Translate

Friday, October 14, 2016

ከሰሞኑ አስደናቂ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻዎች ሁለቱ !

Tadesse Biru Kersmo
ከሰሞኑ አስደናቂ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻዎች ሁለቱ !
1. በ1997 ምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የአመጽ አማራጮችን ሁሉ ይቃወም የነበረው ሰላማዊ ታጋይ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አሁን የአመጽ ጥሪ ማቅረቡ በንጽጽር እየቀረበ ትናንት “ሰላምን በመስበክ ሲያሞኘን የነበረ ሰው ዛሬ ይኸው በይፋ ጦርነት አወጀብን” እያሉን ነው። በህወሓት ፕሮፖጋንዲስቶች ትንተና መሠረት፣ ይህ የአቋም ለውጥ የመጣው ስልጣን ፈላጊ ስለሆነ ነው።
ፕ/ር ብርሃኑ ከመነሻው የትጥቅ ትግል አማራጭን አለመስወዱ፤ ለሰላማዊ ትግል እድል መስጠቱ፤ በሰላማዊ መንገድ ታግሎ ለውጥ ለማምጣት በሙሉ እምነትና ጉልበት መንቀሳቀሱ ያስመሰግነዋል እንጂ እንዴት ሊያስወስቅሰው ይችላል? ትንሽ የማሰላሰል ችሎታ ያለው ሰው “ለመሆኑ በ 1997 ምን ሆነ? ከ 1997 በኋላ የዚህን ሰው አቋም የሚያስቀይር ነገር ምን ተፈፀመ?” ብሎ አይጠይቅም ብለው ለማመን እንዴት ቻሉ?
ምርጫ 97 ለፕ/ር ብርሃኑ ያረጋገጠለት ህወሓት በሰላማዊ ምርጫ ስልጣን እንደማይለቅ ነው። ባይሆን “በ97ስ እንዴት በምርጫ ይለቃል ብሎ አመነ?” ቢባል እንኳን ትንሽ ወግ ያለው ጥያቄ በሆነ። ይኸ ጥያቄም ብዙ ጊዜ ተጠይቆ መልስ ሰጥቶበታል “ወያኔ በሰላም ለመልቀቅ ተፈጥሮው አይፈቅድለትም ከሚል ነቢባዊ ውሳኔ በተግባር ተፈትኖ የሚሰጥ ውሳኔ ይሻላል” ዓይነት ምላሽ ሲሰጥ ብዙ ጊዜ ሰምቸዋለሁ።
ይኸ ጉዳይ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ታህሳስ 4 ቀን 2002 ዓ. ም. (December 10, 2009) የኖቤል የሰላም ሽልማት ሲቀበሉ ያደረጉት ንግግር ያስታውሰኛል። እንዲህ ብለው ነበር።
“እውነቱን በመቀበል እንጀምር − ብጥብጥ ያለበት ቅራኔን በእኛ እድሜ ማስቀረት አንችልም። ለወደፊቱም ሕዝቦች − በግልም ሆነ በጋራ − ኃይልን መጠቀም አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ከሞራል አንፃርም ተገቢ የሚሆንበት ሁኔታ ይኖራል። ... አንሳሳት! ክፋት በዓለም ላይ አለ። በሰላማዊ ትግል ሂትለርን መግታት አይቻልም ነበር። ... አንዳንዴ ጉልበት መጠቀም ያስፈልጋል ማለት ከሃቅ የራቀ ምፀት አይደለም፤ ይልቁንስ ታሪክን በቅጡ መረዳት፤ የሰውን ልጅ ድክመቶችን ማወቅ እና የምክንያታዊነት ውስንነትን መገንዘብ ነው። ... ሰላም ተመራጭ መሆኑ መታመኑ ብቻውን ሰላምን ለማስገኘት አይበቃም።”

2. ፕ/ር ብርሃኑ ከግብጽ መንግሥት 500,000 የአሜሪካ ዶላር “ተቀብሎ ሲደለደልድ” በብሔራዊ የደህንነት መረብ “የረቀቀ” ስለላ የተገኘ የተባለው ድምፅ ሌላው አስገራሚ ጉዳይ ነው።
ይህ ጉዳይ በቀጥታ እኔን የሚመለከት በመሆኑ ትንሽ ዘርዘር አድርጎ መግለጽ ያስፈልጋል። ማንም ሰው የኔን ስምና የአያት ስም (Tadesse Kersmo) google search ውስጥ ቢያስገባ በብዛት የሚያገኘው አንድ የከሸፈ የኢንሳ የስለላ ታሪክ ነው። ከብዙዎቹ ጽሁፎች ኒውዮርከር ያወጣውን “Hacked by One’s Own Government” የሚለውን በዚህኛው ሊንክ ያገኙታል።
ነገሩ በአጭሩ የሚከተለው ነው። ደብረጽዮን በበላይነት የሚቆጣጠረው በስልኮች፣ በራድዮና የቴሌቪዥን ሞገዶች ላይ አፈና የሚያደርግ፤ በኢንተርኔትና ማኅበራዊ ሚያዎች (በተለይም ፌስ ቡክ) ስለላ ላይ የተሰማራ INSA የሚሉት አሳፋሪ ድርጅት አለ። ይህ ድርጅት እንደብዙዎቹ የህወሓት ተቋማት አጠቃቀሙን ባያውቅበት ውድ እቃዎችን መግዛት ይወዳል። ከሁሉ በላይ ውድ ወጪ ያስወጣው FinFisher የተባለው Gamma International የብርታኒያ ካምፓኒ የሚያመርተው የስለላ ሶፍት ዌር ነው። ባለሙያዎች እንደነገሩኝ ሶፍት ዌሩ 500 000 የእንግሊዝ ፓውንድ ያወጣል፤ እሱ በተጫነበት እያንዳንዱ ኮምፒተርም 100 000 የእንግሊዝ ፓውንድ ሰርቪስ ያስከፍላል። ኢንሳ ይህንን “አውዳሚ” መሳሪያ 2012 እአአ ታጥቆ በዚያኔው ግንቦት 7 ላይ ዘመተ።
የዚህ ሶፍት ዌር አንዱ ታርጌት የእኔ ላፕቶፕ ሆነ። ባለሙያዎች ለእንግሊዝ ፓሊስና ፍርድ ቤት ባቀረቡት መረጃ መሠረት FinFisher በኔ ላፕቶት “been active on or around 9 June 2012”. ከዚህ “ኢንቨስትመንት” ያገኙት የአንድ ቀን የስካይፕ ውይይት ነው - ዶ/ር ብርሃኑ የመራው እኔም የነበርኩበት። የተነጋገርነው እዚህ ከቀረበው ጋር ፈጽሞ ተያያዥነት የሌለው ነገር ነበር፤ ስለግብጽ አልተነሳም፤ ግኑኝነት ኑሮን ስለማያውቅም ሊነሳ አይችልም ነበር። ቆራርጠውና ቀጣለው አሁን ከካፕሽን የታጀበውን ቪድዮ በዩቱብ ለቀቁት። ይህ የተፈፀመው በ2012 መሆኑን ልብ በሉ።
በሰብዓዊ መብት ጉዳዮች በሚሠራው Privacy International ድጋፍ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ስናቀርበው አንዱ የጉዳት ማስረጃዬ በዩቱብ የተለቀቀው ቪዲዮ ነበር። በመጀመሪያው የፍርድ ሂደት ተከሳሽ ሆኖ የቀረበው የብሪታኒ የጉምሩክና የአገር ውስጥ ገቢ መሥሪያ ቤት ነበር - ለ Gamma International ይህን ሶፍት ዌር ለኢትዮጵያ ደንበኞቹ እንዲሸጥ ፈቃድ መስጠት አለመስጠቱ የሚገልጹ መረጃዎችን ይፋ አንዲያደርግ ነበር። ተፈረደልን፤ ይህም በወቅቱ ትልቅ ዜና ነበር። የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ማየት ለሚፈልጉhttps://www.privacyinternational.org/node/57
አሁን ክሱ ወደ Gamma International ዞሮ በሂደት ላይ ነው። እኔ እንዲከሰስ የፈለግሁት “የኢትዮጵያ መንግሥት” በሚል ኦፊሲያላዊ መጠሪያ የሚታወቀው የህወሓት አገዛዝ ነበር፤ ጠበቆች ማሳመን ባለማቻሌ ግን Gamma International ላይ ተወሰንን። ይህ ጉዳይ ዓለም ዓቀፍ ሚዲያዎች የሚከታተሉት በቢቢሲ ሬድዮም መግለጫ የሰጠኹበት፤ የኢትዮጵያ ኤምባሲም በተደጋጋሚ ተጠይቆ “ልማት ላይ ተጠምደናልና ዜጎቻችንን በመሰለል ጊዜና ገንዘብ አናጠፋም” ዓይነት ፈጣጣ ምላሾች እየሰጠቡት የነበረ ጉዳይ ነው። የዩቱብ ማስረጃን ከመንግሥት ወይም INSA የማዛመድ ችግር ነበር ጠበቆቹ የታየቸው። እነሆ አሁን ይኸንኑ ቪዲዮ በብሄራዊ ቴሌቪዥናቸው አወጡት !!! Bingo !!!!
[በነገራችን ላይ ከ FinFisher ትንሽ አነስ ያለ Hacking Team የሚሉት ሶፍትዌርና በዚሁ ስም የሚጠራ የጣልያን ድርጅት አለ። እሱን ገዝተው ደግሞ ኢሳት ጋዜጠኞች ሞከሩት፤ እሱም ወዲያው “በቁጥጥር” ስር ዋለ። የሚገርመው ኢሳት ላይ ጥቃት ከተቃጣ ጥቂት ጊዜ በኋላ Hacking Team ራሱ Hack ተደረገና መረጃዎቹ በኢንተርኔት ተዘረገፉለት። INSA ለ Hacking Team የከፈለበት የ 1.2 ሚሊዮን ዮሮ አካባቢ ደረሰኝ ተገኘ። ከዚህ በላይ ደግም “እረ ባካችሁ ይኼ ነገር አልሠራ አለን” አቤታዎች ይፋ ሆኑ። ይህንን Wickileaks ላይ ማግኘት ይቻላል]

No comments:

Post a Comment