Translate

Wednesday, October 12, 2016

ለመለስ የተፃፈ ደብዳቤና የመለስ መልስ

ፍቃዱ ጌታቸው ለመለስ ወለላዬ ለመለስ መልስ

meles-z


ከፍቃዱ ጌታቸው ለመለስ
እንደምን አለህ ጋሼ እንደምን ነህ መለስ
ትመጣለህ ስንል ቀረህ ሳትመለስ
እኛማ ይሔውልህ
ባንተ ሌጋሲና ባንተ ትልቅ ራዕይ
በየአደባባዩ እንላለን ዋይ ዋይ
ዛሬም ጀነራልህ ተኩስ ነው ትዕዛዙ
ወገን ያጋድማል የግፍ አፈሙዙ
ለምንድን ነው ስንል ስምክን አስቀድመው
ከክርስቶስ በላይ ምስልህን አትመው
ቅዱስ መጽሐፍ ይመስል
ባንተ ራዕይና በሌጋሲህ ምለው
ቢረፈርፉንም አላለቅንምና
ደብዳቤ ላክንልህ ከሞት የተረፍነው!


የሆነስ ሆነና ግን አንተ ደህና ነህ
እኛማ ይኸውልህ
ደርሰህ ስትናፍቀን
አይሞትም የምትል ሙዚቃ ሞዝቀን
መቃብርህን ልንስም አበባ ልናኖር ሥላሴ ብንመጣ
ፌደራል ያይሃል እስረኛ ይመስል ሾልከህ እንዳትወጣ
መቼም ሥላሴ ውስጥ
ባለስም ነውና የሚቀበርበት
አንተን አየት አርገን ዞር ስንል ድንገት
እነፊታውራሪ
ግራ’ዝማች
ቀኝ’ዝማች
ፊተኛ ባለስም የሆኑት አባቶች
ያለዘብ ቆመዋል እነ አብዲሳ አጋ
ጀግና መሃል ሳለህ ምነው በድንህ ሰጋ!

የሆነስ ሆነና
ኃየሎም ደህና ነው
እዛም ትግል ይመራል
እስር ቤት ሰባብሮ ታራሚ ያስፈታል
እዛም ከፊት ሆኖ ጭቁን ያታግላል
እዛም በጀግንነት በለኮሳት ሻማ
ነፃ ነኝ ባለባት ርዕሰ ከተማ
ትንሽ ግሮሰሪ ይገባ ይሆን ደፍሮ
እዛስ ጀማል ያሲን ፈጠረ አምባጓሮ
ኃየሎምን ሰዋው በሐሺሽ ናላው ዞሮ
እኛማ ይኸውልህ ብዙ ኃየሎሞች ፈጥረን ስናበቃ
እልፍ ጀማል ያሲን ይሆናል ጥበቃ
ይኸው ባደባባይ የጀግኖቻችን ደም በየቦታው ፈሶ
አለ ጀማል ያሲን ሞት ሚበይንበት ፍርድ ቤቱ ፈርሶ!!

ግን አንተ ደህና ነህ
አቡነ ጳውሎስስ ብፁው እንዴት ናቸው
እዚያም እንደምድሩ አንድ አንቀጽ ያክላል መጠሪያ ስማቸው
ደረታቸው ግድም “ሽጉጥ” የሚያደርጉት አለ መስቀላቸው
እኛማ ይኸውልህ
ዳያስፖራ ጳጳስ ሾመን ባደባባይ
ከበዓል ቀን ውጪ ፊታቸውን አናይ
ሰው ሲሞት
ህዝብ ሲያልቅ
እምነት ሲተራመስ አያውቁም ግሳጤ
ዝም ዝም ናቸው
ቆባቸው የጳጳስ ነብሳቸው የአጤ!!

እንደምን አለህ ጋሼ እንደምን ነህ መለስ
ትመጣለህ ስንል ቀረህ ሳትመለስ



ከቻልክ ፃፍልን ለደብዳቤያችን መልስ!!**
ከመለስ ለፍቃዱ ጌታቸው
(ወለላዬ)
ደብዳቤህ ደርሶኛል ሰሞኑን የላከው
እንዴት! ከረምክልኝ? ፍቃዱ ጌታቸው
ነበልባሉ መሃል፣ በሲዖል አዳራሽ
በተነጠፈልኝ ሠፊ የእሳት ፍራሽ
እየተጠበስኩኝ፣ በቁጭት በምሬት
ጽሑፉን በሙሉ አንብቤ ጨረስኩት
ምነው ቀረህ ያልከኝ በዛው ሳትመለስ
አጣድፎ ወስዶኝ ነው አባቴ ዳቢሎስ
ያስጨኹኛል ያልከው በየአደባባዩ
ባላስጮኹኽ ነበር እዚህ እኔን ቢያዩ
ውሸት ቦታም ብሆን እውነት ለመናገር
መከራ እየቀመስኩ እያየሁ ነው አሳር
ሥላሴ በመሄድ እኔን የፈለከኝ
እንደው ለፋህ እንጂ እዛ የታለሁኝ
ለሥልጣን ዕድሜያቸው ለማወናበጃ
አ’ርገው አስቀምጠውኝ እኔን መቀለጃ
ሌጋሲው እያሉ እያወናበዱ
ሰማሁኝ በስሜ እንደሚነግዱ
እንኳንስ የተውኩት ዕራይ ሊኖረኝ
የራሴው ራዕይ ለራሴም አልበጀኝ
አስራ ዘጠኝ ዓመት በከተማ መሃል
አስራ ሰባት ዓመት በበረሃ ትግል
ሃያ አንድ ዓመታት ሀገር ሳተራምስ
ሳላየው ከርሜ የኔን ጉድጓድ መማስ
ከሄድኩበት ቀረኹ በዛው ሳልመለስ
ሌሎቹም አይቀሩም ተጠርቷል ስማቸው
አንተስ! እንደምነህ ፍቃዱ ጌታቸው?
የህወሓት አባላት ኃየሎም ምናምን
አሰፋ ማሞና ክንፈ ገ/መድህን
በደህና ጊዜ ነው ወደዚህ የመጡት
ይብላኝ በአሁን ሰዓት በሥልጣን ላይ ላሉት
በህዝብ ተይዘው ልክ! እንደጋዳፊ
እየተወገሩ በርግጫ በጥፊ!
ይመጣሉ እዚሁ አይቀርም ሞታቸው
ይፈንጩ ግድ የለም እስከዛ ተዋቸው
እንደው ለመሆኑ በረከት ስምኦን
እንዴት አደረጋት የቆየች ህመሙን?
እንዴትስ! ዘገየ እስካሁን ሳይመጣ?
ፊቱስ ምን መሰለ? ጠቆረ ወይ ነጣ?
እነ አቦይ ስብሓት፣ እነ ስዩም መስፍን
እነ ገነት ዘውዴ፣ እነ ደብረጽዮን
እነ አባይ ፀሓዬ፣ ቴዎድሮስ አድኃኖም
ሳሞራ፣ አባዱላ፣ እነ ኃይለማርያም
ወርቅነህ ገበየሁ፣ እርከበ እቁባይ
እያወናበዱ ተቀምጠው አንድ ላይ
እስከመቼ ድረስ ሊኖሩ አስበዋል?
ከኔ ከተለዩ ስንት ሰው ገድለዋል?
ምን ያህል ገዘፉ፣ ምን ያህል ከበሩ?
ስንት ብር አሸሹ? ስንት ፎቆች ሠሩ?
የተማከርነውን የአማራንስ ማጥፋት
ከኦሮሞ ጋራ ማስነሳቱን ግጭት
እንዴት አደረጉ ከምን አደረሱት?
ዕቅዱ ተሳካ እነሱው ጨረሱት?
እንደው በከንቱ ነው መግደል ማሰራቸው
በቅርብ ይመጣሉ ግዴለም ተዋቸው
አንተስ እንደምነህ ፍቃዱ ጌታቸው?
አባ ጳውሎስንም ያነሳህ መሰለኝ
ወደዛ ተዋቸው አሁን ምን ሊረቡኝ
አክብሬ አስመጥቼ ጎኔ ሳደርጋቸው
ሳጠፋ ገስፀው በአባትነታቸው
ምናለበት ነበር ቢመክሩ ቢቆጡኝ
ልጄ ልጄ እያሉ ለዚህ ከሚያበቁኝ
አሁንማ አብረውኝ የሲዖልን ስቃይ
እየቀመሱ ነው ከኔ ጋር አንድ ላይ
የራሳቸው ጉዳይ ሁሉንም ተዋቸው!
ፊትም እማይረቡ ወራዳዎች ናቸው
ደግሜ ልናገር ወራዳዎች ናቸው
አንተስ እንደምነህ ፍቃዱ ጌታቸው?

No comments:

Post a Comment