Translate

Tuesday, October 31, 2017

ህወሓት የኦህዴድን የበላይነት በመቀበል ኦሮሞ ጠ/ሚኒስትር ሊሾም ነው

  • ጉዳዩ በህወሓት ዘንድ መጠነኛ መከፋፈል ፈጥሯል
“ኃይለማርያም ደሳለኝ የመስዋዕት በግ?” ሲሉ የመረጃው ሰዎች አዲሱን ዜና ይጀምራሉ። የጎልጉል ታማኝ መረጃ አቅራቢዎች በኦሮሚያ ከአሁን በኋላ የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ኃይል – ህወሓት ዕድል ፈንታ እንደሌለው ማመኑን ይጠቁማሉ። የኦሮሞ ጥያቄ የወንበር መሆኑን ህወሃት እንዳመነና ይህንኑ እምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ መነሳቱን ለ“ወዳጆቹ”፣ ጌቶቹና አሳዳሪዎቹ ማሳወቁንም ይጠቁማሉ። በሌላ ወገን ደግሞ ይኸው ሁኔታ በህወሓት ውስጥ መጠነኛ መከፋፈልን እንደፈጠረ ይነገራል።

እንደዜናው ሰዎች ከሆነ ህወሓት “የወለደውን፣ ያሳደገውንና፣ የሾመውን” ካድሬ ኢትዮጵያን እንዲመራ አጭቶታል። መረጃው ጎልጉል ካነጋገራቸው የተለያዩ ወገኖች በአሉታዊና በአዎንታዊ መልኩ አስተያየት ቢሰጥበትም ለማ መገርሳ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆንና የኦሮሞ ህዝብ ተቃውሞ ጭጭ እንዲል በጓዳ ጎንበስ ቀናው ተጧጡፏል።
ቀደም ሲል በማሸማቀቅ፣ ሲቀጥል በእስርና በስውር አፈና ታፍኖ የቆየው የኦሮሚያ እንቅስቃሴ እያደር እየበሰለ ወደ ከፋ ተቃውሞ አደገ። በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት የህወሓትን መንደር አራደው። አገዛዙ ካለው ባህሪና ከፈጸማቸው እርኩስ ተግባራት አንጻር ስልጣን የመልቀቅ ጉዳይ የሚታሰብ ባለመሆኑ ተቃውሞውን በጅምላ ጭፍጨፋ፣ እስር፣ አፈና፣ ቶርቸር፣ ማስፈራሪያ ለማስቆም ቢሞክርም ተሳነው። በሺህ የሚቆጠሩ የኦህዴድ አባላትን አባሮ አዲስ ቢተካም አልሆነም።
ማባረሩ ብቻ ሳይሆን 150 ሺህ የሚገመት ሚሊሺያ አደራጅቶ በጥልቅ ተሃድሶ ስም ቁልል ገንዘብ ቢበጅት፣ ሥራ እሰጣለሁ ብሎ ቢምልና ቢገዘት፣ የልዩ ጥቅም አዋጅ ቢያውጅ … የኦሮሚያ ህዝባዊ ማዕበል የሚቆም አልሆነም። ደም በፈሰሰ ቁጥር ለተቃውሞው ኃይል እየጨመረ አገዛዙን ጤና ነሳው።
በመጨረሻም ህወሓቶች በልዩነትና በንትርክ ሳይወዱ በግዳቸው የኦሮሞ አመጽ የሚረግበው የሥልጣን ጥያቄው መልስ ሲያገኝ ብቻ እንደሆነ አመነ። የመረጃ ሰዎቹ እንዳሉት ህወሓት እዚህ ደረጃ የደረሰው ተጀንጅኖ ወይም ጫና ተደርጎበት ሳይሆን ክንዱ ዝሎ ትኩረቱን ሊመሰርታት ካሳባት “ታላቋ ትግራይ” አጎራባች ክልሎች ላይ ማተኮር እንዳይሳነውና ያስቀመጠው የ“ታላቅነት” የጊዜ ገደብ ሳይደርስ ነገሮች መልካቸውን እንዳይቀይሩ በመስጋት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ለማ መገርሳ?
ለማ መገርሳ በኦሮሚያ መንበረ ስልጣኑን ከያዘ በኋላ የሚያደርገው ንግግር፣ የንግግሩ ጠንካራነት፣ በንግግሩ ውስጥ የሚታየው ገዝፎ የመውጣት እንደምታ፣ ንግግሩ ወደ አማርኛ እየተመለሰ በማህበራዊ ገጾች ቡፌ መሆኑና በተለይም በኦሮሞ አክቲቪስቶች ዘንድ በስፋት እንዲራገብ መደረጉ በርካቶችን ያነጋገረ ጉዳይ ነው።
ከጅምሩ በጽንፈኝነት ብዙ ጉዳት ሲደርሱ የኖሩ አሁን ኢትዮጵያዊ ሆነው፣ በኢትዮጵያዊነት ስሜት ውስጥ የተጠመቁ “ዳግም ውልድ” ኢትዮጵያዊ ሆነው መታየታቸው የሚነቀፍ ባይሆንም የኋላ ታሪካቸው ጥርጣሬ ውስጥ የጣላቸው ይበዛሉ። ለማ መገርሳ ገና በአፍላው ህወሓት ጉዲፈቻ አድርጎ ያሳደገው፣ ያጠመቀውና በዋና ዜጎችን በሚበላው የደህንነት ተቋም ውስጥ ያፋፋው ሰው መሆኑን የሚያውቁ ለማን “ነጻ ሰው” ለማለት ስለሚከብዳቸው ገና ከጅምሩ ጠርጥረውታል።
ከወርቅነህ ገበየሁ ወልደኪዳን “ነገዎ” ጋር እጅግ ቅርበት ያለው፣ በአንድ ክፍል ውስጥ በዩኒቨርሲቲ የተማረና በደኅንነት መዋቅር ውስጥ ተጋምደው ሲሰራ የነበረው ለማ ብቻ ሳይሆን፣ ምክትሉ አብይ አህመድም በደብረጽዮን በሚመራው ኢንሳ ውስጥ ቁልፍ ሚናና የሚታመን ኃላፊ መሆኑን የሚያውቁ በጥልቅ ተሃድሶ ስም ሁሉም ተጠቃለው ኦህዴድን እንዲመሩ መደረጋቸው ህወሓት ከጀርባ ምን አስቦ ነው? የሚል ከጅምሩ አስነስቶ ነበር።
ጥልቅ ተሃድሶ ቁልፍ የደኅንነት ሰዎችንና እጃቸው ያደፉ የህወሓት ወዳጆችን ወደ አመራር ያመጣ እንደሆነ የሚናገሩ፣ አሁን ህወሓት የደረሰበት ድምዳሜ ተግባራዊ ቢሆንም ከጀርባ ሆኖ አገሪቱን መምራት እንደማይሳነው ያምናሉ። በዚሁ መነሻ የለማ ሹመትና ኦህዴድ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሚና መያዝ የሕዝቡን ጥያቄ አይመልስም የሚል ስጋት አላቸው። በሌላ በኩል ግን ከዲያስፖራው የኦሮሞ አክቲቪስቶች ጋር “የተፈቀደ ግን ህቡዕ የሚመስል” ሲሉ የሚጠሩት ግንኙነት የጥርጣሬያቸውን መልክ ሊያስቀይረው እንደሚችልም ይገምታሉ።
ኦህዴድና ዲያስፖራ
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዲያስፖራው ወስጥ ኦህዴድን የቀረቡ እንዳሉ በመነገር ላይ ነው። ውስጥ አዋቂ ነን የሚሉ ደግሞ ግንኙነቱ የኦህዴድን መዋቅር በመገልበጥ በውጭ አገር ያሉትን የትግል አራማጆች ዓላማ እንዲተገበሩ ማድረግና ድርጅቱን በመንፈስ ከህወሓት መነጠል እንጂ ሌላ ስትራቴጂ የለውም ሲሉ ይከራከራሉ። ከሁሉም የተለዩትና “ንጋትና ጥራት አድሮ ነው” የሚሉት ክፍሎች እነ ለማ መገርሳ “የተፈቀደ፣ ነገር ግን ህቡዕ የሚመስል” ግንኙነት በዲያስፖራ ውስጥ ባሉ የኦሮሞ አክቲቪስቶችና ኦህዴድ መካከል ስለመዘርጋቱ አይጠራጠሩም።
በዚህ ዓይነቱ የአመለካከትና የዕይታ መስተጋብር ውስጥ ግን ለማ መገርሳን አግንኖ የማውጣትና በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ እንደ አዲስ ነጻ አውጪ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ እንደ “ዳግም ውልድ ኢትዮጵያዊ” አድርጎ የመሳሉ ሥራ ከዳያስፖራው የኦሮሞ እንቅስቃሴ ጋር በትሥሥር እየተሠራ መሆኑንን ያምናሉ። እነዚህ ክፍሎች “የሜንጫ ፖለቲካ ወደ ኢትዮጵያዊነት”መሸጋገሩንም የዚሁ የቅንጅት መስተጋብር ውጤት እንደሆነ ማሳያ አድርገው ያቀርባሉ።
“ቢስማሙስ?” ምን ነውር አለበት የሚሉት ወገኖች “ወያኔን ማንበርከኩ ብቻ ነው የሚፈለገው፤ ቢቻል ድጋፍ ሊደረግ ይገባል እንጂ ሊነቀፉ አይገባም” ሲሉ ይከራከሩላቸዋል። አርባ ዓመት ብረት አንስቼ ታገልኩ የሚለው ኦነግ ያላመጣውን ውጤት ኦህዴድ ካስገኘና ይህ ድል በእነ ለማ መገርሳ ዘመን እውን ከሆነ እነ ለማ ለይቅርታም እንደሚመጥኑ ከወዲሁ ንድፈ ሃሳብ እየሳሉላቸው ነው። እነዚህ ክፍሎች እንደሚሉት እነ ለማ ከዲያስፖራው የኦሮሞ አክቲቪስቶች ጋር ስምምነት ሊያደርጉና ስምምነት ሊደርሱም እንደሚችሉ ይገምታሉ። ይሁን እንጂ በ“ህቡዕ” የሚባለው ስምምነት ከህወሓት ዕውቅና ውጪ ሊሆን እንደማይችል ከየትኛውም ወገን በአመክንዮ የሚከራከር መኖሩ አጠራጣሪ ነው።
አባዱላ – ከፊት ወይስ ከኋላ?
ማንም ተቀበለውም አልተቀበለው አባዱላ ገመዳ የጁነዲን ሳዶን ካቢኔ ሲያፈርስ ኦህዴድ በመርህ ደረጃ አካሉ ሙሉ በሙሉ ኦሮሞ ሆኗል። አባዱላበመለስ ያለውን መታመን ተገን አድርጎ በክልሉ የሰጠው ነጻነት ከካቢኔ እስከ ታች የቀበሌ መዋቅር ድረስ ተቀባይ አድርጎታል። ሁሉም አምነውና ወደው “ጃርሳው” ሲሉ የክብር ሹመት ቀብተውታል። ከዚህ ተቀባይነቱ የተነሳ ካድሬው አባዱላን የመሃላ ስም ሁሉ አድርጎት ነበር። ለዚህም ይመስላል ከክልል ተነስቶ ወደ ፌዴራል (በአፈጉባዔነት) ይቀየራል ሲባል ድፍን ካድሬው በአንድ ድምጽ አንቀበልም በማለት ተቃውሞውን ያስነሳው።
አባዱላ በደም እጁ አድፏል በሚል የሚከራከሩ ቢኖሩም የሚወዱት የኅብረተሰብ ክፍሎች ቁጥር ቀላል አይደለም። አንዳንዶች እንደሚሉት ኦህዴድ ጠረኑና መልኩ ሙሉ በሙሉ የተቀየረው  “በሹመት” ስም አባዱላ ክልሉን ለቅቆ እንዲወጣ ከተደረገ በኋላ ነው። ለዚህም ይመስላል ኃይለማርያም የአባዱላን መልቀቂያ እያየነው ነው ሲል የተናገረው። አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት አባዱላ፣ ወርቅነህ ገበየሁና ለማ መገርሳ ሶስቱ የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ሆነው አገሪቱን እንዲመሩ ሲደረግ የኦሮሞ ጥያቄ ወደ ውዳሴ የሚቀየር ይሆናል።
ይህ ወያኔ የቀመመው አዲሱ ስልት ተግባራዊ ይሆን ዘንድ አባዱላ ወሳኝ ሰው እንደሆነ የሚገምቱ ክፍሎች፣ አባዱላ የሸፈተውን ካድሬ እንዲመልስ ከፍተኛ ኃላፊነት እንደሚጠብቀው የሚናገሩ ወገኖች ህወሓት እጁን የሰጠ መስሎ የሚቀምመው ቅመም በምንም መልኩ የጤና እንደማይሆን እየወተወቱ ነው።
ኃይለማርያም ደሳለኝ የጋለ ምጣድ ላይ የተቀመጠው አቅም አልባው መሪ
ሊስትሮም ሁን ከተባልኩ እሆናለሁ” ያለው ኃይለማሪያም ዕጣ ፈንታው ምን ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ ባይታወቅም፣ አዲሱ ኦሮሚያን ያስተነፍሳል የተባለው ዕቅድ ተግባራዊ ከሆነ የመስዋዕት በግ ሆኖ ይቀርባል የሚለው አስተያየት የገነነ ነው። የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ ከያዘ በኋላ በግምገማ “ብቃት የለህም” ተብሎ ሲበጠር የነበረውና የይስሙላ ኃላፊነት ተጭኖበት የኖረው ኃይለማሪያም ሞት ያወጀበት ህዝብ ዘንድ ተመልሶ እንደሚቀላቀል ግምት አለ። እናም በዚሁ መነሻ ኃይለማርያም አሁን ምጣድ ላይ እንደተቀመጠ ጦጣ መመሰሉ ነው እየተጠቆመ ያለው።
ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ (May 23, 2015) [ሥልጣን ወደ ህወሃት?! “በሃይለማርያም አፈርኩባቸው” – በየነ ጴጥሮስ] በሚል ርዕስ ባስነበበው ዘገባ ስለ ኃይለማርያም ይህንን ብሎ ነበር፤
“የካቲት 3 ቀን 2006 ዓ.ም. ጓድ ሃይለማርያም ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ በቀጣዩ ምርጫ ለጠ/ሚ/ርነት ይወዳደራሉ? ተብለው ለተጠየቁት ሲመልሱ ድርጅታቸው “የጋራ ውሳኔ የሚሰጥ ድርጅት” መሆኑን በመጥቀስ ድርጅታቸው “በሚመድባቸው ቦታ” የሚሠሩ መሆናቸውን አስቀድመው ተንብየው ነበር። ትንቢቱን ሲያጠናክሩም እንዲህ አሉ “ይህ ድርጅት 20 ዓመታት ሙሉ ሲመራ ይህንን (የምደባ) አሠራሩን ለማወቅና ለመገንዘብ ይቸግራል የሚል ግምት የለኝም። በድርጅታችን ውስጥ መዳቢ ኮሚቴ አለ። እኔንም ጨምሮ የሚመድብ ማለት ነው። ይህ ኮሚቴ እዚህ ቦታ ትሠራለህ ሲል እኔም እሠራለሁ። ድርጅታችን ከዚህ ተነስተህ ወረዳ ታገለግላለህ የሚለኝ ከሆነ የወረዳ ሊቀመንበር ሆኜ እሠራለሁ። ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነህ ብታገለግል የተሻለ አስተዋጽኦ ታበረክታለህ ከተባልኩ ደግሞ አገልግሎቱን እሰጣለሁ። ታላቁ መሪያችን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ድርጅቴ ሊስትሮ ሁን ብሎ የሚመድበኝ ከሆነ ሊስትሮ ለመሆን ዝግጁ ነኝ ብለው ነበር። እኛ እንደዚያ ነን።” (ምንጭ፤ ሪፖርተር 12 February 2014)”
ዓቅም አልባው ኃይለማርያም አሁንም ህወሓት በሚሰጠው ምደባ “ለማገልገል” የተዘጋጀ ይመስላል።
ከሱዳን – ዘፈኖች
መለስ ከመፈናጠሩ በፊት ነጠላ ለብሶ ሚሌኒያም አዳራሽ ከበሮ እየተደለቀለት ሲዘል ምርጫው ያደረገው የሱዳን ዘፈን ነበር። ዛሬም ኦህዴድን የአገር መሪ አድርጎ የኦሮሞን ጥያቄ ወደ ውዳሴ ለመቀየር  የነደፈው ንድፍ ሲያፈተልክ ከወደ ሱዳንም የተሰማ ወሬ ነበር። ወሬው አቶ ሌንጮ ለታና አቶ ዲማ ነገዎ ሱዳን ከወያኔ ጋር ንግግር አደረጉ የሚል ሲሆን ሁለቱም አስተባብለዋል።
ሁለቱም ከግጭት ጋር በተያያዘ በጻፉት መጽሐፍና ባጠኑት ጥናት የአፍሪካ ህብረት ጋብዟቸው ወደ ሱዳን እንዳመሩ ለኢሳት አስረድተዋል። ይሁን እንጂ ከወያኔ ሰዎች ጋር መገናኘታቸውን አስመልክቶ፣ ያገኟቸው ሰዎች በኃላፊነታቸው ሳይሆን በባለሙያነታቸው ሱዳን በመገኘታቸው መሆኑን አመልክተዋል። ማስተባበያውም ሆነ ሃሜቱ ቁብ የማይሰጣቸው፣ ዜናው መደራረቡ ብቻ ስሜት እንደሚሰጥ ሃሳብ ሲሰጡ ይደመጣል።
በኦህዴድና በህወሓት መካከል ተፈጥሯል ስለሚባለው ሽኩቻና የኦህዴድ ገንኖ የመውጣት ትግልን በቅርብ የሚከታተሉ እንደሚሉት ኢህአዴግ ካሁን በኋላ በህወሓት የበላይነት የማይቀጥል መሆኑን ራሱም አውቆታል። በዚህ ዓመት የኢህአዴግ ሸንጎ (ፓርላማ) ከተከፈተ በኋላ ኃይለማርያም የሥራ ሪፖርት ባቀረበበት ወቅት አዳራሹ ኦህዴድ አልባ እንደነበር የሚናገሩ ወገኖች ከፕሬዚዳንቱ (ሙላቱ) የመክፈቻ ንግግር በኋላ በተጠራው የራት ግብዣ ላይ እንዲሁ ኦህዴዶች አለመገኘታቸውን እንደ አስረጅ ይጠቅሳሉ።
ህወሓት ኦሮሞን ጸጥ ለማሰኘት ለማ መገርሳን ወደ ሥልጣን ማመጣቱ እውነተኛ ተሃድሶ ሳይሆን በመርዝ የተለወሰ ማር አድርገው የሚወስዱ ክፍሎች ዳያስፖራው ይህንን በጭፍን የመቀበሉ ጉዳይ ፍጹም የሥልጣን ጥመኛ መሆኑን ያሳብቅበታል ይላሉ። ከዚሁ ጋር አያይዘው ይልቁንም ኢህአዴግ ትንፋሽ ለመሳብ ይህንን ከተገበረ በኋላ በቅድሚያ ህወሓት ለትግራይ ያቀደውን እንዲያሳካ ተጨማሪ ዕድል ይሰጠዋል በማስቀጠልም ኢህአዴግ በዚሁ ትንፋሽ አስቀድሞ ሲብላላ ወደነበረው ራሱን ወደ ኅብረብሔር ፓርቲ የመለወጥ ዕቅዱን ተግባራዊ ያደርግበታል ይላሉ።
ከዚህ ሁሉ የፖለቲካ ቁማር ውጪ የተደረገው የአማራው ክፍል ራሱን በአንድ ማስተባበር አቅቶት የበይ ተመልካች ሆኖ መቅረቱ እልህ ውስጥ ሊያስገባው ይገባ ነበር። ሆኖም ይላሉ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ራሱን በተለያየ ስያሜ የሚጠራው የአማራው ክፍል በአንድ የትግል መንፈስ መቀናጀት ሳይችል ቀርቶ እርስ በርሱ ጎራ ለይቶ መናቆሩና በአብዛኛው የመግለጫና የዘገባ ሥራ እየሠራ መቀጠሉ ትግሉን እንመራለን የሚሉትን በእጅጉ ሊያሳስብ የሚገባ ጉዳይ ነው ይላሉ።
አዲሱን የኦሮሞ አመራርና የእነ ለማ መገርሳን ወደ ሥልጣን ከፍታ መውጣት የሚቃወሙ አክራሪ ህወሓቶች “የትግሬ ክብር ተነክቷል” በሚል ይህንን አካሄድ በጥብቅ እንደሚቃወሙ ይሰማል። አስቀድሞም የጠቅላዩ ሥልጣን ለኃይለማርያም የተሰጠው በስህተት ነው፤ መለስ መንገዱን ያመቻቸው ለህወሓት በማሰብ የነበረ ቢሆንም እርሱ ከሞተ በኋላ እርሱ በሌለበት ኃይለማርያምን መሾም አልነበረብንም፤ አሁንም ሥልጣኑ ወደ ህወሓት መመለስ መቻል አለበት በሚል በውስጥ የመከፋፈል መንፈስ እንዳለ ቢነገርም ከዚህ በፊት እንደተካሄዱት ህንፍሽፍሾች ያህል የጎላና ህወሓትን ለመሰንጠቅ የሚበቃው እንደማይሆን ይነገራል።
ህወሓት አሁን በከፍተኛ ውጥረት ባለበት ወቅት አልበርድ ያለውን የኦሮሞ ተቃውሞ ለማስተንፈስ አዲሶቹ የበረሃ ልጆቹን የፊት ሰልፈኛ አድርጎ “ዕድሜ ማራዘሚያ” ኪኒኑን እየቀመመ መሆኑ ጎልጉል ያገኘው መረጃ እንድምታ ያሳያል (የነበቀለ ገርባን መፈታት ሳይጨምር ማለት ነው)። ለዚህ ተግባራዊነት በአገር ውስጥ እና በዳያስፖራ በስልት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ይህንን ዕቅዱን ደግሞ ለቀለብ ሰፋሪ ምዕራባዊ ጌቶቹ አሳማኝ በሚመስል መልኩ አቅርቧል። ትግራይን ነጻ ለማውጣት የተነሳው ህወሓት በአብዮታዊ ዴሞክራሲዊ ጥምቀት ራሱን በኢህአዴግ ካባ በመሸፈን “ኢትዮጵያዊ” እንዳደረገው፤ ላሁኑ ደግሞ የበረሃ ልጆቹን ከጽንፈኝነት ጎራ ወደ “አንድነት፣ ኅብረት፣ ኢትዮጵያዊነት” ድንኳን በማስገባት ቅቡል የማስደረግ ሥራውን በተሳካ ሁኔታ ካጠናቀቀው ህወሓት “በክፍል ሁለት” ሊቀጥል የማይችልበት ምክንያት እንደማይኖር የጎልጉል ታማኝ መረጃ አቀባዮች ግላዊ ምልከታቸውን ይሰጣሉ።

No comments:

Post a Comment