Translate

Wednesday, December 23, 2015

በነ ኦነግና ግንቦት ሰባት አታሳቡ ይላል ሪፖርተር ጋዜጣ – የሚሊዮኖች ድምጽ


ገዢው ፓርቲ ሕወሃት/ኢሕአዴግ በኦሮሚያና በጎንደር ለተከሰተው ቀዉስ ጣቶቹን በዉጭ ያሉ አመጽ ቀስቃሽ ኃይሎች በሚላቸው ላይ ማድረጉ ይታወሳል። አቶ ጌታቸው ረዳ ፣ የመንግስት ቃል አቀባይም አፋቸዉን ሞልተው ተቃዉሞ ያሰሙትን በመቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችንን “ጋኔኖች” ፣ በዉጭ ያሉ “ጋኔኖችን” የሚያንቀሳቀሱ ያሉዋቸዉን ደግሞ “ጠንቁዋዮች” የሚል ከአንድ ትልቅ አገር የመንግስት ቃላቀባይ በጭራሽ የማይጠበቅ ርካሽ ንግግር መናገራቸው ይታወሳል።

አገር ዉስጥ የሚታተመው ሪፖርት ጋዜጣ ግን አይስማም። የተፈጠረው ችግር የዉጭ ኃይሎች የሚባሉ ያመጡት ሳይሆን የስርዓቱ ጸረ-ዴሞክራሲያዊ አሰራር የፈጠረው እንደሆነ ሪፖርተር በርእስ አንቀጹ ተንትኑዋል። በሌለ አባባል ሪፖርት ከአገዛዙ “በነ ኦነግና ግንቦት ሰባት በመሳሰሉት አታሳቡ። ችግሩ ያለው እናንተ ጋር ነው” ማለቱ ነው።
“ድምጻቸው እንደታፈነባቸው የሚሰማቸው ወገኖች፣ ሕገ መንግስቱን ያረጋገጠላቸው መብትና ነጻነት ባለመከበሩ ምክንያት ሁከት ማንሳታቸው ሳይነገር፣ ከበስተጀርባ ስላሉ ኃይሎች በብዛት ሲነገር ይሰማል። አንድ ዜጋ መሰረታዊ መብቶቹ ከተከበረለትና በአገሩ በነጻነት እየኖረ መሆኑን ማረጋገጥ ከቻለ፣ ከድህነት ሊያወጣው የሚችልን ልማት ሊቃወም አይችልም፡፡ሌላ ፍላጎት ላላቸውም መሳሪያ አይሆንም” ያለው ሪፖርተር “ መንግስት ይህንን በፍጥነት በማጤን ሕግ መንግስቱን ማስከበር አለበት። ሕግ መንግስቱ ሳይከበር ቀርቶ ድንገተኛ አመጽ እየተከሰተ የዜጎችን ሕይወት የሚቀጥፍበት ምንም ዓይነት ሰበብ ሊኖር አይገባም። መንግስትም በግባትዊነት የሚፈነዱ ብጥብጦች ከሕግ የበላይነት መጥፋት ጋር የታያያዙ መሆናቸው የግድ ማመን አለበት። ከበስተጀርባ አሉ የሚባሉ ኃይሎች አመጹን የመምራት እድል የሚያገኙት ዜጎች መብታቸው ሳይከበርላቸው ሲቀር መሆኑ መታወቅ አለበት። የሕዝብን መሰረታዊ መብቶች የሚጋፉ ተግባራት ይወገዱ” ሲል አገዛዙ የችግሩ መንስኤ ዋና የሆነው፣ አምባገነናዊ አሰራር እንዲወገድ ጠይቁዋል።
ሕወሃት/ኢሕአዴ ለዲሞክራሲ ቆሚያለሁ እያለ የሚመጻደቅ ደርጅት ነው። የደርጅቱ መሪ አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ስለ ዲሞክራሲ ብዙ ጊዜ ሲናገሩ “ዴሞክራሲ የሕልዉና ጉዳይ ነው” ይላሉ።
ሪፖርት ግን አገዛዙ ለዲሞርካሲ ያለውን ቁርጠኝነት ትልቅ ጥያቄ ምልክት ዉስጥ ውስጥ ያስገባዋል ።በሌላ አባባል፣ ዲሞክራሲ፣ ዲሞርካሲ እያላችሁ፣ በከንቱ ህዝቡን ባትዋሹና ራሳችሁን ባታስገመቱ ይሻላል ነው ሪፖርት እያለ ያለው።
“የዜጎች ድምጽ የሚሰማባቸውን መድረኮች አለመክፈቱ ትልቅ ፈተና ነው። የመንግስት መገናኛ ብዙሃን የተለዩ ድምጾች ካልተሰማባቸው፣ አመለካከትን በነጻነት የሚገልጹባቸው መድረኮች ከሌሉ፣ ሰላማዊ ሰልፎችና ሕዝባዊ ዉይይቶች ካልተከናወኑ፣ የዜጎችን ሐሳቦች የሚያስተጋቡ የሲቪል ማህበራት ከጠፉ፣ በፖለቲካ ምህዳሩ መጣበብ ምክንያት የፖለቲካ ፓርቲዎች ከተልፈሰፈሱና መሰረታዊ መብቶች ካልተከበሩ ዴሞክራሲ ማለት ምን ማለት ነው ?” ሲል ሪፖርት በመጠየቅ ነው፣ የዛሪይቱ የሕወሃት/ኢሕአዴግ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲ የሰፈነባት ሳይሆን ዲሞክራሲ የራቃት እንደሆነ ለማሳየት የሞከረው።
ገዢው ፓርቲ ባለስልጣናት ብዙ ጊዜ ሕግ መከበር እንዳለበት በአደባባይ ሲሰብኩ ይሰማሉ። “ሕገ መንግስታችን” ይላሉ። ሆኖም ብዙ ጊዜ ሕዝቡ በሚያሰማቸው ተቃዉሞዎች “ሕገ መንግስቱ ወረቀት ብቻ” እንደሚባለው፣ ሪፖርተር ጋዜጣም በመስማማት፣ “ሕግ መንግስቱ ካልተከበረ በጽሁፍ ሰፍሮ መቀመጡ ምን ይጠቅማል ? “ ሲል ፣ ተግባር በሌለበት ሁኔታ ያለው ሕግ መንግስት ጥርስ የሌለው ወረቀት ብቻ እንደሆነ ነው ለመገልጽ ሞክሩዋል።

No comments:

Post a Comment