Translate

Saturday, January 20, 2018

የህወሀት ጸሀይ እየጠለቀች ነው

Image may contain: 1 person
መሳይ መኮንን
ብዙ ምልክቶች በመታየት ላይ ናቸው። ተመልሶ የሚያንሰራራበት እድል ያለ አይመስልም። እየተንፏቀቀ ጊዜ ሊወስድ ይችላል። እግሮቹ ተሰብሮ በደረቱ እየተሳበ ከቤተመንግስት የተወሰነ ጊዜ ሊቆይ ይችላል። ስጋው አልቆ በአጥንቱ ቆሞ ጥቂት ጊዜያት መቆየቱ የማይቀር ነው። በዘላቂነት ግን አልቆለታል ማለት ይቻላል። የህዝቡ ተቃውሞ ሳይቋረጥ ከቀጠለ፡ ከያቅጣጫው የበረታው ግፊት ጉልበቱን ጨምሮ ይበልጥ ከገፋ የሚንፏቀቀውን፡ እግሮቹ የተሰበረውን፡ በአጥንቱ የቀረውን ህወሀት ከታሰበው ጊዜ በጣም በቅርብ ዘላለማዊ ሞቱን የሚጨልጥ ስለመሆኑ አያጠራጥርም። እስቲ ምልክቶቹን አንድ በአንድ እንመልከታቸው፥-
የትግራይ ህዝብ
ህወሀት ከ2010 ዓም ዋዜማ ጀምሮ መቀሌ ከቷል። ላለፉት አምስት ወራት በስብሰባ፡ በኮንፈረንስ፡ በግምገማ፡ በህንፍሽፍሽ፡ በጉባዔ ተጠምዶ ከርሟል። አሁንም እንደሚኖር ይጠበቃል። ትግራይ የህወሀት የመጨረሻ ምሽግ ናት። ስልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ አንስቶ የኢትዮጵያ ልብ ማግኘት ያቃተው ህወሀት አክ እንትፍ፡ ተብሎ መተፋቱን አረጋግጧል። የኢትዮጵያን ህዝብ በፍቅርም፡ በጉልበትም መምራት እንደማይችል ተረድቶታል። ከእንግዲህ ወርቅ እንኳን ቢያነጥፍ የሚቀበለው እንደሌለ አውቆታል። ስለዚህ ወደ መጨረሻ ምሽጉ ፊቱን አዙሯል። ይህ ምሽግ የተወሰነ ዕድሜ እንደሚያዘልቀው ተማምኗል። በኋላ ኪሱ የሸጎጣትን ''የትግራይ ሪፑብሊክ'' ምስረታ ከተሳካለትም ይሞክራል። በኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግስት በበላይነት መቆየት ካልቻልኩ ያሉኝ አማራጮች ብሎ ከያዛቸው እርምጃዎቹ አንዱ ወደ ትግራይ ጠቅልሎ ገብቶ ምሽጉን ማጠናከር ነው።ለዚህም የትግራይን ህዝብ ልብ ሙሉ ለሙሉ ለማግኘት ቃል በመግባት ተግቶ እየሰራ ነው።

ህወሀት ምሽጉን ለማጠናከር እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ነው። ከእነዚህም አንዱ የትግራይን ህዝብ ታች ወርዶ ይቅርታ መጠየቅ ነው። በልማት ማንበሽበሽ ነው። ቀድሞውኑ ያዘነበለውን ተጠቃሚነት ይበልጥ አጠናክሮ መቀጠል ነው። ሰሞኑን እንደተሰማውም የትግራይ ህዝብ ለከፈለው መስዋዕትነት የሚመጥን ልማት ሊዘረጋለት ተወስኗል ተብሏል።። ከወዲሁ በሌላው የኢትዮጵያ ክፍል እስከአሁን ተገንብቶ የማያውቅ በፌደራል መንግስቱ በጀት በ2ቢሊየን ብር የኮንክሪት አስፋልት ግንባታ ስምምነት ተደርጓል። ኢፈርት የዘመናዊና ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች ግንባታ ስምምነቶችን እያጣደፈ ነው። ከአማራና ከኦሮሞ አርሶአደሮች ከመደበኛው የገበያ ዋጋ ከፍ ባለ መጠን የተለያዩ የእህል አይነቶች እየተገዙ ወደ ትግራይ እየተጫኑ ነው። በትግራይ በተለያዩ አከባቢዎች ግዙፍ ጎተራዎች ተተክለው እህሎች እየተከመረባቸው ነው። ምናልባት ነገሮች ከረው ወደትግራይ የሚወስዱ መስመሮች ቢቋረጡ በሚል ብዙ ምርቶች በገፍ ተገዝተው እየተጠራቀሙ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።
ህወሀት የትግራይን ህዝብ እየተለማመጠ፡ እየተማጸነ መሆኑ የሚያሳየን ነገር ቢኖር ዞሮ መግቢዬን፡ መቃብሬን አጣለሁ ከሚል ስጋት ሊሆን እንደሚችል መገመት ቀላል ነው። የመቀሌው ኮንፍረንስ የህወሀት የነፍስ አድን ጥሪ እንደሆነ ይነገራል። የመጨረሻ ምሽጉን አስተማማኝ ለማድረግ ነው። የህወሀት አመራሮች ''ልባችሁን ክፈቱልን። በጠላት እጅ ላይ ከምንወድቅ በእናንተ ክንድ ላይ የመጨረሻዋ እስትንፋሳችን ታልፍ ዘንድ ፍቃዳችሁ ይሁን'' ዓይነት ልመና ባደረጉበት የቅርብ ጊዜው ኮንፍረንስ ያሰቡትን ያህል ስለማግኘታቸው የሚታወቅ ነገር የለም። አይናቸውን በጨው አጥበው ግን ''ከማንም በላይ መስዋዕትነት ስለከፈላችሁ ትካሳላችሁ። ጊዜው ደግሞ አሁን ነው '' የሚል በሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ኪሳራ ለትግራይ ባላት ላይ ሊከምሩባት፡ ወስነዋል። የሚያስጨንቃቸው ስልጣናቸው ነው። አዲስ አበባ ላይ ተነቃንቋል። ቢያንስ መቀሌ ላይ ምሽጋቸውን አጠናክረው ትንሽ ጊዜ የሚያቆያቸውን ሃይል ማጠራቀም አለባቸው። ማምሻም እድሜ ነውና።
የትግራይ ህዝብ ውሳኔ ምን ሊሆን እንደሚችል አይታወቅም። የህወሀት ካድሬዎችን፡ ደጋፊዎችንና አባላትን ጩሀት ለሰማ ተስፋ ሊቆርጥ ይችላል። ጨፍነው ግፋ እያሉት ነው። አበጀህ የእኛ ልጅ ከሚል ሞራል ጋር የህወሀትን የጥፋት ዕቅድ እየደገፉት ነው። ይህ ስሜት የትግራይ ህዝብ በሙሉ ነው ለማለት ይከብዳል። ድምጹ ስለማይሰማ፡ የሚጮሁት ጥቂቶች የሌላውን የኢትዮጵያ ህዝብ ስሜት ቀይረው በጅምላ የትግራይን ህዝብ ከወገኑ እንዳይነጥሉት ስጋቱ አለ። የትግራይ ህዝብ ለህወሀት የመጨረሻ ምሽግ መሆን የለበትም። ህወሀት ያልፋል። በቅርቡ። ከማያልፈው ህዝብ ጋር ሰልፉን እንዲያስተካክል ይጠበቃል። ህወሀት እየገነባ ያለውን የመጨረሻ ምሽግ ቀድሞ ማፍረስ ያለበት የትግራይ ህዝብ ነው።
የኢኮኖሚው ቀውስ
አይ ኤም ኤፍ ሰሞኑን እንዳስታወቀው የህወሀት መንግስት ያለው የውጭ ምንዛሪ ክምችት ከአንድ ወር ከ8ቀናት በላይ የሚያዘልቀው አይደለም። መረጃዎች የሚያሳዩት ግን ከዚህም በላይ አስደንጋጭ ነው። ከአንድ ቢለየን ዶላር በታች የደረሰው የውጭ ምንዛሪ ክምችት ህወሀትን እጅና እግሩን አሳስሮ አስቀምጦታል። አይ ኤም ኤፍ ለህወሀት የሚጨክን አንጀት ስለሌለው እውነተኛውን ቁጥር ስለመግለጹ ጥርጣሬ አለ። የሆኖ ሆኖ የአይ ኤም ኤፍ መረጃ በራሱ ብዙ ነገሮችን ይነግረናል። አንድ መንግስት በዚህ ደረጃ የውጭ ምንዛሪ አቅም ላይ ከደረሰ ምንም ነገር ማድረግ አይችልም። ኢኮኖሚው በከፍተኛ ፍጥነት ወደ እየወደቀ ነው። የአገዛዙ ጠበቃ የሆነው ሪፖርተር ጋዜጣ ''ለመንግስት ከባድ አደጋ መጥቶበታል'' ሲል በተቆርቋሪነት ስጋቱን ገልጿል።
የውጭ ንግድ ተዳክሟል። ኢንቨስትመንት የኋሊት እየገሰገሰ ነው። የንግድ ስርዓቱ ተፋልሷል። ግብይቱ ተረባብሿል። የቱሪዝሙ ዘርፍ እያቃሰተ ነው። በእንቅርት ላይ እንዲሉ የብር የመግዛት አቅም በ15 በመቶ እንዲቀንስ መደረጉ ቀውሱን አባብሶታል። የዋጋ ግሽበት ከአንድ አሀዝ ወደ ሁለት አድጓል።በሀገሪቱ በተለያዩ አከባቢዎች እየተካሄዱ ባሉ ተቃውሞችና ህዝባዊ አመጾች ምክንያት የንግድ ቦታዎች ስራ ፈተዋል። በየጊዜው የሚመታው አድማ መደብሮችንና ሱቆችን ጾማቸውን እንዲከርሙ እያደረገ ነው። በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ተቃውሷል። መፍትሄው ከህወሀት አቅም በላይ ሆኗል። ከውስጥ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የህወሀት አገዛዝ በድጋሚ የብርን የመግዛት አቅም ለመቀነስ እየተዘጋጀ ነው። ይህ ከሆነ በኑሮ ውድነት ጀርባው የጎበጠው የኢትዮጵያ ህዝብ የመኖር ህልውናው ያከትማል ሲሉ መጪውን ጊዜ በስጋት የሚገልጹ ወገኖች አሉ። የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚሉት ተጠያቂነት ባለባቸው ሀገራት እንዲህ ዓይነት ቀውስ በሩብ ያህል ቢከሰት እንኳን መንግስትን የሚመራው አካል በራሱ ጊዜ ከስልጣን ይወርዳል። በህወሀት መዝገበ ቃላት ግን ስልጣን መልቀቅ በተአምር የሚታሰብ አይደለም።
ህወሀት የኢኮኖሚው ነገር ከአቅም በላይ ሆኖበታል። መሰረታዊ አገልግሎቶችን ማቅረብ ተስኖታል። ውሃ መብራትና ሌሎች አገልግሎቶች የሚቆራረጥባቸው፡ ጭራሽኑ የማያገኙ ከተሞች እየጨመሩ መጥተዋል። የነዳጅ እጥረቱ ተባብሷል። ለነዳጅ መግዣ የሚሆነው የውጭ ምንዛሪ እየተሟጠጠ በመሆኑ በቀጣይ ቀውሱ ሊከፋ እንደሚችል ይጠበቃል። ለመድሃኒት መግዥ የምትሆነዋ የቀረችው የውጭ ምንዛሪም ተመናምናለች። ህገወጥ የመድሃኒት ዝውውር ይህን ተከትሎ የሚዛመት በመሆኑ ከፍተኛ የጤና ቀውስ ይከሰታል ተብሎ ይሰጋል። በአንዳንድ አከባቢዎች የመንግስት ሰራተኞች ደመውዝ ሳይከፈላቸው ወራት እንደሚቆጠሩ ተሰምቷል።
በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የከፈቱት የውጭ ምንዛሪ ተአቅቦም ለህወሀት መንግስት ራስምታት መፍጠሩ እየተነገረ ነው። የውጭ እርዳታ በነጠፈበት፡ ብድር ሰጪዎች እጃቸው ባጥረበት በዚህን ወቅት የህወሀትን ኢኮኖሚ ደጋግፎ የያዘው ሪሚተንስ(ከውጭ ወደ ሀገር ቤት የሚላክ ገንዘብ) እንዲቀንስ የተጀመረው ዘመቻ ውጤት እያሳየ ነው። ህወሀት ብርክ ይዞታል። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የህወሀትን አገዛዝ ነፍስ ቀጥ አድርጎ የያዘው የሪሚተንስ ገንዘብ ነው። እሱ በአንዳች ሁኔታ ከቀነሰ ለማፈኛ ተቋማቱ የሚከፍለው ገንዘብ አይኖረውም። ይህም የማፈን አቅሙን ያዳክማል።ያ አቅሙ ከተዳከመ ደግሞ ይገነደሳል። አዲዮስ ህወሀት!
የፖለቲካ ምሁራን እንደሚስማሙት በኢትዮጵያ እስከአሁን ከተደረጉት ህዝባዊ ተቃውሞዎች በላይ ሀገር አቀፍ የሆኑ አመጾችና እምቢተኝነቶች መቀጣጠላቸው አይቀርም። የኢኮኖሚው ሁኔታ በዚሁ ከቀጠለ ከተሞች፡ መንደሮች፡ አውራጎዳናዎች በተቃውሞ ይጠለቀለቁ ዘንድ የሚጠበቅ ነው። የአገዛዙ ደጋፊ የሆኑ ሚዲያዎችም ይህን ሀቅ እየጎመዘዛቸውም ቢሆን እየተናገሩት ነው። ሪፖርተር እንዳለው መንግስት በአስቸኳይ መፍትሄ ካልሰጠ የኢኮኖሚው ቀውስ የበለጠ የህዝብ ተቃውሞዎችን ያመጣል። በየቀኑ የአመጽ ሰልፎችን የምናይበት ጊዜ ሩቅ አይደለም።
ውስጣዊ ቀውስ
ህወሀት በራሱ ውስጥና እንደኢህአዴግ ከአባል ድርጅቶች ጋር የገባበት ቀውስ የሚሰክን አልሆነለትም። ከመቀሌው የነፍስ አድን ኮንፍረንስ ጎን ለጎን እየተለቀቁ ያሉት ሚስጢሮች ህወሀት ይበልጥ በውስጣዊ ቀውስ እየተሰቃየ ለመሆኑ ምልክት የሚሰጥ ነው ማለት ይቻላል። በተሸነፈው ቡድን የሚዘከዘኩት ጉዶችና ቅሌቶች በህወሀት መንደር ያለው አንድነት መናጋቱን የሚያመላክት ነው። በተለይ የህወሀት ሊቀመንበርና የትግራይ ክልልን በም/ፕሬዝዳንትነት እንዲመራ የተሰየመው የወሲቡ ሻምፒዮን ደብረጺዮን ገብረሚካዔል ላይ የተከፈተው የማጋለጥ ዘመቻ ለህወሀት ትልቅ አደጋ እንደሚሆን ይገመታል። የተመታው ቡድን እጁን አጣጥፎ እንዳልተቀመጠ እያስመሰከረ ነው። ያለድርጅታዊ መተዳደሪያ ደንብ ወደ መቀሌ ዳግም እንዲከትና በኮንፍረንስ እንዲጠመድ ያደረገው የውስጣዊ ሽኩቻው እየበረታ በመምጣቱ እንደሆነም ይነገራል። በትግራይ ሽማግሌዎች እግዚዮታና ልመና ለጊዜው ጋብ ቢልም ህወሀት እንደ ድርጅት ለመቀጠል የሚያስችል ውስጣዊ አንድነቱ እንደሰባበረ የሚደብቁት አልሆነም።
ከኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የ17 ቀናቱ ዝግ ስብሰባ በኋላ ''ልዩነታችንን ፈተናል። አንድ ሆነናል'' የሚለው መግለጫ በወረቀት ላይ እንጂ መሬት ላይ እንደሌለ ከዚያን ወዲህ የተፈጠሩ ነገሮችን በመጥቀስ መግለጽ ይቻላል። ለጊዜው ውጥረትን ማስተንፈስ የቻሉ ቢመስልም አንድነታቸው ላይመልስ መናጋቱ ከማይደበቅበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። የኦህዴድና የብአዴን አመራሮች አሁንም በአቋማቸው እንደጸኑ ናቸው። የአቶ ለማ መገርሳ ቡድን ከዝጉ ስብሰባ በኋላም የሚያደርጋቸው፡ የሚናገራቸው ለህወሀት ምቾት የሚሰጡ አልሆኑም። በ17ቱ ቀናት ዝግ ስብሰባ ያደረግነውን ተጋድሎ ህዝቡ ቢያውቀው ጥሩ ነበር ያሉት አቶ ለማ ስምምነት እንደሌለ በጎን እየነገሩን እንደነበረ አልተረዳናቸውም። በእስረኞች መፈታት ላይ በተለይ የኦህዴድ አመራር የያዘው አቋም አሁንም ኢህአዴግ ቤት ቀውስ እንዳለ ግልጽ መልዕክት ነው። የፌደራል መንግስቱን የፍቺ መስፍርት አልቀበልም ያለው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ህወሀቶች የሚተናነቃቸውን ''የፖለቲካ እስረኞች'' ን በሙሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደሚፈታ አስታውቋል።
አቶ ለማ የኢትዮጵያን ህዝብ ቀልብ የገዙበትን የፍቅርና የአንድነት መልዕክታቸውን ከዝጉ ስብሰባ በኋላም ቀጥለውበታል። ህወሀት ያወገዘውን ''የመርህ አልባ ግንኙነት'' የቀጠሉት አቶ ለማ መገርሳ ''ነፍስ ዘር የላትም'' በሚል አዲስ ቀልብ ሳቢ መልዕክታቸው ብቅ ብለዋል። ከዚያም ተሻግረው በለገጣፎ የኦሮቶዶክስ ቤተክርስቲያን የገጠማትን የጥገኛ ባልስልጣናት አደጋ አስወግደው ቤተክርስቲያኒቱ ይዞታውን አግኝታ አገልግሎቷን ያለምንም ችግር እንድትቀጥል ማድረጋቸው በእርግጥም ሰውዬው የህወሀትን የልዩነት ግንብ ሳይደረምሱ እንቅልፍ እንደማይወስዳቸው ያረጋገጡበት ውሳኔያቸው ነው። የድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን የባህርዳሩ ኮንሰርትም ከህወሀት ፍላጎት ውጪ ስለመፈቀዱ ምንም ጥርጥር የለውም። ኮንሰርቱ በመካሄዱ ህወሀት የሚያተርፈው አንዳችም ነገር ፈልጌ ላገኝ አልቻልኩም። ይልቅስ የገዱ ቡድን በብአዴን ውስጥ ያለውን የህወሀት ተላላኪ አመራርና የመቀሌውንም ገዢ ቡድን ተጋፍጦ የፈቀደው ኮንሰርት መሆኑን መግለጽ ይቻላል።
እናም ኢህአዴግ ውስጥ የገባው ንፋስ ህወሀትን እያናጋው ቀጥሏል። ወደ መቀሌ አማትሮ የመጨረሻ ምሽጉን እንዲያጠናክር ያደረገውም በኢህ አዴግ ውስጥ የነገሰው ክፍፍል በቀላሉ የሚጠገን ባለመሆኑ እንደውም ህልውናን የሚያጠፋው እንደሆነ በመረዳቱ ነው።
የአፍሪካው ቀንድና የምዕራባውያን አቋም
የምዕራባውያን ፍላጎት የህወሀት አገዛዝ እንደምንም ብሎ በስልጣን ላይ ቢቆይላቸው ነው። አሁን ግን ያ የሚሆን አልመሰላቸውም። ህወሀት የተለከፈበት በሽታ ለእነሱም መዘዝ እንደሚያመጣ የተረዱት ይመስላል። ከወዲሁ አንዳንዶቹ እጃቸውን መሰብሰብ ጀምረዋል። ለህወሀት ፊት መነሳታቸውን የሚያረጋግጡ ምልክቶችን በአደባባይ እያሳዩ ነው። በጀርባ አዝለው ከአራት ኪሎ ቤተመንግስት ያስገቡት የአሜሪካው ዲፕሎማት የሰሞኑ የቲውተር መልዕክት አንድ ፍንጭ የሚሰጥ ነው። ከ27ዓመት በኋላ የህወሀት ጭራቅነት የተገለጠላቸው ዲፕሎማቱ ሀርማን ኮን የኢትዮጵያ ህዝብ የደረሰበት አቋም አስደንግጦአቸዋል። ''ከህወሀት ደርግ የተሻለ ነበር''
በእርግጥም አሜሪካ እየተንሸራተተች ነው። ከህወሀት አገዛዝ ጋር ለዘመናት የተጣበቀችበትን የውጭ ፖሊሲዋን ልትቀይረው መውሰኗን ታውቋል። የአሜሪካው የመከላከያ ሚኒስትር ሰሞኑን እንደተናገሩት ''አሜሪካ የጸረ ሽብር አጋርነት ላይ የተመሰረተው የውጭ ፖሊሲዋ አብቅቷል'' ይህ ውሳኔ ለህወሀት አገዛዝ ታላቁ መርዶ ሊባል የሚችል ነው። ድሮውኑም ከፖለቲካ ድጋፍ በቀር ከህወሀት ጋር የኢኮኖሚ ወዳጅነት ያልፈጠረችው አሜሪካ ብቸኛውን የግንኙነት መስመር ለመበጠስ መወሰኗ ለነጻነትና ዲሞክራሲ ናፋቂ ኢትዮጵያውያን ትልቅ የምስራች ሲሆን ለህውሀትና ደጋፊዎቹ አስደንጋጭ ዜና ነው። ይህ ውሳኔ ህወሀትን የሚያሳጡት በርካታ ነገሮች አሉ። በዓለም ዓቀፍ ዲፕሎማሲ ላይ የአሜሪካንን ጭራ እየተከተለ ድጋፍ ሲያሰባስብ የከረመው ህወሀት በተላላኪነት ያገኘውን ተሰሚነት የሚያጣበት ይሆናል። በጸረ ሽብር አጋርነት የሚያገኛቸውንና ኢትዮጵያውያንን የሚገድልባቸውን አሜሪካ ሰራሽ የጦር መሳሪያዎችን ከእንግዲህ ይነጥፍበታል። በዚሁ የጸረ ሽብር አጋርነት የሚሰጠውም ዶላር ይቆማል። ይህ በፖለቲካ ድጋፍ የሚያገኘው ዶላር ለህወሀት የመኖር ዋስትናው ሆኖ ቆይቷል። የእንጀራ ገመዱ ነበር።
የአፍሪካው ቀንድ ፖለቲካዊ ትኩሳት ላይ ነው። የግብጽና የሱዳን ፍጥጫ በርትቷል፡፡ የአረብ ሀገራት በረጅም እጃቸው የሚያምሱት ቀጠና ሆኗል። ወደለየለት አጠቃላይ ቀውስ ባይገባም ከወዲሁ የሚታዩት ፍንጮች ለህወሀት አገዛዝ ህልውና ወሳኝ መሆኑ አይቀርም። የህዝብ አመጽ ገፍቶ ከቀጠለ ከአፍሪካው ቀንድ ቀውስ በፊት ህወሀት ሊሰናበት ይችላል። ካልሆነም ቀውሱ የህወሀትን ዘላለማዊ ሞት እንደሚያስከትል የፖለቲካ ምሁራን ይገልጻሉ። ለዚህም በርካታ ምክንያቶችን ቢደረድሩም የኢትዮጵያ ህዝብ ህወሀትን የመሰለ ጨካኝ አገዛዝ ቤተመንግስት አስቀምጦ የትኛውንም የውጭ ወራሪ ሃይል ለመዋጋት የሚሰለፍ አለመሆኑ ዋናው ምክንያት እንደሆነ ይስማማሉ። ሻዕቢያ መጣብህ እያለ ህዝባዊ ድጋፍ ማሰባሰብ ከእንግዲህ የሚቻል አይደለም። እንኳን ሻዕቢያ ግብጽም ከመጣች ጦርነቱ የህወሀትና የግብጽ እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ አይሆንም የሚለው አቋም ከወዲሁ በኢትዮጵያውያን ዘንድ እየተመላለሰ ይሰማል። ህወሀትን ይዞ ጦርነት አያዋጣም። እንደውም ህወሀትን ለመሰናበት ጥሩ አጋጣሚ ሊፈጥር ይችላል።
ማጠቃለያ
አስቸኳይ አዋጅ ያላስቆመው፡ የደህንነት ምክርቤት ማጠንቀቂያ ያላበረደው፡ የኢህአዴግ መግለጫ ያልገታው፡ የእስረኞች ፍቺ ያላዘናጋው ህዝባዊ ተቃውሞ ቀጥሏል። የጥምቀት ዋዜማ የከተራ በዓል በጸረ ህወሀት መልዕክቶች ደምቆ ነው የተከበረው። በአምቦ፡ ጎንደር፡ ነቀምት ፡ ወልዲያ አንድ መልዕክት ይሰማል ''ቻው ቻው ወያኔ፡'' ዛሬ በወልዲያ አራት ሰዎች የተገደሉበት ተቃውሞ ፡ በባህርዳርና ጎንደርም በተመሳሳይ እየታየ ያለው የህዝብ የእምቢተኝነት እንቅስቃሴም የሚያመላክተው የኢትዮጵያ ህዝብ የትኛውንም መስዋዕትነት ከፍሎ ህወሀት የሚባል ኋላቀር፡ አውሬ አገዛዝን ለመገላገል መቁረጡን ነው። አዎን! የህወሀት ጸሀይ እየጠለቀች ነው።

No comments:

Post a Comment