Translate

Wednesday, December 4, 2013

ከሰማይ የራቀችው ምድር ከምድሪቱ የራቀው ሰማይ

(ሠዓሊ አምሣሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

ethio saudi 16
ሲጀመር ገዥው ፓርቲ (ቡድን)  የዜጎችን ስደት በተመለከተ ማንነቱን አሳምሮ ለሚያውቀው ሕዝብ ምንም የማለት የሞራል (የግብረ-ገብ) ብቃት ጨርሶ አልነበረውም፡፡ ራቅ ካለው ታሪኩ እስከ ቀረብ ካለው ከዚያም እስከአሁን ካለው ታሪኩ አሁን ባለበት ሁኔታም ተስፋ የሚሰጥ ምንም ነገር ባለመኖሩ ነገም ከሚኖረው ታሪኩ ስንመለከት ይሄንን ክስ የሚያስተባብል ሆኖ አናገኘውም ፡፡ ከዚህ አንጻር ትኩረቱን በጣም አጥቦ በአራቱም አቅጣጫዎች በእግር እግራቸው ወደ አመራቸው በሚሰደዱ ታዳጊ ሕፃናትና ወጣቶች ላይ ማድረጉ በቦሌ በኩል በተለያየ ጫና ፣እንግልትና ውክቢያ ሳይወዱ ሀገራቸውን ጥለው በሚሰደዱት፤ ሕዝቡ በሌለው አቅም አስተምሮ ላቅ ላለ ደረጃ ያበቃቸው ፤በሀገርና በሕዝብ ጉዳይ ላይ ንቁ ተሳታፊ የሆኑ ውድ ልጆቹ ምሁራን ላይ አለማድረጉ የቦሌዎቹ ተሰዳጆች የማይጎዳ የእግረኞቹ የሚጎዳ የሚያጎል ነው ብለው አስበው ሳይሆን ስለስደት ማውራት ካለባቸው የርእሰ መሬያቸው ጠባብ አማራጭ እነሱው በመሆናቸው ብቻ ነው፡፡
ወደ ተሰዳጅ ወገኖቻችን ስመለስ ይሄኛው ወይም ያኛው የኅብረተሰብ ክፍል መሰደዱ የሚጎዳና የማይጎዳ የሚል ሒሳብ ውስጥ ከተገባ ብዙ ነገር አለ ሲጀመርም እዚህ ስሌት ውስጥ ልንገባ አይገባንም፡፡ ዜጎች ተማሩም አልተማሩ ዜጎች በመሆናቸው ጥበቃና እንክብካቤ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ያልተማሩም ቢሆኑ እነሱን የማይተካ ሀገር የምትጠብቅባቸው ለሀገር የሚያበረክቱት ብዙ ነገር መኖሩ አይቀርምና ፡፡ የሚያሳትፋቸውና የሚጠቀምባቸው ዓይናማ መንግሥት ካገኙ፡፡ እናም ‹‹መንግሥት›› በቦሌ በኩል ለሚሰደዱት ሥልጣን ከያዘ ማግሥት ጀምሮ (ሀገሪቱ የተማሩ ብርቅዬ ዜጎቿን ስታጣ የሚደርስባት ከባድ ጉዳትና የምታጣው ጥቅም ኢምንት እንኳን ሳያሳስበው 42 ሲቀነስ 1 በአብዛኛው ዶክተሮችን ፕሮፌሰሮች የሚበዙበትን የምሁራንን ቡድን በአንድ ጊዜ አባሮ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን (መካነ-ትምህርትን) ወና ካደረገበት እስከ 1997ዓ.ምሕረቱ ምርጫ ማግስት ምሁራን የፖለቲካ ፓርቲ (የእምነተ አስተዳደር ቡድን) መሥርተው አሸናፊ ከሆኑ በኋላ ሥልጣን ለማስረከብ ባለመፍቀዱ ከሕዝቡ ያገኙትን ድምፅ እንኳን ባይሆን ከተሳትፎ በዘለለ የወሳኝነት ሥልጣን አጋርቶ አስተዋጽኦዋቸውን እንዲያበረክቱ ማድረጉ ለሀገር ሳይሆን ለቡድኑ ስላልተስማማው ብቻችንን ዐወቅንበትም አላወቅንበት፣ ገባንም አልገባን እስክናልፍ ድረስ ብቻችንን እንደመሰለን እያባከንንም፣ እያበላሸንም፣ እያጨማለቅንም እንማርበታለን እንጅ እናንተን ከጎናችን አስቀምጠን አንጋለጥም፣ አንሸማቀቅም፣ አንዋረድም በሚል ደንቆሮና ጠባብ አስተሳሰብ ሀገር ይረቡኛል ብላ በድሀ ሕዝቧ አቅም ያስተማረቻቸው የምትጠብቅባቸውንም ለማበርከት ንቁ ተሳታፊ ሆነው ለተፍጨረጨሩት ምሁራን የስደት ግብዥ በማቅረብ ተገደው እንዲሰደዱ እንዳደረገና ምሁራንን የሚያስጠላ ከባድ በሽታ እንዳለበት በግልጽ በአደባባይ ተናግሯልና፡፡
ከዚህ ይልቅ ‹‹አቋም አስተሳሰባችንን እስከተቀበለና እስከ ደገፈ ጊዜ ድረስ መሀይምም ቢሆን በሚንስትር ደረጃ እንሾማለን›› በማለት ያለአንዳች ሀፍረትና መሸማቀቅ በድንቁርና ጀብደኝነት በይፋ በብዙኃን መገናኛ ተናግሯልና፡፡ እንግዲህ በመሀይም ተመርተን ታዲያ የት እንድንደርስ ይጠበቃል ? በዚህ ንግግር ውስጥ ብዙ ነገር ልብ ማለት እንችላለን፡፡ “አፍ ሲከፈት ጭንቅላት ይታያል” ይባላል ይህ ንግግር የሰዎቹን የብስለት ደረጃ አስደንጋጭ በሆነ መልኩ ደካማ መሆኑን፣ የሥልጣን ባለቤት ሕዝብ አለመሆኑን (ባልተማረ ወይም በመሀይም መመራት የሕዝብ ፍላጎት አይደለምና) ፣ አንባገነንነታቸውን ሀገሪቱን እንደሌሎች አንባገነኖች ሁሉ እንዳሻቸው ሊያደርጓት እንደሚችሏት የግል ንብረታቸው አድርገው እንደሚቆጥሯት ፣ራስን ጎድቶ ለሀገር ሊከፍሉት የሚችሉትን (ከራስ፣ከቡድን በላይ ሀገርን የማየት) ከዜጎች የሚጠበቅ የግዴታ ኃላፊነት ጭላጯ ስሜት እንኳ የሌላቸው መሆኑን ወ.ዘ.ተ.
በመሆኑም የምሁራኑ ስደት ለደቂቃ እንኳ አስደስቶት እንጅ አሳስቦት የማያውቅ ‹‹መንግሥት›› ዛሬ ላይ ድንገት ተነሥቶ የምሁራን ስደት (brain drain) አሳሰበኝ ቢል ‹‹መንግሥት›› ልብ ገዛ እንዴ? ተጸጸተ እንዴ? ከሚለው ይልቅ እንደልማዳቸው እየቀለዱብን ነው የሚለውና እውነትነቱን ለማመን የሚቸገረው እጅግ ይበዛልና፡፡ እነሱም በመቃብራቸው ላይ ካልሆነ በቀር እንዲህ ዓይነቱ ነገር ሲያልፍም አይነካካቸው፡፡ ምንም እንኳ የእግረኞቹ ስደተኞችም መንስኤ መጀመሪያና መጨረሻ እራሱው ቢሆንም ቢያንስ እንደቦሌዎቹ ስደተኞች የተሰደዱ አዋጅ በይፋ የተናገረበት ጉዳይ አይደለምና የፈለግነውን ብንል በሕዝብ ዘንድ አያሳብቀንም አያሳጣንም ብለው ያስባሉ፡፡ የሚገርመውም ይኼው  ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ የፈለገውን እውነት የሚመስል ነገር ቢል የሚናገረው የጉዳዩ ባለቤት ለሆነውና በጉዳዩ ለተቸገረው ሕዝብ በመሆኑ ለቀባሪው ለማረዳት መሞከሩን በመሆኑም ከቶውንም ማታለል አለመቻሉን አለማወቁ ነው፡፡
እርግጥ ነው ከስደት  መንስኤዎች አንደኛው የኢኮኖሚ (ሥራ ፍለጋ) ሥደተኝነት ነው፡፡ ነገር ግን ይሄንን መንስኤ እንዲያው በደፈናው ብለነው ልናልፈው የማንችለውና በውስጡ ብዙ ጣጣ ያለበት በቀጥታም ከፖለቲካ (ከእምነተ-አስተዳደር) ጋር ግንኙነት ያለው ጉዳይ ነው፡፡
ሁላችንም እንደምናውቀው በዛሬዋ ኢትዮጵያ አይደለምና በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በግል ድርጅቶች እንኳን ሳይቀር ሥራ ለመቀጠር በግልጽም ይሁን በሥውር የሚጠበቁ መስፈርቶች በቀጥታ እምነተ-አስተዳደራዊ ሆነዋል፡፡ በነገራችን ላይ ዛሬ ተቀጥሮ ለመሥራት አይደለም ለመማርም እንኳ ገዥው ፓርቲ የሚፈልገው የእምነተ አስተዳደር አቋም ካልተያዘ ደጋፊው ካልተሆነ ዜጎች በገዛ ሀገራቸው መሠረታዊ መብታቸውን መማርን ከቶም የማይችሉበት ደረጃ እንደደረስንና እንዲህ ዓይነት ሀገርም ልትኖረን ግድ የሆነብን ዘመን ደርሰናል፡፡ ወደ ኋላ እመጣበታለሁ፡፡እንደሚታወቀው በሀገራችን ትልቁ ወይም ከፍተኛው ሥራ ቀጣሪ አካል መንግሥት ነው፡፡ የግልና መንግሥታዊ ያልሆኑ የልማት ድርጅቶች ድርሻ በተለይ በአሁኑ ሰዓት ማለትም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (NGO’s) ለብዙዎች ከገዥው ቡድን ቀንበር እራሳቸውን ነፃ ለማውጣት የሕሊና ነፃነታቸውን ለመጠበቅ የፈለጉት ዜጎች ማኩረፊያና መሸሸጊያ መሆናቸውን የተረዳው ገዥው ፓርቲ (ቡድን) ማኩረፊያና መሸሸጊያ ለማሳጣት አዲስ ደንብ አውጥቶ በጣም ጥቂት ከሆኑት በስተቀር የሚበዙትን እንዲዘጉ ካደረገ በኋላ ከፍተኛው ሥራ ቀጣሪ መንግሥት መሆኑን ሊያጠናክረው ችሏል፡፡ ያ ዜና አሁን ገዥው ቡድን በያዘው የቅጥር አቋም ወይም መስፈርት  ምክንያት ለዜጎች የመርዶ ያህል መጥፎ ዜና ሆኗል፡፡ ምክንያቱም ሠርቶ ለማደር ሲሉ የማይወዱትን ወይም የማይፈልጉትን እምነተ-አስተዳደራዊ (ፖለቲካዊ) አቋም አመለካከት ከመያዝ አንሥቶ ሕሊናቸውን እስከመሸጥ ድረስ ይገደዳሉና ፡፡
ለወትሮው የግል ድርጅቶች ነፃ ቀጠና ነበር፡፡ ማለትም ፖለቲካዊ አቋም የማይጠየቅበትና የማይጠበቅበት፡፡ ዛሬ ላይ ግን ይህ ሁኔታ ለመልካም ነገር ሲሉት እንጅ ለሸርና ለተንኮል ሲሉት ግን በመተብተብና በማቀናበር የሚስተካከለው የሌለው ገዥው ፓርቲ ለእነሱም መላ አላጣላቸውም ፡፡ ብዙ ጊዜ በዘልማድ በዘልማድም ሳይሆን ታስቦበት ባለጸጎች በድርጅቶቻቸው ዘመዶቻቸውን በመቅጠር ደካማና ሊረዷቸው የሚፈልጓቸውን ዘመዶች በድርጅቶቻቸው እየቀጠሩ ያለው የሌለውን የሚረዳበት የሚደግፍበት ለሌለው ወገኑ የሚደርስበት ልማድ ወይም አሠራር ነበር፡፡ ዛሬ ላይ ይሄ ጉዳይ ታሪክ እየሆነ ነው ፡፡ ከሕገመንግሥታዊና ሰብአዊ ሕግጋቶች አንፃር ሲታይ ፍጹም ሕገወጥ (ወንጀል) በሆኑ አቋሞቹ በሕዝብ ወይም በመንግሥት ድርጅቶች ላይ ያሻውን ማድረጉ ያልበቃው ገዥው የእምነተ-አስተዳደር ቡድን ወደ ግል ድርጅቶችም በመውረድ እሱ የሚልክላቸውን ወይም የሚሰጣቸውን የራሱን እምነተ-አስተዳደራዊ አቋም የተቀበሉትን አባላት እንዲቀጥሩና እንዲጠረነፉ እያደረገ ነው፡፡ እንቢ ቢሉ የሚከተላቸውን ችግርና የሚገጥማቸውን ጣጣ የሚረዱ ባለሀብቶች ሳይፈልጉ አሠራሩን መቀበል ግድ ሆኖባቸዋል፡፡ በዚህ አሠራር ምክንያት ብዙ ባለጸጎች ወይም ባለሀብቶች የገዛ ዘመዶቻቸውን እያሰናበቱ ቅጠሩ ተብለው የተላኩትን ግለሰቦች ለመቅጠር ተገደዋል ፡፡ በሁኔታውም አመለካከታቸውን ጨምሮ ብዙ ነገሮቻቸው ለስለላ የመዳረግና በገዛ ድርጅቶቻቸው ነፃነታቸውን ያጡበት ሐሳባቸውን ለመግለጽ ያልቻሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ሁኔታው ከዚህም አልፎ ጭራሽም ደጋፊ ወይም አባል ያልሆነ ባለሀብት ሠርቶ ማደር የማይችልበት ከባቢ ተፈጥሯል፡፡ ገዥው ፓርቲ ይሄንና መሰል ድርጊቶቹን መካድ ከሚችልበት ደረጃ ስላለፈና ተራራን በጋቢ እንደመሸፈን የማይቻልና እጅግ ከባድ ስለሆነበት ለመካድ አይሞክርም “የመልካም አስተዳደር ችግር” በምትል ኃረግ የማይከሳቸውንና ለፍርድ የማያቀርባቸውን የታችኛው የአሥተዳደር መዋቅሩ አባላቱን ለይስሙላ በመወንጀል ሸፋፍኖ ለማለፍ ይሞክራል እንጅ፡፡
መጋቢት 6, 2004ዓ.ም አንድ ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ ላይ ካሉ ሕጎች ውጭ በሆነ ወይም በማይፈቅዱት ሁኔታ ተቋቁሞ በሕገወጥ መንገድ ሲሠራ የቆየና የራሱን የኢኮኖሚ ኢምፓየር (የሀብት ግዛት) እስከ መገንባት የደረሰ አሁን ባለበት ሁኔታ ደግሞ ባለንብረትነቱ የማን እንደሆነ በማይታወቅ የሬዲዮ (የነጋሪ-ወግ) ጣቢያ ላይ አንድ ሳምንታዊ ዝግጅት በመተላለፍ ላይ ነበር፡፡ ይህ ምስናድ የቀጥታ ዝግጅቱን በሚያስተላልፍበት በዚህ ዝግጅቱ ስቱዲዮ (መከወኛ ክፍል) እስኪገኙላቸው ድረስ የምስናዱ አዘጋጆች ለሥራቸው ሲሉ ሌላ ሌላ ምክንያቶችን በመስጠት ለምን ጉዳይ እንዳመጧቸው አያውቁ የነበሩት መከወኛ ክፍል ውስጥ እንዲገኙ የተደረጉት እንግዳ አዘጋጆቹ ለሚጠይቋቸው ጥያቄዎች መልስ ሲሰጡ ከቆዩ በኋላ በድንገት በብሶት በመገፋት ሁላችንም የምናውቀውን ደፍረን ግን በአደባባይ የማናወራውን ነገር መናገር ጀመሩ፡፡ እንዲህም አሉ ‹‹እኔ ልጀን ጠልቸ አይደለም  ልጀን እንዴት እጠላለሁ? ለ26 ዓመታት በረሀ ተቃጥዬ ነው ያሳደኳቸው ነገር ግን የት ይደርሱልኛል ያልኳቸው ተስፋ የጣልኩባቸው ልጆች ከንቱ በመሆናቸው ውስጤ በጣም ስለተጎዳ ጤና አሳጥቶኝ፤ ይህች እንደምታይዋት ጎረምሳ አታሏት ካስወለዳት በኋላ ዞር በይ አላውቅሽም ብሎ ሸኛት ሕይወቷን አበላሸብኝ ያኛው የሷ ታላቅ ጥሩ ጭንቅላት ነበረው ጎበዝ ተማሪ ነበር አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የዲግሪ ተማሪ ነበር አባል ካልሆንክ አትማራትም እያሉ ይሄው ለሦስተኛ ጊዜ  ዘንድሮም እዲያቋርጥ አደረጉት እስካሁን ተመርቆ ነበር›› እያሉ እንባ በተናነቀው ድምፅ እየተናገሩ እንዳሉ ጋዜጠኞቹና የነጋሪተ-ወጉ ኃላፊዎች እንዲናገሩ የማይፈልጉትንና የማይፈቅዱትን አደገኛ ነገር እኒያ አባት ሳያስቡት በመናገር ላይ እንዳሉ በድንገቱ የተደናገጡት አዘጋጆቹ ተጣድፈው አቋረጧቸው፡፡ አሁን እንግዲህ ይሄ ልጅ በገዛ ሀገሩ ላይ ተምሮ መለወጥ ሠርቶ ማደር ባለመቻሉ ያለመሰደድ ሌላ አማራጭ አለውን? ይሄኔ ተሰዶም ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ተማሪ የደረሰበት ችግር ሁሉም ላይ የሚደርስ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ገዥው ፓርቲ ከብቃት መለኪያዎች ውጭ በፖለቲካዊ አቋምና ደጋፊዬ አባሌ ካልሆናቹህ እያለ በልዩነት ማስተናገድ ከፈለገ በሕዝብ ወይም በመንግሥት ንብረት ሳይሆን በራሱ በፓርቲው ወጪ፤ ከአባላት መዋጮ ውጭም አንድ ፓርቲ የገቢ ምንጭ እንዲኖረው አይፈቀድምና በአባላቱ መዋጮ የራሱን ዩኒቨርስቲ (መካነ-ትምህርት) ገንብቶ እንጅ የኢትዮጵያ ሕዝብ ንብረት በሆኑ በኢትዮጵያ ሕዝብ ገንዘብ በተገነቡ የትምህርት ተቋማት አይደለም፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተገነባው በኢትዮጵያ ሕዝብ ገንዘብ እንጅ በገዥው ፓርቲ ገንዘብ አይደለም፡፡ በራሱ በሕዝቡ ገንዘብ በተገነቡ የት/ተቋማት የባለቤቱን የሕዝቡን ልጆች አትማሩም ብሎ እንዲከለክል ዕድል እንዲነፍግ የሚያስችለው አንዳችም ሕጋዊ መሠረት የለም፡፡ አሠራሩ የለየለት ወንጀልና ሕገወጥ ድርጊትም ነው፡፡ “መንግሥት” ተጠሪነቱ ለሕዝብ እንጅ ሕዝብ ተጠሪቱ “ለመንግሥት” አይደለም ይሄንን ገልብጦ ለመሥራት መሞከር ወንጀል ነው፡፡ አስተሳሰቡም ማለትም በሀገሪቱ ያለው ነገር ሁሉ የገዥው መገልገያ የግል ንብረት እንደሆነ ማሰብ ሞቶ የነበረ ፊውዳላዊ አስተሳሰብ ነው፡፡ ምክንያቱም ሳር ቅጠሉ ሁሉ የገዥው የንጉሡና እንደፈለጉ የሚያዝዙበት የግል ንብረት እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠር ነበርና፡፡ የሕዝብ ነው ከተባለ ግን መብቱና ተጠቃሚነቱ ሕዝብ ይሆናል እንጅ ግላዊ ወይም ቡድናዊ ፍላጎትና ጥቅም ያላቸው የመንግሥትነት ሥልጣን የያዙ ቡድኖችና ግለሰቦች ሊሆኑ አይችሉም፡፡ የተጠሪነት ጥያቄ ያስነሣልና፡፡ ሲጀመርም እንዲህ ዓይነቱ የጥቅምና የፍላጎት ግጭቶች የሚያጋጥመው ኢዲሞክራሲያዊ (ኢበይነ-ሕዝባዊ) አስተዳደር በሰፈነበት የመንግሥት አስተዳደር እንጅ በበይነ-ሕዝባዊ አስተዳደር ሥርዓት አይደለም፡፡
በገጠሩ የሀገራችን ክፍልም በአሁኑ ወቅት ለእኛ ሁሉንም አማራጮች ተጠቅመን ምርትን ማሳደግ ፣በምግብ እራስን መቻል፣ የህልውናና የብሔራዊ ደኅንነት አንገብጋቢ ጉዳይ በሆነበት ወቅት ገበሬው ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ለማግኘት በእምነተ-አስተዳደራዊ አቋሙና ወገንተኝነቱ እየተለየ እንደሚስተናገድ ለቁጥር የሚያታክቱ ተደጋጋሚ ክሶች እንደሚቀርቡ ግልጽ ነው፡፡ እንግዲህ ከዚህ የከፋ ድንቁርና ከቶ ከወዴት ምንስ ዓይነት ድርጊት ይገኛል? ለነገሩማ እንደሚታወሰው ሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችም ክስ እንዳቀረቡበትና እንደመሰከሩት ተርበውና ተቸግረው እሚበሉት አተው ነፍስ ለማቆየት እርዳታ የሚጠብቁ ዜጎችን በፖለቲካ አቋማቸው ምክንያት እርዳታውን ከከለከለና የዚህን ያህል በገዛ ዜጎቹ ላይ ከጨከነ ‹‹መንግሥት›› የማዳበሪያውና የምርጥ ዘሩ ጉዳይ ምን ይደንቃል? ነገር ግን ሰብአዊ ሕሊና ያለው እንዲህ ዓይነቱን ነገር ማድረግ አይደለም ማሰብስ ይቻለዋልን?፡፡
እንግዲህ ልብ በሉ በገዛ ሀገሩ ተፈጥሮአዊና ሕገመንግሥታዊ በሆነው መብቱ የመሰለውን አመለካከት ይዞ ኅሊናው እንዳዘዘው በፈቃዱ አድሮ በዜግነቱ በብቃትና በችሎታ ብቻ ተመዝኖ ሠርቶ ማደር ፣ተምሮ ለቁም ነገር መብቃትና ሀገሩን ቤተሰቦቹን እራሱን መርዳት የነበረበት ዜጋ የገዛ ሕገ መንግሥታቸውን በመተላለፍ በመጣስና በመደፍለቅ እኛ በምንልህ እኛን ተቀብለህ ብቻ ካልሆነ መብቱ የነበሩትን ነገሮች ማግኘት ከቶውንም አትችልም ተብሎ የተተፋ፣የተገፈተረና በገዛ ሀገሩ ባይተዋር የበይ ተመልካች እንዲሆን የተደረገ በአረመኔያዊ ጭካኔ ያለምንም አማራጭ የተተወ ዓይኑ እያየ ለችግር ለረሀብ የተሰጠ ትውልድ ከሞት ጋር ተፋጦ እግሩ ወዳመራው ቢሰደድ ቢተም የሚገርም ነገር ይሆናልን? ይወነጀላልን?ሊወቀስ ይገባልን? እንዲህ ዓይነት አስገዳጅ ሁኔታ ባይፈጠርበት ኖሮ አስቀድመው የወጡቱ ምን ዓይነት አሰቃቂ አደጋ እንደደረሰባቸው በየ ብዙኃን መገናኛው እየተለፈፈ እየሰማ ፈጽሞ ዓይኑን ጨፍኖ ወደ ሞትና መከራ የሚተም ዜጋ ባልኖረ ነበር፡፡
ይሄንን ሁሉ ጉድና ገመና ሸርና ማነቆ የማያውቀው ወይም ለማወቅ የማይፈልገው ካልሆነም ገዥው ፓርቲ በደላሎቹ (lobbies) እንዲወናበድ የተደረገው የተባበሩት መንግሥታት የሥደተኞች ከፍተኛው መሥሪያ ቤት (UNHCR) በየባዕዳን ሀገራት እሥር ቤቶች ፣በየጫካው መከራ የሚያዩትን ፣ የሚቅዝበዘበዙትን፣ የሚዋትቱትን፣ የአውሬና የዓሣ ሲሳይ የሆኑትንና እየሆኑ ያሉትን አቋጣሪ  ተቆርቋሪ ያጡ ምንዱባን እኅት ወንድሞቻችን ከዚህ ሁሉ ሞትና መከራ ተርፈው በተለያዩ ሀገራት የደረሱትንም በጅምላ የኢኮኖሚ (ሥራ ፈላጊ) ስደተኛ እንደሆኑ በመደምደም በስደተኝነታቸው ያላቸውን ከድርጅቱ ሊያገኙ የሚገባቸውን አገልግሎት፣ ጥበቃ፣ ጥቅምና መብት ሁሉ በመንፈግ ወይም በማጓደል እንዲጉላሉ፣ እንዲንገላቱ ፣እንዲቸገሩ እንደገና የመከራ ዓይነት እንዲቆጥሩ ይደረጋል፡፡ ግፍ ቆጣሪው አምላክ ይሄንን ሁሉ ግፍ ዓይቶ ቆጥሮ ይቅር ያለን ጊዜ አቤት ምን ያህል እንተዛዘብ? ይሄንን ሁሉ ጉዱን ይዞና ይሄንን የስደት ማዕበል የፈጠረውን ጉዳይ ጠንቅቆ የሚያውቀው ነገር ግን ለመሸፋፈን የሚጣጣረው ገዥው ፓርቲ ደግሞ አዛኝ ቅቤ አንጓች ውኃ የማይቋጥር ልፈፋውን በሕዝብ የብዙኃን መገናኛዎች ሲደሰኩር መታየቱ ምን ያህል ለሞራል(ለግብረ-ገብ) ጥያቄዎች ተቆርቋሪና ተጠያቂ ኅሊና ያለመኖሩንና ዴንታ እንደሌለውም ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡
እናም እባካቹህ የችግሩን መንስኤ በሚገባ ታውቁታላቹህ በእርግጥም እያላቹህት እንዳላቹህት በየበረሀው፣ በየባዕዳንሀገራትእሥር ቤቶች፣ በየባሕሩ፣ በየጫካው የሚረግፉት፣ የሚበሉት፣ ሊሰሙት የማይቻል ዘግናኝ ኢሰብአዊ ድርጊት የሚፈጸምባቸው ሕፃናት እኅት ወንድሞቻችን የሚያሳዝኗቹህና የሚገዷቹህ ከሆኑና ሰብአዊ ሕሊና ካላቹህ ሌላ ምንም አይደለም የገዛ ሕገ መንግሥታቹህን ብቻ ብታከብሩልን ለጊዜው ይሄው ይበቃን ነበር፡፡  እርግጥ ሕገ መንግሥቱ ሀገርን ሊያፈራርሱ የሚችሉ ሊወገዱ የሚገባቸው አደገኛ አንቀጾች ያሉበት ቢሆንም ከሰብአዊ መብት አንፃር ግን ብዙ ጥሩ ጥሩ ድንጋጌዎች አሉት፡፡ ነገር ግን ግንጥል ጌጦች ናቸው ምክንያቱም ሕገ መንግሥቱ ለቡድን መብት የሰጠውን ዕውቅናና ጥበቃ ያህል ለግለሰብ መብትም በተመሳሳይ መስጠቱ ገዥው ፓርቲ በቡድን(ማኅበራት) ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ በሥውር ተመሳስሎ ሰርጎ በመግባት መከፋፈል፣ ለስኬት እንይበቁ፣ዓላማቸው ግቡን እንዳይመታ፣ጠነካሮችና አንድነታቸው የጸና እንዳይሆኑ እያደረገ እንደምናየው ሁሉ ለግለሰብ መብት ዕውቅናና ጥበቃ ከተሰጠ ሰው መብቱን እንዳይጠቀም ለማድረግ ለዚህ ዓይነት ተንኮል ስለማይመች በዚያም ምክንያት ለመቆጣጠር ጨርሶ ስለማይቻል ሕገ መንግሥታቸውን ሲቀርጹ የግለሰብን መብት እንዳያውቅ አድርገውታል፡፡ በመሆኑም የግለሰቦችን መብት የማያውቅ ሕገ መንግሥት ስለ ሰብአዊ መብቶችና የቡድን መብቶች የፈለገውን ያህል ቢያወራ ጥቅምና እርባና አይኖረውም፡፡ ምክንያቱም በቀኝ እጁ የሰጠንን ባዷችንን አስቀርቶ መልሶ በግራ እጁ ወስዶታልና፡፡ የዜሮ ብዜት ውጤት ነው፡፡ ይሄንንና ሌሎችን የተቀሩትን የተቀመሩ ክፋቶችንና ማታለሎችን የሚያደንቅ ሰው ቢኖር ሌላ ምንም ዓይነት የሕክምና ማረጋገጫ ሳያስፈልገው ጤነኛ አለመሆኑን ሊያረጋግጥ ይችላል፡፡ የተማርኩ ነኝ የሚል ከሆነም እንደገና ይመለስና ሀ ብሎ ፊደል ይቁጠር።  ከባዱና አስቸጋሪው  ሆኖ ለመገኘትም ፈታኙ ነገር ቀናነቱ እንጅ ክፉነቱ አይደለምና፣ትክክለኝነቱ እንጅ ስሑትነቱ አይደለምና፣ ገንቢነቱ እንጅ አፍራሽነቱ አይደለምና፣ማኅበራዊነቱ እንጅ ግለኝነቱ ወይም ቡድናዊነቱ አይደለምና፣ እውነተኛነቱ እንጅ ሐሰተኛነቱ አይደለምና፣ንጹሕነቱ እንጅ ቆሻሻነቱ አይደለምና፣ ዐዋቂነቱ እንጅ ድንቁርናው አይደለምና፣ ቅድስናው እንጅ እርኩሰቱ አይደለምና ወዘተ፡፡
እናም እባካቹህ? እባካቹህ? ለነገሩ ምን አማራጭ አላቹህ ሕዝብ ወዶና ፈቅዶ ሊቀበለው የሚችለው ዓላማ ፣ ሥራና ተግባራዊ የመልካም አስተዳደር ሥርዓት የሌላቹህ ከመጀመሪያው ታሪካቹህንና ማንነታቹህን ከሕዝብና ከሀገር ጥቅሞች በተፃራሪ ያቆማቹህ፣ እስከዛሬ ድረስ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ልብ መግባት ያልቻላቹህና ባዕድ እንደሆናቹህ የቀራቹህ፣ ክፉ ነገር በተከሰተ በተፈጸመ ቁጥር እንደጠላት በቅዲሚያ የሚጠረጥራቹህ “መንግሥት” በዚህ ደረጃ ጨክናቹህ አስገድዳቹህ ለመግዛት ካልሞከራቹህ እንደምን ሆናቹህ በምንስ ተአምር በመንግሥት ዙፋን ላይ የመኖር ዕድል ልታገኙ ትችላላቹህ? ስለሆነም ይህ አሁን እያየነው ያለው የአገዛዝ ዓይነት (እኩይ ሰይጣናዊና ኢሰብአዊ ሸርና ክፋት የተሞላ አንባገነንነት) ለገዥው ፓርቲ አማራጭ የሌለው እጣ ፋንታው ነው፡፡ የተራራቁት ሰማይና ምድር ሰማዩ ወደ ምድሪቱ ምድሪቱም ወደ ሰማዩ ተቀራርባው (ፈጣሪን ስለበደልን በኃጢአት ስለረከስን ሰብሮና አድክሞ ለእነዚህ መጫወቻ አሳልፎ እንደሰጠን አውቀንና አምነን በንስሐ ወደ እግዚአብሔር ተመልሰን እግዚአብሔርም በምሕረት ወደኛ ቀርቦ ይቅር ብሎን ዕርቅ ፈጥረን) የወሰደብንን ወኔና ድፍረት መልሶልን እንደ ቀደምቶቹ የዓለም አምባ ገነን መንግሥታት ሁሉ ለዚህም‹‹መንግሥት›› ሕዝቡን አነሣሥቶ ተመሳሳዩን እጣ ፈንታ እስኪሰጠው ድረስ፡፡
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
ይሄ ግን በብዙ ሀገራት ታሪክ እንደምንረዳው በዕድል ካልሆነ በስተቀር ውጤቱ በተለይም ለአንባገነኖቹ የሚጠቅም አይሆንም፡፡ በመሆኑም ጨቋኞች ሆይ እንዲያው ለራሳቹህ እንኳን ስትሉ ሕዝቡ አመፅን ብቸኛው አማራጩ እንደሆነ እንዲያምን ባታስገድዱትና እንዲያምፅ ባታደርጉትስ? እውስጣቹህ ነግሦ የቀደምቶቻቹህ አንባገነኖች እጣ እንደማይደርስባቹህ የሚሸነግላቹህን የአመፃ መንፈስ አትመኑት በፍጹም አትመኑት ጉድ ሊሠራቹህ ነው፡፡ እናንተ ከዚህ ቀደም ከነበሩት አንባገነኖች ትበረታላቹህን? ካልሆነስ ምንም ማምለጫና መተማመኛ የላቹህም ማለት አይደለምን? የራሳቹህ ጉዳይ!!!

No comments:

Post a Comment