Translate

Wednesday, November 20, 2013

በግብታዊነት የተደራጀ የልማት ሰራዊት ውጤቱ ጥፋት ነው -ከአስገደ ገ/ስላሴ ወ/ሚካኤል መቐለ

ህ.ወ.ሃ.ት ትግራይን በመልካም አስተዳደር ፣ በፍትህ፣ በነፃነት፣ በልማት፣ በግብር አሰባሰብ ፣ በባለሃብቶች ፍሰት የኢንቨስትመንት ግበአት፣ በከተማ ልማት በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት እድገት በእርሻ እድገት በአርሶ አደሩ ሞዴልነት በኢንዱስትሪ በጤና ፣ በትምህርት፣ ጥራት፣ በማህበራት ኣደራጃጀት በሁሉም አይነት ዲሞክራሲ መብት አጠባበቅ ሞዴል፤ ለሁሉም ክልሎች እንደሰርቶ ማሳያ ተደርጎ ነዉ የሚቀርበው የህ.ወ.ሃ.ት መሪዎች ሲደሰኩሩበት የቆዩና ያሉት ። ሃቁ ግን በሚከተሉት ፅሁፍ አንቀፅ በአንቀፅ ላስቀምጣቸዉ እሞክራለሁ።
በትግራይ ክልል ብዙ ብቁ ምሁራኖች ከዲፕሎማ እስከ ዶክትረት ደረጃ የተማሩ ሊቃኖች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በእርሻ ምርምር በጤና ፣ በትምህርት፣ በመአድን፣ በኢኮኖሚክስ ፣ በሂሳብ፣ በመሃንዲስነት በአስተዳደር ወ.ዘ.ተ የተሰማሩ አሉ። እነዚህ ግን በሞያቸዉ ተሰማርተዉ ቢሰሩ ኖሮ በክልላችን ያሉ እጅግ ብዙ የተበላሹ ነገሮች ማስተካከል ይችሉ ነበር። ነገር ግን በክልላችን እየተሰራ ያለዉ ሙሁሩን በማግለል ምንም ሞያ የሌላቸዉ በህ.ወ.ሃ.ት መሪዎችና በፖለቲካ ታማኝነት መሆናቸዉ ተብሎው የታመነባቸዉ አዛዥነት ነዉ የሚሰራዉ ምንም ሞያ የሌለዉ የማሌሊት ካድሬ ከክልል እስከ ቀበሌ ቢዘረጋ ደግሞ የክልሉ ሃብት ከማባከን በሙስና ከመዝረፍ አልፎ ምንም ለውጥ ሊያመጣ አልቻለም።በህ.ወ.ሃ.ት መንደር ሙሑሩ ቦታ የለውምና።

ለዚሁ ምሳሌ በ2004 ዓ/ም ለትግራይ ክልል ከተመደበዉ አመታዊ በጀት 49% ብር ሳይሰራበት ለፌዴራል መንግስት ተመላሽ ሆነዋል። የ2005 ዓ/ም ካፒታል ባጀት 29% ብር ሳይሰራበት ተመላሽ ሆነዋል። በምስራቅ ዞን በእንዳ አብርሃ ወአፅበሃ የሚገኘዉ የሚሊኒየም ጎል ሰርቶ ማሳያ በእርዳታ የተገኘው የ2005 ዓ/ም ብቻ ለእርዳታ ሰጪዎቹ ተመላሽ የሆነ ገንዘብ 195 ሚሊዮን ብር ነው። በዚሁ ክልል በ1984 ዓ/ም እና ከዛ በኃላ የ ህ.ወ.ሃ.ት ታጋዮች ለነበሩ ማቋቋምያ ተብሎ ከመንግስት ውጭ የሆነ 2.3 ቢሊዮን ብር እስከ አሁን ሂሳቡ አልተወራረደም፡፡ በትግራይ በሁሉም ወረዳዎች እስከ አሁን የጠራ የኦዲት ስራ አልተሰራም፡፡
ከላይ የተጠቀሰው የገንዘብ ስምሪትና ተመላሽ የሆነዉ በሙስና የተመዘበረዉ አይጨምርም። በትግራይ ያሉት ባለስልጣኖች ከክልል እሰከ ቀበሌ ያሉት ግን ምንጩ ያልታወቀ ቤትና ሃብት አካብቷል። ልጆቻቸውና ዘር መንዘራቸዉ በተቀማጠለና በንተዳደለ ኑሮ ይኖራሉ።ለውሃ ለመስኖ ስራ የተመደበ ባጀት ተመለሰ፡፡
ይህ ገንዘብ ያ የተማረ ሃይል ሰዉ በሙያዉ ዘርፍ ቢሰራ ኑሮ የተመለሰዉ ገንዘብና ተሰራበት የሚባለዉ ገንዘብ ከብልሽት ድኖ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ቢሰራ ንሮ ውጤት በነበረው ፡ በህ.ወ.ሃ.ት መሪዎች ግን ተቀባይነት የለዉም።ግን በህ.ወ.ሃ.ት መሪዎች ወደ ክልሉ በመንግስትና በእርዳታ ሰጭ ድርጅቶች የሚሰጥ ( የሚመደብ) ገንዘብ ሙሁራዊና ከሙስና የፀዳ አመራር ቢያገኝ ኖሮ ወደ ስደት የሚፈልሰዉ ፣ በጎዳና ተዘርግቶ የሚውለዉ ያለ የተማረ የሰዉ ሃይል ባገሩ ሰርቶ ለመኖር በቻለ ነበር። ነግር ግን የህ.ወ.ሃ.ት መሪዎች ምን ግዳቸዉ። ዘር መንዘራቸዉን ለትምህርት ውጭ አገር ልከዋል በሃገር ውስጥም ምንጩ ያልታወቀ ሃብት ተርፏቸዋል። ሁሉም ስራ በዘመድና በጋብቻ ይዘውታል።
የተማረ የሰው ሃይልም ታግሎ እንደ መስተካከል አንቀላፍቶ ይገኛል፡፡
በትግራይ የሚሰሩ የመሰረተ ልማት ስራዎች ባሉን ብቁ ምሁራኖች ባለመመራታቸው በልማት ዘማች ሰራዊት ጥናት በጎደለዉ በግብታዊነትና ስሜት ስለሚመሩ ሁሉም ተበላሽተዋል ወይም ሳያገለግሉ ፈርሰዋል። ከወልድያ እስከ ኮምበልቻም 120ኪሎሜትር ፈርሰዋል፡፡
ለዚሁ ተጠቃሽ የሚሆነዉ በትግራይ ክልል የተሰሩ የስፓልት መንገዶች ከቤትማራ እስከ ውቕሮ የሚገኘዉ 100 ኪሎ ሜትር ስፓልት መንገድ ከ 20 አመት በላይ ዋስትና አለዉ የተባለዉ ሰባት አመት ሳይሞላዉ ፈርሷል፡፡ ከሽሬ እሰከ ተከዜ ሑመራ ያለዉ 140 ኪሎ
አቶ አስገደ ገ/ስላሴ
ሜትርም 5 አመት ሳይሞላዉ ፈርሷል። ይህ እንደማሳያ ነዉ እንጂ ሌሎችም የፈረሱና መፍረስ የጀመሩ ብዙ ናቸዉ። ለዚሁም ከአላጀ እስከ አላማጣ ያላዉ 120 ኪሎ ሜትርም ጭራሹን ፈርሷል። በሌላም በትምህርት በጤና፣ ግንባታ፣ በውሃ ግድቦች፣ በውሃ ጠለፋም በሙሉ ከሽፏል። በከተሞችና በገጠር ለህዝብና ለእንስሳ ለሚጠጣ ውሃ ተብለዉ የተቆፈሩ ጥልቅ ጉድጓዶች ሙሁራዊ የሆነ ጥናት ስለሌላቸዉ ተበላሽተዋል( ደርቋል) ። ህዝቡ በውሃ ጥማት ተቸግረዋል፡ ቆሻሻ ውሃ እየጠጣ ለውሃ ወለድ በሽታ ተጋልጧል፣ ሌላ ቀርቶ ለመቐለና ለዞን ከተሞችም ውሃ ሊያቀርቡ አልቻሉም።
በትግራይ ክልል በመንግስት ቁጥጥር የሆኑ ብዙ ኢንተርፕራይዞች ድርጅቶች በኪሮስ ቢተዉ የእርሻና የተፈጥሮሃብት ቢሮ ሃላፊና የክልሉ ም/ፕረዚደንት የሚመሩ ቀደም ሲልም በአባይ ወልዱ ይመሩ የነበሩ እንደ ገጠር መንገድ የኮንስትራክሽን ዲዛይን የውሃ ቁፋሮ የውሃ መስኖ ኢንተርፕራይዝ ወ.ዘ.ተ እነዚህም ምሁራዊና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በመምራት ፈንታ በመሃይም የልማት ስራዊት ስለሚመሩ በውጭ እርዳታ የመጣ ገንዘብ ሳይሰራበት አሁንም ተመልሷል። ሰርተናል የሚሉንም አብዛኛዉ ገንዘብ ተበልቷል ባክኗል። ለዚህም መገለጫ ለምሳሌ,
የትግራይ ክልል ውሃ ሃብትና ውሃ አገልግሎት ሰጭ በዋናነት ይጠቀሳሉ። እነሱም አንደኛ የትግራይ ውሃ ሃብት ኢንተርፕራይዝ ከ4 አመት በፊት በአባይ ወልዱ ቦርድ ዳይሬክተርነት የተመራ ጊዜ በመቶ ሚሊዮን የሚገመት ገንዘብ ተበልቷል፤ ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ የጨረሰ ፕላስቲክና መለዋወጫ እቃ ተገዝቶ ጥቅም ላይ ሳይውል ተጥሎ በሃራጅ እየተሸጠ ይገኛል። ምክንያቱም በሞያተኛ ጥናት ስላልታገዘ ነዉ ( በልማት ሰራዊት ስለተገዛ ነዉ)።
አሁንም ይህ ድርጅት በኪሮስ ቢተዉ ቦርድ ዳይሬክተርነት በአቶ ነጋ በርሀ የ ህ.ወ.ሃ.ት ማ/ኮሚቴ ቢሮ ሃላፊነት የሚመራ ባለፉት አመታት በሙስና ተበልቷል፣ ያልሆነ የግድቦች ኮንትራት ተሰጥቶ በሙስና ተበልቷል ተብሎ በአጠቃላይ ይህ ድርጅት ድሮ ከነበረዉ በባሰ በሙስና ተዘርፏል ተብሎ በሰራተኛዉ ጥያቄ ተነስቶ ተገምግሞ በአቶ ነጋ የሚመራዉ ቢሮ በሚገመገምበት ጊዜ መሪዎችና ሰራተኛዉ ተጣልተዉ እስከ ግድያ ሙከራ ተደርጎ በክልሉ መሪዎች ሚስጥሩ እንዳይታወቅ በድፍንፍን ጊዚያዊ እርቅ አድርገዉ ደፍነውታል። የድርጅቱ ቢሮም ምዝበራ ተፈፅሞበታል ተብሎ እስከ አሁን ድረስ በፌዴራል ፖሊስ ሲጠበቅ ሰንብቷል።
የቢሮዉ ሃላፊ አቶ ነጋ በርሀ ግን የመቐለ ህዝብ መቼ ወደ ሙስኞች መንደር ይሄዳል እያለ ሲጠብቅ በሚኒስቴር ዲኤታ ማእርግ ተሹሞ የህ.ወ.ሃ.ት ካድሬዎች ማሰልጠኛ ማእከል አዲስ አበባ ተመድቧል። በመንግስት ሹመትና ደምወዝ ለ ህ.ወ.ሃ.ት ፓርቲ ለማገልገል እዉስነታቸዉ ሁሉም ነገር በእጃቸዉ ስለሆነ በአሁኑ ጊዜ የትግራይ ውሃ ሃብት ኢንተርፕራይዝ ሰራተኛ በትልቅ ሞራል ውድቀት ይግኛሉ። ሙስናውን ያጋለጡ ዜጎችም የስራ ዋስትናቸዉ አደጋ ላይ ወድቋል።አቶ ነጋ ግን ሳይፈተሹ አዲስ አበባ ገቡ።
ኮብል ስቶን የስራ አጥነት ፈቺ ሳይሆን የሙስና ምንጭነቱ ይበልጣል። መንግስት የኮብል ስቶን ስራ ለተማሪዎች ሲያሰማራ ትርፍ አግኝተዉ ሊለወጡ ሳይሆን ትምህርት ጨርሰዉ ስራ ፈትተዉ ቁጭ ካሉ ለስርአቱ አስጊ በመሆናቸዉ እንደ እሳት አደጋ ማጥፊያ ለማብረድና ለጊዜ ፍጆታ ነበር። በሌላ በኩል ግን የ ህ.ወ.ሃ.ት መዋቅር ይህ ፕሮጀክት ለሙስና በሚጠቀምበት መንገድ እየሰሩ ይገኛሉ። ለዚሁ ምሳሌ በሁሉም የትግራይ ከተሞች ሙስና የሚፈፀምበት ሆኖ እንደ ሞዴል ግን በመቐለ የተሰራዉ ሙስና ለመጥቀስ ለአንድ የኮብል ስቶን ድንጋይ ከጠራቢዎች (አምራች) አርሶ አደሮች ከ 2.50 እስከ 3.00 ብር እንዲገዛ በእቅድ ተይዟል የመቐለ ፋይናንስ ክፍል ዩኔን ተወካዮች ግን ለአንድ ኮብል ስቶን ድንጋይ 8.00 ገዝተውታል። ከአንድ ኮብል ስቶን 5.00 ብር ይሰርቃሉ ማለት ነዉ፡፡ ይህ ገንዘብ እጅጉን ብዙ ነዉ፡፡ በመቐለ ብቻ ብዙ ሚሊዮን ድንጋይ ተገዝቷል ስለሆነ ሙስናዉ ትልቅ ነዉ። ለዚሁ ተጠያቂዎች ተብለዉ 3ት ሰዎች ከፋይናንስ ዘርፍ ተይዘዉ ታስረዉ ይግኛሉ። በህዝቡ የሚነሳዉ ጥያቄ ግን ታስረዉ ያሉት ተራ ሰዎች ናቸዉ፡ ከነዛ በላይ ያሉ ነፃ ናቸዉ ወይ በኔ እምነት በስተጀርባ ሌላ ትያተር እንዳይኖር ነዉ።ህዝቡም ይጠረጥራል የሚገርመዉ ግን ለኮብል ስቶን የሚወጣዉ ገንዘብ የእርዳታና የብድር ነዉ በሙስና የተበላ ገንዘብም የኢትዮጵያ ህዝብ እዳ ነዉ።
የውሃ ጥም በትግራይ ከተሞች የውሃ ችግር ሊፈታ አልቻለም፡፡ የህ.ወ.ሃ.ት መሪዎች በየጊዜው መድረክ ላይ እየወጡ ሲነግሩን የውሃ ችግራችን 70% 80% 90% ተፈተዋል ይላሉ።ይህን ያህል ጉድጓድ ተቆፍረዋል፤ተጠንተዋል ለግደቡ ጥናት ለመቐለ፤ ለሽሬ ከእስራኤል ጋር ኮንተራት ኣስረናል ወዘተ ብለው ይዋሻሉ። እስከ ኣሁን ግን በመቐለ እንኳን ውሃ ሊያቀርቡ ኣልቻሉም፡፡ ለኮንስትራክሸን ስራ ይቅርና ለሰው እንኳን ሊያቀርቡ ኣልቻሉም አሁንም በጭንቀት ላይ ነን በሳምንት ወይም በሁለት ሳምንት፤ በወር ውሃ የማይገኝበት ሁኔታ አለ። በሽሬ ከተማ ህ.ወ. ሃ. ት ወደ ስለጣን ከመጣ ጀምሮ ውሃ የለም። በወረዳዎች በገጠር ያለ ጥናት በሌለበት ውሃ ይቆፈራል ረጅም ጊዜ ሳይቆይ ይደርቃል፡፡ ይህ ሁኔታ ተቆርቋሪ የሆነ ዜጋ ዞሮ ሊያየው ይችላል። በትግራይ እኮ በትላልቅ ከተማ የውሃ ጥም ሲያጋጥም እንደ ሌሎች ክልሎች በቦቴ እንኳን ድጋፍ አይደረግም ።በዚህ ላይ ህዝቡም አንገቱን ደፍቶ ያማል እንጂ ችግርህ መግለጥ ለህ.ወ.ሃ.ት መሪዎች እንደ ማጋለጥ ይመለከተዋል በሌላ በኩልም ይሰጋል። በትግራይ ያለ የውሃ ጥም መቛጫ አይገኝለትም ጨልሟል ።መሪዎችና ሃብታሞች ግን የተሻለ ውሃ አላቸዉ። ህዝቡም ዝም ብሎ ይታመማል ይሞታል፡፡
የትምህርት ጥራት፤ ለማረጋገጥ አሁንም የሚመሩት በመማር ማስተማር የተካኑ ሙያተኞች ሳይሆኑ በቀበሌ የተደራጁ ምንም ከሞያው ጋር ግንኝነት የሌላቸው መሃይሞች ናቸው። አሰተማሪውን የሚገመገሙት እነሱ ትምህርት ቤት ገብተው አስተማሪው ተማሪውን ያደራጃሉ ይመለምላሉ። አስተማሪዎች በሞያቸው ሳይሆን የሚገመግሙት ለህ.ወ.ሃ.ት ፖለቲካ ባሳዩት ታማኝነትና ተላላኪነት ነዉ። አሰተማሪዎች ያለማቋረጥ ለተማሪዎቻቸው በማስተማር ፈንታ ማስተማሩን ትተው ገጠር ድረስ በሜሄድ በፖለቲካ ስራ ይሰማራሉ። አስተማሪዎች ከሌጅ ገብተው ባጭር ጊዜ ሞያቸው እንዳያሻሽሉ በክረምት ኮርስ በመጓተት ትምህርቱን ጨርሰው ሳይሰሩበት ያረጃሉ። ከህ.ወ.ህ.ት መሪዎች ጋር ጠበቅ ያለ ግንኝነት ያለው ግን ጊዜ ተሰጥቶበት በፈለጉት ዩኒቨርሰቲ ያሳድጉታል።መምህር እድገቱ ያዘገመ ነው።ሞራሉ ወድቋል ማህበራዊ ኑሮ ሊመሰርት አይችልም።
ጠንካራ አስተማሪ ሰነፍ ተማሪ ማለፍ የለበትም ካለና ተማሪ ከወደቀ ከስራ እንዲባረር ይደረጋል፡፡ በአጠቃላይ በትግራይ የትምህርት ጥራት ውደቀል ተጠያቂ የህ.ወ.ሃ.ት አመራርና ካድሬዎች ናቸው። ምክንያቱም ከክልል ትምህርት ቢሮ ጀምሮ እስከ ታች የህ.ወ.ሃ.ት ካድሬዎች ናቸው። ሳይንሳዊ የትምህርት አመራር ቦታ የለውም። የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሐላፊ ጎበዛይ ወልደአረጋይ ባለፈው ክረምት የክልሉ ከፍተኛና መካከለኛ አመራር ግምገማዊ ስልጠና ያቀረበዉ ሪፖርት የትምህርት ጥራት በአንደኛና በሁለተኛ መለስተኛ ደረጃ 94% ደርሷል ለሚመጣዉ አመት 100% ይደርሳል ብሏል። የዘንድሮ 10ኛ ክፍል ማትሪክ የወሰዱ ግን 72% ወድቋል በአሁኑ ጊዜ የትግራይ ከተሞች በ10ኛ እና 8ኛ ክፍል በወደቁ ህፃናት ተማሪዎች ተጥለቅልቀዋል። በጫት ቤት ተሰማርተዉ ይገኛሉ። ከዚህ ጎን ለጎን በአሁኑ ጊዜ 8ኛ እና 10ኛ ክፍል ተማሪዎች ወታደር እንቀጥራለን ተብሎ ማስታወቂያ ተለጥፏል።የተበላሸ ስርአት የሚኖረዉ ክፍት የስራ ቦታ ህዝቡን እሚያፍንበት ወታደር ነዉ፡፡ በትግራይ ክልል አስተማሪዎችና የእርሻ ባለሞያዎች ወደ ስደት ፈልሰዋል ምክንያቱም በቂ ክፍያ የለም ለቤት ክራይ ፣ ለልብስ፣ ለቀለብ፣ የሚሆን በቂ ክፍያ የላቸዉም ፤በሞያቸዉ መስራት ትስኖአቸዋል። ስለሆነም ትግራይ በትምህርት ጥራት ከሁሉም ክልሎች ጅራት ነዉ የምትሰለፈዉ።
በትግራይ ከ2.4 ቢሊዮን ግብር 2.2 ቢሊዮን ግብር ተሰብስቧል፤ ግብር መክፈል የዜጎች ግዴታ ነዉ በትግራይ እየተደረገ ያለዉ የግብር አሰባሰብ ግን ነጋዴዉ ባለሃብት ገንዘቡና ሃብቱ እየቀማ ወደኪስ ማስገባት አይነት ነዉ እየታየ ያለዉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ብዙ ነጋዴዎች አዲስ አበባ ፣ኦሮሚያ፣ ደቡብ ሄደዋል ፤ብዙ ሰራተኛ ይይዙ የነበሩ የህንፃ ተቋራጭ ጠፍቷል ፤በክለሉ የሉም ብዙ ባለሃብቶች አንቨስት እናደርጋለን ብለዉ ቦታ ተቀብለዉ ቤቱን ገንብተዉ ጥለዉት ሄደዋል፡፡ በ2004 ዓ/ም ከትግራይ ከ3000 በላይ ነጋዴዎች ንግዳቸውን ዘግተዉ ሄደዋል የዘንድሮም ብዙ ነጋዴዎች እየዘጉ ናቸዉ። ብዙ የትግራይ ነጋዴዎች በአዲስ አበባ መርካቶ፣ ፒያሳ 22 ማዞሪያ በአዳማ ወ.ዘ.ተ ስራ አጥ ሆነዉ ቦዝነዉ ይገኛሉ ።ይህ የባለሃብቶችና ነጋዴዎች መበታተን ለህ.ወ.ሃ.ት መሪዎች ደስታቸዉ ነዉ።ህ.ወ.ሃ.ት ድሮዉም ፀረ ባለሃብት የኮሚኒስት አቋም ነዉ ያለውና። ለሚመጣዉ 2006 አመትም አባይ ወልዱ ብርሃነ ፅጋብ የገቢዎች ሃላፊ 2.6 ቢሊዮን ግብር እንሰበስባለን ብለውናል፤ በዚህ በግብር አሰባሰብም በሞያ ጥናት ከህብርተሰቡ አቅም አዛምደዉ ሳይሆን እየሰሩ ያሉት አሁንም በግብታዊነት ( በችኮላ ) የተደራጀዉ የልማት ሰራዊት ዘማች ነዉ።የዚህ የጥፋት መሃይም የልማት ሰራዊት አሰራረ ምሁሩ ፣ ነጋዴዉ፣ መላዉ ህብረተ-ሰብ አንገቱን ደፍቶ ማየቱ ትልቅ ወንጀል እየፈፀመ ይገኛል፡፡
በትግራይ ወታደራዊ የበላይነት ነግሶ ዳኝነት እየተነጠቀ ነዉ፡፡ ለዚህም የህግ የበላይነት ከነአካቴዉ አለ ከተባለ ዳኞች የፈረዱት ፖሊስ አዘዉ ካላስፈፀሙ አልፈታም ብሎ ስልጣኑን ተጠቅሞ ለዜጎች ሲያስር ይታያል፡፡ ይህ ተግባር በትግራይ በሁሉም ቦታ እንዳለ ሆኖ ለምሳሌ በመቐለ ሰሜን ወረዳ ፍ/ቤት ምድብ ችሎት፤ በትግራይ ደቡብ ምስራቅ ዓዲጉደም ወረዳ በመጥቀስ በነዚህ ወረዳዎች ሰዎች በወንጀል ተጠርጥረዉ ፍርድ ቤት ቀርበዉ በዋስ ይለቀቃሉ ብለዉ ዳኞች ሲወስኑ የፖሊስ ኮማንደሮች ግን አንፈታም ብለዉ ቀሩ ። ይህ ጉዳይ የፈጠረዉ የሞራል ውድቀት በአሁኑ ጊዜ በትግራይ ክልል የሚገኙ ዳኞች ተስፋ ቆርጠዉ የስራ መልቀቂያ ያስገባሉ፡ በተለይ በመቐለ አብዛኞቹ እየለቀቁ ናቸው፡፡
ምሁራን በጎዳና በአሁኑ ጊዜ የትግራይ የዞንና ወረዳ ከተሞች ከዩኒቨርሲቲ እና ከኮሌጅ የተመረቁ ስራ አጥተዉ በየጎደናዉ ቆመዉ ይታያሉ። የነዚህ ምሁራን ብዛት በዞን በከተሞች እና በመቐለ ያሉትን እንተወውና በአንድ ትንሽ ከተማ 35000 ህዝብ ያለበት ውቕሮ ከተማ ከ4500 ምሁራኖች አሉባት ።ከነዚህም ከወረዳና ከክለሉ ባለስልጣኖች ግንኙነት ያላቸዉ 250 ምሁራኖች በክብል ስቶን ተሰማርተዋል ፡፡ አምና በኮብል ስቶን ተሰማርተዉ የነበሩት ከስረዋል ከአዲስ ስራ አጤዎች አብረዉ እያለቀሱ ናቸዉ።ባሁኑ ጊዜ የኮብል ስቶን ስራ ለህ.ወ.ሃ.ት መሪዎች አሁንም የእሳት አደጋ ማጥፊያ ሊሆነዉ አይችልም፡፡ ለሁሉም ስራ ሊፈጥርለት አይችልም የህ.ወ.ሃ.ት መሪዎች አሁንም የምሁሩ ችግር ምናቸዉም አይደለም። ስልጣናቸዉ እንዳይቀማ እያቃሰተ ያለዉ ህ.ወ.ሃ.ት የሚባለው ፓርቲ እንዴት እናድነው ነዉ ጥያቄያቸዉ ፡፡በሃገራቸን ስራ አጥነት እሚጠፋ ከሆነ የሀገራችንን ሃብት በሙስና መዘረፍ ቀርቶ ሁሉም ገንዘብ መጥጦ ትላልቅ የስራ መስክ ከፍቶ ወደ ስራ መሰማራት ብቻ ነዉ።
ምሁራን ግን ለምን ከ ህ.ወ.ሃ.ት መሪዎች ተስፈኛ ይሆናሉ? ቀለም የቆጠሩና የሚገነዘቡ ናቸዉ በየጎደናዉ በወላጆቻቸዉ ቤት እያቃሰቱ ከሚሞቱት ህገ- መንግስቱን በመጠቀም በሰላማዊ መንገድ ተደራጅተዉ የበሰበሰውን ስርአት አይቀይሩትም ? በኔ እምነት
ጠንካራ ናችሁ አልልም አሁንም የተማራችሁ ሰዎች ናችሁና ለዚህ በግብታዊነት የሚነዳ የልማት ሰራዊት አትንበርከኩ። ይህ ሰራዊት የጥፋት እንጂ የልማት አይደለም፡፡
የ ህ.ወ.ሃ.ት መሪዎች በሁሉም የመንግስት ሰራተኛ ስጋት ፈጥሯል፡፡ ባሁኑ ጊዜ የመንግስት ሰራተኛ አብዛኛዉ የህ.ወ.ሃ.ት አባልም ሳይቀር በህ.ወ.ሃ.ት ነፃ ሆኖ ለመስራት እድገት ለማግኘት አልቻለም፡፡ ያለችዉ ደምወዝም ለህ.ወ.ሃ.ት አባላት ለቀይ መስቀል፤ ለትግራይ ልማት ማህበር፤ ለአባይ ግድብና ሌሎችም መዋጮ ተቆርጦበት የምትቀረዉ ለቤት ኪራይ ለትምህርት ለልብስ የፅዳት መሳሪያ ሆኖ ካለዉ ምግብ ፍጆታና የእቃ ዋጋ ውድነት ይቅርና ለወር የምግብ ፍጆታዉ አትበቃም ተጨንቋል ቸገረኝ መረረኝ ብሎ ከጠየቀም በጠላትነት ይፈረጃል። የ ህ.ወ.ሃ.ት ተጠቃሚዎችና ምንም ተጠቃሚዎች ያልሆኑ የመንግስት ሰራተኛ ስታዩ ኑሮዋቸዉ የተለያየ ነዉ። ባለባበሳቸዉ በልጆቻቸዉ በሚስታቸዉ አለባበስ አመጋገብ ፍፁም የተለየ ነዉ ስለሆነም አብዛኛዉ የመንግስት ሰራተኛ ነፃነት የሌለዉ በህ.ወ.ሃ.ት መሪዎች ደስተኛ ያልሆነ ነዉ ግን ደግሞ እነዚህ የመንግስት ሰራተኛ ሰግተዉ ፈርተዉ እስከ መቼ ነዉ የሚኖሩ?
‹‹የትግራይ አርሶ አደር 100% ሞዴል ገበሬ ሆነዋል›› ጠ/ር ሃ/ማርያም ደሳለኝ በትግራይ መሪዎች ከቀበሌ እስከ አባይ ወልዱ በውሸት የተቀናበረ ሪፖርት ነዉ ያነበቡት፡፡ የትግራይ ህዝብ ባንዳንድ ለም ቦታ ከሚያሳዩት ለፖለቲካ ፍጆታ ካልሆነ በስተቀር የተባለዉ ሃሰት ነዉ፤ ይልቁንም አቶ ሃ/ማርያም ታች ወርደዉ አንድ ቀበሌ በኣንድ ዞን ቢመለከቱ ወይም ታማኝ ነፃ ሞያተኛ ቢልኩ ይልቁንም የትግራይ ገበሬ 70% ወይም ከ44 አመት እድሜ በታች ታራሽ መሬት የለዉም፡፡ ይህ ሃይል ባለጡንቻዉ አምራች ነዉ ይህ ጉልበት ከ13 እስከ 44 አመት እድሜ ያለው ወደ ስደት ፈልሷል፡፡ በየገጠሩ ያለ አርሶ አደር ሽማግሌ ነዉ ፡፡በትግራይ ከ44 አመት እድሜ በታች ያሉ ሴቶች ወደ ስደት ፈልሷል ወይም ወደ ዝሙት ስራ ተሰማርቷል ፡፡እስኪ ወደ ገጠር ወረድ ብሉ የትግራይ አርሶ አደር 100 % ሞዴል ሆነዋል የተባለው ይመልከቱና ይመስክሩ? ይህ ውሸት የተናገረ መሪ በሰለጠኑ አገሮች ከስልጣኑ ያስወርዳል። በህ.ወ.ሃ.ት መንደር ግን መዋሸት ያሸልማል፡፡
እነዛ አልምተናቸዋል የሚሉት የመስኖ ቦታዎች እህል እኮ አይደለም እያመረቱ ያሉት የጫት አዝመራ ነዉ እያመረቱ ያሉት። ከስደት የቀረ ወጣት እያሳበደዉ ነዉ ያለዉ። እንደ ማስረጃ ቢሆንዎት በሳምረ ሰሓርቲና በሕንጣሎ ዋጅራት በአላጀ ወረዳዎች የጫት በአኣለማጣ በጨርጭር ወዘተ ዘመናዊ እርሻ ይመልከቱ? እነ አቶ አባይ ወልዱ እኮ ይህ እርሻ ነዉ እየመሩ ያሉት የትግራይ አርሶ አደር 100% ሞዴል ገበሬ ከሆነ ስንት ኩንታል ነዉ የሚያስገባዉ እነ አባይ ወልዱ በሄክታር 30፣40 ኩንታል እናስገባለን የሚሉት የንፋስ ወሬ ነዉ፡፡ ሃብታም የሚባል የትግራይ ገበሬ ሙሉ ግብር ከሆነች 50 x100 ሜትር 5000 ሜትር ካሬ ናት። ባሁኑ ጊዜ ሃብታም ገበሬ የትግራይ አመት ሙሉ ከሚያመርተዉ እስከ የካቲት ነዉ የሚመገበዉ ሃቁ ይህ ነዉ።ከዛ በኃላ ወደ ስደት ነዉ።
የጤና ሽፋን በትግራይ ክልል የጤና ሽፋን ከ90% በላይ ተብሏል፡፡ አሳፋሪና አስነዋሪ ውሸት ባሁኑ ጊዜ እኮ የትግራይ ህዝብ ወደ ደብተራ ጠንቋይ ወ.ዘ.ተ ነዉ እየዞረ የሚኖረዉ ህክምና ቢኖርስ መድሃኒት የት አለ እነዛ የጤና ኬላ የሚባሉ እኮ ሰውና መድሃኒት የላቸዉም አንድ ነገር ግን የገረመኝ የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሚመራዉ አገር አቀፍ ግምገማ ሲያካሂድ በሰሜን ምእራብ ዞን በፃዕዳ እምባና ቀላቕል ከ 13 አመት በፊት የተከሰተዉ ሰዉ ገዳይ በሽታ ጉበት ፣ኩላሊት ፣አንጀት አበስብሶ መላው አካላቱን አመንምኖ የሚገድል መድሃኒት ያልተገጀለት ባሁኑ ጊዜ ወደ ሁሉም ወረዳዎች ትግራይ አለፈ የተከሰተዉ ወደ አማራ ክልልም ተዛምቶ ያለዉ በተለይ ደግሞ በዘንድሮዉ ክረምት በሕሞራ አካባቢ ብዙ ህዝብ የቀጠፈ በሽታ ከሰዉ አልፎ በእንስሳ ግድያም የሚታወቀዉ በሽታ እንደ አጀንዳ ይዘዉ ባለመወያየታቸዉ አዝናለሁ። ለዚህ በሽታ ቴድሮስ እድሓኖም ፣ገብረአብ ባርናባስ በዚሁ ክልል እያሉ እያወቁ እንዳላወቁ እየሰሙ እንዳልሰሙ ሆነው ቆይተዋል ፡፡አሁንም እየደገማቹሁት ነው ። ባለፉት አመታት ተቆጣጥረነዋል በሽታው ታውቀዋል ብላቹህ የውሸት ተስፋ ሰጥታችሁ ነበር። በሽታው ግን አልተሻሻለም ተባብሶበት በዙ ህዝብና እንስሳ እየጨረሰ ይገኛል። ይህ ጉዳይ ነገ በሃገራችን ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊ ሞራላዊ አደጋ ሊፈጥር ነው እባካቹህ ይህ ህዝብ አድኑት።ህዝባዊ ሃላፊነት ይሰማችሁ የኢትዮጵያ ህዝብም ጥያቄ ማንሳት አለበት። ነገ ወደ ራሱ ሊዘምት ነው፡፡
የመቐለ ስቴድዮም በወሬ ብቻ ተሰራ፤ የመቐለ ስታዴም ከተጀመረ አመታት አስቆጥረዋል።ይህ ኳስ ሜዳም እንደ ሌሎች የትግራይ ሰራዎች ተጀምሮ እድሜ እየቆጠረ በሄደ ቁጥር ዋጋው እየጨመረ ኪሳራው እየበዛ ስራው እየተጓተተ ይገኛል፡፡ በወሬ ግን ሰው ጠግበዋል። የመቐለ ህዝብም አንቀላፍቷል ጥያቄ አያነሳም፡፡
ብሁሃን መገናኛ በትግራይ ብዙ ኤፍኤሞች ቴሌቪዥን ኢዜአ የህ.ዋ.ሃ.ት ደግሞ ድ.ወ.ት ይገኛሉ እነዚህ ብዙሃን መገናኛ አሁን ላሉ የህ.ዋ.ሃ.ት መሪዎች ምን ያስደስታቸዋል እያሉ ልክ እንደ መሪያቸዉ በግብታዊነት የሚነዱ የህዝብን ልብ ትርታ ችግር የማይዘግቡ ለስጋቸዉ አዳሪ ናቸው። እነዚህ ብዙሃን መገናኛ እስከ አሁን የህዝብ ብሶት ትንፍሽ ብለው አያውቁም እነዚህ በትግራይ ህዝብ ተጠያቂዎች ናቸው፡ ምክንያቱ ጣብያዎቹ በህዝብ ገንዘብ ለህዝብ እንዲያገለግሉ የተሰሩ ነበሩና። በአሁኑ ጊዜ ከህ.ወ.ሃ.ት ሳንባ ውጪ አይተነፍሱም።
በትግራይ በሁሉም ነገር ሞዴል ናት ይባላል ይህ አባባል ከማለት አልፎ እንዴት ብሎ እስከ አሁን የገለፅኩት ትግራይን መእከል አድርጌ ነበር ግን ደግሞ በትግራይ ያለ ጉድ በመላው ሀገራችን እንዳለ በሌሎች ክልሎች እንዳለ ዘንግቼ አይደለም። በሁሉም እኩል ነው። አሁንም ለአንባብያን እማሳስበው በዚህ ፅሁፍ ያስቀመጥኩት ገለብጣቹህ በአማራ፤ በጋንቤላ፤ በኦሮሚያ፤ በደቡብ፤ በዓፋር ወ.ዘ.ተ አንበቡትና ተረዱት በትግራይ ያለ ግፍ ውሸት አምባገንነት፣ ፋሺዝም ፣ሙስና፣ አድልዎ አንድ ነዉ፡፡ በትግራይ ያለዉ ኣፈና ግን ቴክኒኩ የረቀቀና የመረረ ነዉ። ስለሆነም አብረን እናስወግደዉ።
የ ህ.ዋ.ሃ.ት መሪዎች ጉዞዋቸዉ ወዴት እየተመለከተ ነዉ? ወደ ዲሞክራሲ ጎደና? ወደ ፀረ-ዲሞክራሲ ኣንባገነን? ወደ ኣንባገነን ፋሺዝም ስርአት ? መልሱን ለገምጋሚዎች
ስብሃት ነጋ <<ሙስና በሚኒሊየን (በቢሊዮን) መሰረቁ አይደለም፡፡ ዋናዉና ትልቁ ሙስና በኮንስትራክሽንና በሌሎች ፕሮጀክቶች ያለ የሙስና ተግባር ነዉ አደገኛዉ፡፡>>ብለዋል፡፡
ከአቶ ስብሃት ጋር በኮንስትራክሽንና በሌሎች ፕሮጀክቶች በእቃ ግዥ የሚፈፀመዉ ሙስና ትልቅና አደገኛ መሆኑ እንስማማለን እንግባባለን ልዩነት የለኝም። ለምሳሌ በመንገድ በስፓልትና በጠጠር ስራ የሚደረገዉ ዜግነታዊ ሃላፊነት የጎደለዉ፤ በገንዘብ ተገዝተዉ ከጥናቱ ጀምረዉ እስከ ስራዉ ያለዉ ጥራት የሌለዉ እንዲሰራ የሚያደርጉ ወገኖች የሃገራችን ሉአላዊነት ከሸጡት ጋር እኩል የሚታዩ ከጅዎች ናቸዉ መወገዝም አለባቸዉ።
በሌላ በኩል ግን አቶ ስብሃት በሚሊዮንና በቢልዮን የሚቆጠር ገንዘብ የሰረቁትን አቃልሎ ማየቱ ግን ፍፁም አልቀበለዉም፡፡ ምክንያቱም ስብሃት ነጋ እነዚህ እያቃለሉዋቸዉ ያለዉ ከሚሊዮን እሰከ ብዙ ቢሊዮን የሚገመት ምንጩ የማይታወቅ ሃብት ባገር ውስጥና በውጭ እየሰበሰቡና ህንፃዎች የገነቡ ብዙ ወዳጆች ስላሉት እነሱን ለማዳን አስቦ የተናገረዉ ይመስለኛል። ስለዚ ሚሊዮን የሰረቀ እና ቢሊዮን የሰረቀ ከኮንስትራክሽንና እቃ ግዥ የሰረቁ ሁሉ ካገር ሻጮች እኩል የሚታዩ ስለሆነ አልቀበለዉም። ይህም ለህዘቡ ማታለል ነዉ።
<<ባሁኑ ጊዜ በሃገር ደረጃ እየተካሄደ ያለዉ ፀረ-ሙሰኞች ዘመቻ ለትግራይ ተወላጆች ያነጣጠረ ነዉ፡፡>> የሚል ዘመቻ አለ፡፡ ይህ እንደ ሃሳብ በማንሳት ዘመቻ የሚያካሂዱ ያሉ ወገኖች እንደልማዳቸዉ ለትግራይ ህዝብ በጠባብና ዘረኝነት ተነሳስቶ መቺ ሃይል ሊጠቀሙበት ስለፈለጉ ነዉ፡፡ የትግራይ ህዝብ ግን ድሮም አሁንም የኢትዮጵያ ህዝብ በትግራይ ተወላጅ ወይም በኦሮሞ ፣ በአማራ፣ በሱማሌ፣ በጉራጌ ቢወረር የራሱ ሃብት መሆኑን አምኖ የሚከላከል እንጂ በትግራይ ተወላጅ የሃገር ሃብት ሲወረር ዝምታ መርጦ ከአማራ ወይም ከኦሮሞ ለይቶ ለትግራይ ተወላጅ ሊከላከል ማለት ዘበት ነዉ።በኔ እምነት የህ.ዋ.ሃ.ት ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ መሪዎች ቆርጠዉ አይጨክኑም እነጂ ጀምረውት ያሉ የሙስና ግንድ ከስሩ ቢመቱት በኢትዮጵያ ህዝብ ተቀባይነት ያገኝ ነበር።ካለበለዚያ እነዛ በሙስና ምክንያት የትግራይ ባለስልጣኖች እየተመቱ ናቸዉ የሚሉት ተቀባይነት የላቸዉም። የትግራይ ህዝብም ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ሃብት ለሰረቁ ሁሉ ጠላቶቹ ናቸው ።ለመሆኑ ለትግራይ ህዝብ መምቻ ማድረጉ እስከ መቼ ነው?
ማጠቃለያ በዚህ ፅሁፍ ለመግለፅ የፈለኩት የ ህ.ዋ.ሃ.ት መሪዎች ደርግን አስወግደዉ ወደ ስልጣን ከወጡ ጀምረዉ የህዝባችን ጊዜያዊ ስሜት በመጠቀም ለሁሉም የህብረተ-ሰብ ክፍሎች እየከፋፈሉ ለጊዜዉ ያዋጣኛል በሚሉት በግብታዊነት በመንዳት ለአንድ ቡድን በመያዝ ለሌላዉ ቡድን በማግለል ለሁሉም ነገር በዘመቻ ግማሹን ሰርተዉ ግማሹን እያበላሹት መጥቷል ።ለምሳሌገልገል ጊቤ ግልፅነት የጎደለዉ ጥናት በማድረግ ግልፅነት ያለዉ ቁጥጥር ባለማድረጉ ግድቡ ተሰርቶ መለስ ከመረቁት በውሃላ ባጭር ጊዜ ፈረሰ፡፡ እሱን ለመጠገን በቢሊዮን የሚገመት ገንዘብ ከሰርን። የተከዜ ግድብም ግልፅነት ያለዉ አሰራር ባለመከተላቸዉ እንደተባለዉ በሙሉ ሃይሉ አገልግሎት እየሰጠ አይደለም።
ይህ የሆነበት ምክንያት የ ህ.ዋ.ሃ.ት መሪዎች ከኃላ ታሪካቸዉ ስናየዉ የሚሰሩ ስራዎች በየስራ ዘርፉ የሚሰማሩ ምሁራኖች አሰማርተዉ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ባለማሰራት ምሁራን በማግለል ሁሉም ነገር ግብታዊ በሆነ ዘመቻ ነበር የሚሰሩት፡፡ ይሰሩ የነበሩት ደግሞ ብዙ ኪሳራዎች ያጋጥሙት ነበር። ይህ ልምድና ባህልም ባሁኑ ጊዜ የህ.ዋ.ሃ.ት መሪዎች መለያ ባህሪ ሆኖ ተገኝቷል።
ይህ ባህሪ ግን በኢትዮጵያ የሚገኙ ብቁ ምሁራኖች ለዚህ ግብታዊ የሆነ ዘመቻ የጥፋት ሰራዊት አሰራር በመቃወም ሃገራችን በሳይንስ ምርመር ውጤት እንድትመራ በግልፅ እንደ መታገል አንገታቸዉን አቀርቅረዉ ሰግተዉ መኖር እጅጉን ውድቀት ነዉ። የህ.ዋ.ሃ.ት ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ መሪዎች ለ90 ሚሊዮን ህዝብ ጨምድዶ በመያዝ እንደፈለገ ሲያደርገዉ በሩቅ መመልከቱ የአንድ ቀለም የቆጠረ ዜጋ ተግባር አይደለም። በተለይ ደግሞ በመንግስት ሰራተኛ ሆነዉ በዘማች ሰራዊት አመራር ተሸማቅቀዉ መገዛቱ እስከ መቼ ነዉ? ሁሉም ነገር ያብቃ ብላችሁ ሃቁን ብትሰሩትስ። ይህ አሰራር በዚች አገራችን ብቁ ሰዉ የለም ወይ መባሉ ከሃቅ የራቀ አይደለም።
ኢትዮሚድያ – Ethiomedia.com

No comments:

Post a Comment