Translate

Sunday, September 27, 2015

ነገረ – ኢሕአዴግ

ሥርዓቱ በሁለት ጫፍ የተሳለ አደጋ አፍጦበታል

eprdf two
በብዙ መልኩ ዴሞክራሲያዊ ገፅታን ያልተላበሰው ኢሕአዴግ ራሱን በገዥ መደብነት “አመቻችቶ” አስቀምጧል፡፡ ግንባሩ በቀደመው ዓመት አስረኛ ድርጅታዊ ጉባኤውን በዝግ በማካሄድ እንደተለመደው ባለ ዘጠኝ ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት አጠናቋል፡፡ በዚሁ ጉባኤ፣ ከዚህ ቀደም ከተካሄዱ ጉባኤዎች በተለይም በ1994 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ከተካሄደው አራተኛው የድርጅቱ ጉባኤ ጀምሮ ይነሱ የነበሩ አጀንዳዎች ቅርፃቸውን ብቻ በመቀየር ይዘታቸውን እንደጠበቁ እስከ አስረኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ድረስ ዘልቀዋል፡፡
በተለይም የመልካም አስተዳደር እጦትና የሙስና ጉዳይ ከድርጅቱ ጋር አብረው የተፈጠሩ እስኪመስሉ ድረስ ችግሮቹ ገንግነዋል፡፡ በ1994ዓ.ም የአዲስ አበባው ጉባኤ አብይ አጀንዳ በመሆን ጉባይተኛው የተወያየበት አጀንዳ “ጥገኛ ዝቅጠት አስተሳሰብ” የስርዓቱ አደጋ መሆኑን ነበር፡፡ የቃላት ሃብታሙ ኢሕአዴግ፣ “ጥገኛ ዝግጠት አስተሳሰብ” የሚለውን ሃረግ “ኪራይ ሰብሳቢ” በሚል አገላለጽ በመተካት በቅርቡ እስከተካሄደው አስረኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ድረስ ይህንኑ አጀንዳ ሲመክርበት ኑሯል፡፡ ከግንባሩ ነገረ ታሪክ መረዳት እንደሚቻለውም ድርጅቱ በስልጣን ላይ እስካለ ድረስ ይሄው አጀንዳ (ኪራይ ሰብሳቢነት) ሲነሳና ሲወድቅ እንደሚኖር እሙን ነው፡፡ ርግጥ ይህ ጉዳይ በመንግስት መስሪያ ቤቶች እየታየ ካለው የመልካም አስተዳደር እጦት ጋር በተያያዘ የማታ ማታ የግንባሩን ፍጻሜ የሚያቀርበው ይሆናል፡፡ በርግጥም ግንባሩ እንደሚለው “ኪራይ ሰብሳቢነት የሥርዓቱ አደጋ ነው”፡፡ ከዚህ አኳያ ሥርዓቱ በሁለት ጫፍ የተሳለ አደጋ አፍጦበታል፡፡
“ኪራይ ሰብሳቢነት” ሲባል
ኪራይ ሰብሳቢነት ሲባል ያልተገባ የኢኮኖሚ ጥቅም በማጋበዝ ብቻ የሚተረጎም ሳይሆን ከዚህ ባለፈ የፖለቲካ ጥቅም ትስስር (ኔት ወርክ) እና ቡድንተኝነትን መሰረት ያደረገ የስልጣን መደጋገፍንም የሚጨምር የትርጉም ይዘት አለው፡፡ የአደጋው መንታ መልክም ይሄው ነው፡፡ የስርዓቱ መሪዎች ለማመን በሚከብዱ የሙስና መረቦች በመተብተባቸው በህዝቡ ላይ እየተፈጠሩ ያሉ ቅሬታዎችን መሰረት አድርጎ ሊፈጠር የሚችለው ህዝባዊ አመፅ የአደጋው አንዱ ገጽታ ሲሆን፤ ሁለተኛው የአደጋው መልክ ደግሞ ባለስልጣናቱ እንደ ቡድን በሚዘረጉት የሙስና መረብ ከጥቅም ትስስራቸው ጋር በተያያዘ እንደ መንግስታዊ መዋቅርም ሆነ እንደ ድርጅት የሚመጡ ግምገማዎችን በጋራ የሚመክቱበት እንዲሁም ባለስልጣናቱ የራሳቸውን የቡድን አባል ወደ ተሻለ የስልጣን ከፍታ ለማውጣት የሚያደርጉት ርብርብ የቡድን ፍላጎት የሚታይበት በመሆኑ፣ ፍላጎቱ ከሌላው ቡድን ጋር የሚጋጭ ከሆነ በዚህ መሀል የሚፈጠረው ልዩነት ከስርዓቱ አልፎ ለአገርም አደጋ የሚሆንበት እድል ይኖራል፡፡ በዚህ አግባብ ኢሕአዴግ በሁለት ጫፍ የተሳለ አደጋ አፍጦበታል፡፡ ‘የግንባሩን ቀጣይ እጣ ፈንታ ከሚወስኑት ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው ኪራይ ሰብሳቢነት ነው’ የመባሉ እውነታም ከዚህ የመነጨ ነው፡፡ በተለይም የፖለቲካ ኪራይ ሰብሳቢነት አዝማሚያ ብሄርን መሰረት ያደረገ ቡድንተኝነት የሚንፀባረቅበት በመሆኑ አደጋው ጠባብነትን መታያው አድርጎ የሚከሰት ሲሆን ፤ ይህን ተከትሎ የሚፈጠረው ችግር ከሥርዓቱ አልፎ ለአገርም የከፋ መሆኑ የሚያከራክረን ጉዳይ አይደለም፡፡
ስርዓቱ “ኪራይ ሰብሳቢነት ለመታገል ጥረት እያደረኩ ነው” እያለ ዲስኩሩን ቢያሰማም፣ ችግሩ ከመባባሱ ውጭ ጠብ ያለ ለውጥ በአደባባይ ሊታይ አልቻለም፡፡ እጅግ አስደንጋጭ የሙስና ሪከርዶች በተወካዮች ምክር ቤት በኩል በሪፖርት መልኩ ሲታለፍ ማየት የሚደንቅ አይደለም፡፡ በመሬትና በፍትህ አስተዳደር እንዲሁም በመንግስት ንብረት ግዢና ሽያጭ ላይ እየታዩ ያሉ ግልጽ የስልጣን መባለጎችን ስናስተውል አገሪቷን እንደ “መንግስት” እያስተዳደራት ባለው ገዢው ግንባር ላይ እምነት እንድናጣ ያደርገናል፡፡
ባገባደድነው አመት የፌዴራል ዋና ኦዲት መስሪያ ቤት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት ሃያ አምስት የሚሆኑ የፌዴራል መስሪያ ቤቶችና ዩኒቨርስቲዎች ህጋዊነት የሌለው የንብረት ግዢና ሽያጭ መካሄዳቸውን፣ ሥራቸውን የለቀቁ ሰራተኞች በሌሉበት እስከ ስድስት ወር የሚደርስ ደመወዝ እንደተከፈላቸው፣ ያለ ጨረታ የኮንስትራክሽን ግንባታ ስራዎች ለተለያዩ ተቋራጮች እንደተሰጠ፣ ህጋዊ የደመወዝ ጭማሪ ላልተደረገላቸው ሰራተኞች በህገ-ወጥ መንገድ ተጨማሪ ክፍያ የከፈሉ መስሪያ ቤቶች መኖራቸውን ያመለከተው ይሄው ሪፖርት፣ በዚህም እንደ አገር ከሶስት ቢሊዮን ብር በላይ ያልተመሳከረ ሒሳብ መኖሩን ይጠቁማል፡፡ ሪፖርቱ የፌዴራል መስሪያ ቤቶችንና የተወሰነ የኒቨርስቲዎችን ብቻ የሚመለከት ሲሆን፤ በየክልሉ ያለውን ምዝበራ ከዚህ ሪፖርት አኳያ ምን ያህል የከፋ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ የፌዴራል ዋና ኦዲት መስሪያ ቤት የንብረት ግዢና ሽያጭ ችግር አለባቸው፣ ህጋዊ የፋይናንስ አሰራር አልተከተሉም በሚል በሪፖርቱ የጠቆማቸው የፌደራል መስሪያ ቤቶችም ሆኑ ችግሩ የታየባቸው የዩኒቨርስቲ አመራሮች በህግ ሲጠየቁ ለማየት አልታደልንም፡፡ በርግጥ በኢህአዴግ ቤት ፖለቲካን እንጂ ገንዘብን መሰረቅ የስርዓቱ አንዱ ገጽታ ነውና የተለየ እርምጃ አይጠበቅም፡፡ ይሁንና እነዚህ ከፍተኛ አመራሮች ከገንዘብ ባለፈ የፖለቲካ ፍንገጣ ያሳዩ ቀን ‘ፋይላቸው’ ከመሳቢያ መውጣቱ አይቀሬ ነው፡፡
በኢህአዴግ ቤት፣ ከሁሉም የሙስና አይነቶች ከባዱ ሙስና የመሬት ወረራን ተከትሎ እየተፈጠረ ያለው ምዝበራ ዋናው ተጠቃሽ ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ እየታ ያለው ሙስና “ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል” እንዲሉ የከፍተኛ አመራሮችን ፈለግ በመከተል ቀበሌ ድረስ ያሉ አመራሮች “ከድርሻቸው” በላይ በወዳጅ ቤተ ዘመድና በሙታን ስም ሳይቀር የመሬት ወረራዉን ተያይዘውታል፡፡ የታችኛው አመራር ምዝበራ አይን እያወጣ በመምጣቱ “ኪራይ ሰብሳቢነትን አየተዋጋሁ ነው” የሚለው ኢሕአዴግ፣ ለአስመሳይ ፖለቲካው ማሳያ ይሆን ዘንድ አልፎ አልፎ የታችኛውን አመራር ጭዳ ሲያደርገው ይታያል፡፡ ነገሩ ‘የኪራይ ሰብሳቢዎች መተካካት’ አይነት ነገር ነው፡፡ የበላ ይሻራል፡፡ ያልበላ ይሾማል፡፡ ኡደቱም በዚህ መልኩ እየቀጠለ ያለ ይመስላል፡፡ ለዚህ ማሳያ ሆኖ የሚቅበው ጉዳይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተሞክሮ ነው፡፡ የከተማ አስተዳደሩ የከተማ ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ የሆነው አቶ ኃየሎም ጣውዩ በነሐሴ ወር ሦስተኛ ሳምንት ለንባብ ከወጣው ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ባደረገው ቃለ መጠየቅ በ2007 የሥራ ዘመን ከመሬት ጋር በተያያዘ ብቻ በየደረጃው ያሉ 315 (ሦስት መቶ አስራ አምስት) አመራሮችና ፈፃሚዎች ከኃላፊነታቸው እንደተነሱ፣ ከእነዚህ ውስጥ በህግ የሚጠየቁ ኃላፊዎች እንዳሉ ተናግሯል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ከተማ አስተዳደሩ 221 (ሁለት መቶ ሃያ አንድ) አመራሮችንና 4100 (አራት ሺህ አንድ መቶ) የሚሆኑ የመንግስት ሰራተኞችን ከሥራ ሊያሰናብት እንደሆነ፣ በህግ የሚጠየቁ መኖራቸውንም ለፋና ብሮድ ካስት አስታውቋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የካቢኔ ሹም ሽር እስከማድረግ የሚደርስ እርምጃ ሊወስድ እንደሆነም መረጃዎች በመውጣት ላይ ይገኛሉ፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ መካከለኛ አመራሮች ከሙስና ጋር በተያያዘ ከሥራ የሚሰናበቱበት አዲስ አበባ እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም ‘አንገት አልባ’ አመራሮችን ተሸክማ በማዝገም ላይ ትገኛለች፡፡ ነገሩ “ጉልቻ ቢቀየር …..” አይነት ነገር ነው፡፡ የበላ ይሻራል፡፡ ያልበላ ይሾማል፡፡ ዑደቱም ይቀጥላል….
ከመሬት ወረራ ጋር በተያያዘ በተለይም ሀሰተኛ የመሬት ባለይዞታነት መረጃ በማዘጋጀትና ህጋዊ ቅድመ ሁኔታ ላላሟሉ ሰዎች በጥቅም ትስስር መሬት የመስጠቱ ሁኔታና የአመራሩ የመሬት ቅርምት ከአዲስ አበባ ከተማ በከፋ መልኩ በሌሎች የክልል ከተሞች እንዳለ ከአንባቢ የተሰወረ አይደለም፡፡ በፍትህ አስተዳደር በኩልም አስደንጋጭ የሙስና ተግባር እየተከሰተ እንዳለ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ከ30 ሺህ እስከ 350 ሺህ ብር የሚደርስ ገንዘብ በመቀበል በሀሰተኛ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ፍርደኞችን የለቀቁ የፌደራልና የክልል ማረሚያ ቤቶች መካከለኛ አመራሮችን እንዲሁም ከሙስና ጋር በተያያዘ የዳኞችን ክስ/ስንብት መስማት ከአመት አመት እየተለመደ መጥቷል፡፡ እንግዲህ በ”ሕግ በምትመራ” አገር ላይ ከአመት አመት አስደንጋጭ የሙስና ዜናዎችን በሪፖርትም፣ በክስም መልክ እየታየ በመሆኑ “መንግስት” የሚባለው አካል ምን እየሰራ እንዳለ መጠየቅ ግድ ይለናል፡፡ የመሬትና የፍትህ አስተዳደርን እንደ ማሳያ አንስተን ተመለከትን እንጂ በሌሎች መንግስታዊ ተቋማቶች ዘንድ ምን አይነት ጉድ ሊፈጸም እንደሚችል መገመት የሚከብድ አይደለም፡፡ በቅርቡ እንኳ የኦሮሚያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ የነበረው አቶ ወንድሙ ቢራቱ በሙስና ወንጀል ተጠርጥሮ የ500 (አምስት መቶ) ሚሊዮን ብር ኦዲት እየተጣራበት ይገኛል፡፡ የምርመራው ውጤት ምን ይሁን ምንም አንድ የክልል ከፍተኛ ባለስልጣን በዚህን ያህል የብር መጠን በሙስና ወንጀል መጠርጠሩ (ኦዲት መደረጉ) ሥርዓቱ በምን ያህል መጠን እንደ ነቀዘ ጥሩ ማሳያ ይሆነናል፡፡
በየአመቱ ተዝቆ ከማያልቁ መንግስታዊ ጉዶች መካከል ጥቂቱን ቆንጥሮ የሚያሳየን የፌደራል የስነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን እንቅስቃሴ ከአሳ ነባሪዎች ይልቅ ትንንሽ አሳዎች ላይ ትኩረት አድርጎ “መረቡ”ን የጣለ በመሆኑ፣ አህአዴግ ስልጣን ላይ እስካለ ድረስ ሙስና የምንግዜም ቀዳሚ አጀንዳ ሆኖ ይኖራል፡፡ ገዢዉ መደብ ኢህአዴግ፣ በጉምቱ ባለሥልጣናቱ ላይ የሚታየውን ሙስና ከመቅረፍ ይልቅ “ሂስና ግለ ሂስ” በሚል ድርጅታዊ ቀኖናዉ ለጉዳዩ ከሚያሳየው መለሳለስ የተነሳ የሙስና ጉዳይ ለፖለቲካዊ አለመግባባቶች የመፍትሄ ማፈላለጊያ እየሆነ መጥቷል፡፡ ግንባሩ እንደሁልጊዜው ሁሉ በአስረኛ ድርጅታዊ ጉባኤው “የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ኪራይ ሰብሳቢነት ሚናን በልማታዊ አስተሳሰብ በመተካት የኢትዮጵያን ሕዳሴ እናረጋግጣለን” ቢልም፣ ጉዳዩ ከተለመደው የአቋም መግለጫነት የዘለለ ጠብ የሚል ነገር እንደማይኖረው የድርጅቱ የቀደመ ተሞክሮ ይነግረናል፡፡
እንደ-መዉጫ
በመቶ ብሮች የሚቆጠር የወር ደመወዝተኛ በበዛባት አትዮጵያ፣ በየመስሪያ ቤቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር ምዝበራ መካሄዱን፣ ይህን ተከትሎ እንደ አገር ቢሊዮን ብሮች በየዓመቱ በመንግስት ሌቦች መመዝበሩን የሚያመለክቱ ሪፖርቶች ከመንግስታዊ ተቋማት ጭምር መስማት መደበኛዉን የትራፊክ አደጋ ሪፖርት የመስማት ያህል እንኳን አላስደነግጠን ብሏል፡፡ በፖለቲካና በነጻ ተቋምነት መሃከል የዋልሉ ተቋማት አሁን አሁን የጠቅላዩ ኢህአዴግ ክንፍ መሆናቸዉን በተግባር እያሳዩን ነዉ፡፡ መንግስት በከሳሽነት በሚቀርብባቸዉ ፖለቲካ-ቅብ የክስ ጉዳዮች ተሸናፊ ሆኖ የታየበት አጋጣሚ የለም፡፡ የፍርድ ቤት ዉሳኔ በማረሚያቤት አመራሮች ሳይፈጸም ሲቀር የታዘብንባቸዉ አጋጣሚዎች ከጣቂት በላይ ናቸዉ፡፡ “ፍትህ”ን በብረትና በገንዘብ የገዙ አካላት አንገታቸዉን ቀና አድርገዉ በሚሄዱባት ኢትዮጵያ፣ የግፉአን ድምጽ በርክቶባታል፡፡ ጎን ማሳረፊያ ያጡ ዜጎች በበረከቱባት ሃገር፣ ከግማሽ ደርዘን በላይ ቪላ ቤቶች በተለያዩ ግለሰቦች ስም ያለዉ የኢህአዴግ መካከለኛ አመራር ፈልጎ ማግኘት ያን ያህል የሚከብድ አይደለም፡፡ በቦታ ርቀት፣ በግንዛቤ ማነስ፣ ከበቂ የምግብ አቅርቦት እጦት ጋር በተያያዘና መሰል ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተነሳ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ህጻናትና ወጣቶች በየአመቱ ትምህረታቸዉን ለማቋረጥ በሚገደዱባት አትዮጵያ፣ ልጆቻቸዉን ከአንድ ቀበሌ የግማሽ አመት በጀት ጋር የሚስተካከል የዉጭ አገር ትምህርት ቤት የሚያስተምሩ የአህአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣናት ቁጥር እንደ ኢኮኖሚ “እድገቱ” ሁሉ በሁለት አሃዝ የሚገለጹ ናቸዉ፡፡ ንጹህ የመጠጥ ዉሃ ያጣ ህዝብ በበረከተባት አገር፣ የአልኮል መጠጥ ፋብሪካ በአክሲዮን ስም የገነቡ፤ ሚለዮኖች የዕለት ጉርሳቸዉን በጡበት ሁኔታ የግል ባንክ ባለቤት የሁኑት ባለስልጣናት የደም እንጀራ እየጎረሱ እንደሆነ ሊረዱት አልቻሉም፡፡
የኢህአዴግ ባለስልጣናትን ነገረ-ስራ በቅጡ ያስተዋለ ሰዉ የሚከተለዉ ድምዳሜ ላይ መድረስ ይቻለዋል፡፡ እርሱም፡- ‘ማንኛዉም የኢህአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣናት ከህግ በላይ ናቸዉ፡፡ የትኛዉም የህዝብም ሆነ የአገር ሃብት የባለስልጣናቱ እንጂ የህዝብ አይደለም’ ባልተጻፈ ህግ እየተተገበረ ያለዉ እዉነታ ይህ ነዉ፡፡ ኢህአዴግ “የ አስራ ሦስት ወር ጸጋ” የተባለላትን አገር ወደ አስራ ሦስት ወር የፖለቲካ ጭቆናና የኢኮኖሚ ብዝበዛ አሻግሯታል፡፡ የአገሪቱ ማህበራዊ ቀዉስ ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አላየንም፡፡ አይነ ስዉሩን ደርግ ሸኝተን ደንቆሮዉን አህአዴግ ተክተናልና ዛሬም እንደ ትላንቱ በደል የማንነት አካል ሆኗል፡፡ አስር፣ እንግልት፣ ስቅየት፣ ስደት፣ ሞት … ከገዥዉ መደብ በተቃራኒ የተሰለፉ ኢትዮጲያዉያን እጣ ፋንታ መሆኑን ሩብ ክፍለ-ዘመን ያካለለዉ የአገዛዙ ተሞክሮ ጮሆ ይመሰክራል፡፡ ገዥዉ መደብ በብዙ መልኩ ኮረብታዉ እርቆት ቁልቁለቱን በሚገርም ፍጥነት ተያይዞታል፤ የአይቀሬዉን አብዮት ማፍጠኛ የተጫነዉ ኢህአዴግ የህልዉናዉ ማክተሚያ ጊዜ ሩቅ አይደለም፡፡ በየአመቱ እንደ “መንግስት” አዋጂ አዲስ ዓመት መግባቱን በሚዲያ ስንሰማ ኑረናል፡፡ አዲስ ነገር በማናይበት ሁኔታ “አዲስ ዓመት” ብሎ ነገር ምናችን ነዉ?! እኛ ኢትዮጵያዊያን አዲስ አመት ሳይሆን አዲስ ስርዓት እንሻለን!!
(የዚህ ጦማር አቅራቢ ጋዜጠኛ ሙሉዓለም ገ/መድህን ሲሆን በቅርቡ “የኢሕአዴግ ቁልቁለት” በሚል ርዕስ የጻፈው መጽሀፍ ለንባብ በቅቷል፡፡ ይህ ጽሁፍ በተለይ ለጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ የተላከ ነው፡፡)

No comments:

Post a Comment