Translate

Thursday, September 22, 2016

ብራቮ ሸገሮች፣ ብራቮ ጋዜጠኛ ሕይወት ፍሬ ስብሐት!!

በፍቅር ወርቁ
Addis Ababa University, Ethiopiaመንግሥት ከሰኞ ጀምሮ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራንና የአስተዳደር ሠራተኞች ጋር የጀመረውን ውይይት በተመለከተ እየሰጣችሁን ያለው መረጃ እጅግ ሚዛናዊና የተብራራ ነው። የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን በሚያሳዝን ሁኔታ ስብሰባው በእጅጉ የተሳካና ያለ ምንም እንከን/ተቃውሞ እየተካሄደ እንዳለ ነው የዘገቡትና እየዘገቡት ያለው …።
ለአብነት ያህል ከሸገር ሬዲዮ ወጪ በመንግሥት ስር የሚገኙትም ሆነ የግሎቹ ኤፍ ኤም ሬዲዮኖች በስብሰባው የመጀመሪያ ቀን መንግሥት ለስብሰባው አጀንዳ ይሆን ዘንድ ባሰራጨው ሰነድ ላይ ፈጽሞ ለእኛ የማይመጥንና አገሪቱ ካለችበት ወቅታዊ ፖለቲካዊ ትኩሳትን ከግምት ውስጥ ያስገባ ባለመሆኑ በሚል- በተቃውሞ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የስብሰባው ተሳታፊ ምሁራን አዳራሹን ለቀው እንደወጡ የዘገበው የሸገር ሬዲዮ ብቻ ነው። በአጠቃላይ ከጅማሬው ቀን ጀምሮ የስብሰባውን ድባብ በሚዛናዊ መልኩ መረጃዎችን ለሕዝብ እያቀረባችሁ ነውና ሸገሮች ምስጋና እና አድናቆት ይገባችኋል። ለዚህ ለዛሬው የቁጭት ስሜት ለተቀላቀለበት አስተያየቴ ምክንያት የሆነኝ ግን፤

የዛሬውን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን የስብሰባ ውሎ ለመዘገብ በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ፣ ዶ/ር እሸቱ ጮሌ አዳራሽ የተገኘችው ባልደረባችሁ ጋዜጠኛ ሕይወት ስለ ስብሰባው ውሎ ከተለያዩ ምሁራን ዘንድ አስተያየት ለመጠየቅ ያደረገችው ሙከራ በግቢው የጥበቃ ምናልባት የደህንነት ሃይሎች ማለት ሳይቀል አይቀርም ሀይልና ማመናጨቅ የታከለበት ሁናቴ መስተጓጎሉን ከምሽት የዜና እወጃችሁ ሰምቼያለሁ።
በእውነት ያሳዝናል። በአገራችን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን፣ ሐሳብን በነፃነት የማጎልበት ረገድ ትልቅ ሚና አለው ከሚባልበት የአገሪቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ውስጥ መረጃን የሚያፍኑና ሐሳብን የመግለጽ መብትን እንደ ዝንብ ለመደፍጠጥ ተግተው የተሰማሩ የመንግሥት የደህንነት ሃይሎች እግር በእግር እየተከታተሉ ጋዜጠኞችን ለማፈን እንዲህ ዓይነት መብት የሰጣቸው መንግሥት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደታችንና አጠናክረን ለመቀጠል በሚል የይስሙላ ስብሰባ በምሁራኑ ጊዜና በአገሪቱ ሃብት ላይ እየተጫወተ እንዳለ ነው የሚሰማኝ። በእውነቱ ይሄ በጣም የሚያሳፍር፣ የሚያስቆጭ ነው።
በትክክል ማለት የሚቻለው ነገር ቢኖር የሸገር ሬዲዮ አገሪቱ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታና ከሰሞኑን መንግሥት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋር እያካሄደ ያለውን ስብሰባ በተመለከተ ለሕዝብ እያደረሰ ባለው መረጃ መንግሥት እየተደሰተ እንዳልሆነ ይህ የዛሬው የሸገሯ ጋዜጠኛ የሕይወት ፍሬ ስብሐት አሳዛኝ ገጠመኝ – በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ የደረሰባት ወከባ፣ እንግልትና ቃለ መጠየቅ ማድረግ እንደማትችል የተላለፈላት ቀጭን የመንግሥት ካድሬ ትዕዛዝ አንድ ማሳያ ነው።
መንግሥት በስብሰባው አዳራሽ ውስጥ ብቻና እኔ ከምፈቅድላቸው ሰዎች/ጋዜጠኞች ውጭ ሐሳባችሁን መግለጽ አትችሉም የሚሉ አፋኝ ሃይሎቹን/ካድሬዎቹን በግቢው ዙርያ አሰማርቶ ስለ የትኛው ዴሞክራሲ፣ ነፃነትና መብት እየተናገረ፣ እያወያየ እንዳለ ግራ የሚያጋባ ነገር ነው። ይህ በምሁራኑ ጊዜ፣ በሕዝብና በአገር ላይ ማላገጥ ነው። መንግሥት የሚሰማ ጆሮ ካለው ሕዝብን አፍኖ መግዛት እንደማይቻል አሁንም ማወቅ እንዳለበት ደጋግሞ ሊነገረው ይገባል።
በእውነት ከሆነ በስብሰባው የመጀመሪያው ቀን አንዳንድ ምሁራን እንዳሉት ለእንዲህ ዓይነቱ የይስሙላ ውይይት የሚባክነውን ገንዘብ በድርቅ ለተጎዱ፣ በልማት ስም ለተፈናቀሉ፣ በችግር ውስጥ ለወደቁ ወገኖች ይሰጥ በማለት የሰጡት አስተያየት የሚገባና ትክክለኛ ሐሳብ ነው።
ሸገሮች በርቱልን፤ ሕዝብ ሁሌም አሸናፊ ነው!

No comments:

Post a Comment