Translate

Sunday, October 1, 2017

ታዋቂው አሜሪካዊ አርቲስት ጄይ-ዚ የሞ አንበሳ አርማ ያለበትን የቀድሞ የኢትዮጵያ ባንዲራ ሲያስውለበልብ አመሸ


(ECADF) — ታዋቂው አሜሪካዊ አርቲስት ጄ-ዚ (Jay-Z)… (የታዋቂዋ አሜሪካዊት አርቲስት ቢያንሴ ባለቤት) እና የቦብ ማርሌ የመጨረሻ ልጅ ደሚያን ማርሌ ትላንት ቅዳሜ ምሽት ሳተርደይ ናይት ላይቭ (Saturday Night Live) በመባል በሚታወቀውና እጅግ በርካታ ተመልካች ባለው የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ እንግዳ ሆነው በመገኘት የሙዚቃ ስራዎቻቸውን ባቀረቡበት ወቅት መድረኩ ላይ የሞ አንበሳ አርማ ያለበት በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመን የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ሆኖ ያገለግል የነበረው ባንዲራ ሲውለበለብ አምሽቷል።

ጉዳዩ በአሜሪካ ሚዲያዎች ከፍተኛ ትኩረት ያገኘበት ሌላም ምክንያት አለ።
በሀገረ አሜሪካ በጥቁር አሜሪካውያን ላይ ፖሊስ ከህግ ውጭ አላግባብ የሚፈጽማቸውን የመብት ረገጣዎች፣ ግድያዎች እና እስራቶች በመቃወም ጥቁር አሜሪካውያን የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም ተቃውሟቸውን በሰላማዊ መንገድ እያሰሙ ይገኛሉ።
በቅርቡ ከፍተኛ ትኩረት ያስገኘው የተቃውሞ ስልት የአሜሪካ ፉትቦል (American Football) ጨዋታዎች ከመጀመራቸው በፊት በሚካሄደው የብሄራዊ መዝሙር ዝማሬ እና የሰንደቅ አላማ ስነስርዓት… ወቅት ከመቀመጫ ባለመነሳት ወይንም በመንበርከክ እየተካሄደ ያለው የተቃውሞ ስልት ነው። ይህን አይነቱን ተቃውሞ በቅድሚያ የጀመረው ታዋቂ ተጫዋች ኮሊን ካፐርኒክ (Colin Kaepernick) ይባላል። በካፐርኒክ ድርጊት በርካታ አሜሪካውያን በተለይም ነጮቹ ከፍተኛ ተቃውሞ በማሰማታቸው እና ካፐርኒክ የሚጫወትበትን ቡድን ባለማየት ማእቀብ (boycott) ያደርጋሉ ተብሎ በመሰጋቱ ወይንም ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ካፐርኒክን የሚቀጥር አንድም የአሜሪካ ፉትቦል (American Football) ቡድን ጠፋ።
ካፐርኒክ የተበደሉ ወገኖቹን ድምጽ በአደባባይ በማሰማቱ እየደረሰበት ያለው ጫና ያስቆጣቸው ደጋፊዎቹ በበኩላቸው የአሜሪካ ፉትቦል ጨዋታዎች ላይ ማእቀብ ለመጣል ዛቱ፣ ሰባት ቁጥር የተጻፈበትን የካፐርኒክን መለያ (Jersey) በብዛት በመግዛትም በአንድ ወቅት ከፍተኛ መለያ (Jersey) በመሸጥ ካፐርኒክ አንደኛ ሆነ።
ሰሞኑን ደግሞ ጉዳዩ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኖ ብቅ ብሏል።
ለንግግሩ ለከት የሌለውና በዘረኛነት እጅግ የሚታማው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአላባማ ክፍለ ግዛት ለደጋፊዎቹ ባደረገው ንግግር ወቅት “በአሜሪካ ሰንደቅ አላማ ስነስርዓት ወቅት ተነስተው የማይቆሙ ተጫዋቾች የውሻ ልጆች ናቸው፣ የፉትቦል ቡድኖቹ ባለቤቶች ሊያባርሯቸው ይገባል…” ማለቱን ተከትሎ በሚቀጥለው የፉትቦል ጨዋታ ቀን ተጫዋቾች፣ አሰልጣኞች እና የቡድኖቹ ባለቤቶች ሳይቀሩ በሰንደቅ አላማ ስነስርዓቱ ወቅት በደቦ በመንበርከክ ለፕሬዚዳንቱ ምላሽ ሰጡ።
ይህ በዚህ እንዳለ ትላንት (ቅዳሜ ማታ) ታዋቂው አርቲስት ጄይ-ዚ (Jay-Z) በአሜሪካ ብቻ ከ11 ሚሊዮን ህዝብ በላይ በሚከታተለው የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ የታጋዩን ስፖርተኛ ኮሊን ካፐርኒክን መለያ (Jersey) ለብሶ ከጀርባ ደግሞ የሞ አንበሳን ባንዲራ እያስወለበለበ መድረኩ ላይ ከቦብ ማርሌ ልጅ ደሚያን ማርሌ ጋር ተከሰተ።
ምንም እንኳን በስልጣን ላይ ያለው የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ዘረኛ ቡድን ባለፉት 26 ዓመታት ኢትዮጵያዊነትን ለማደብዘዝ እና ኢትዮጵያን ታሪክ አልባ ሀገር አድርጎ ለመሳል ሲደክም ቢኖርም በዓለም ዙሪያ በመላው ጥቁር ህዝቦች ዘንድ ኢትዮጵያዊነት መኩሪያ፣ ኢትዮጵያ ድግሞ የነጻነት ተምሳሌት ሀገር ሆና መታየቷ ቀጥሏል። ይህን ክብር ላጎናጸፉን ቀደምቶቻችን ክብር ይገባቸዋል።

No comments:

Post a Comment