Translate

Monday, November 18, 2013

የስደት ውርደት በዛ! ኢትዮጵያዊነትም ረከሰ

በሳዑዲ ዓረቢያ በኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ላይ እየተፈጸመ ያለውና እየተስተጋባ ያለው አሰቃቂ ግድያና ድብደባ ይዘገንናል፣ ይሰቀጥጣል፣ ያቅለሸልሻል፡፡ አረመኔያዊ ነው፡፡ 
የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት የራሱን ሕግ ማስከበር እንዳለበት እናምናለን፡፡ በሕገወጥ መንገድ አገሪቱ ውስጥ የገቡትን ሰዎች ወደ አገራቸው ቢመልስ ወይም ቢያባርር ተቃውሞ የለንም፡፡ ጥያቄያችንና ተቃውሞአችን ግን በሕገወጥ መንገድ የገቡትን ኢትዮጵያውያን ለምን መለስካቸው?ለምን አባረርካቸው?የሚል አይደለም፡፡ ሕገወጦችን መቆጣጠርና ሕግን ማስከበር የማንም አገር መብትና ኃላፊነት ነውና፡፡

ግን! ነገር ግን! በሕገወጥ መንገድ የገቡትን ኢትዮጵያውያን በሕጋዊ መንገድ ወደ አገራቸው ይመልሳል ወይም ይቀጣል እንጂ፣ ግድያና ማሰቃየት ማካሄድ የለበትም፣ አልነበረበትም፡፡ 
እኛም እንደምንከታተለው የዓለም መገናኛ ብዙኃንም እያስተጋቡት እንዳለው፣ በመጀመሪያ ከኢትዮጵያ የሄዱት የቤት ሠራተኞች እንደ ባርያ እንጂ እንደ ነፃ ሰው አይታዩም፡፡ እንደ እንስሳና እንደ ባርያ ነው የሚቆጠሩት፡፡ በሕጋዊ መንገድ የገቡትም ጭምር፡፡ 
ከዚያም አልፎ በየቤቱ ፖሊስ እየገባ ሕገወጥ ናችሁ እያለ ሲገድልና አስከሬን በየጎዳናው ሲወረውር በግልጽ በሚስቀጥጥ ሁኔታ እየታየ ነው፡፡ የሳዑዲ መንግሥት የራሱን ሕግ የማስከበር መብት እንዳለው ሁሉ፣ ማክበር ያለበትና የሚገደድባቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕጎች እንዳሉም ሊገነዘብና ሊተገብር ይገባዋል፡፡ 
በተለይም በዘፈቀደ አንዳንድ የሳዑዲ ዓረቢያ ተወላጆች የሚፈጽሙት ግፍ አልበቃ ብሎ፣ የመንግሥት የፀጥታና የፖሊስ ኃይል ቤት ለቤት እየገባ ግፍና ወንጀል በኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ ሲፈጽም፣ በማያወላዳ መንገድ ዓለም አቀፍ ሕግን መጣስ ነው፡፡
ሕግ መጣሱና ወንጀል መፈጸሙ አሳዛኝ መሆኑ እንዳለ ሆኖ፣ በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያውያን በባህልና በታሪክ የማይገናኙዋቸው አውሮፓና አሜሪካ ሄደው እንዲህ ዓይነት ግፍ አልተፈጸመባቸውም፡፡ ለዘመናት በታሪክ፣ በባህል፣ በቋንቋና በሥነ ልቦና ከሚቀራረቡት የሳዑዲ ዓረቢያ ሕዝብ ይህ ዓይነቱ ግፍ ሲደርስባቸው የሚፈጥረው ስሜት ውግዘት ብቻ ሳይሆን ምፀትም ነው፡፡ ሕዝባችን ከሳዑዲ ዓረቢያ ሰዎች ጋር ብቻ ሳይሆኑ ከሌላው ዓለም ሕዝብ ጋር በአገሩም ሆነ በውጭ በፍቅርና በመተሳሰብ መኖር የሚችል ነው፡፡
በሳዑዲ ዓረቢያ እየተፈጠረ ባለው አስደንጋጭ ድርጊት እንደ ኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ብዙ ልንማረውና ልንፈጽመው የሚገባን ነገር አለ፡፡  ከሁሉም በፊት እንደ መንግሥትም እንደ ሕዝብም ይህንን ድርጊት በይፋና በግልጽ ልናወግዘው ይገባል፡፡ አላስፈላጊ ረብሻና ግርግር በመፍጠር ሳይሆን ድርጊቱን በትክክል እንዳወቅነው፣ ሕገወጥና አረመኔያዊ እንደሆነና በጥብቅ እንደምናወግዘው በግልጽ መልዕክታችንን እናስተላልፍ፡፡  

No comments:

Post a Comment