Translate

Wednesday, September 16, 2015

የሞላ ኣስገዶም ጉዳይ ስርዓቱ የቆመበትን መሰረት ማሳያ ነው

ገለታው ዘለቀ
ከኣመታት በፊት በምርጫ ዘጠና ሰባት ኣካባቢ ኣዋሳ ከተማ ውስጥ የገጠመኝ ነገር ትዝ ይለኛል ። በኣዋሳ ከተማ ቆይታየ ጊዜ ከኣንድ ታዋቂ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ እሳተፍ ነበር። በዚህ ድርጅት መሳተፍ እንደጀመርኩ ብዙም ሳልቆይ የወጣቶች ጉዳይና የድርጅት ጉዳይ ሆኘ ተመደብኩ።ታዲያ በዚያ ኣጭር ጊዜ ቆይታየ የመንግስትን የስለላ ስራና ተፈጥሮ እንድረዳ እድል ስለሰጠኝ ያ ጊዜ ኣስተማሪየ ሆኖ ይሰማኛል ። በውነት ለመናገር ያ የኣዋሳ ቆይታየ ስለ ወያኔ ያለኝን መረዳት ኣራምዶት ነበር።
ዛሬ የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (TPDM) መሪ የነበረው ኣቶ ሞላ የተወሰኑ ታጋዮችን ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ገባ የሚለው ዜና ከተሰማ በሁዋላ ያ የኣዋሳው ትዝታየ የኋሊት በምናብ ታወሰኝ። በተለይም የኣቶ ሞላ ኣስገዶምን ኢንተርቪው ሳይ “እኛ ከመንግስት ጋር ስንሰራ ቆይተናል። ግንኙነት ነበረን” ሲሉ የኣዋሳ ገጠመኘን በጣም ኣጉልቶ ኣሳየኝ።
እስቲ ኣዋሳ የሆነውን ላውጋችሁ። ኣዋሳ ከተማ ውስጥ እሳተፍበት በነበረው የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ከኮሚቴዎቹ መካከል ኣንዱ ማለትም የህዝብ ግንኙነት ክፍል ሃላፊው በጣም ይቀርበኝ ነበር። ኣቶ ኤልያስ ይባላል። ይህ ሰው ትሁት፣ ተቆርቋሪ፣ ለኣገር ኣሳቢ ነው። ኣቶ ሞላን ይመስላል። በስብሰባዎች ወቅት ማስታወሻ መያዝ ይወዳል። ስብሰባዎችን ስንጨርስ ኣቀፍ እያደረገ ወደ ጎን ወሰድ ያደርገንና ለድርጅቱ ያለውን ፍቅር፣ የእኛን ኣስተዋጾ ያደንቃል። እኔም እውነቱን ለመናገር ኣመንኩት። ታዲያ ከእለታት ኣንድ ቀን የተለመደውን ስብሰባችንን ኣጠናቀን ስንጨርስ
“ የማወራህ ብርቱ ሚስጥር ኣለኝና ኣብረን ወጣ እንበል” ኣለኝ ለስላሳው ኣቶ ኤልያስ
በደስታ። እንዴውም እኔም ዛሬ የማካፍልህ ኣሳብ ኣለኝ::

በተለይ በኣዋሳ ዩኒቨርሲቲ ኣካባቢ ልዘረጋው ያሰብኩትን መዋቅርና ፕላን ለማሳየት ፋይሌን ከፈትኩና ኣንድ ገጽ ወረቀቴን ይዤ ወጣሁ። እንደተለመደው ኣቶ ኤልያስ ኣቀፍ ኣርጎኝ እየመራኝ ከጽህፈት ቤቱ ግቢ ወጥተን ጉዞ ጀምረናል። ወደየት እንደምናመራ ኣልገባኝም፣ ኣልጠይቅምም። የኣዋሳው ዩኒቨርሲቲ ፕላኔ መስጦኝ ስለነበር በዚያ ዙሪያ ኣንዳንድ ኣሳብ እያነሳሁለት እንጓዛለን። ከጥቂት ጉዙ በኋላ ወደ ኣንድ የማይመች ኣጣብቂኝ ቦታ ይዞኝ ገባ።
ወደ ተሻለ ቦታ ሄደን ሻይ ቡና እያልን ብናወራ ኣይሻልም ኣቶ ኤልያስ?
ኣንድ ርምጃ ፈንጠር ብሎ ቆመና ጥቂት ዝም ኣለ። ግብዣየን እያሰበበት መስሎኝ ደግሜ ጠየኩት።
ኣቶ ኤልያስ ቀና ኣለና
“ኣይ! ሌላ ጊዜ ይሻላል ኣሁን ግን የማጫውትህ ብርቱ ምስጢር ኣለኝ “
ኣጫውተኝ፣ ምን ችግር ኣለ……….። ፈርጠም ብየ። የመሰለኝ ያው ከድርጅቱ እቅድ ጋር የተያያዘ ጉዳይ ነውና ።
“ችግር ገጥሞኛል እባክህ” ኣለ ኣቶ ኤልያስ ተስፋ እንደቆረጠ ሰው ፊቱን ኣቀጭሞ።
ምን ችግር ገጠመህ? መልሱን ሁሉ በኪሱ እንደሞላ ሰው ዘና ብየ
“ተይዣለሁ”
ማን ነው የያዘህ …. ማለቴ ኣልገባኝም??…..
“ይዘውኛል”
እነማን ናቸው የያዙህ ኣቶ ኤልያስ?
“ደህንነት ይዞኛል”
ኣልገባኝም?
“የመንግስት ደህንነት ይዞኝ ለነሱ እየሰራሁ እገኛለሁ”
ግራ ገባኝ በውነት።
ለነሱ እየሰራሁ ነው ስትለኝ ምን ማለት ነው?
“በቃ የደህንነቱ ዋና ሃላፊ ይዞኝ ለኛ ሰላይ ሁን ኣለኝ፣ ለኛ የማትሰልል ከሆነ በኣንተና በቤተሰብህ ላይ ፍረድ ስላለኝ ለነሱ እየሰራሁ እገኛለሁ። ቀን ቀን ከናንተ ጋር ተሰብስቤ ማስታወሻ ስይዝ እቆይና ማታ ማታ በሚኖረን ስብሰባ ላይ ሪፖርት ኣደርጋለሁ። በተለይ ኣንተ ወደዚህ ከመጣህ በሁዋላ የኣንተን ንግግሮች በሚገባ ማስታወሻ ይዤ ሪፖርት እንዳደርግ ታዝዤ ይህንን በማድረግ ላይ እገኛለሁ። ደህንነቱ ይከታተልሃል።”
ስንት ጊዜ ሆነህ እንዲህ ስታደርግ?
“ከዓመት በላይ ይሆነኛል” ልክ ኣቶ ሞላ ኣስገዶም ከዓመት በላይ ከመንግስት ጋር ስሰራ ነበር እንዳሉት::
ይህንን ጉዳይ ለድርጅቱ መሪዎች ኣሳውቀሃል?
“በፍጹም:!” ምላሱን ጎልጉሎ
ኣቶ ኤልያስ ቀጠለ …….“ ላንተ ብቻ ነው የምነግርህ…. ላንተ የምነግርህም በተለይ ስብሰባዎች ላይ የምትናገረውን እንድትጠነቀቅ፣ ይህንን የኣዋሳ ዩኒቨርሲቲ እቅድህን እንድታዘገየው ነው። “
እውነቱን ለመናገር በጣም ግራ ተጋብቼ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ሰው ኣሁን ይህን የሚነግረኝ ለእኔ ኣሳቢ ስለሆነ ነው ብየም ኣሰብኩ። ሁለታችንም መሬት መሬት እያየን ነገሮችን በማላመጥ ላይ እያለን። ኣንድ የቸኮለ ሰው የሚመስል በጎናችን ሲያልፍ
“ሰላም ኤልያስ” ኣለ።
ሰውየው በጎኔ ሲያልፍ ኣየሩን ቀዝፎት ነበር። ለምን በዚያ መጠጋጋት በስራችን እንዳለፈ ኣላውቅም። ለማስፈራርትም ሊሆን ይችላል።
የኣየር ላይ ሰላምታ ተለዋውጠው ሲያበቁ ኤልያስ ጠበብ ያለ ሳቅ ጀመረ።
“ይሄም የኛ ሰው ነው….ሰላይ ነው… ማታ ማታ ሁሌ እንገናኛለን”
ኣሁን ጨዋታ በቃኝ። ብቻየን መሆንና ማሰብን መረጥኩ።
ጥሩ ኣቶ ኤልያስ ስለ ሰጠኸኝ መረጃ ኣመሰግናለሁ። ሌላ ጊዜ እንጫወታለን። እጄን ዘረጋሁ። ለሰላምታ።
“ኣንተንም በቅርቡ ሊያነጋግሩህ ሊጠሩህ እንደሚችሉ እገምታለሁ።”
እኔን?
“ኣዎ! ” ደሞ ይስቃል
ውስጤ በሸቀ። ዛሬ ማታደህንነቱን ስታገኘው ወደኔ ኣትምጡ በልልኝ ብየ የማመናጨቅ ያህል ሰላም ብየው ተለየሁ።
ጉዳዩን ሮጦ ለሌሎች ከመናገር በፊት መመርመር መረጥኩና ጋሪ ተሳፍሬ ወትሮም ወደምወደው የኣዋሳ ሃይቅ ዳር ኣመራሁ። በዛ ቁጭ ብሎ የኣዋሳን ግርማ እያዩ ማሰቡ ይረዳል።
ኣዋሳ ሃይቅ ዳር ቁጭ ብየ ማሳብ ጀመርኩ።
ይህ ሰው እንዴት ይህን ብርቱ ምስጢር ሊነግረኝ ቻለ?
ለምንስ እኛን ሰላማዊ ታጋዮችን በዚህ ደረጃ መሰለል ኣስፈለገ?
ምን የተደበቀ ነገር ኣለን?
ምን ስለላ ያስፈልገናል? ብዙ ጥያቄዎች ያለ ወረፋ በኣይምሮየ በፍጥነት ይጎርፋሉ። ኣንድ ደረጃ ከፍ ብየ ማሰብ እንዳለብኝ ተሰማኝ።
ያኔ ኣገሩ ኣንጻራዊ የሆነ ሰላም ነው። ብዙ የፖለቲካ ድርጅቶች በተሻለ ኣንጻራዊ ነጻነት ይሰራሉ ፣ ምንድነው ይሄ ነገር?……… ኣሳብ ሳወጣ ሳወርድ ከቆየሁ በሁዋላ የወያኔን ዘዴ ለመረዳት ብዙ ኣልተቸገርኩም። የኣዋሳ ጀምበር ደህና እደር ኣዋሳ ስትል፣ የሃይቁ ፍጡራን እነ ጉማሬ በውሃ ሲጫውቱ ከተቀመጥኩበት ተነሳሁ። ከሃይቁ ዳር ዳር ቀጥፌ የነበረውን ሳር ወደ ውሃው ወረወርኩና ሽቅብ ወደ ማረፊያየ ኣቀናሁ።
ግምቴን ይዤው ጥቂት ቀን ቆየሁና የሚቀጥለው የኮሚቴው ስብሰባ ላይ ተገኘሁ። ስብሰባው ቅዝቅዝ ብሏል። ኣዲስ ኣሳብ ኣይሰነዘርም። ጥቂት የኮሚቴው ኣባላት ላይ ምክንያት የለሽ ደረቅ ፈገግታ ኣያለሁ። እርስ በርስ መተያየት ተያይቶ ሲያበቁ ፈገግ ማለት ሆነ ስራችን። እንዲሁ የሆነ ያልሆነውን ጥቂት ኣወራንና የመለያያ ጊዜ ደረሰ። ኣቶ ኤልያስን ሰረቅ እያደረኩ ኣይ ነበር:: ለሌሎችም ተመሳሳይ ነገር ነግረው እንደሆነ ከኣይምሮኣቸው መረጃ ለመስረቅ ጥረት ኣደረኩ። ለማናቸውም ኣንዱን የኮሚቴ ኣባል መጨረሻ ላይ በጎን በጎን ኣድርጌ በማውራት ለሌሎችም ይህን ለኔ የነገረኝን መንገሩን ለመረዳት ኣስቤ ጠየኩት። በርግጥም ለእኔ የደረሰኝን ኣይነት መረጃ ለዚህ ሰውም እንደደረሰው ገባኝ።
ነገሩ እያደር እየበራልኝ መጣ። ኣቶ ኤልያስ በርግጥ የስለላ ስራ ይሰራል። የስለላ ስራውን የሚሰራው ግን እንገልሃለን ስለተባለ ሳይሆን ለረጅም ጊዜ የወያኔ ኣባል ነው። ኣሁን የተሰጠው ሚሽን በዚህ እኔ በምሳተፍበት የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ በሃላፊነት ቦታ ሰርጎ በመግባት በዚህ ቀጣና ያለውን ሰላማዊ ትግል ማፍረስ ነው። ኣቶ ኤልያስ ደምበኛ ወያኔ ሲሆን ለእኔ ያንን ምክር መሳይ ማስፈራሪያ የሚነግረኝ በስብሰባዎች ላይ ኣሳብ እንዳላቀርብ፣ ፈርቼ ቶሎ ከዚያ ድርጅት እንድወጣ ነው። ይህ ሰው ተልእኮው ይሀ ነው። ኣቶ ኤልያስ ጥሩ ሰው ይምሰል እንጂ እየተቅለሰለሰ ስራ ይጎትት እንደነበር ኋላ ላይ መገምገም ችየ ነበር።
ወያኔ የተቃዋሚ ድርጅቶችን ለመምታት የሚጠቀማቸው ስልቶች ብዙ እንደሆኑ ይህ ጉዳይ ያሳየኝ ጀመር። ተገረምኩ። ኣብሪ ጉዳይ ሆኖ ታየኝ። ጉዳዩ ኣገራዊ ሆኖ ገዝፎ ታየኝ። በርግጥ በማእከላዊ ደረጃ፣ በሁሉም ፓርቲዎች ዘንድ ይህ ኣይነቱ የወያኔ ኣሰራር ወጥነት ሊኖረው እንደሚችል ኣመንኩ። በውነት ኢትዮጵያ ያሳዘነችኝ ያን ቀን ነው። ኣሳዘነችኝ። ሚናው ያለየለት ትግል ውስጥ ሆና ግራ ተጋብታ ታየችኝ። ወያኔ ትግሉን እንዴት እንዳወሳሰበው ሳይ ኢትዮጵያን ለቆ የመውጣቱ ጉዳይና የታጠቁ ሃይሎችን የመቀላቀሉ ጉዳይ በውስጤ ሲደምቅ ይሰማኝ ነበር። የታጠቁት ሃቀኛ ናቸው፣ ወያኔ ሰርጎ ኣልገባባቸውም የሚለውን እምነት ከየት እንዳፈስኩት ባላውቅም የተሻለ ኣማራጭ መስሎ ግን ታየኝ።
ከሁሉ በላይ ግን የወያኔ ስርዓት በምን ላይ እንደቆመ የመመርመሩ ጉዳይ ዝንባሌየን ሳበው። ይህ ጥያቄየም የሃገሬን የፖለቲካ ችግር የሚያስረዳኝ ለወደፊት ተሳትፎየም በመረዳት ላይ ያተኮረ ድጋፍ ለመስጠት የሚረዳኝ መሰለኝ።
ብዙ ሰው እንደሚረዳው የወያኔ መራሹ መንግስት በትግል ሂደቱም ሆነ ኣሁን ስልጣን ከያዘ በሁዋላ የሚጠቀምበት ስልት ጠለፋ (haijacking)መሆኑ በመረጃ ተደግፎ ገባኝ ። በሰፊው ኣገራዊ ችግርም ሆኖ ስለታየኝ ኣዲስ ነገር መሰለኝ።
ህወሃት ራሱ “ኢሃዴግ” ብሎ የሚጠራውን ካባ ለመልበስ ሲል የተለያዩ የብሄር ድርጅቶችን የፈጠረ ሲሆን እነዚህ ድርጅቶች በወያኔ ሙሉ በሙሉ የተጠለፉ ናቸው። እንቅሳቃሴዎቻቸው ሁሉ በህወሃት የተጠለፈ፣ መጠለፍ ብቻ ሳይሆን በቁጥጥር ስር የዋሉ ናቸው። ህወሃት እነዚህን ድርጅቶች ጠልፎ ጠልፎ ኣንድ “ኢሃዴግ” የሚባል ካባ ይለብስና መንግስት ሲመሰርት ደግሞ መንግስትን ራሱን በሙሉ ሲጠልፈው እናያለን። ሰኪዩሪቲው፣ወታደሩ፣ ሲቪል ሰርቪሱ በሙሉ የመንግስት ተቋማት በህወሃት ተጠልፈው እናያለን። ይህ ብቻ ሳይሆን የተቃዋሚውን ክፍል ሰላማዊውን ትግልና የትጥቅ ትግሉንም መጥለፍ ለዘላቂ ስልጣን ይጠቅመኛል ብሎ ስለሚያስብ ኣንዳንዴ ራሱ መንግስት ተቃዋሚ ነን የሚሉ ድርጅቶችን እየፈጠረ ኣንዳንዴ በእውነተኛ ተቃዋሚ ድርጅቶች ውስጥ እስከ ሃላፊነት ደረጃ የሚደርሱ ኣስመሳይ ወያኔዎችን እየሰገሰገ የጠለፋውን ስራ ሲሰራ እናያለን። ይህ የሚያሳየው ራሱ መንግስት በጠለፋ ላይ የተዋቀረ መሆኑን ነው። ይህ የህወሃት መሰረታዊ ት በስልጣን ላይ የመቆያ እምነትና ዘዴ ነው። ህወሃት ወደ ስልጣን ሲመጣም ከመጣም በሁዋላ የማይለወጥ ይህ የጠለፋ ዘዴው በዜጎች ሁሉ ዘንድ መታወቅና መጋለጥ ኣለበት። እውነተኛ የተቃዋሚ ድርጅቶችም በተለይ ኣመራር ኣካባቢ ያሉ ሰዎች ትግሉ እንዳይሄድ ሲያደርጉ ይህን የወያኔን የጠለፋ ተፈጥሮ በመገንዘብ ኣባላት ኣመራሮቹን ወጥሮ ሊይዝ ይገባል። በየጊዜው ትግሉ የት ደረሰ? ብሎ ወጥሮ ሊይዝ ይገባል። የየፖለቲካ ፓርቲ ኣባላትና ንጹሃን ኣመራሮች ድርጅታቸው ወደ ኣንድነት የማያመራበትን ምክንያት ኣጥብቀው መጠየቅ ወደ ኣንድነት የማያመራ ከሆነ መልቀቅና ማጋለጥ ያስፈልጋል።
ለዛሬው ጽሁፌ መነሻ ወደ ሆነኝ ጉዳይ ልመለስና በትህዴን ሊቀመንበሩ በኣቶ ሞላ ኣስገዶም ጉዳይ ልንደነቅ ኣይገባም ለማለት ነው የቆምኩት።ይህ ጉዳይ የስርዓቱ መሰረት መገለጫ ነው ለማለት ነው። ኣቶ ሞላ ኢትዮጵያ ከገቡ በኋላ የሚነግሩን ከመንግስት ጋር ስንሰራ ኣንድ ኣመት ኣልፎናል ረዘም ላለ ጊዜ ስንሰራ ነበር ይላሉ። ይህ ማለት ኣቶ ኣንዳርጋቸውንም ያሳፈኑት እነሱ ናቸው ማለት ነው። ኣንዳርጋቸውን ሲያታልሉ ሲሰልሉ ነው የከረሙት። ያሳዝናል።
ሲሰልሉ የቆዩበት ጊዜ ግን ውሸት ነው። ወያኔ በጣም ይፈራ የነበረው የታጠቁ ሃይሎችን ሲሆን እነዚህን ሃይላት ለመጥለፍ እንደ ትህዴን ኣይነቱን መጥለፍ ወሳኝ መስሎ ነው ይሚታየውነው።ከስልጣን የሚያስለቅቀው ሃይል ሲፈጠር ደግሞ ለመጨረሻ ጊዜ ኣማራጭ (worst case scenario) የሚያገለግል ሃይል ኣድርጎም ነበር የሚያየው።
በመሆኑም በዚህ ድርጅት ውስጥ ከመሪው ጀምሮ እንደ ኣዋሳው ኣቶ ኤልያስ ኣይነት ሰው ኣስቀምጦ የትጥቅ ትግሉ እንዳይራመድ ማድረግ፣ የትጥቅ ትግሉ እንዳይራመድ ብቻ ሳይሆን በስርዓቱ ተማረው በትጥቅ ትግል ወያኔን ለመጣል ከኢትዮጵያ የሚመጡትን ኢትዮጵያዊያንን ይዞ በማቆየት፣ ወይም በማጥፋት ወይም ኣሳልፎ በመስጠት ስራቸውን ሲሰሩ ቆይተዋል። ኣቶ ኣንዳርጋቸው ኣንዱ ሰለባ ናቸው።
ልብ በሉ …..ትህዴን ከተቋቋመ ረጅም ጊዜው ሲሆን ብዙ ወታደር ኣለው ተብሎ ይወራል። የሚገርመው ግን ኣንድ ቀበሌ እንኳን ሲይዙ የትጥቅ ትግሉን ሲያጠናክሩ ኣይታይም።ህወሃት በተቋቋመ በስድስት ወሩ ከፍተኛ ውጊያዎችን ኣድርጎ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ነጻ መሬት እያሰፋ ነበር የሄደው። እነ ሞላ ኤርትራ ቁጭ ብለው ሌሎች ተቃዋሚ ሃይላትን እያዳከሙ የወያኔ ደጀን ሆነው ቆይተዋል። እነዚህ ሃይሎች የትጥቅ ትግሉን የሚጠልፉ ቡድኖች ናቸው። ይህ ማለት ግን ኣብዛኛውን የዋህ የትህዴንን ኣባል ኣይወክልም። በየትኛውም የተቃዋሚ ድርጅት ውስጥ ወያኔ ግዙፉን ህዛባዊ ድጋፍ ኣያገኝም። ህዝቡ ተቃዋሚዎች ኣለን የሚሉትን መርህ ስለሆነ የሚደግፈው ወያኔ ይህን ሃይል መቼም ቢሆን ሊጠልፈው ኣይችልም። ይሁን እንጂ ኣመራር ላይ ያሉትን ኣንዳንዶችን እንዲህ እየጠለፈ ትግሉን ማጓተቱ ኣንዱ የስርዓቱ እምነትና መሰረት መሆኑን መረዳት ኣለብን። ለዚህ ነው ሰፊው ህዝብና ኣባላቱ ድርጅቶቹን ውጤት ተኮር ግምገማ ሊያደርግባቸው ይገባል የሚያስብለን።
ወያኔን ከጠለፋ ስራው የምናጋልጠውና ትግሉ የሚ ጠናከረው ፓርቲዎችን ወደ ተግባር በምንገፋው የግፊት መጠን ነው። የወያኔ መርህ የሆነውጠለፋ በመንግስት፣ በተቃዋሚዎች ደረጃ ብቻ ሳይሆን በኣለም ኣቀፍ ተቋማት ኣካባቢ የሚቃወሙትን፣ የሰባዊ መብት ረገጣውን በሚያጋልጡ ድርጅቶች ሁሉ ላይ ያነጣጠረ ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ። የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ጠብቀው ሲያጋልጡትና ርዳታ ሲያስቀሩበት ወያኔ ዝም ይላል ብሎ ማሰብ የወያኔን ቂመኛ ባህሪ ያለማወቅና የዋህነት ነው። ስለዚህ እኛ ኢትዮጵያውያን ለነዚህ ተቋማትና ለለጋሽ ኣገራት የወያኔን የህዝብ ግንኙነት ስራና ተንኮል ማጋለጥ ኣለብን።
ኢትዮጵያውያን የወያኔን ስርዓት ኣወቃቀር በሚገባ ልንረዳ ይገባናል የሚያስብለን ትግሉን ወደፊት ለማራመድ ዘዴኛ እንድንሆን እንጂ ሁሉን እንድንጠረጥርና ተስፋ እንድንቆርጥ ኣይደለም። ስርዓቱ የቆመበት ይህ የማታለልና የጠለፋ ድርጊት መፍረስ ኣለበት። በሌላ በኩል ስለ ወያኔ ተፈጥሮ ስናወራ መርሳት የሌለብን ወያኔ ራሱ ድርጅቱ እንደ ፖለቲካ ድርጅት የሚታይ ኣይደለም። ህወሃት የማህበራዊ ኢኮኖሚ ተቋም ሲሆን ይህ ተቋም መንግስትን በተለይም ወታደሩንና ሰኪዩሪቲውን ጠልፎ የሚኖር ነው። የህወሃት ውስጣዊ ማንነት ኤፈርት ነው። ምንም ኣይነት የጠራ የፖለቲካ ርእዮት የማናየው፣ ኣገሪቱ ወደ ተሻለ መድብለ ፓርቲ ስርዓት የማትራመደው የወያኔ ተፈጥሮ ፖለቲካዊ ዝንባሌ ያለው ሳይሆን የሶሺዮ ኢኮኖሚክ ተቋምነት ባህርይ ያለው በመሆኑ ነው። ይህንን ስርዓት የሚቃወሙ ሃይላት በፍጹም በጎሳ ላይ መደራጀት የለባቸውም። ጎሳ ተኮር የሆነ ትግል በመርህ ደረጃ ከወያኔ ኣይለይም።
ምን ኣልባት በየዋህነት ለውጥ በዚህ መንገድ ይመጣል ብለው የተነሱ ሃይለት ኣሁን የሚረዱበት ዘመን ይመስላል። ከመጣመድ ከግንባር ወጥተው መዋሃድ ኣለባቸው። ጎሳዊ ስም ይዞ በኣንድ በኩል በኢትዮጵያ ኣንድነት ኣምናለሁ የሚለው ፍልስፍና በሚገባ መጤንና ስህተትነቱ ሊገባን ይገባል። ሚናው የለየለት ትግል ውስጥ ካልገባን ወያኔ ለጠለፋ ስራው የሚጠቅመውን ሁኔታ እናመቻቻለን።
የኣቶ ሞላ መኮብለል የሚያሳየው ሃቀኛ ትግል እያየለ መምጣቱን ሲሆን ኣሁንም ቢሆን ፓርቲዎች እያጠሩ ቶሎ ወደ ውህደት መራመድ ኣለባቸው። ውህደት በራሱ የሚያፈርሰው ብዙ የወያኔ ሴራ ኣለ። በሌላ በኩል ወያኔ ኣደገኛነቱ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለኤርትራውያንም ነው። ኣጠቃላይ የሃበሾችን መጻኢ እድል እያወሳሰበ ያለ መጥፎ ሰርዓት ነው።
እዚህ ላይ ኣንድ ነገር በግልጽ መናገር ጥሩ ነው። ይሄ “ወያኔ” የሚለው ኣጠራር ትርጉሙ ፈጽሞ ከትግራይ ተወላጆች ጋር መያያዝ የለበትም። የትግራይ ወጣቶችም ይህን ስያሜ ከባህላዊ ቡድናቸው ማንነት ጋር ማያያዝ የለባቸውም። ወያኔ የብሄር መጠሪያ ኣይደለም። ወያኔ ማለትራሱ ስርዓቱና የስርዓቱን ተዋንያን የሚያሳይ ሲሆን ኣዲሱ ለገሰም፣ በረከት ስምዖንም፣ ኣባዱላ ገመዳም፣ ሃይለማርያም ደሳለኝም፣ ቴድሮስ ኣድሃኖምም፣ ወያኔዎች ናቸው።እነሱም ሁላችንም ወያኔዎች ነን ብለዋል። የትግራይ ወጣቶችም ሆኑ ሌሎች ወገኖች ከዚህ ከማንነት ፖለቲካ መራቅ ኣለብን። ሃበሾች ለነጻነታችን ስንል ከዚህ ከፋፋይ ኣስተሳሰብ ጋር መታገል ኣለብን። የተባበረችውን ኢትዮጵያን የምንገነባው ወጣ ባለ ኣሳብ ነው።ከሁሉ በላይ የወያኔን የጠለፋ ስርዓት ስንረዳው በየጊዜው የሚከዱ፣ ትግሉን ሲጎትቱ የሚያዙ የተቃዋሚ መሪዎችን ነገር ግን የወያኔ ሰላዮችን ስናይ ግራ ሳንጋባ የበለጠ የዴሞክራሲ ትግላችንን እናቀጣጥላለን። ጉዳያችን ከመርህ ጋር የተጣበቀ፣ ከኢትዮጵያ ኣንድነት ጋር የተጣበቀ ይሁን። ሚናው የለየለት ህብረት እንመስርት። ሚናው የለየለት የትግል ኣውድማ ውስጥ እንግባ። ከዚያ ብዙ ህዝብ የሚጠብቀው የትግል ፍሬ ይታያል።
የተባበረችውን ኢትዮጵያን እንገንባ
እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ
geletawzeleke@gmail.com

No comments:

Post a Comment