Translate

Tuesday, May 29, 2018

በአዲስ አበባ፣ አውሮፓና አሜሪካ ለ“ዘመቻ ዓቢይ” የስውር ምልመላ ተጀምሯል!

የ“ዘመቻ ዓቢይ” - አዝማቾችን ዓቢይ ያውቋቸዋል?



  • ኃይሌ ገብረሥላሴ መልማይ መሆኑ ታወቀ
የሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በዳላስ ሊያካሂድ ያሰበው ሰላሳ አምስተኛ የስፖርት ፌስቲቫል ከወዲሁ እጅግ ጥንቃቄ በሚያሻው ጉዳይ ተወጥሯል። የጎልጉል የመረጃ አቀባዮች እንዳሉት በአገር ውስጥ፣ በአሜሪካና በአውሮፓ የሕዝብ ግንኙነት የሚሠሩ ክፍሎች በምሥጢር እየተመለመሉ ነው። ኃይሌ ገብረሥላሴ አገር ውስጥ ሆኖ ይህንኑ የምልመላ ሥራ እየሠራ ነው። አነጋጋሪ የሆነው ይህንን ዘመቻ የሚያከናውኑት ክፍሎች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ እውቅና ይኑራቸው አይኑራቸው አለመታወቁ ነው።

ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ በፖሊሲ ጉዳዮች፣ ሕዝብ ባነሳቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች፣ አፋኝ ህጎችን ከማንሳት አኳያ፣ የፖለቲካ እስረኞችን ሙሉ በሙሉ ከመፍታትና የአስቸኳይ አዋጁን በማንሳት፣ ቀጣዩ ምርጫ ነጻና ገለልተኛ እንዲሆን ምርጫ ቦርድን ከማፍረስ ጀምሮ ተግባራዊ ውሳኔ ያላሳለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ዳላስ በሚካሄደው የስፖርት ፌስቲቫል ላይ ተገኝተው ንግግር እንዲያደርጉ ፈቃድ መጠየቃቸውን ተከትሎ ነው በምሥጢር  የሕዝብ ግንኙነት ሥራ የሚሠሩ ሰዎች እንዲመለመሉ የተደረገው።
እንደ ጎልጉል መረጃ ሰዎች ከሆነ ለህወሓት/ኢህአዴግ በአገር ውስጥ፣ በአሜሪካና በአውሮፓ የውስወሳና የሕዝብ ግንኙነት ሥራ እንዲሠሩ የታጩትን የሚያነጋግረው ኃይሌ ግብረሥላሴ ነው። “ዳያስፖራውንና ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማቀራረብ ነው ዓላማው” በሚል በግል ሰዎችን የሚመለምለው ኃይሌ፣ የማግባባት ሥራውን በስልክ ሲሠራ በተጠቀሱት ቦታዎች የሚዲያ ሥራ የሚሠሩ፣ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ የሚያከናውኑና የማግባባት ሥራ የሚሠሩ ሰዎች እየተመለመሉ መሆኑንን አረጋግጧል።
ቀደም ብሎም ቢሆን ጎልጉል በአሜሪካ በምሥጢር ሰዎችን የመመልመልና የማደራጀት ሥራ በኤምባሲው እየተሠራ መሆኑ መረጃ ደርሶት ነበር። ነገሮችን በጥበብ መያዙና የጉዳዩን አካሄድ መከታተል አስፈላጊ በመሆኑ በወቅቱ ይፋ አላደረገም። ይሁን እንጂ ይህ የውስጥ ለውስጥ አሠራር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ከተናገሯቸውና አራምደዋለሁ ከሚሉት ጉዳይ ጋር ፍጹም የሚጻረር ሆኖ በመገኘቱ ዜናውን ለማተም ተገድደነናል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ በርሳቸው ስም የተጀመረውን የምሥጢር ምልመላ የሚያውቁት ስለመሆኑ መረጃ የለም። በተመሳሳይ ይህ ድርጊት ከእርሳቸው ዕውቅና ውጪ በስማቸው እየተከናወነ ላለመሆኑም የጎልጉል ምንጮች ማረጋገጥ አልቻሉም።
ቅቡል ንግግሮችን በማቅረብ፣ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ በማድረግ፣ የሴቶችን ሚና በማጉላት፣ በጎረቤት አገራትና በሳዑዲ አረቢያ እስር ቤት ሲማቅቁ የነበሩ ዜጎችን በማስፈታት፣ በሰው በላ ጽንፈኞች ተሰይፈው በረሃ የተጣሉትን ወገኖች አስከሬን እሰበስባለሁ፣ ወዘተ በማለታቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ተቀባይነትን ያገኙት ጠ/ሚ/ሩ በጁላይ ስድስት የኢትዮጵያ ቀን ላይ እንዲገኙ ያቀረቡት ጥያቄ መልስ ሳይታወቅ በምሥጢር ዳያስፖራውን ለመከፋፈል እየተሠራ ያለው ሥራ ከፍተኛ ቅራኔ እንደሚያስነሳባቸው ይጠበቃል።
ከጀርባውም ይሁን ውስጡ ምን እየተሠራ እንደሆነ ያልተረዳው የሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለውሳኔ እንዳይጣደፍ ሲሉ የጎልጉል የአዲስ አበባ ተባባሪዎች ጠቁመዋል። እንደ ተባባሪዎቹ ከሆነ ፌዴሬሽኑ ሰከን ብሎ ነገሮችን መመርመር ካልቻል በሰላሳ አምስተኛ ዓመቱ የመቀበሪያውን ጉድጓድ ይቆፍራል።
የህወሓት አንደበትና መልዕክት አስተላላፊ የሆነው ዳንኤል ብርሃኔ ማብራሪያ ሳይሰጥ ፌዴሬሽኑ “ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመጋበዝ ወሰነም አልወሰነም ጉዳዩ የሰሜን አሜሪካውን የተቃውሞ ካምፕ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ቦታዎች እንደሚተረትረው ይጠበቃል” በማለት በፌስቡክ ገጹ ላይ አስፍሯል።
ድንገት ከኢትዮጵያዊያን ጫንቃ ላይ በተስፈነጠረው መለስ ትዕዛዝ በሌብነት ተጠርጥሮ በሳዑዲ እስር ቤት የከረመው አላሙዲና የእሱ አስፈጻሚ በሆነው አብነት ገብረመስቀል ምልምሎች አማካይነት ዶላር በትነው ሊንዱት፣ ሊያፈርሱት፣ ሊያከስሙት፣ ሊሰነጥቁት ሁሉ አይነት ሙከራ አድርገውበት በሕዝብ ትግል የተረፈውን ፌዴሬሽን መጠበቅ የዚህ ቦርድና አመራር ኃላፊነት እንደሆነም የመረጃው ባለቤቶች አሳስበዋል።
ለህወሓት ስልታዊ አካሄዶች ግንባር በመሆን እያገለገለ ያለው ኃይሌ ገብረሥላሴ በምሥጢር የሚመለምላቸው ሰዎች አድሮ ስለሚታወቁ ከወዲሁ ጥንቃቄ ቢያደርጉ፣ በንግግራቸው የሕዝብን ቀልብ የሳቡት ጠቅላይ ሚኒስትርም ይህ በሳቸው ስም የተጀመረው ዘመቻ እንደማይመጥናቸው፣ በእሳቸው አባባል ካነገሳቸው ሕዝብ ጋር የከፋ ጸብ ውስጥ እንደሚከታቸው በመረዳት ይህንን የድብብቆሽ አሠራር እንዲያስቆሙ የጎልጉል የመረጃ ሰዎች አሳስበዋል።
“አስቡት” ይላል የጎልጉል የአዲስ አበባ ዘጋቢ ያነጋገረው አስተያየት ሰጪ “አስቡት የአማራን ህዝብ ያዋረደ፣ የሸጠና ለማያባራ መከራ የዳረገው ካሳ ተከለ ብርሃን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን ተቀምጦ ንግግር ሲያደርግ … ነፍሰ በሎች በዲስኩር ብቻ አታለውን ፖለቲካዊ ድል በራሳችን ግብዣ ሲወስዱብን” በማለት ፌዴሬሽኑ ራሱን ከታሪካዊ ስህተት፣ ሊፋቅ ከማይችል ውርደት ሊጠብቅ እንደሚገባ ያሳስባል።
በቀጣዩ ምርጫ በግል ከሚወዳደሩት ምልምሎች መካከል አንዱ የሆነው ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ ያወቀ መስሎት እዛም እዚህም ጥልቅ ማለቱ፣ እጅግ ለሚተላው የህወሓት ጎሰኛ ቡድን ተላላኪ መሆኑ አድሮ ዋጋ እንደሚያስከፍለው ከወዲሁ እንዲረዳ በተደጋጋሚ ሲነገረው መቆየቱ አይዘነጋም።http://www.goolgule.com/tplf-on-pr-campaihn-for-abiys-visit-to-the-us-and-europe/

No comments:

Post a Comment