Translate

Thursday, September 22, 2016

በአልሞ ተኳሽ እና በመሬት ስርቆት የታወቀው ህወሓት ለኢትዮጵያ አደጋ ተጠያቂ ነው – አክሎግ ቢራራ (ዶር)

አክሎግ ቢራራ (ዶር)
“እኛ ጠንካራ ለመሆን የምንችለው በመተባበር ብቻ ነው፤ በተጻራሪው፤ እኛ ደካማ የምንሆነው በመከፋፈል ነው።” ጀሪ ሮሊንግ፤ የቀድሞው የጋና ፕሬዝደንት
Ethiopia's killing squadዛሬ ግብጾች ስለ ኢትዮጵያ ያወጡትን ዘገባ ስሰማ ከዚህ በፊት ስለ ተሃድሶ ግድብ በተከታታይ ያቀረብኳቸውን ትንተናዎችና ማስጠንቀቂያዎች አስታወሰኝ። በአጭሩ ያሳሰብኩት ህወሓት/ኢህአዴግ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከፋፍሎና አፍኖ ይህን ለዚህ ግድብ ዋስትና ሊሰጥ አይችልም የሚል ነው። መጀመሪያ፤ ህወሓት ለራሱ የበላይነት በማሰብ ብቻ፤ ታላቋን ትግራይን ለመፍጠር ባለው ህልም ብቻ፤ ኢትዮጵያን በፈጠራ የሕዝብ ስርጭት ከፋፈላት፤ መተከልን ወደ ቤን ሻንጉል፤ ብዙ የጎንደርና የወሎ አማራ መሬቶችን ምንም ውይይት ሳይደረግ፤ ፓርላማው ሳያውቅ ወደ ታላቋ ትግራይ ቀላቀለ። የትግራይ ወሰን በአንድ ጊዜ ሱዳንን አካለለ፤ ወደ ደቡብ ሄዶ ቤን ሻንጉል ደረሰ። ታላቁን የተሃድሶ ግድብ ለአደጋ በሚያመች ሁኔታ ወደ ወዳጁ ሰሜን ሱዳን አስጠጋው። የግድቡ የውሃ ፈሰስ ለሱዳኖች እንዲጠቅም አደረገ፤ አደጋውን ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲሸከም ወሰነ።

ህወሓቶች በበላይነት በቋንቋና በጎሳ ልዩነት ያዋቀሩት ስርዓት ዛሬ በግልጽ ለኢትዮጵያ ዋና የውጭ ጠላቶች መሳሪያ እየሆነ ነው። በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጦርነት ቢነሳ ባድሜ እንደሆነው ሕዝብን ከዳር እስከ ዳር ለመቀስቀስ አይችልም። ህወሓት ሕዝብን እየገደለ ከህወሓቶች ጋር አብሮ የሚቆም ያለ አይመስለኝም። ሆኖም፤ የግብጾች ፕሮፓጋንዳ የሚለውን አልቀበልም። የኦሮሞ ሕዝብ ለግብጽ አጎብዳጅ አይደለም። የሚከፈለውን ዋጋ የሚያውቅ ሕዝብ ነው። የኦሮሞው፤ የአማራውና ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የህወሓትን አገዛዝ ተቃወመ እንጅ የኢትዮጵያን ነጻነት፤ ዳር ድንበር፤ አንድነትና ሉዐላዊነት አልተጻረረም። ሕዝቡ ለነጻነቱና ለአገሩ ሉዐላዊነት ከፍተኛ ቦታ ሰጥቶታል፤ እየሞተለት ነው። የህወሓቶች ክፉነት እና ጨካኝነት፤ ኢሳት እንዳቀረበው “የመሬት ስርቆት ሱስ” እና የአገርን ኃብት መዝረፍና ከአገር ማውጣት ዋናው ባህሪው መሆኑ በብዙ መረጃዎች ተረጋግጧል። ህወሓቶች አዲስ የመስፋፋት ካርታ ቀርጸው ወጣት ትግሬዎችን እንደሚያስተምሩ፤ የአማራውን ሕዝብ ለማድከምና ድሃ ለማድረግ የደጀን ተራራን፤ ራያና አዘቦን፤ ላሊበላን፤ የዋልድባን ገዳምና ለም መሬት፤ ወልቃይት ጠገዴና ሌሎችን ከወሰዱና ለመውሰድ ከወሰኑ አስር አመታት አልፈዋል። እስካሁን የሕዝቡን አቤቱታ የሚሰማ አልነበረም። ህወሓቶች ሰርቀውና ቀጥፈው “ይቅርታ” መጠየቃቸው ወደው ሳይሆን ሕዝቡ ስላስገደዳቸው ነው። ገና፤ ገና ብዙ ይቅርታ የሚጠይቁባቸው አበይት ጉዳዮች አሉ። በተለይ ግድያን በሚመለከት። ይህ ሂደት መተባበርን፤ የሕዝብ አጋር መሆንን ይጠይቃል።
ያልተባበረ ሕዝብ ሁልጊዜም ተጠቂ ይሆናል። የተባበረ ግን ጊዜ ቢወስድም፤ ጥቃት ቢደርስበትም ምን ጊዜም አሸናፊ ሆኖ ይወጣል። ለዚህ ትምህርት የሚሆነኝ በጎንደር፤ በደብረ ታቦር፤ በወልቃይት ጠገዴና በሌሎች መንደሮች፤ ከተሞች፤ የገጠር ነዋሪዎችን ጨምሮ የሚደረገው አስደናቂና ብልሃት ያለው የትግል ስልት ነው። በኦሮምያም የሚደረገው ተመሳሳይ ነው። የመገናኛ ብዙሃን ሙሉ በሙሉ በተዘጋበትና ሁሉም በህወሓቶችና በአካባቢ ቅጥረኞች የአይን ቁራኛ ስለላ በሚካሄድበት ሁኔታ ተራው ሕዝብ የመጣው አደጋ ይምጣ፤ ያሰሩትን ይሰሩ፤ የገደሉትን ይግደሉ፤ እስር ቤቱን፤ መኖሪያ ቤቱን፤መንደሩን፤ ገበያውን፤ ድልድዩን ወዘተ ያውድሙት፤ የአፈኑትን ያፍኑ፤ ከዚህ የባሰ ምንም ሊመጣ አይችልም እያለ ሕዝባዊ እምቢተኛነቱን ሲያስተጋባ ማየት ታሪክ ሲፈጠርና ሲሰራ እንደማየት ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ የትምህርት ተቋሞች አይንቀሳቀሱም። አስተማሪዎች ሕዝብ እያለቀ ለምን በዚህ ጉዳይ አንነጋገርም እያሉ ነው። አንድ አስተማሪ መሰለኝ እንዲህ ብሏል። “እኔ ከአሁን በኋላ በፍርሃት ዓለም አልኖርም።” የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያካሂደው ትግል አስደናቂና ታሪክን ፈጣሪ ሆኗል። በራሱ ጥበብ፤ በራሱ መሪዎች፤ በራሱ መደጋገፍ። የጎንደር ሕዝብ እቀባ አድርጎ ከራሱ ምግብ ተካፍሎ የሌላቸውን ይመግባል። ይህ ነው ታሪክ ፈጣሪ! ይህ ነው ሕዝብ አፍቃሪ! ይህ ነው ከስግብግብነት ይልቅ፤ ርህራሄ፤ ሰብእነት፤ ፍቅር፤ መንፈሳዊነት የሚገዛው ሕዝብ። ለዚህ ነው ትግሉ ችግሩን ተቋቁሞ አሁንም የቀጠለው፤ ማንም አያቆመውም።
በውጭ ለምንኖር ትውልደ ኢትዮጵያ ከዚህ የበለጠ ቆራጥነት፤ ጀግንነት፤ ደፋርነት፤ አገር ወዳድነት ወዘተርፈ ሊመጣልን አይችልም። ሕዝቡ ፍርሃትን ሰብሮና ቀብሮ ጨካኝነትን ለመቋቋም መነሳቱን በተከታታይ አሳይቶናል። እ. አ. አ. ከSeptember 19, 2016, ጀምሮ የጎንደርና የጎጃም ሕዝብ ተመካክሮና ተባብሮ የኢኮኖሚ እቀባውን በቤቱ እየዋለ መቀጠሉ አስደናቂ ነው። ይህ መተባበርን፤ መቀነትን ሆነ ቀበቶን ጠበቅ ማድረግን፤ ቆራጥነትን፤ መተሳሰብን ይጠይቃል።
ነጋዴው፤ የቤት ባለቤቱ፤ የመንግሥት እና የቀን ሰራተኛው፤ አስተማሪው፤ ተማሪው፤ ገበሬውና ሌላው ተባብሮ ይህን እቀባ ማድረጉ ለኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ነጻነትና ፍትህ ለሚፈልጉ ሕዝቦች ሁሉ ከፍተኛ ትምህርት ነው እላለሁ። እኛ የማናደርገውን ተራው፤ ድሃው የኢትዮጵያ ሕዝብ እያደረገው ነው።
ለምን? ብለን ራሳችን እንጠይቅ። ህወሓቶች በበላይነት የሚያሽከረክሩት ስርዓት ከሁሉም በላይ ጨካኝ፤ ለሰው ህይወት ምንም ርህራሄ እንደሌለው በየቦታው እያየን ነው። በኮንሶ የሆነው ለህሊና የሚቀፍ ነው፤ መንግሥት የሚባል ነገር እንደሌለ ያሳያል። እ. ኣ.አ. ከSeptember 5-September 19, 2016 ድረስ ቢያንስ “30 ንጹህኢትዮጵያዊያን ተረሽነዋል፤ ከ 1,500 በላይ የሚገመቱ ቤቶች ተቃጥለዋል።”  በጎንደር ከተማ እኔ በልጅነቴ የማስታውሰው በኢትዮጵያ ታሪክ ያለው ገበያ ተቃጥሏል። በትላንቱ እለት ህወሓቶች ያልተቃጠለውን ሙሉ በሙሉ ለማቃጠል የትግራይ ተወላጆችን፤ አንዲት ሴት ጨምረው ልከው ለማቃጠል ሲዘጋጁ ሕዝቡ ጠቁሞ የከተማው ፖሊሶች ያዟቸው። የተረፈውን ማቃጠል የቂም በቀል ተልእኮ ነው። ህወሓት የዚህን ያክል ጨካኝና ወራዳ መሆኑ ነው።
በደብረ ታቦር፤ በጎንደር፤ በባህር ዳር፤ በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች እስር ቤቶች ተቃጥለዋል። የፖለቲካ እስረኞች ከቃጠሎው ለማምለጥ ሙከራ ሲያደርጉ የህወሓቶች አልሞ ተኳሾች ሰለባ ሆነዋል። መረጃዎች እንደሚሉት ከሆነ በቅሊንጦ ከታሰሩት መካከል ብዙዎቹ በወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ ምክንያት የፖለቲካ እስረኞች ሆነው በዚህ እስር ቤት ህይወታቸው ያለፈው ብዙ እንደሆነ ይነገራል። ይህ የሚያሳየው ሆነ ተብሎ የአማራውን ወጣት ትውልድ ለማጥፋት የተደረገ፤ የተቀነባበረ ስራና ሴራ መሆኑን ጭምር ነው።
በዐማራው ክልል በተከታታይ የሚታየው ስእል አንድና አንድ ብቻ ነው። ይኼውም፤ ህወሓቶችና የእነሱን ድርጊት ፈጻሚና አስፈጻሚ የሆኑ ግለሰቦችና ቡድኖች በወገኖቻቸው ላይ ወንጀል ለመፈጸም ወደ ኋላ የማይሉ መሆናቸውን ነው። ከአንድ ቤት ወደ ሌላ እየሄዱ ወጣቶች ሲያፍኑ ቆይተዋል። በባህር ዳር እና አካባቢ ብቻ “ከ 11,000” በላይ የሚገመቱ የዐማራ ወጣቶች የት እንደተወሰዱ፤ ምን አደጋ እንደደረሰባቸው አይታወቅም። ሞቱ? አካላቸው ስንኩል/ሽባ እንዲሆን ተደረጉ? በጫካና በሸለቆ ተወረወሩ፤ ተቀበሩ? መርፌ ተወግተው ወይንም ለህይወታቸው፤ ለጭንቅላታቸው አደንዝዝ መድሃኔት ተሰጣቸው? የሚሉ አግባብ ያላቸው ጥያቄዎች እየተነሱ ነው። ቁም ነገሩ፤ የዐማራው ብሄር ተተኪ መሪዎች፤ ተተኪ ባለሞያዎች፤ ተተኪ ተቆርቋሪዎች እንዳይኖሩት እየተደረገ ነው።
ህወሓቶች/ኢህአዴጎች በወንጀል እንዳይከሰሱ ሁሉንም መረጃ ይደመስሳሉ፤ መገናኛ ብዙሃን እንዳይኖር ያደርጋሉ። በአካባቢው የሚኖረው የተማረ ግለሰብ፤ ቤተሰብ፤ ስብስብ ማድረግ ያለበት መረጃውን መሰብሰብና መደበቅ፤ ውጭ ለሚኖሩ ተቆርቋሪዎች ማስተላለፍ ነው። ይህን በሚመለከት በቅርቡ በሕዝብ ጥረት፤ ወጣቷ የወልቃይት ጠገዴ ዐማራ፤ ንግሥት ይርጋ የምትሰራውን ጀግንነት እና የደረሰባትን አፈናና ጭካኔ ይፋ መደረጉ በጣም ጠቃሚ መረጃ ነው። ይህች ወጣት እናትሰቃይ፤ እንዳትገደል አቤቱታ ማቅረብ አለብን። የሞቱትንና እንዲሰወሩ የተደረጉትን ወጣቶች ስም ዝርዝር መሰብሰብ አስፈላጊ ነው። የተባበሩት መንግሥታት ህግ አንድ መንግሥት ወይንም የዚህ መንግሥት ተጠሪ የሆነ ግለሰብ ወይንም ቡድን ግለሰቦችን አስገድዶ መሰወር ሕገ ወጥ መሆኑንና በሕግ የሚያስጠይቅ ወንጀል መሆኑን አስምሮበታል (Enforced disappearances are crimes against humanity). በተመሳሳይ በቅሊንጦ ከተረሸኑት መካከል ጀግናው ሻለቃ ይላቅ አሸናፊ ይገኝበታል፤ የሌሎቹን ስም ዝርዝር መሰብሰብ ወሳኝ ነው።
የዐማራው ሕዝብ እልቂት ዛሬ የተጀመረ ባይሆንም አሁን ያለው አደጋ የመኖር/ አለመኖር፤ ማለትም የህልውና አደጋመሆኑን መቀበል ግዴታችን ነው። ህወሓቶች በብዛት የሚጠቀሙበት የዐማራ ሕዝብ እልቂት ዘዴ አስገድዶ መሰወር ነው(enforced disappearances). ይህ የሆነበት ምክንያት የተሰወረ በምንም አይገኝም በሚል የተሳሳተ ስሌት ነው።
ህወሓቶች፤ በተለይ የህወሓት መስራቾች፤ “ዐማራውን አህያ” ከማለት ደረጃ የደረሱብት የራሳችን ድክመት፤ ዝምታ ማብዛትና በጥቃቅን ነገሮች ለመተባበር አለመቻል ጭምር ነው። አሁንም፤ ብዙ የዐማራ ምሁራንና ባለሞያዎች ከዳር ቆመው ያያሉ፤ ምን እንደሚጠብቁ ምርምር ቢደረግ መልካም ነው። ለአሁኑ ግን እያንዳንዳችን ራሳችን መፈተሽ አለብን  እላለሁ። የህወሓቶች ኤታ ማጆር ሹም ጀኔራል ሳሞራ ዩኑስ ለትግራይ ሕዝብ ንግግር ሲያቀርብ እንዲህ ብሏል። “ህወሓት ማለት መስመር ነው! ህወሓት ከሌለ የትግራይ ሕዝብ የለም!” ይህ ብሂል የትግራይን ሕዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መለየት መሆኑን ማሳሰብ ያለበት የትግራይ ምሁርና ሕዝብ ነው። በዚህ ሃተታ ለማሳሰብ የምፈልገው የዐማራው ሕዝብ ከሌለ፤ የኦሮሞው ሕዝብ ከሌለ ኢትዮጵያ የምትባል አገር አትኖርም ነው። እኔ እስከማውቀው ድረስ የአማራውና የኦሮሞው ሕዝብ በወንድሞቹ፤ በእህቶቹ በትግራይ ሕዝብ ላይ አልተነሳም፤ አይነሳም፤ መነሳትም የለበትም። የሰላማዊ ሕዝብ እምቢተኛነት ኢላማ የህወሓት ጭካኔና አፋኝነት እንጅ የትግራይ ሕዝብ አለመሆኑን አምናለሁ።
ቢቻል ኖሮ፤ ህወሓቶች የጣናን ኃይቅ፤ የአባይን ወንዝ ወደ ትግራይ እንደሚወስዱ መረጃዎች ብዙ ናቸው። አንድ የውጭ አገር ቱሪስት ጎንደር ከተማ ሆቴል አርፎ ምን ልታይ መጣህ? ተብሎ ሲጠየቅ ቤተ ክርስቲያኖችን፤ የፋሲልን ግንብና “በትግራይ ክልል የሚገኘውን የዳሸን ተራራ” ብሎ ይመልሳል። ይህ የጎንደር አንጡራ ኃብት የሆነ ተራራ ወደ ትግራይ መጠቃለሉን የማያውቅ ወጣት ገርሞት ተራራው እኮ በጎንደር እንጅ በትግራይ አይደለም ሲል “እኔ የተነገረኝ ትግራይ ውስጥ መሆኑን ነው” ሲል ተናግሯል። “ተራራውም ይሰረቃል” የሚለው ብሂል የመጣው ከዚህ ነው። የላሊበላ ገዳማት ተነጥቀው ወደ ትግራይ ተላልፈዋል፤ ነገ የፋሲለደስ ግንብ፤ በደብረ ታቦት የኢየሱስ ተራራና ቤተክርስትያን ትግሬ ነው ቢባል ምን ያስደንቃል። ወይ ጉድ! እንዴት ጎንደሬውን፤ እንዴት አማራውን ቢንቁት ነው ተራራ የሚነጥቁት የሚሉ ብዙ ናቸው። የራስ ዳሸን “ትግራይነት” የችግሩን ክብደት ያጠናክረዋል። የሰው ዜግነት መከበር ከተፈጥሮ ኃብት ባለቤትነት ተለይቶ ሊታይ አይችልም። ይህ በምንም አይነት ማባበል ሊፈታ አይችልም።
በባህር ዳር ከተማ እነ በረከት ሰምኦን፤ አዲሱ ለገሰና ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ መኮነን ሕዝቡን ለማባበል ያደረጉት ሙከራ በጎንደር ከተደረገው የተለየ አይደለም። ህወሓቶችና ታዛዦቻቸው ወጣቱን እየገደሉ ግድያው እንዲቆም የራሳቸውን የበላይ አዛዥ ህወሓትንና በዐማራው ሕዝብ ላይ “ማንኛውንም እርምጃ ሊወሰድ ይችላል” ብሎ ትእዛዝ የሰጠውን ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝን “ይህ ትእዛዝ በአስቸኳይ ይነሳ” በማለት ፋንታ ተጠቂውን የዐማራ ሕዝብ ማነጋገራቸው ለዐማራው ሕዝብ ያላቸውን ንቀት ያሳያል። በአምባ ጊዎርጊስ የተረሸኑት ወጣቶች ብቻ ከፍተኛ ዋጋ እንዳላቸው ምንም አልተረዱትም፡፡ በእነሱ ግምት የትግሬዎች ኃብት መቃጠል ከህይወት በላይ ሆኗል ማለት ነው። አስደናቂው ቁም ነገር ግን ይህ አይደለም። ከወረዳ ጀምሮ እስከ ክፍለ ሃገር ድረስ የብአዴን አባላት፤ ዝቅተኛና መካከለኛ ኃላፊዎች “ወንበራችሁን አንፈልግም፤ ተረከቡን” ማለታቸው ነው። ብአዴኖች፤ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩን ጨምሮ በታሪክ ተጠያቂ እንዳይሆኑ ከፈለጉ የሕዝቡን ትግል ሙሉ በሙሉ መደገፍ ግዴታቸው ነው። ወገኖቻቸው እንዲገደሉ አጋር መሆን ከወንጀለኛነት አያድናቸውም፤ ተባባሪ ናቸውና። የዩንቨርስቲ አስተማሪዎች የተለመደውን የህሓት ግምገማ እንዲያዳምጡ ተጠርተው ምንም ድምጽ አንሰጥም ብለዋል። አንድ ተማሪ እንዲህ ብሏል። “እኔ ፈርቸ ፈርቸ ፍርሃቴ ለቆያኛል፤ ለምን አሁን ስላለው እልቂት፤ ስላለው ሁኔታ አንወያይም?” የሚል ጥያቄ አቅርቧል፤ ሁሉም የሚፈልገው ጥያቄ። በተደጋጋሚ እንዳሳሰብኩት የዐማራው ወጣት ትውልድ እየታፈነ፤ እየተገደለ፤ እየቆሰለ፤ እየተራበ ነው። አስተማሪው፤ ተማሪው፤ ሰራተኛው በአንድ ላይ፤ ለአንድ ዐላማ መነሳትና መታገል አለበት።
በሕዝቡ ዐመጽ ያልተሰበሰበው ህሊናውን መጠየቅ አለበት። ሆዱ ከጎንደሬው ሆድ፤ ከኦሮሞው ሆድ፤ ከኮንሶው ሆድ የተለየ አይደለም። ለአንድ ህይወት ከመሳሳት ለፍትህ፤ ለነጻነት፤ ለእኩልነት፤ ለዲሞክራሲ ራስን መስ ዋእት ለማድረግ መነሳት ይመረጣል። ታሪክ ስሩ። ምክንያቱም፤ ተራው የጎንደር፤ የባህር ዳር፤ የደብረ ታቦር፤ የኮንሶ፤ የአዋሳ ወዘተርፈ ሕዝብ “ከአሁን በኋላ በህወሓት/ኢህአዴግ አንገዛም” እያለ ነው። ታሪክ እንስራ፤ ሕዝቡን እንደግፍ። ተቃውሞን በዝምታ፤ ተቃውሞን በእገባ፤ ወዘተ ሲያሳዩ ችግሩ ስር የሰደደ እና ህወሓት/ኢህአዴግ ሊፈታው ከማይችልበት ደራጃ መድረሱን ያሳያል። ግምገማ የሚባለው ዘዴ “እኔን እመኑኝ” ከማለቱ ሌላ የሕዝቡን መሰረታዊ ችግር አይፈታም። የዝግ ችሎት አድርጎ ራሱን መገምገም ያለበት አፋኙ አገዛዝ ነው። ይህን አያደርግም።
ለመደምደም፤
በዐማራው ሕዝብ ላይ የብሄር ማጽዳትና እልቂት የሚካሄድ መሆኑን የሚያሳይ በውጭ አገር ባለሞያ ዶኪመንተሪ ቀርቧል፤ ወደፊትም እንደሚቀርብ ይገመታል። በጉዳዩ ክብደትና ስፋት መሰረት በሙሉቀን ተስፋ መጽሃፍ ተጽፎ በአዲስ አበባ እንዳይበተን ተከልክሏል። የተከለከለበት ምክንያት ሕዝቡ ሃቁን እንዳያውቀው ነው። ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማሪያም ይህን እልቂት አያውቅም የሚል ግምት የለኝም፤ ያውቃል። ይህን ጭካኔ እያወቀ ለህወሓቶች ደህንነትና ሰራዊት “የግድያ ፈቃድ” መስጠቱ ስርዓቱ በጠቅላላ ለሰው ህይወት ደንታ እንደሌለው በተደጋጋሚ ያሳያል። የህወሓት የስለላና የመከላከያ ኃይል 30 ሚሊየን የዐማራ ሕዝብ ለመቆጣጠር እንችላለን፤ “እንኳን ለዚህ ሕዝብ ለአፍሪካም የሚመጥን ኃይል አለን” ብለው ፎክረዋል። ጥናቶች የሚያሳዩት ማንም ኃላፊነት የሚሰማው አመራር በራሱ ሕዝብ ላይ ጦርነት እንደማያውጅ ነው፤ ከወሰደ ህይወቱ አጭር እንደሚሆን ነው።  ነገ ከትግራይ ውጭ የሕዝቡ እምቢተኛነት አገር አቀፍ ቢሆን ሕዝቡን በጀትና በሄሊኮፕተር፤ በታንክና በሌላ መሳሪያ ሊጨፈጭፉት ነው?
ምን ይደረግ?
“አንድነት ኃይል ነው” ብለን እንነሳ!
“አንድ ሰው ሲገደል የሁሉም ኢትዮጵያዊያን መገደል ነው” እያልን እናስተጋባ!
“አዲስ ዓመት ምንም አዲስ አይደለም” ለማለት እንድፈር
“ተራው ገዳይና ተራው ሟች ወንድማማቾች ናቸው! ተጠያቂው ህወሓት ነው! ለማለት እንድፈር
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር! ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን መብትና እኩልነት አብረን እንስራ!

No comments:

Post a Comment