች ያች ልጅ ) ለውጥ አያመጣም ! ድንገት ከደረሰ ግን ባለቤት ስትሆኑ እናተም አከራይ እንዳታሰቃዩ አደራ ! 

ወደዛሬው ጉዳይ ስመለስ ገና በጧቱ ነበር እቃየን ሰብስቤ ቤት የለቀኩት እውነቱን ለመናገር ከእቃዎቸ ማነስ የተነሳ መኪና ከመኮናተር ይልቅ በሱፐርማርኬት የእቃ ጋሪ እየገፋሁ ወደአዲሱ ቤቴ ባዘግም ይሻለኝ ነበር ! ቢሆንም ግን ለወግ ለማረጉ ብየ አንዲት ትንሽ መኪና በመኮናተር ወደቤቴ አካባቢ ስደርስ የአካባቢው ፖሊስ ያደራጃቸው ‹‹ወንጀልን በጋራ እንከላከል ›› የሚል የቲትረን የደንብ ልብስ የለበሱ ወጣቶች በሲጃራና ጫት የበለዘ ጥርሳቸውን እየገለፈጡ መኪናዋን ተከትለው ወደግቢው ተነረጋጉ (ሳልጠራቸው )

መቸስ መንግስት አደራጅቶ ከላከብን ምን አደርጋለሁ ብየ እቃየን አሳየኋቸውና መኪና ላይ ስንት ትጭናላችሁ ስላቸው ‹‹ፀጉራቸውን እያፍተለተሉ እርስ በእርሳቸው አንተ ተናገር አንተ ሲባባሉ ቆዩና ‹‹በቃ አንተም እንዳትጎዳብን ብራዘር ….ስምንት ›› ብለውኝ እርፍ ! ወደአማርኛ ሲተረጎም ‹ስምንት መቶ የኢትዮጲያ ብር ›› ማለት ነው ! ስምንተኛው ሽ ቆምጨ ሁኖ ፊቴ የቆመና ስሙን ያስተዋወቀኝ ነበር የመሰለኝ ! 

ኮስተር ብየ ‹‹ከዚህ አካባቢ ጥፉ ›› አልኳቸው ሊሄዱ መሰላችሁ ኮራ ብለው አንዱ የራሴ ፍራሸ ላይ አንዱ ወንበሬ ላይ ተንፈላሰው ተቀመጡና ‹‹እሽ ስንት ይሁን ብራዘር ›› አሉኝ ! የሚገርመው ነገር ጓደኛ ተባብሮ እቃ ቢጭን ወይም ከውጭ የመጡ ሌሎች ሚስኪን ወዛደሮች ብትጠሩ እነዚህ ወጠምሻ የተደራጁ ሌባወች አያስገቡም ! ትንሽ የመንደር መንግስት ሁነዋል ! እቃችሁን ታቅፋችሁ ትውሏታላችሁ እንጅ እነዚህ ቦዘኔወች ካልፈቀዱ ንቅንቅ የለም …ካስፈለገም ግር ግር ፈጥረው ሊመነትፏችሁ አልያም እቃችሁን ሊሰብሩላችሁ ይችላሉ ማን ሃይ ይላቸዋል !!

በመጨረሻ በስንት ጉድ ክርክር አምስት መቶ ብር ለአምስት ፍሬ እቃ ከፍየ በአስር ደይቃ ጭነው ጨረሱ ! አንድ የእነዚህ አስቀያሚ ጎረምሶች ባህሪ ያበሳጨው ሰው አንዱን በሽጉጥ ገድሎ ዘብጥያ መውረዱን በዜና መስማቴ ትዝ ብሎኝ ሽጉጥ ባለመኖሬ ፈጣሪነ አመሰገንኩ …ታንክ ቢሰጠኝ ግን አለቃቸውም ነበር ! እንዴት እንደሚያስጠሉኮ ብታዩ !! 

ወደአዲሱ ቤቴ መንገድ ስጀምር ደግሞ ጋሽ ታፈሰ ‹‹አብርሃም አብርሃም ›› እያሉ ሲጮኹ ሰምቸ መኪናውን አስቆምኩ ! 
‹‹አንተ እንደው ደህና ሁኑም ሳትል ብድግ ብለህ ትሄዳለህ ›› ብለው ተቆጡ ምርጥ ጎረቤቴ ናቸው ! 
‹‹ጊዜ እኮ አጥቸ ስጣደፍ …›› ብየ ማስተባበያ ላቀርብ ስጀምር 
‹‹ኤዲያ የምን ጊዜ ማጣት የምን ጥድፊያ ነው …ይሄን ያህል ቤት እንጅ አገር አትለቅ ›› አሉና አገላብጠው ስመው ሸኙኝ ! ምነው ባደረገልኝና አገር በለቀኩ! ስእለት ሁሉ አገባለሁ ድፎው ጠላው ያገርቤት ፋንድያው ታወሰኝ ምናምን እያልኩ ላላለቅስ ! ብቻ እግሬ በወጣች ከዚች አገር ! 


መኪናዋ መንገድ ስትጀምር አከራየ በአፈንጫው እስኪደፋ እየተደነቃቀፈ ወደመኪናዋ ሲሮጥ ተመለከትነው አጠገባችን እንደደረሰ እያለከለከ እንዲህ አለ ‹‹ የሻወሩ ቧንቧ በደንብ አይዘጋም ያንጠባጥባል አሰራልኝ ወይም ብሩን ስጠኝ እራሴ አሰረዋለሁ !››

አዲሱ ቤቴ ስደርስ ምን እንደጠበቀኝ ታውቃላችሁ ….ሌላ የተደራጁ ሌቦች ‹‹ በቃ አንችም እንዳትጎጅብን ጋሸ ስድስት ክፈይና እናወርደዋለን ›› አስር ይሆናሉ !! ቆይ ግን መንግስት ለምን እነዚህን ወጠምሻወች ጠመንጃ አስታጥቆ ህዝቡን ጨፍጭፉልኝ አይላቸውም ? በቀኑ ዝርፊያ ! አንደው አዚች አገር ላይ አቅመቢስ ህግ እና ህዝቡን የረሳ መንግስት ተዳምረው ሕገ- መንግስት እናስከብራለን ሲሉ ይገርመኛል !

መንግስት ግን ስራህ ምንድን ነው ….የውሃ ችግር አልፈታህ …የመብራት ችግር አልፈታህ የስልክ የትራንስፖርት ችግር አልፈታህ በዛ ላይ በየቦታው ህዝብ ሲጉላላ ገንዘቡን ጊዜውን ክብሩን ጭምር ሲቀማ ‹‹ተው ›› አትል ! አሁንማ ህገ መንግስት አስከባሪ ሳይሆን ህገ ዶክሜንታሪ ፊልም ተራች ሁነህ ቀረህ ! ኧረ ተው መንግስት ተው …..ወደቀልብህ ተመለስ ረጋ ብለህ አስብና ይሄን ህዝብ መላ በለው !

እኔ መቸም ዛሬ ኢትዮጲያ ውስጥ ሳይሆን ሶማሊያ ሂጀ ቤት የተከራየሁ ነው የመሰለኝ….የመንደር ገዥወች በየሰፈሩ ያሻቸውን ግብር የሚያስከፍሉባት ኢትዮጲያ ….. እናተ የእቃ ጫኝና አውራጆችን ትላላችሁ …መንግስት አደራጀን የሚሉ የታክሲ ተራ አስከባሪወችን ድርጊት ብትመለከቱ ይገርማችኋል ከሚሰሩት በጎ ስራ ጎንለጎን መዝረፍ በሚባል ደረጃ የታክሲ ሹፌሮችን አፍንጫቸውን አንቀው ገንዘብ ሲቀበሏቸው ያሳዝኗችኋል ! ሚስኪን የታክሲ ሹፌር ከትራፊክ ፖሊስ ጉቦ የተረፈውን ሳንቲም ለተራ አስከባሪ ….በዚህ በተቆፋፈረ መንገድ በየቀኑ የሚሰበር እቃ ማስቀየር አለ በተጨናነቀ ትራፊክ የሚባክነው ነዳጅም የትየለሌ ….. 

መብራት ሃይል የተበጠሰ ገመድ ለመቀጠል ጉቦ የቴሌ ሰራተኞች ያው …. እቃ እንግዛ ብትሉ እንደኢትዮጲያ ተልካሻና ጥራቱን ያልጠበቀ የቻይና ኮተት መድፊያ የሆነ አገር አለ ? በተለይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ከሞቱ በኋላ መንግስት የሚባለው አካል መላ ሰውነቱ ደንዝዞ ኢቲቪ የሚባል ምላሱ ብቻ የሚቅለበለብ ጉድ ሁኗል ! 

በየመንደሩ መንግስት በየመንደሩ ህግ ተርጓሚ ህግ አርቃቂ ህግ አስፈፃሚ ያለባት ሱማሊያዊት ኢትዮጲያ ውጥ ነን !

No comments:

Post a Comment