Translate

Sunday, March 18, 2018

ዛሬ ልወቅስ ነው፣ ራሴን ጨምሬ…

መሳይ መኮንን
Waldeba monastery priests, political prisoners in Ethiopia.
ዛሬ ልወቅስ ነው። ራሴን ጨምሬ በጽሁፍ ጅራፍ ልጋረፍ ነው። በእውነት ይህን ጽሁፍ ስሞነጫጭር ውስጤ በእልህና ቁጭት ድብን እያለብኝ ነው። በዚህም አሰብኩት። ወደዚህም ወሰድኩት። አገለባብጬ ተረጎምኩት። ዝምታችን ከፍርሃት በቀር ምክንያታዊ አልሆንልህ አለኝ። መቼም የትግራዩ አገዛዝ ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ የሞራል ልኬታችን ፈሩን ስቷል። የህሊና ፍርዳችን ተዛብቷል፡፡ ሰው የመሆን ሚዛናችን ጎድሏል።
አገዛዙ ይዞብን የመጣው እሴት አልባ፡ ራዕይ የለሽ፡ ክብረ ነክ ወረርሽኝ ውስጣችንን ገዝግዞ፡ እንደምስጥ ስጋችንን በልቶ፡ ዝም ብለን የምንከላወስ፡ በልቶ ማደር፡ ጠጥቶ መነሳት መኖር የሚመስለን ሆነን ቀርተናል። ስንቱን በጎነታችንን፡ የሞራል ልዕልናችንን አራግፈን ጥለን ፡ በፍርሃት ቆፈን በተቀፈደደ፡ በእንጭፍጫፊ ሰበብና ምክንያቶች በተለበጠ፡ ኢትዮጵያዊ ክብርና ሞገሱን በተገፈፈ ማንነት ደረታችንን ነፍተን፡ ልክ ነን ብለን ልክ አጥተን የምንኖር ዜጎች ሆነናል።
አዎን! ለሃይማኖቱ ቀናዒ፡ ለእምነቱ ክብር አንገቱን ለሰይፍ ከመስጠት ወደኋላ አይልም በሚባልለት ኢትዮጵያዊ አፈር ላይ በዚህ ዘመን የሃይማኖት አባቶች ተዘቅዝቀው አርባ ይገረፋሉ። የነጭ ወራሪ ባንዳ ሶላቶ ባህር ተሻግሮ ሊወረን በመጣ ጊዜ ታቦት ተሸክመው፡ በማርያም ምለው ዘምተው፡ በጊዮርጊስ ቀን ድል አድርገው ለመላው ጥቁር ህዝብ የነጻነት አክሊል ያጎናጸፉ ኢትዮጵያውያን በበቀሉባት ምድር ላይ ዘንድሮ መነኮሳት፡ ወፌ ላላ እየተገረፉ፡ መሬት ለመሬት እየተጎተቱ፡ ሰውነታቸው ደም እስኪያዥ በኤሌክትሪክ ሽቦ እየተጠበሱ፡ ታላቁን ስቃይና ሰቆቃ ይጋታሉ። ለሀገር ነጻነት ደረታቸውን ለጥይት ሰጥተው፡ መራሯን ሞት በአደባባይ ተጎንጭተው ሃይማኖቷንም፡ ሀገራቸውንም አስከብረው፡ በክብር የተሰዉትን የታላቁን ፓትርያርክ አቡነ ጴጥሮስን አጽም በተሸከመችዋ የአሁኗ ኢትዮጵያ መስቀልና መጽሀፍ ቅዱስ ብቻ ይዘው ዓለምን ተጠይፈው ገዳም የገቡ መናኞች የክህነት ልብሳቸውን አውልቁ ተብለው ግፍ ይፈጸምባቸዋል።
ይሄ ሁሉ ጉድ ይሰማል። ድብቅ አይደለም። መሀል ኢትዮጵያ፡ ከአዲስ አበባ እምብርት እየተፈጸመ ያለ ሰቆቃ ነው። ኸረ ለመሆኑ የታላቁ መንፈሳዊ አባት
ልጆች ይህን መከራ አልሰሙም? እነዚያ ለእምነታቸው ክብር እስከሞት ዋጋ የሚከፍሉ ናቸው የሚባልላቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ምዕመናን ከማዕከላዊና ቂሊንጦ በመናኞች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ስቃይ እንዴት በዝምታ ተመለከቱት? ምን ነካቸው? ከነክህነት ልብሳቸው እጆቻቸው በብረት ካቴና ተቆላልፎ በአጋዚ ቅልብ ወታደሮች ተከበው በአደባባይ የሚታዩ የመንፈስ አባቶቻቸው ሁኔታ ምን ስሜት ሰጣቸው? በእውነት የኢትዮጵያ የተዋህዶ ልጆች ከየት ነው ያላችሁት? እነዚህ የዋልድባ መነኮሳት ታላቅ ግፍ እየተፈጸመባቸው እንዴት አስቻላችሁ? እንዴትስ እንቅልፍ ይወስዳችኋል? የእምነት ትርጉሙ ምንድን ነው? መንፈሳዊ ህይወት ሲባል እንዲህ ነውን? ግፍ እያዩ ዝም። አባቶች ሲዋረዱ ጸጥ። ቋርፍ በልተው የሚኖሩ፡ ስጋቸውን ለመንፈሳዊ ዓላማ ሲሉ ያደከሙ መናኞች ተዝቅዝቀው ሲገረፉ እንዳላየ፡ እንዳልሰማ ሆኖ ማለፍ።
የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፈተናዋ በዝቷል። የቤተመንግስት አጋንንት ከቧታል። በቅጥሯ የተሾሙት አባትና በየሀገረ ስብከቱ የተሰገሰጉት የትግራይ ገዢ ቡድን አባላት ቤተክርስቲያኒቱን አፍነው ይዘዋል። ለስለላ ብለው ገብተው ቆብ ደፍተው በዚያው እስከ ጵጵስና የደረሱ የትግራይ ገዡ ቡድን አባላት የአባይ ጸሀዬንና ስብሃት ነጋን ቃል እንጂ የመጽሀፍ ቅዱስን መንፈሳዊ ህግ የሚያከብሩ እንዳልሆነ ይታወቃል። ይህ በመሆኑም ከቤተክህነት የሚጠበቅ አንዳች ተስፋ የለም። በጉልበት የተሾሙት ፓትርያርክ አቡነ ማቲያስ የዋልድባ አባቶች መከራና ስቃይ ሲደርስባቸው፡ ቤተክርስቲያኒቱን የሚያዋርድ ተግባር ሲፈጸምባቸው፡ አንዲትም ቃል ሳይተነፍሱ ስልጣን አልባው ጠቅላይ ሚኒስትር ስልጣን ሲለቅ ቤተመንግስት ድረስ ዘልቀው ውዳሴና ቡራኬ የሚያቀርቡ፡ ከንቱ አባት በመሆናቸው ከእሳቸውም የሚጠበቅ ነገር የለም። ምዕመኑ ግን ምን ነካው? ከዚህ ልቆ የሚያስፈራ ምን አለ?
ማህበረ ቅዱሳን የት ነው ያለው? የቤተክርስቲያኒቱን ገዳማትና ነዋየ ቅድሳት ከትውልድ ትወልድ ተጠብቆ እንዲቆይ እስከ ገጠር ቀበሌ ድረስ የዘለቀ መጠነ ሰፊ ተግባራትን በመከወን የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ዘብ ጠባቂ እንደሆነ የሚነገርለት ማህበረ ቅዱሳን የእነዚህን መናኞች ግፍና ስቃይ አልሰማ ይሆን? ወይስ ለመናኞች፡ ለመነኮሳት ደህንነትና ክብር እንዲጮህ መተዳደሪያ ደንቡ አይፈቅድለትም? ቢያንስ ክሳቸው በአግባቡ እንዲታይ፡ ሰብዓዊ መብታቸው እንዲከበር ለመጠየቅ የሚያስችል ወኔ ማህበረ ቅዱሳን ዘንድ እንዴት ሊጠፋ ቻለ? ገዳማት ያለመናኞች ምንድን ናቸው? ለገዳማት ተጨንቆ ለመንፈሳዊ አባቶች ግድ ማጣት ምን የሚሉት መንፈሳዊ መስመር ነው?
በእውነቱ እነዚህ አባቶች በማዕከላዊና ቂሊንጦ የደረሰባቸው ግፍ ለሃይማኖታቸው እስከመጨረሻው ዋጋ ይከፍላሉ በሚባሉ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ በሆኑ ኢትዮጵያውያን መኖሪያ በሆነችው ኢትዮጵያ መፈጸሙ ያስደነግጣል። አንድም ቀን በዚያ የግዞት ስፍራ ማደር አልነበረባቸውም። እንኳን ተዘቅዝቀው ሊገረፉ፡ ሰውነታቸው ላይ አንዲትም ዱላ ማረፍ አልነበረባትም። ምን ጉድ እንደመጣብን አላውቅም። እንዲህ ዓይነት ሰቆቃ እየተፈጸመ ዝምታችን ግራ ያጋባል። ለምን አባቶቻችን ታሰሩ ብሎ መጠየቅ እንዴት አልተቻለም? ለምን እንዲህ ክብራቸው ይነካል የሚል ድምጽ እንዴት ለጆሮአችን ይናፍቀናል? አባቶቹ እኮ አይደሉም የተዋረዱት። ማዕከላዊ ተዘቅዝቅው የተገረፉት መናኞቹ አይደሉም። እጆቻቸው በካቴና የተቆላለፈባቸው የዋልድባ መነኮሳት እኮ አይደሉም። አዎን! የተዋረደችው ቤተክርስቲያኒቱ ናት። ወፌ ላላ የተገረፈችው የአቡነ ጴጥሮስ ቅጥር የሆነችው የኦርቶዶክስ ቤት ናት። እጆቿ የታሰሩት እናት ቤተክርስቲያናችን ናት። ይህ ካላመመን፡ ይህ ካልቆጨን፡ ይህ ካልተሰማን በእውነት እኛ የተዋህዶ ልጆች ነንን?
ድምጽ ይሰማል። የአባቶች የሲቃ ጩኸት።አብያተ ክርስቲያናት በየጸሎታቸው ሊያነችሷቸው ይገባል። ምዕመናን ዘውትር ከጸሎት ባሽገር የእምነት አባቶቻቸው ላይ ጫና በመፈጠር ስለተዋረደችው ቤተክርስቲያን ሲሉ ከፍርሃት ቆፈን ተላቀው ተቃውሞአቸውን ሊያሰሙ ግድ ይላል። እያሪኮም በጩኸት ፈርሳለች። እንጩህ! የግፈኞች ግምብ መፈረሱ አይቀርም። የቤተመንግስት አጋንንት ይለቀን ዘንድ በአንድነት እንጩህ። ልቦና ይስጠን።

No comments:

Post a Comment