Translate

Saturday, February 28, 2015

ኢህአዴግ 98ቢሊዮን ብር ነጠፈበት!!

“ታላቅ ሥራ ተሰርቷል! እናመሰግናለን!” ኦባንግ

anuak-woman-abobo
 
ኢህአዴግ በዓለም ባንክ በኩል ከእንግሊዝ የዓለምአቀፍ ልማት ተራድዖ መ/ቤት ሊለግስለት ታቅዶ የነበረው 4.9 ቢሊዮን ዶላር (98ቢሊዮን ብር) የገንዘብ ድጋፍ ነጠፈበት፡፡ አቶ ሬድዋን አልነጠፈብንም ይላሉ፡፡ ኦባንግ ሜቶ በበኩላቸው “የታላቅ ሥራ ውጤት ነው፤ እናመሰግናለን” ብለዋል፡፡
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ጥቅምት 2፤2005 (October 12, 2012) “ኢህአዴግ በ600 ሚሊዮን ዶላር አጣብቂኝ ውስጥ ገባ!! ብያኔው ከጸና ኪሣራው በቢሊዮን ዶላር ሊደርስም ይችላል!” በሚል ርዕስ የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ያካሂድ ስለነበረው ፕሮግራም በዘገበበት ወቅት የሚከተለውን ዜና አትሞ ነበር፡- “ከ1998ዓም ጀምሮ የመሠረታዊ አገልግሎት ጥበቃ ፕሮግራም (Protection of Basic Services “PBS Program”) በሚል በአራት ተከታታይና ሁለት ተጨማሪ የገንዘብ ድጎማ የሚደረግባቸውን ፕሮግራሞች የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡ ይህ መሠረታዊ የሆኑ አገልግሎቶችን ለማሟላት ተወጥኖ የሚካሄድ ፕሮጀክት በትምህርት፣ በጤና፣ በእርሻ፣ በንጹህ ውሃ አቅርቦት፣ በገጠር መንገድ ሥራ፣ ወዘተ መስኮች ላይ እንዲውል (PBS I, PBS I-AF (Additional Financing), PBS II, PBS 11-AF, PBS-Social Accountability Program and PBS III) በማለት በተለያዩ ደረጃዎች ለተከፋፈለው ኦፐሬሽን ማስፈጸሚያ የሚውለው ገንዘብ ከ13ቢሊዮን ዶላር የሚበልጥ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ከፍተኛው የዓለም ባንክ ድርሻ 2ቢሊዮን ዶላር ሲሆን የተቀረው በሌሎች ለጋሽ መንግሥታት እና ድርጅቶች የሚሸፈን ነው፡፡ PBS III የተሰኘውን በሦስት ንዑሳን ፕሮግራሞች የተከፋፈለውን ፕሮጀክት ለማስፈጸም በአጠቃላይ የሚፈጀው 6.3ቢሊዮን ዶላር በላይ ነው፡፡”
ይህ ለመሠረታዊ ልማት እንዲውል በዓለም ባንክ በኩል የሚሰጠውን ገንዘብ የሚደጉሙት ምዕራባውያን አገራት ሲሆኑ አንዷ ተጠቃሽ አገር እንግሊዝ ናት፡፡ ሆኖም ኢህአዴግ ከምዕራባውያን በዓለም ባንክ በኩል የሚያገኘውን ገንዘብ ለራሱ የፖለቲካ መጠቀሚያነት እያዋለው መሆኑ ለዓለም ባንክ ተደጋጋሚ መረጃዎች ሲቀርቡ ቆይተዋል፡፡ በተለይ ሟቹ መለስ በቀጥታ በሰጡት ትዕዛዝ 424 የአኙዋክ ተወላጆች ከተገደሉ በኋላ ኢህአዴግ በቦታው ያሰማራው የመከላከያ ሠራዊት በሥፍራው የሚኖሩትን ከመኖሪያ ቀያቸው በማፈናቀል እምቢ ያሉትን በግድ በማስነሳት፣ በመግደል፣ አስገድዶ በመድፈር፣ በማሰቃየት፣ ወዘተ ግፍ ሲፈጽም መቆየቱ በተለያዩ ዓለምአቀፋዊ ዕውቅና ባገኙ ዘገባዎች ሲነገር ቆይቷል፡፡ የዓለም ባንክ ለመሠረታዊ ልማት በማለት የሚሰጠው ገንዘብ ኢህአዴግ ወታደሮቹን የግፍ ሥራ ላይ በማሰማራት ደመወዝ የሚከፍልበት መሆኑን በመጥቀስ ወደ ኬኒያ የተሰደዱ የክልሉ ነዋሪዎች አቤቱታ አቅርበው እንደነበር ጎልጉል በወቅቱ የዘገበው ዜና ነበር፡፡ ““ኢህአዴግ አንገቱን ታንቋል”፤ዓለም ባንክ ርምጃ ለመውሰድ ጫፍ ደርሷል” በሚል ርዕስ የተጻፈውን ዜና ለማንበት እዚህ ላይ ይጫኑ፡፡
money lostከዚሁ ጋር በተያያዘ “ሚስተር ኦ” በመባል የሚጠሩት አኙዋክ ተወላጅ ኢህአዴግ የዕርዳታ ገንዘብ ለሰብዓዊ መብት ረገጣና ለራሱ የፖለቲካ መጠቀሚያነት እንዳዋለው በመጥቀስ የእንግሊዝ መንግሥት ከግብር ከፋይ ዜጎቹ የሚያገኘውን ገንዘብ አምባገነንነት እየደገፈበት መሆኑን በተለይም የዓለምአቀፍ ልማት ተራድዖ መ/ቤቱ ተጠያቂ ስለሆነ ከዚህ እንዲታቀብ ክስ መመሥረታቸው ይታወቃል፡፡ የክሱ ሒደት እየተካሄደ ባለበት ባሁኑ ወቅት ሚስተር ኦ በተደጋሚ እንደመሰከሩት ኢህአዴግ ነዋሪዎችን በግዳጅ ከቀያቸው በማፈናቀል የሚያካሂደው የግዳጅ ሰፈራና የመንደር ምሥረታ ሕገወጥ መሆኑ በመቃወማቸው በተደጋጋሚ ከፍተኛ ድብደባ እንደረሰባቸው ተናግረዋል፡፡ ብዙዎች ለአካላዊ ሥቃይ ደርሶባቸዋል፣ ሴቶች ክብረንጽህናቸው ተደፍሯል፣ አዛውንትና ህጻናት ለአሰቃቂ መከራ ተዳርገዋል፤ ይህንንም እርሳቸው እንዳዩ ሚስተር ኦ ይመሰክራሉ፡፡
የሚስተር ኦ የፍርድቤት ጉዳይ ወደ ውሳኔ ሊደርስ ባለበት ወቅት የልማት መ/ቤቱ ይህንን ዓይነት ውሳኔ መውሰዱ ከፍርድ ቤቱ ጉዳይ ጋር የሚያያዝ እንደሆነ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ይናገራሉ፡፡ የልማት ተራድዖ መ/ቤቱ ቃል አቀባይ ግን የመ/ቤታቸው ውሳኔ ከሚስተር ኦ የፍርድቤት ጉዳይ ጋር ያልተያያዘ እንደሆነ መናገራቸውን የእንግሊዙ ዘጋርዲያን ጋዜጣ ዘግቧል፡፡ መ/ቤቱ ለዚህ ውሳኔ የደረሰው ኢትዮጵያ “የዕድገት ስኬት” እያስመዘገበች በመምጣቷ የመሠረታዊ ልማት አገልግሎት የገንዘብ ዕርዳታ የማያስፈልጋት በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡
ይህ መጠኑ እጅግ ከፍተኛ የተባለውና ለኢህአዴግ ንጹህ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ የሚያስገኝ ገንዘብ እንደነጠፈበት መሰማቱን አስመልክቶ ጋዜጣው የኢህአዴግ ፅ/ቤት ሃላፊ የሆኑትን ሬድዋን ሁሴን በጠየቃቸው ወቅት የመለሱት አልነጠፈብንም የሚል እንድምታ ያለው ነው፡፡ “እነርሱ ያሉት ዕርዳታውን አንሰጥም ወይም እናቆማለን ሳይሆን ዕርዳታ አሰጣጡ እንደገና ይዋቀራል ነው” በማለት ሬድዋን ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ ሆኖም 4.9 ቢሊዮን ዶላር (98ቢሊዮን ብር) ዕርዳታ ለመስጠት ከዓለምባንክ ጋር ስምምነት የነበረው የእንግሊዝ የልማት ተራድዖ መ/ቤት “ኢትዮጵያ አድጋለች” በማለት በ2015/2016 በፓውንድ 256ሚሊዮን ብቻ (5በመቶ) ዕርዳታ ለመስጠት መወሰኑን የኢህአዴግ ጽ/ቤት ሃላፊው ሬድዋን ሁሴን አላብራሩም፡፡
ኢህአዴግ ለዕርዳታ የሚሰጠውን ገንዘብ ዜጎችን ለማሰቃየት፣ ወታደር ለመቀለብ፣ ወዘተ እንደሚጠቀምበት በተደጋጋሚ ዘገባዎች እና ማስረጃዎች ሲወጡበት የከረመ ቢሆንም ማስረጃዎቹን ተከትሎ የዓለም ባንክ በዕርዳታ አሠጣጡ ላይ አንዳች ውሳኔ እንዳያደርግ ብዙ ሲደክም ቆይቷል፡፡ በዚህም ምክንያት ጉዳዩ ውሳኔ ሳይሰጥበት እንዲስተጓጎል በማድረግ ለሁለት ዓመታት ያህል እንዲጓተት ማድረጉን ከጉዳዩ ጋር ቅርበት ያላቸው ወገኖች ይመሰክራሉ፡፡
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ኦባንግ ሜቶ ጉዳዩን ገና ከጅምሩ የሚያውቁትና ድርጅታቸው ለዓመታት ሲሰራበት የነበረ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በመሆኑንም ይህንን የእንግሊዝ የልማት ተራድዖ መ/ቤት ውሳኔ የጋራ ንቅናቄያቸው ከደጋፊዎቹ ጋር በመሆን ያገኘው ድል እንደሆነ በፌስቡክ ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት አስታውቀዋል፡፡ “ገና ከጅምሩ ከጋራ ንቅናቄያችን ጋር በመሆን ይህንን ሥራ በመደገፍ የተባበራችሁንን ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እወዳለሁ፤ ታላቅ ሥራ ተሰርቷል፤ እናመሰግናለን” ብለዋል “ጥቁሩ ሰው” ኦባንግ ሜቶ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ አቶ ኦባንግ በተለይ ከጎልጉል ለቀረበላቸው አጭር ጥያቄ በሰጡት አስተያየት የጋራ ንቅናቄያቸው ደስታውን የገለጸው የልማት ገንዘብ በመቋረጡ ሳይሆን በልማት ስም የሚሰጠው ዕርዳታ ለሰብዓዊ መብት ረገጣ በመዋሉና ለዚህም ደግሞ ከበቂ በላይ ማስረጃ ድርጅታቸው ያለው በመሆኑ ነው፡፡ “አገር ብትለማ የሁሉም ደስታ ነው” ያሉት ኦባንግ አገርን በማልማት ሽፋን ደጋፊና ተቆርቋሪ የሌላቸውን ንጹሃን መበደልና የመኖር መብታቸውን መንፈግ ግን በየትኛውም መልኩ እርሳቸውም ሆነ አኢጋን የሚቀበለው እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡
ኢህአዴግ በቅርቡ አካሂዳለው ለሚለው ምርጫ እንደ ዕቁብ ዕጣ በማውጣትና በማስወጣት “አልደረሳችሁም” እያለ የተቀናቃኝ ፓርቲ አመራሮችን ከምርጫ እያስወገደ ባለበት፤ ሌሎችንም ሕጋዊ አይደላችሁም እያለ በተለጣፊ ድርጅት በማስበት ኅልውናቸውን እያሳጣ ባለበት ባሁኑ ወቅት በዜጎቹ ላይ የሚያካሂደውን መረን የለቀቀ የመብት ገፈፋ ለሥልጣን ያበቁትን ምዕራባውያንን ያስደሰተ እንዳልሆነ ይነገራል፡፡ የአውሮጳ ኅብረት ምርጫውን አልታዘብም ከማለቱ በተጨማሪ በሚዲያ ላይ የተጫነው አፈና በዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብት ድርጅት ይፋ ከሆነ ወዲህ ማነቆው በኢህአዴግ ላይ እየከረረ መምጣቱን ያሳያል፡፡ ኢህአዴግን ለሥልጣን ከማብቃት አልፋ ነፍጥ አንጋቢዎቹን የህወሃት መሪዎች ጸጉርና ጺም ከርክማ፤ ልብስ አልብሳ፤ ቋንቋ አስተምራ፤ የከተማ አኗኗር እንዴት እንደሆነ አሠልጥና፣ ቶሎ ባይገባቸውም ፕሮቶኮል አስተምራ፣ እስካሁንም ተንከባክባ እዚህ ድረስ ያቆየቻቸው እንግሊዝ እንዲህ ያለውን የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ስታደርቅ “ቀጣዩስ ምን ይሆን?” የሚል ጥያቄ እንዲነሳ አድርጓል፡፡ “ምዕራባውያን መግደልም ማንሳትም ያውቁበታል” በማለት አስተያየት የሚሰጡ ወገኖች እንደሚሉት ቀጣዩ የኢህአዴግ ጉዞ በከፍተኛ ሁኔታ ለህወሃት ሲቀጥል ለኢህአዴግ አስጊ ከመሆን ባሻገር በውጭ ምንዛሪ እጥረት በየጊዜው የሚፈጠረውን ግሽበት በዕርዳታ ገንዘብ የሚያስተካክለው ኢህአዴግ እንዲህ ያለው የገንዘብ ማዕቀብ ክፉኛ ያነጥፈዋል ሲሉ ግምታቸውን ይሰጣሉ፡፡ ሙስናው መረን በለቀቀባት አገር ከሕዝብ እየተዘረፈ በተለያዩ አገራት ባንኮች በውጭ ምንዛሪ የሚከማቸውን ገንዘብ በሚካፈሉትም ላይ የድርሻ ቅነሳ የማስከተሉ ጉዳይ አብሮ የሚታይ እንደሆነ ይነገራል፡፡
ከዚህ ዜና ጋር ተያያዥነት ያለውን ጥቅምት 2፤2005 (October 12, 2012) ያተምነውን ዜና ከዚህ በታች እንደሚከተለው እንደገና አትመነዋል፡፡

ኢህአዴግ በ600 ሚሊዮን ዶላር አጣብቂኝ ውስጥ ገባ!!

ብያኔው ከጸና ኪሣራው በቢሊዮን ዶላር ሊደርስም ይችላል!

ኢህአዴግ ከዓለም ባንክ ያገኘውን 600 ሚሊዮን ዶላርና በተመሳሳይ ፕሮጀክት ወደፊት ሊያገኝ የሚችለውን ከፍተኛ ገንዘብ በተመለከተ አደጋ ውስጥ መውደቁ ተሰማ። ኢንስፔክሽን ፓናል (Inspection Panel – IP) የተሰኘ ተቋም ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው ኢህአዴግ የቀረበበት ውንጀላ ከተረጋገጠ የሚያጣው ገንዘብ በቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ታውቋል። ይፋ የሆነውን መረጃ አስመልክቶ ከኢህአዴግ ወገን እስካሁን በይፋ የተሰጠ ምላሽ የለም።
ግፍ የሚፈጽሙ መንግስታትን፣ በልማት ስም የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈጽሙ ወንጀሎችን መረጃዎችን በስፍራው በመገኘትና ከመሠረቱ ዘልቆ በመግባት አደራጅቶ ተጠያቂ የሚያደርገው ኢንክሉሲቭ ዴቨሎፕመንት ኢንተርናሽናል Inclusive Development International (IDI) ከሰለባዎቹ ውክልና ተሰጥቶታል። ተቋሙም በውክልናው መሰረት ለኢንስፔክሽን ፓናል በዝርዝር የሰለባዎቹን በደል በማተት አሳውቋል።
የኢህአዴግ መከላከያ ሠራዊት የሚያደርሰውን እስራት፣ ግርፋት፣ አስገድዶ መድፈር፣ ከመኖሪያ ቦታ ማፈናቀል፣ የግዳጅ ሰፈራ ወዘተ በማምለጥ ወደ ኬንያ የተሰደዱ የጋምቤላ ነዋሪዎች ይህ ሁሉ ግፍ የሚፈጽምባቸው የኢትዮጵያ መንግሥት በልማት ስም ከዓለም ባንክ በሚያገኘው የዕርዳታ ገንዘብ በመሆኑ ለባንኩ በላኩት የአቤቱታ ደብዳቤ አመልክተዋል።
አቤቱታውን መሠረት በማድረግ የሚደረገው ምርመራ ውጤት ይፋ ሲሆን፣ በሌሎች አገሮች እንደተደረገው በዕርዳታ ስም የሚገኝን ገንዘብ ኢህአዴግ ለፖለቲካ ተግባር መጠቀሙ ሲረጋገጥ፣ በመስከረም ወር መጀመሪያ አካባቢ ከዓለም ባንክ ተፈቅዶ የነበረው 600ሚሊዮን ዶላር ሊከለከል ይችላል፡፡
የዛሬ ዘጠኝ ዓመት አካባቢ በሟቹ ጠ/ሚ/ርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ መለስ ዜናዊ ቀጥተኛ ትዕዛዝ በጋምቤላ ክልል በተለይ የተማሩ ወንዶች ላይ በማተኮር 424 ንጹሐን የአኙዋክ ተወላጆች በተገደሉበት ወቅት በሺዎች የሚቆጠሩት ወደ ጎረቤት አገር ኬንያ መሰደዳቸው ይታወሳል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ክልሉ ሰላም የለም፡፡ በየጊዜውም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሲካሄዱበት ቆይቷል፡፡ በተለይም ለም የሆነውን እጅግ ሰፋፊ መሬት ለውጪ ባለሃብቶች በሳንቲም በመሸጥ ላይ የሚገኘው የኢህአዴግ አገዛዝ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቀድሞው የደርግ ዘመን ሲካሄድ ከነበረው ባለፈ መልኩ እጅግ በሚያሰቅቅ ሁኔታ በመንደር ምስረታና አስገድዶ የማስፈር ፖሊሲ ከመኖሪያ ቀዬ የማፈናቀል ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የኦክላንድ ተቋም፣ ሂውማን ራይትስ ዎች፣ … የመሳሰሉ ድርጅቶች ያወጧቸው ዘገባዎች ይጠቁማሉ፡፡
ከ1998ዓም ጀምሮ የመሠረታዊ አገልግሎት ጥበቃ ፕሮግራም (Protection of Basic Services “PBS Program”) በሚል በአራት ተከታታይና ሁለት ተጨማሪ የገንዘብ ድጎማ የሚደረግባቸውን ፕሮግራሞች የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡ ይህ መሠረታዊ የሆኑ አገልግሎቶችን ለማሟላት ተወጥኖ የሚካሄድ ፕሮጀክት በትምህርት፣ በጤና፣ በእርሻ፣ በንጹህ ውሃ አቅርቦት፣ በገጠር መንገድ ሥራ፣ ወዘተ መስኮች ላይ እንዲውል (PBS I, PBS I-AF (Additional Financing), PBS II, PBS 11-AF, PBS-Social Accountability Program and PBS III) በማለት በተለያዩ ደረጃዎች ለተከፋፈለው ኦፐሬሽን ማስፈጸሚያ የሚውለው ገንዘብ ከ13ቢሊዮን ዶላር የሚበልጥ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ከፍተኛው የዓለም ባንክ ድርሻ 2ቢሊዮን ዶላር ሲሆን የተቀረው በሌሎች ለጋሽ መንግሥታት እና ድርጅቶች የሚሸፈን ነው፡፡ PBS III የተሰኘውን በሦስት ንዑሳን ፕሮግራሞች የተከፋፈለውን ፕሮጀክት ለማስፈጸም በአጠቃላይ የሚፈጀው 6.3ቢሊዮን ዶላር በላይ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ የባንኩ ድርሻ የሆነውን 600ሚሊዮን ዶላር ቦርዱ መስከረም 5ቀን 2005ዓም አጽድቋል፡፡
በአስገድዶ ማስፈር፣ መንደር ምስረታና ሌሎች በርካታ የሰብዓዊ መብቶቻቸው የተጣሱባቸው በኬንያ የሚገኙ ሦስት የአኙዋክ ስደተኞች ተወካይ ድርጅቶች በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙ ሌሎች የሰብዓዊ ድርጅቶች ጋር በመሆን ባንኩ ሊሰጥ የወሰነውን ገንዘብ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅም ከመዋል ይልቅ ለኢህአዴግ የፖለቲካ ዓላማ ማስፈጸሚያ እየዋለ መሆኑን በመጥቀስ ለባንኩ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጂም ዮንግ ኪም መስከረም 6፤ 2005ዓም ደብዳቤ ልከዋል፡፡ በጥያቄያቸውም መሠረት በዓለም ባንክ በኩል ወደ ኢትዮጵያ የሚፈሰው ገንዘብ “በልማት ስም የኢትዮጵያ መንግሥት በጋምቤላ ክልል ለሚያካሂደው የመንደር ምስረታ እየዋለ ነው” በማለት ይከሳል፡፡ ሲቀጥልም የአኙዋክ ሕዝብ ለዘመናት ከኖረበት መንደር በማፈናቀል “የተሻለ አገልግሎት ይሰጣችኋል” በማለት በግድ የማስፈር ተግባር እየተፈጸመ ሲሆን “የተባለው አገልግሎትም ሆነ ለእርሻ የሚሆን በቂ ቦታ እንዲሁም ለከብቶች የሚበቃ የግጦሽና የውሃ ቦታ የላቸውም” በማለት ሰፈራውን የተቃወሙ ሁሉ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ረገጣ እየደረሰባቸው እንደሚገኝ ጠቁሟል፡፡ ይህንን ግፍ የሚፈጽሙት ደግሞ የዓለም ባንክ ለመሠረታዊ አገልግሎት ጥበቃ ፕሮግራም (Protection of Basic Services “PBS Program”) ስም ለልማት እንዲውል ከሚሰጠው የዕርዳታ ገንዘብ በመንግሥት ተቀጥረው ደመወዝ የሚከፈላቸው ሠራተኞች መሆናቸውን ገልጾዋል፡፡ ይህንን ጉዳይ ከዓለም ባንክ ጋር እንዲነጋገሩላቸው Inclusive Development International (IDI) የተባለውን ድርጅት መወከላቸውን አስታውቀዋል፡፡ (የደብዳቤው ሙሉ ቃል እዚህ ላይ ይገኛል)
ተመሳሳይ ጉዳዮችን በዓለምአቀፍ ደረጃ በመከታተልና በማስፈጸም የታወቀው IDI በመስከረም ወር አጋማሽ ላይ ጉዳዩ በቀጥታ ለሚመለከተው የመልሶ ማቋቋምና ልማት ዓለምአቀፍ ባንክና (International Bank for Reconstruction and Development (IBRD)) የዓለምአቀፍ ልማት ማኅበር (International Development Association (IDA)) ሥር ለሚገኘው የኢንስፔክተር ፓናል ባለ 18ገጽ ደብዳቤ ጽፏል፡፡ (የደብዳቤው ሙሉ ቃል እዚህ ላይ ይገኛል) ይህ የኢንስፔክተር ቡድን ከፍተኛ ሥልጣን ያለው መ/ቤት ሲሆን የዓለም ባንክ የሚሰጠውን ገንዘብ በትክክለኛ ቦታ ላይ አለመዋሉን በመጥቀስ ክስ የሚያቀርቡ ወገኖችን ጉዳይ በመከታተልና ቦታው ድረስ የራሱን ምርመራ በማካሄድ ውጤቱ ተግባራዊ እንዲሆን የባንኩን እጅ የማስጠምዘዝ ዓቅም ያለው እንደሆነ ከዚህ በፊት ያካሄዳቸው የምርመራ ውጤቶች ይጠቁማሉ፡፡
ይህ የመርማሪ ቡድን የቀረበለትን አቤቱታ መቀበሉንና በጉዳዩ ላይ የማንም ተጽዕኖ የማይደረግበትን የራሱን ምርመራ እንደሚያደርግ ከትላንት በስቲያ ባወጣው ባለ 8ገጽ መግለጫ ላይ አሳውቋል፡፡ ይህ የአቤቱታ ፋይል ቁጥር የተሰጠው ጉዳይ በግልባጭ ለባንኩ ፕሬዚዳንትና ለከሳሽ ተወካይ ድርጅት (IDI) እንዲደርስ ተደርጓል፡፡(የደብዳቤው ሙሉ ቃል እዚህ ላይ ይገኛል)
ጎልጉል የሰሜን አሜሪካ ዘጋቢ ባጠናከረው መረጃ መሠረት ቡድኑ ከያዝነው ዓመት የጥቅምት አጋማሽ በኋላ ወደ ምስራቅ አፍሪካ ያቀናል። ቡድኑ ስደተኞቹ የሚገኙባቸውን፣ እንዲሁም ጉዳዩን በሚመለከት አስፈላጊ የሚላቸውን ቦታዎችና ግለሰቦች ሙሉ በሙሉ ያነጋግራል። ለስራው መሳካት የሚሆነውን ሁሉ በሚፈለግበት ቦታ በመገኘት በግንባር እንደሚያከናውን ለማወቅ ተችሏል።
በተለያየ ጊዜ ኢህአዴግ የሚፈጽመውን ግፍና በደል በማደራጀት ሥርዓቱ ላይ ከትጥቅ የጠነከረ ትግል ማካሄድ እንደሚቻል አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል:: አያይዘውም በመላው አገሪቱ የሚፈጸመውን የሰብአዊ መብት ረገጣና የመብት ጥሰት በማሰባሰብ የኢህአዴግን የገንዘብ ምንጭ የማድረቅ፣ ብሎም በእርዳታ ገንዘብ የሚገነባቸውን የአፈና ተቋማት ማስለል እንደሚቻል አስታውቀዋል። ይህንን ታላቅ ስራ የሰሩትን አካላት ልምዳቸውን ለሌሎች በማካፈል አስፈላጊውን ስራ ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል። (የመግቢያው ፎቶ የተወሰደው: ዘጋርዲያን)

No comments:

Post a Comment