Translate

Wednesday, January 17, 2018

ከድንዛዜው መውጣት አለብን፣ የህወሀት አጀንዳ እንዲመራን አንፍቀድለት

መሳይ መኮንን
Merera Gudina is a professor and politician in Ethiopia.
Merera Gudina
ሰሞኑን የህወሀት አገዛዝ ከወዲህ ወዲያ እየዘለለ ነው። በፍትህ ስርዓቱ ላይ ጢባ ጢቤ እየተጫወተ ነው። ጠዋት የተናገረውን ከቀትር በኋላ ይሸረዋል። ምሽት ላይ የወሰነውን ንጋት ላይ ይሰርዘዋል። ይፈታሉ፡ አይፈቱም። ይቅርታ ነው። የለም ምህረት ነው። የፖለቲካ እስረኛ የሚባል የለም። ፖለቲከኞች ይፈታሉ። በሁለት ቀናት ውስጥ ይፈታሉ። በሁለት ወር ውስጥ ውሳኔ ያገኛል። ሪፖርተር ሌላ። ሬዲዮ ፋና ሌላ። ዋልታ ወዲህ- ኢቲቪ ወዲያ። ዥዋዥዌ።

የጀርመን ሬዲዮን የትላንት ዘገባ ሳዳምጥ ነበር። ዶ/ር መረራ ይፈታሉ በሚል ከ1ሺህ በላይ የዶ/ር መረራ ደጋፊዎች በፈረስ ሆነው አዲስ አበባ ገብተው እየተጠባበቁ ነው። ጠበቃቸው ዶ/ር መረራ እንደሚፈቱ እርግጠኛ ሆነው ይናገራሉ። የዋልታን ሰበር ዜና አልሰሙ ይሆናል። ወይም ደግሞ ማምሻውን ሌላኛው የህወሀት አባወራ ይፈታሉ ብሎ ተናግሮ ሊሆን ይችላል።
ከእስር ቤቱ ግቢ እግር እስክትወጣ ማመን የሚቻል አይደለም። እናም ጀርመን ሬዲዮ ላይ እንደሰማሁት ለዶ/ር መረራ አቀባብል ሽር ጉድ እየተባለ ነው። ለህወሀት እንዲህ ዓይነት ድምቀት ይመቸዋል። ሰዉ ትኩረቱን በፍቺው ላይ ይሆናል። ጀግናውን ተቀብሎ ወደቤቱ እንዲገባ ያደርገዋል። በቃ!
ዥዋዥዌው ታቅዶ የሚካሄድ ነው። በህወሀት መንደር ስምምነት አለመኖሩ እንዳለ ሆኖ የፍቺው ወሬ የህዝቡን ቀልብ እንዲቆጣጠረው በህወሀት ዘንድ ተፈልጓል። እስረኞችን በአንድ ጊዜ መፍታቱ የሚያዋጣ አይደለም። እያባበሉ፡ ጌዜ እየወሰዱ፡ የተምታቱ መግለጫዎችን እያቀረቡ፡ ህዝቡን አጀንዳ ማሳጣትና በፍቺ ወሬ ሰማይ ምድሩ እንዲሞላ የተፈለገ ይመስላል። የህወሀት ሚዲያዎች ግራ የሚያጋቡ፡ የተምታቱ መረጃዎችን በማከታተል እየለቀቁ ህዝቡን ለቀናት፡ ብሎም ለወራት ከትግል ስሜትና፡ ከተቃውሞ ሙቀት ውስጥ እንዲርቅ ለማድረግ ታቅዷል ማለት የሚቻል ነው።
ህወሀት መተንፈሻ ፈልጓል። አየር መውሰድ አለበት። ናላውን ካዞረው የህዝብ አመጽ እፎይ የሚልበት አጀንዳ ያስፈልገዋል። በእስረኞች መፈታት የሚፈነጥዘውን ህዝብ በፍቺ ወሬ እያደነዘዙ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን የስልጣን ዕድሜን ለማራዘም ማቀዱን ከዥዋዥዌው መረዳት ይቻላል።
ከድንዛዜው መውጣት አለብን። የህወሀት አጀንዳ እንዲመራን አንፍቀድለት።ጀግኖቻችን ቢፈቱ ደስ ይለናል። ትግሉ ግን ከእነሱ መፈታትም በኋላ ተጠናክሮ ይቀጥላል የሚለውን መልዕክት ለህወህትቶች እስኪተናነቃቸው መንገሩ ላይ መዘናጋት አይገባም። ይልቅስ የተበጠረቀው የህወሀት የሚስጢር ቋት ላይ እናተኩር። እየተዘከዘከ ያለውን ጉዳቸውንና ቅሌታቸውን ለመሸፋፈን የሚያደርጉትን መፍጨርጨር በማጨናገፍ በሰጡን ዱላ እንቀጥቅጣቸው። ከተከላካይነት ወደአጥቂነት የምንሸጋገርበት ምዕራፍ ላይ እንገኛለንና።

No comments:

Post a Comment