Translate

Tuesday, December 10, 2013

በብሔር ፖለቲካ ሥር “የተቀበረው ፈንጂ”! – (ዳዊት ሰለሞን)

(ከዋለልኝ እስከ ህወሃት/ኢህአዴግ)

የብሔር ጥያቄ በኢትዮጵያ ምላሽ እንዳገኘ የሚያስተጋባው ኢህአዴግ “የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች” በዓልን ማክበር ከጀመረ ስምንት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በአንፃሩ “ተመልሷል” የተባለው ጥያቄ እንደተቀበረ ፈንጂ በየጊዜው በየቦታው እየፈነዳ በህይወት፣ በንብረትና በኢትዮጵያዊነት ላይ አደጋ ማድረሱን ዳዊት ሰለሞን ሁነቶችን በመጥቀስ ይሞግታል፡፡
ከአስርት አመታት በፊት
የኢትዮጵያ ተማሪዎች በለውጥ አብዮት ናፍቆት እየተናጡ ነው፡፡ እዚህም እዚያም በተፈጠሩ ቡድኖች የማርክሲስት-ሌኒንስት ፍልስፍናን የሚሰብኩ የርዕዮተ ዓለም ጽሁፎች ይነበባሉ፡፡ ተማሪው ይከራከራል፣ የሌኒኒዝም ፍልስፍና ቀለም ቀለም መሽተት ለጀመረው የ1960ዎቹ ትውልድ ልብ የቀረበ ሆኗል፡፡ ፍልስፍናውን በአገራቸው የፖለቲካ ግለት ለመተርጐም የቋመጡት ወጣቶች በሁለት ጠርዝ ተሰልፈው በኢትዮጵያ ያለው “የመደብ ወይስ የብሔር ጭቆና ነው” በሚል በጠረጴዛ ዙሪያ ይፋለማሉ፡፡
የብሔር ጭቆና በአገሪቱ መስፈኑን ለማሳመን ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከሩ ከነበሩ ተማሪዎች መካከል የብዙዎችን ቀልብ ለመስረቅ የበቃው ዋለልኝ መኮንን በተማሪዎች መጽሔት “On the Question of Nationalities in Ethiopia” የሚል ጽሑፉን ማስነበብ ጀመረ፡፡ ዋለልኝ በጽሑፉ ኢትዮጵያ አንድ አገር ሳትሆን ብዛት ያላቸው ብሔሮች በአማራ የበላይነት ተጨፍልቀው የሚኖሩበት መሆኗን ሞገተ፡፡ የዋለልኝን መከራከሪያ የተቀበሉ ተማሪዎች የብሔር ጥያቄን ዋነኛ መፈክራቸው አድርገው አረፉት፡፡ በአገሪቱ የሰፈነው ጭቆና የመደብ መሆኑን በመግለጽ “አንዱን ብሔር ጨቋኝና ሌላውን ተጨቋኝ” በማድረግ የተነሱትን እነ ዋለልኝን የተቃወሙ ተማሪዎች የብሔር ጭቆናን በሚያስተጋቡ ተማሪዎች “የነፍጠኛ ልጆች” የሚል ተቀጥላ ተበጀላቸው፡፡

ዋለልኝ ከማርክሲስት – ሌኒኒስት ፍልስፍና በቀጥታ የገለበጠባቸውን ቃላቶች በመጠቀም ኢትዮጵያን “የብሔሮች እስር ቤት” በማለት ሰየማት፡፡ በዋለልኝ እንደተዋወቀ የተነገረለትን የተጨቆነ ብሔርን ነፃ የማውጣት ፍልስፍና የትግራይ ተማሪዎች መሬት ላይ ለማዋል በማቀድ የነጻ አውጪነት ቡራኬን ተቀብለው ደደቢት በረሃ ገቡ፡፡ ወጣቶቹ ትግላቸውን በማስመልከት በእጅ ጽሑፍ ባሰፈሩት የመጀመሪያ ማኒፌስቷቸው ትግራዋይ በአማራ ጨቋኝ ብሔር ሲጨቆን መቆየቱን በመግለጽ ጨቋኙን (አማራን) ብሄር በጠብ መንጃ ትግል በመፋለም ትግራይን ነፃ ለማውጣት መነሣታቸውን አወጁ፡፡ በለስ የቀናቸው የትግራይ ነፃ አውጪዎች መላዋን ኢትዮጵያን በመዳፋቸው ስር ካስገቡ በኋላ በ1987 በጸደቀው ህገ መንግሥት የጆሴፍ ስታሊንን የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች አተረጓጐም ሳይጨምሩና ሳይቀንሱ እንዲሰፍር በማድረግ የስታሊን ደቀ መዛሙርት መሆናቸውን በተግባር አሳዩ፡፡
የአገሪቱ የመንግሥት አወቃቀርም ብሔር ተኮር ፌዴራሊዝም እንዲሆን ተፈረደበት፡፡ ከብዙ አስርት አመታት በኋላ በዋለልኝ መኮንን “የብሄሮች እስር ቤት” ተብላ ከተጠራችው ኢትዮጰያ የተጨቆኑ ብሄሮችን ነፃ ለማውጣት ብሶት አርግዞት እንደወለደው የነገረን ገዥው ፓርቲ ራሱን በነጻ አውጪዎች ሰረገላ ካስቀመጠ 22 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የነገው የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓልም በገዥው ፓርቲ እምነት ጥያቄው ምላሽ ለማግኘቱ አይነተኛ ማሳያ ነው፡፡ ለፓለቲካ ፍጆታ እየዋለ ከሚገኘው ህዳር 29 በስተጀርባ መሬት የረገጡ እውነታዎችን ለመፈተሽ የተነሱ ሰዎች ከ73 የሚልቁ ብሄር ተኮር የፖለቲካ ድርጅቶችን ያገኛሉ፡፡ የእነዚህ ፓርቲዎች ዋነኛ የትግል ማዕቀፍ “ጥያቄው” አለመመለሱን የሚያሳይ ነው፡፡ በአገሪቱ ከመቼውም ግዜ በላይ መንግስትን በትጥቅ ትግል ለማንበርከክ ዱር ቤቴ ያሉ “ብሔር ተኮር” ድርጅቶች ስለመኖራቸውም እየተደመጠ ነው፡፡
በመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ጭምር ዘውጌ ተኮር ግጭቶች በስፋትና በብዛት እየተደመጡ ነው፡፡ “በኢትዮጵያዊነት” ጥላ ተሰባስበው የትውልድ መንደራቸውን በመልቀቅ በሌሎች ክልሎች ሀብትና ንብረት ያፈሩ ኢትዮጵያዊያን በገዛ አገራቸው እንደ ባይተዋር ተቆጥረው “እየተገደሉ ነው፡፡ በአሩሲ፣ በአርባጉጉ፣ በበደኖ፣ በአፋር፣ በትግራይ፣ በወለጋ፣ በአሰበ ተፈሪ፣ በጋምቤላ፣ ኦጋዴን፣ ጉራፈርዳና በቦረና “ከክልላችን ውጡ” የተባሉ የሌላ ክልል ተወላጆች ተፈናቅለዋል፣ ንብረታቸውን ተዘርፈዋል፣ ከእነ ህይወታቸው ጉድጓድ ውስጥ ተወርውረው ሴቶቻቸው ተደፍረዋል፡፡
በዘመነ ደርግና ከዚያ ቀደም በነበሩ አስተዳደሮች ግጭቶች የሚነሱባቸውና የሰው ህይወት ለከፋ ጉዳት የሚጋለጥባቸው አጋጣሚዎች የነበሩ መሆናቸውን መካድ ባይቻልም እነዚህ ግጭቶች ግን ይነሱ የነበሩት በግጦሽ መሬት ፍለጋ እንደነበር መዘንጋት አይገባም፡፡ በአገሪቱ የጐሳ ፖለቲካ አየሩን ከተቆጣጠረበት ከ22 ዓመታት ወዲህ ግን የግጭቶች ይዘትና መንስኤ ወደ አንድ ጫፍ በማዘንበል ላይ ይገኛል፡፡ “ክልላችንን ለቅቃችሁ ውጡ” የሚለው ድምፅ በሁሉ ልብ ማስተጋባት ሲጀምር “በህዝብ መካከል አለመተማመንን በመዝራት በመጨረሻ የሚያሳጭደው ውጤት አገርን ለመበታተን ይዳርጋል፡፡ የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል የሚከበረውም “እኛና እነርሱ” በሚል መንፈስ መሆኑም የተቀበረው ፈንጂ ሰዓቱን እየሞላ እንዲሄድ ከማድረግ ውጪ የሚፈይደው ነገር ስለመኖሩ ብዙዎች ይጠራጠራሉ፡፡
ሁሉም የራሱን መንደር እየፈለገ ወደቀረበው እንዲሄድ የሚያደርግ መድረክ መፈጠሩን የሚተቹት ዶክተር ዘውዱ ውብእንግዳ “የፌደራሊዝም ታሪካዊ አመጣጥ” በሚለው መጽሐፋቸው ትዝብታቸውን እንዲህ ያሰፍራሉ፡፡ “በደርግ ዘመን ቀበሌዎች ስብሰባ ህዝቡን ሲጠሩ በ … ቀበሌ የምትገኙ … አዳራሽ ስብሰባ ስላለ እንዳትቀሩ ይሉ ነበር፡፡ አሁን ግን … ብሔር ተወላጅ የሆናችሁ … አዳራሽ እንድትገኙ ማለት ተጀምሯል፡፡ በፊት በአንድ ቀበሌ መኖር የአብሮነት መለኪያ ተርጐ ይወሰድ ነበር፡፡ አሁን ግን በአንድ ቀበሌ መኖር ብቻ በቂ ሳይሆን የብሔር ማንነት እንደመታወቂያ እየተወሰደ ነው” ይላሉ፡፡ ልዩነቶቻችን ጐልተው እንዲታዩ የሚደረጉባቸው መድረኮች በመንግሥት አታሞ እየተጐሰመላቸው አጀንዳ ሲሆኑ ከማየት የበለጠ ህመም የሚፈጥር ነገር የለም፡፡
በዓሉ የሚከበርባቸው ሥነ ሥርዓቶች ለኢህአዴግ ቱባ ባለስልጣናት አትሮንስ በመሆን ከማገልገል በዘለለ የብሔር ፖለቲካው፣ ፌዴራሊዝሙና የክልል መንግሥታት ነጻነት ለውይይት የሚቀርብባቸው መድረኮች አለመዘጋጀታቸውና እስካሁን ብሔርን/ዘውጌን ተገን በማድረግ በተፈጠሩ ቀውሶች ዙሪያ ውይይት የሚደረጉባቸው መንገዶች አለመፈጠሩ በእኔ እምነት በዓሉን “ከፈንጠዝያ” የዘለለ አያደርገውም፡፡ የአማራው ባህል ለትግሬው፣ የጉራጌው ለኦሮሞው፣ የከምባታው ልጅ ለስልጤው እየተሰጠች ያደግንባት አገር፣ አፋሩ ለሃድያው ዘብ የሚቆምባት ምድር ያፈራችን ሰዎች ለአክሱም ሀውልት ጋምቤላው የሚጨነቅባት የቅኖች ምድር ኢትዮጵያ በብሔር ፖለቲካ በናወዙ ጥቂት ቡድኖች ትልቁን ምስል ጠብቃ እንድትኖር እነዚህ መድረኮች “የእኛና የእነርሱ” የሚሉ ስሜቶች ስር ሳይሰዱ የሚቀርቡባቸው ሊሆኑ ይገባል፡፡ ያን ጊዜም “የተቀበረው ፈንጂ” ይመክናል፡፡
የብሔር ፖለቲካ መዘዝ
በአገሪቱ ከ84 የሚልቁ ብሔረሰቦች እንዳሉ ከመነገሩ ባሻገር የትኛው የማኀበረሰብ ክፍል ብሔር፣ የትኛው ብሔረሰብ ወይም ሕዝቦች የሚሰኙት የትኞቹ እንደሆኑ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ በአንዳንድ አደባባዮች የጆሴፍ ስታሊንንና የዋለልኝ መኮንን ንግግሮች እንደወረደ በመደስኮር “አንደበተ ርትዕ” ተብለው የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ እንኳን እነዚህን የማኀበረሰብ ክፍሎች ሳይተነትኑ አልፈዋል፡፡ ከስምንት ዓመት ወዲህ መንግሥት የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል በተለየዩ ሥነ ሥርቶች እንዲከበር እያደረገ ነው፡፡
በዚህ ቀን ከተለያዩ የማኀበረሰብ ክፍሎች የመጡ ሰዎች በመሰባሰብ እለቱን ይዘክራሉ፡፡ በዚህ ቀን እንኳን የትኛው ብሔር፣ የትኛውብሔረሰብ፣ የትኞቹ ደግሞ ህዝቦች መሆናቸው አይታወቅም፡፡ ነገር ግን ፍቺ ባልተገኘበት ሁኔታ በዓሉ ይከበራል፡፡ ሌላው አስገራሚ ነገር በህገ መንግሥቱ “ሕዝቦች” ተብለው የተጠቀሱ ክፍሎች ምንም አይነት መገለጫ የሌላቸው መሆኑ ነው፡፡ ለምሣሌ ህገ መንግሥቱ ስለመሬት የሚለውን እንውሰድ፡፡ መሬት የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ስለመሆኑ ተጠቅሷል፡፡ በዚህ መነሻነትም ክልሎች በቋንቋ መነሻነት የየራሣቸውን ወሰን እንዲካለሉ ተደርገዋል፡፡ ህዝቦችስ? ነገሩን ትንሽ ለጠጥ በማድረግ እንውሰደው፡፡
በጉራፈርዳ ሰፍረው የነበሩ አማሮች “እንደ ህገወጥ ሰፋሪ ታይተው በክልሉ መንግሥት ውሣኔ ለአመታት ይዘውት የቆዩትን መሬት ጥለው እንዲሰደዱ ተደርገዋል፡፡ መሬቱን እንዲለቅቁ የተደረጉት “የክልሉ ተወላጅ” ባለመሆናቸው ብቻ ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች የክልሉ ተወላጅ ባይሆኑም ሕዝብ በመሆናቸው እንደ ህገ መንግሥቱ የመሬት ባለይዞታነት መብታቸው ሊከበርላቸው ይገባ ነበር፡፡ የፌዴራሊዝሙ ተሳክሮት ዶክተር ዘውዱ በመጽሐፋቸው ለፌዴራል መንግሥት ምስረታ መንስኤ የሚሆን መሠረታዊ ነጥብ “ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ መንግስታት ወይም የየራሣቸውን መንግሥታዊ አስተዳደር ያካበቱ ሕዝቦች በፈቃደኝነት ላይ ተመስርተው የሚያቋቁሙት ሦስተኛ መንግሥት ነው፡፡ ስለሆነም ፌዴራላዊ መንግሥት ከትንሹ ቁጥር ሳንነሳ የሦስት መንግሥት ጥምር ነው” ይላሉ፡፡ በዘውዱ ገለፃ ፌዴራሊዝምን በማስተዋወቅ የመጀመሪያዋ ተጠቃሽ አገር ለመሆን የበቃችው ለ100 ዓመታት ያህል በእንግሊዝ ቅኝ ተገዝታ የነበረችው አሜሪካ ናት፡፡
ቅኝ ገዢዋ እንግሊዝ ሀገሪቱን በ13 የቅኝ ግዛት አስተዳደሮች በመከፋፈል ስታስተዳድር ቆይታለች፡፡ አሜሪካኖች ራሣቸውን ነፃ ካወጡ በኋላ ተከፋፍለው የነበሩት ክልሎች በፌዴራሊዝም አማካኝነት መልሰው አንድነታቸውን አግኝተዋል፡፡ ሌሎች በቅኝ ግዛት ስር የነበሩና የተለያዩ አስተዳደሮችም የአሜሪካውን ፌዴራሊዝም በአርአያነት በመከተል የተበታተኑት አንድ መሆን ችለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ የመንግሥት አወቃቀር ግን የጐሳ በመሆኑ በአለም ከሚታወቀው የፌዴራሊዝም አመሰራረት ጽንሰ ሀሣብ ያፈነገጠ ነው፡፡
በህገ መንግሥቱ ድንጋጌ መሠረት የክልል መንግሥት ለማቋቋም መመዘኛ ሆኖ የቀረበው ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝቦች በሚል መነሻነት ነው፡፡ አስቀድሜ ለመግለጽ እንደሞከርኩት በአገሪቱ ውስጥ ከ84 የሚልቁ ብሔረሰቦች ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን ክልል እንዲመሰረቱ እውቅና የተሰጣቸው ዘጠኙ ብቻ ናቸው፡፡ ቀሪዎቹስ? ለምን ክልል የመመስረት መብትን ተነፈጉ?
በህገ መንግሥቱ በዘጠነኛ ክልልነት የተቀመጠው “የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል” ተብሎ እንዲቀመጥ ተደርጓል፡፡ የፌዴራሉመንግሥት ክልሎች የተመሠረቱት ቋንቋን ማዕከል ባደረገ መልኩ ቢሆንም ይህ ወደ ደቡብ ሲያመራ “ጂኦግራፊያዊ” እንደሆነየተፈለገበት መንገድ ለማንም ግልጽ አይደለም፡፡ በደቡብ ክልል ከ46 የሚልቁ ብሔረሰቦች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ብሔረሰቦች በሌሎች ክልሎች የሚገኙ ብሔረሰቦች የራሣቸውን ክልልና መንግሥት የሚመሰርቱበትን መብት ሲጐናጸፉ በደቡብ ያሉት ግን ይህንን መብት ተነፍገዋል፡፡
የፌዴራሊዝሙ አወቃቀር በቋንቋ በአንድ ቦታ ሲሰራ በሌላ ቦታ በጂኦግራፊ መሆኑም የአወቃቀሩን ተሳክሮት ወለል አድርጐ ያሳያል፡፡ በጎሳ ላይ የተንጠለጠለ የመንግሥት አወቃቀር በሩዋንዳ፣ ሶማሊያ፣ ኮሶቮና ሩሲያን በመሳሰሉ አገራት የፈጠረውን ሰብአዊ ቀውስ የተመለከቱ ሰዎች የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግሥት የአወቃቀር ተሳክሮት በአገሪቱ ላይ በጊዜ የማይተነብይ ምስቅልል ሊፈጥር እንደሚችል ይጠቁማሉ፡፡
http://www.goolgule.com/
posted by Gheremew Araghaw
Share this:
• LinkedIn
• Twitter
• Facebook
• Print
• Email
• Google
• 
Like this:
Like Loading...
Posted in Political Opinion | Leave a Comment 
10 Dec 2013 
አቶ ሙሐመድ ኢብራሒም ማእከላዊ እስር ቤት ዉስጥ በደረሰባቸው ድብደባ ህይወታቸዉ ማለፉ፤ ሆድ-እቃቸዉ ተከፍቶ ኩላሊታቸዉ መሰረቁ ታወቀ 

“አስክሬን ምንሊክ ሆስፒታል ሄደን እንድንወስድ ስልክ ተደወለልን፤ ለሞቱ ከደነገጥነዉ በላይ አስክሬኑን ስንመለከት ፍጹም ተረብሸናል፤ ከአዉሬ አፍ የተረፈ አስክሬንነበር ሚመስለዉ…ሰዉነቱ ተቦጫጭቋል!” ጓደኞች
አቶ ሙሐመድ ኢብራሒም ማ
ዋሽንግተን ዲሲ፤ ህዳር 30/2006 (ቢቢኤን) ፦ በአዲስ አበባ ዉስጥ በቦሌ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የነበሩት አቶ ሙሐመድ ኢብራሒም ቀደም ሲል በጥቅምት 4/2006 በአካባቢዉ ላይ ፈንድቶ ከነበረዉ ቦንብ ጋር በተያያዘ መልኩ ለምርመራ ማእከላዊ እስር ቤት መግባታቸዉ እና በማእከላዊ ቆይታቸዉ ምግብ እንዳይገባላቸዉ ቤተሰብ እንዳይጠይቃቸዉ መከልከሉም ለማወቅ ተችሏል።
እንደ አቶ ሙሐመድ ጓደኛ አገላለጽ ግለሰቡ ለተጠረጠሩበት ወንጅል የሚያበቃቸዉ ጉዳይ ባይኖርም፤ከገቡበት ማእከላዊ እስር ቤት በደረሰባቸዉ ከፍተኛ ድብደባ በህይወት መዉጣት አልቻሉም።
ለሐያ ዘጠኝ ቀናት ማእከላዊ እስር ቤት የታሰሩት አቶ ሙሐመድ ምን ያህል ድብደባ እንደደረሰባቸዉ ባይታወቅም ጭንቅላታቸዉ በጣም መጎዳቱን፣ሰዉታቸዉ እንደበለዘ፣ብዙ ሰንበሮች መታየታቸዉ፣ሆድ እቃቸዉ ተከፍቶ ኩላሊታቸዉ መሰረቁን ለአስራ ሁለትአመታት የሚያዉቋቸዉ ጓደኛቸዉ በሐዘን ይገልጻሉ።የዱር አዉሬ ቦጫጭቆ የገደለው ይመስላል በማለት ሁናቴዉን የሚገልጹት ጓደኛ ከመንግስት አካላትም ይሁን አስክሬኑ ከመጣበት የሚኒሊክ ሆስፒታል ስል አቶ ሙሐመድ አሟሟት የተሰጠ መረጃ አለመኖሩን፤ በደም በተጨማለቀ ከፈን የተከፈነ አስክሬን ብቻ መመለሱን ገልጸዋል።
ቤተሰቡ ጉዳዩን ለሰብአዊመብት ተሟጋች ለሆኑ ድርጆቶች እንዳያመለክት ከፍተኛ ዛቻ ደርሶበታል፤በቅርበት የሚያዉቋቸዉ እንኳ በሞታቸዉ ከማዘን በስተቀር ስለ አሟሟታቸዉ ከፍርሃት የተነሳ መናገር አይችሉም በማለት የሚያስረዱት ጓደኛቸዉ ሁሉም ለሞቱ ከደነገጠዉ በላይ አስክሬኑን በማየት ተሸማቋል ይላሉ።
በጥሩ ስነምግባራቸዉ የሚታወቁት አቶ ሙሐመድ ኢብራሒም ሐማኖትን ተግባሪ፣ የቤተሰብ አስተዳዳሪ ከመሆን በስተቀር አገርን ወገንን ሊጎዳ በሚችል የአሸባሪ ተግባር የሚጠረጠሩ አይደልም በማለት በሐዘን የሚናገሩት ጓደኛ ሟቹ የሰባት ልጆች አባት እንደነበሩ ቤተሰቡም ለአደጋ መጋለጹንም አስረድተዋል።
በጥቅምት 4/2006 መንግስት በቂ መረጃ ለህዝብ ማቅረብ ባልቻለበት፤ የመንግስት ደህነነቶች አለም አቀፋዊ ትኩረትን ለመሳብና ፖለቲካዊ ጥቅምን ለመጎናጸፍ በቦሌ ክፍሌ ከተማ አደርሰዉታል ተብሎ በሚነገረዉ የቦንብ ፍንዳታ፤ ማመካኛን ለማግኘት የሱማሌ ብሔር ተወላጅ የሆኑትን የአቶ ሙሐመድ ህይወትን መንግስት መስዋዕት አድርጓል በማለት አስተያያት የሚሰጡ ወገኖች አሉ።በትላንትና እለትዉ የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን በጅጅጋ ከተማ ድረስ ባሸበረቀ መልኩ አከበርኩ ለሚለዉ መንግስት፤ የአገሩን ዜጋ በብሔር ነጥሎ ማእከላዊ እስር ቤት አስገብቶ መግደሉ ለመንግስቱ አሳፋሪ ከመሆኑም ባሻገር የስርዓቱን መላሸቅ አመላካች ነዉ የሚሉም አሉ።
የአቶ ሙሐመድ ኢብራሒም ታስሮ ለህልፈት መብቃት፤ የሆድ እቃቸዉ ተቀዶ የኩላሊታቸዉ መሰረቅ ከፍተኛ ምርመራ የሚያሻዉ ቢሆንም፤በሟች አስክሬን ላይ የተፈጸመው ወንጀል ስርዓቱ በህይወት ባሉ ብቻ ሳሆን በሙታንም ላይ ግፍ እንደሚፈጽም የሚያረጋግጥ ነዉ፤ በሐሰት አስሮ በመደብደብ፣በመግረፍ፣እስር ቤት ዉስጥ ከማሰቃየት አልፎ፤ ታሳሪዎች እስር ቤት ዉስጥ ሲሞቱ ሆድ እቃ ተከፍቶ የሰዉነት አካል መቸርቸር ተጀምሯልና!.. ኢትዮጵያ ወዴት እያመራች ነዉ? የሚለዉ ጥያቄ የብዙሐኑ ነዉ።
http://goo.gl/DxqNyV
posted by Gheremew Araghaw

Share this:
• LinkedIn
• Twitter
• Facebook
• Print
• Email
• Google
• 
Like this:
Like Loading...
Posted in News | Leave a Comment 
10 Dec 2013 
ግልጽ ደብዳቤ ለግንቦት ሰባት መሪዎችና አባላት – ግርማ ካሳ 


በቅድሚያ ሰላምታዬ ይድረሳችሁ። ከአምስት አመታት በፊት ከአንዳንዶቻችሁ ጋር፣ በቅርበት፣ በቅንጅት ድጋፍ ማህበራት ዉስጥ አብረን ሰርተናል። አብረን ለሰላም ለዲሞክራሲ፣ ለሕግ የበላይነት መስፈን፣ ለዜጎች ሰብዓዊ መብት መከበር፣ ለሕሊና እስረኞች መፍታት ስንጮህ፣ ስንሰራ፣ ስንደክም፣ ስንመክር ነበር። መሃከል መንገድ ላይ የፖለቲካ ስትራቴጂ ልዩነቶች ተፈጠሩ። «ሁለ ገብ» የሚል የትግል ስልት መርጣችሁ የተለየ መስመር ያዛችሁ። እኛ ደግሞ በዚያ በሰላሙ መንገድ ቀጠልን። አንዳንዴ ልዩነቶቻችን ከረዉ በድህረ ገጾች፣ ፓልቶክ ክፍሎች፣ ጋዜጣዎች ፣ ሬዲዮኖች የተካሰስንበትም ጊዜ ጥቂት አይደለም።
ወቅቱ ትብብርን ይጠይቃል። በተቃዋሚዉ ጎራ ያለው ወገን ሁሉ በአንድነት ይሰባሰብ ዘንድ፣ እናንተም የተቃዋሚዉ አንዱ አካል እንደመሆናችሁ፣ እናንተ ዘንድ ያሉ፣ መሰባሰብ እንዳይኖር እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮችን፣ ትመረምሩና ታስተካክሉ ዘንድ ይሄን ጽፊያልሁ። ክስ ሳይሆን፣ መረጃ ላይ የተመረኮዘ ምክር አዘል አስተያየት በማቅረብ፣ ቻሌንጅ ላደርጋቹህ እሞክራለሁ።

ኤርትራና ኤርትራ የምትረዳቸው ድርጅቶች
ግንቦት ሰባት የተቋቋመው ሰኔ ወር 1999 ዓ.ም ነዉ። ከስድስት ወራት በኋላ ስድስተኛ አመቱን ያከብራል። ድርጅታችሁ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ብዙ የምናውቀዉ ነገር የለም። ነገር ግን ከኢሳያስ አፈወርቂ ጋር የቅርብ ግንኙነት እንዳላችሁ ግን ግልጽ አድርጋቹሃል። የኤርትራ መንግስት እናንተ ወታደሮች ስለሌላችሁ፣ ከትግራይ ብሄራዊ ዴሞክራሲ ንቅናቄ(ትብዴን) ጋር አብራችሁ እንድትሰሩ እንደጠየቃችሁና እንደተስማማችሁ አንዳንድ መረጃዎች ይጠቁማሉ። እናንተ ፖለቲካዉን ልትይዙ፣ እነርሱ ደግሞ ሚሊታሪዉን። (ልክ ያኔ ሕወሃት ሚሊተሪዉን ይዞ፣ እነ ታምራት ላኔ ደግሞ ፖለቲካዉን እንደያዙት)
በጎንደር፣ በወሎ በሸዋ.. ፊት ፊት እየቀደሙ ፣ በፕሮፖጋንዳ ሕዝቡን እያሳምኑ፣ ትልቅና ወሳኝ የፖለቲካ ሥራ እየሰሩ፣ ሕወሃትን አዲስ አበባ ያስገቡት እነ ታምራት ላይኔ ነበሩ። ታዲያ፣ ምናልባት የኤርትራ መንግስት፣ ታሪክን ደግሞ፣ እናንተን ዳግማዊ ታምራት ላይኔዎች ሊያደርጋቹህ፣ የርሱን ፍላጎት ሊያስጠብቁ የፈጠራቸዉን ስልጣን ላይ ሊያስወጣ አስቦ እንደሆነ፣ ገምታችሁ ታውቃላችሁ ? እስቲ ጠይቁ፣ ኦነግ፣ የአርበኞች ግንባር የመሳሰሉ በርካታ ድርጅቶችን በልጦ፣ እንዴት ትብዴን በወታደራዊ አቅሙ ጠንካራ ሊሆን ቻለ ? ምናልባትም የ«ትግራይ ሽምቅ ተዋጊዎች» የተባሉት በርግጥ የትግራይ ሰዎች መሆናቸውን የሚያሳይስ ምን ማረጋገጫ አለ ? ከሰራኤ፣ ሐማሴን አኮሎ ጉዛይ የመጡ ኤርትራዉያን ቢሆንስ ?
ከሕወሃት በስተቀረ የኤርትራ መንግስት የረዳቸዉና የደገፋቸው ድርጅቶች፣ አንዳቸዉም ለቁም ነገር ሲደርሱ አላየንም። አልሻባብ እየተመታ ነዉ። በሶማሊያ በፑትላንድ፣ በሶማሊላንድ፣ በጁባላንድ እና ሞቃዲሾ አካባቢ ለአመታት ታይቶ ያልታወቀ መረጋጋት እየታየ ነዉ። በመሆኑም ኦብነግ መሳሪያና ስንቅ የሚያሳልፈበት ቀዳዳዎች እየተዘጉበት ነዉ። ድርጅቱ እየተከፋፈለ ፣ እየመነመነ፣ አብዛኞቹ አባላቱም ከሕወሃት/ኢሕአዴግ ጋር በመነጋገር ላይ ናቸው።
ኦነግን ከተመለከትን ደግሞ፣ በአስገራሚ ሁኔታ ፈረካክሷል። እንደ ከማል ገልቹ፣ ሃይሉ ጎንፋ የመሳሰሉ ተወዳጅና ኢትዮጵያን ወዳድ ጀነራሎች የቁም እስረኞች ሆነዋል። እንደ ዶር ዲማ ነግዎ፣ ሌንጮ ለታ ያሉ አንጋፋ የቀድሞ አመራር አባልትና መስራቾችም፣ የኦሮሞዎች ጥያቄ በመገንጠል ሳይሆን በዲሞክራሲ ይፈታል ብለዉ፣ እራሳቸዉን ከኤርትራ መንግስት ለይተው፣ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመታገል፣ የኦሮሞ ዴሞርካሲያዊ ግንባርን መስርተዋል። ብዙ አልተረጋገጠም እንጂ፣ ወደ አገር ቤት ገብተው ለመታገል ሃሳብ እንዳላቸውም የሚገልጹ ዜናዎችም የተናፈሱበት ሁኔታም አለ።
ሌላዉ በኤርትራ በኩል ይንቀሳቀሳል የሚባለው የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ነዉ። ይህ ግንባር በተለያዩ ጊዜ የተለያዩ የአመራር አባላት ነበሩት። ነገር ግን ድርጅቱ ጠንከር በሚልበት ጊዜ አመራር አባላቱ እየታሰሩ ፣ ይሰወራሉ። ሻእቢያ ጠንካራ የኢትዮጵያዊነት ስሜት ያለው ድርጅት እንዲወጣ በፍጹም ፍላጎት ስለሌለው ፣ የአርበኞች ግንባርም አደግ ሲል እየተኮረኮመ፣ ይኸው ከአመታት በፊት የነበረበት ደረጃ ነዉ ያለው።(እንደዉም ሳይብስ)
እንግዲህ ይሄን ሁሉ የምተነትነዉ ፣ ከኤርትራን መንግስት ጋር መስራት ታክቲክሊና ሚሊታሪሊ እንደማያዋጣ ለማሳየት ነው። በኤርትራ በኩል እንታገላለን የሚሉ አንዳቸውም፣ ይኸው ሕወሃት/ኢሕአዴግ ስልጣን ከያዘ 21 አመታት አለፉ፣ አንድ ቀበሌ ነጻ አላወጡም። ወኔዉና ጀግንነቱ ሳይኖራቸው ቀርቶ አይደለም። ነገር ግን የኤርትራ መንግስት መዳፍ ዉስጥ ስላሉ እንጂ። እናንተንም ለጊዜዉ መጠቀሚያ ያደርጓቹሃል። ትንሽ አደግ ስትሉ ግን መመታታችሁ አይቀርም። ከኦነግ፣ ከአርበኞች ግንባር ከመሳሰሉት መማር አለባችሁ። ግድ የለም ከሻእቢያ ጥገኝነት ዉጡ።

ኢሳያስና የኤርትራ ሕዝብ
ምን ያህል የኤርትራን ፖለቲካ እንደምትከታተሉ አላውቅም። የኤርትራን ሕዝብ ከተቀረዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለይቼ ስለማላየው የኢትዮጵያ ድህረ ገጾችን እንደማነበዉ፣ የኤርትራን ድህረ ገጾች እከታተላሁ። እናንተም እስቲ ጊዜ ወስዳችሁ ተከታተሉ። እስቲ ኤርትራዉያንን ቀረብ ብላችሁ አነጋግሩ። የሚያሳዝን፣ የሚያስለቅስ ታሪኮችን ነው የምትሰሙት።በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ በሱዳን በኩል አድርገዉ፣ ኢትዮጵያ ለመግባት ሲሰደዱ፣ እባብ እየነደፋቸው፣ ተይዘው እየተገደሉ ሞተዋል። በሳዋና በተለያዩ ቦታዎች የኤርትራ ወጣቶች እየተቃጠሉ ነዉ። ኢሳያስ የኤርትራን ሕዝብ እያረደ ያለ እብድ ነዉ።
እናንተ፣ ቢያንስ ቢያስንስ «ለሰብዓዊነት ፣ ለፍትህ፣ ለሰላም፣ ለዲሞክራሲ የቆምን ነን» ትላላችሁ። ለዚያም ስትሉ አንዳንዶቻችሁም በቃሊቲ ትልቅ ዋጋ ከፍላቹሃል። ነገር ግን ከዚህ እብድ ጋር መስራታችሁ ምን ይባላል? ይሄስ አያሳንሳችሁምን ? በጣም ያሳንሳቹሃል። ከዚህ እብድ ጋር ባበራችሁ ቁጥር፣ ከኤርትራ ሕዝብ ጋር እየተጠላችሁ ነዉ። ኢሳያስ የጉበት በሽተኛ ነዉ ይባላል። እንቁላላችሁን ሁሉ እርሱ ቅርጫት ዉስጥ ከከተታችሁ፣ ነገ ሰዉዬው የሞተ እለት፣ ምን ልትሆኑ ነው ?

እርግጥ ነዉ ኢሳያስ ጥቂት አየር መቃወሚያዎችን ፣ ጥቂት ሺህ ዶላሮችን ፣ የወታደር ጫማዎችን ሊወረወርላችሁ ይችላል። ኮምፖሽታቶ ዳር፣ ከፈራረሱ ፎቆች አንዱ ዉስጥ ጽ/ቤት ሊሰጣችሁ ይችላል። ነገር ግን ሕሊናችሁን ከመሸጥ፣ በአፍሪካ ከነኢዲአሚን ጎን በሚሰለፍ ቡድን፣ ሰይጣናዊ የሰብአዊ መብት ረገጣ ሲፈጸም እያያችሁ፣ እንዳላየ ሆናችሁ ዝም ከማለት፣ ከሕዝቡ ጋር በመጣላትና ታሪካዊ ጠባሳ ከመፍጠር ፣ ከወዲሁ ከዚህ ያበደ አገዛዝ እንድትለዩ እማጸናቹሃለሁ። ግድ የለም ከሻእቢያ ጥገኝነት ዉጡ።

ኤርትራና የአለም አቀፍ ማህበረሰብ
እንደምታውቁት ኢሳያስ በአለም አቀፍ ማህበረሰብ የተገለለ ነዉ። ከቀይ ባህር አሳዎች ጋር በስተቀረ፣ ከኤርትራ አጎራባቾች ሁሉ ጋር ጦርነት ገጥሟል። የኤርትራዉያን ደም ቢፈስ ምንም የማይመስለው፣ የሕዝቡን ደም በመጠጣት የሚረካ የተረገመ ሰው ነዉ።

በዚህም ምክንያት የተባበሩት መንግስታት የፀጥታዉ ምክር ቤት፣ በኤርትራ ላይ በርካታ ዉሳኔዎችን አላስልፏል። ከዉሳኔዎቹ መካከል ፣ ምንም አይነት የጦር መሳሪያ ወደ ኤርትራ እንዳይገባ፣ ኤርትራ የጎሮቤት አገሮች ላይ የምታደርሰውን «ሽብር» እንድታቆም፣ ከጎሮቤት አገሮች ጋር ያላትን ችግር በሰላም እንድትፈታ፣ በግዛቷ ያሉ ሽምቅ ተዋጊዎችን መደገፍ እንድታቆም የሚጠይቁ ዉሳኔዎች ይገኙበታል።

እንግዲህ ይሄ የሚያሳየው ከሻእቢያ ተወዳጅቶ የሚደረግ እንቅስቃሴ ከአለም አቀፍ ማህበረሰብ ጋር የሚያጋጭ መሆኑን ነዉ። በተዘዋዋሪ መንገድ የጸጥታው ምክር ቤት ዉሳኔን እየጣሳችሁ ነዉ። የአለም አቀፍ ማህብረሰብን ከበሬታ እያጣችሁ ነዉ። አንድ ምሳሌ ልጥቀስ። በቅርቡ ከግንቦት ሰባት አመራር አባላት ጋር የቅርብ ግንኙነት የነበራቸው የተከበሩ አና ጎሜዝ አዲስ አበባ መሄዳቸዉን እና በዚያም ከነአባ ዱላ ጋር መነጋገራቸው በሰፊው ተዘግቧል። የአና ጎሜዝ ወደ አዲስ አበባ መሄድ፣ የተለያዩ ትርጓሜ ሊሰጠው ይችላል። ነገር ግን፣ ቢያንስ ቢያንስ የግንቦት ሰባት ድርጅታችሁን የዲፕሎማሲ ሽንፈትና ኪሳራ በግልጽ ያሳየ ነዉ። ግድ የለም ከሻእቢያ ጥገኝነት ዉጡ።


ማጠቃለያ
እንግዲህ የመከራከሪያ ነጥቦቼን በግልጽ አስቀምጫለሁ። እዉነት ለመስማት ከለመፈለግ የተነሳ፣ የቀረቡ ሃሳቦች ላይ ሳይሆን፣ ሃሳብ አቅራቢዎች ላይ ማነጠጠሩን ልትመርጡ ትችላላችሁ። እንግዲህ የእናንተዉ ምርጫ ነዉ። ነገር ግን ተስፋ አደርጋለሁ፣ ቆም ብላችሁ እንደምታስቡ።

ይሄን መረዳት አለባችሁ፣ ነጻነታችንን ኢሳያስ አፈወርቂ አይሰጠንም። ጠዋትና ማታ አገዛዙን ስለረገምን ለዉጥ አናመጣም። በአሁኑ ወቅት ብቸኛው አማራጭ እኛው እራሳችን የምናደርገዉ የተባበረ ሰላማዊ ትግል ነዉ። ኢትዮጵያዉያን በአንድ ላይ ተባብረን፣ ሰላማዊ በሆነ መንገድ፣ ጥቂቶች የዘረጉትን ቀንበር መስበር እንችላለን። እባካችሁ የኢትዮጵያን ሕዝብ ኃይል አሳንሳችሁ አትመልከቱ። ከሻእቢያን ጥገኝነት ዉጡ። ወደ ቀደሞዉ ወደ «ቅንጅት» መንፈስ ተመለሱ። ያኔ በዘጠና ሰባት የጠበቅነዉን ያላገኘነው፣ በቂ ድርጅታዊ ሥራ ስላተሰራና በአመራር አባላት መካከል መከፋፈል ስለተፈጠረ፣ ሕዝቡ በአንድ ላይ በተደራጀት መልኩ፣ በሁሉም ክልሎች ማንቀሳስቀስ ስላልተቻለ እንጂ፣ የሰላማዊ ትግል ስላልሰራ ወይን የኢትዮጵያ ሕዝብ አቅም ስለደከመ አልነበረም። ካለፈዉ ትምህርት በመዉሰድ፣ ጥንቃቄ በተሞላበት፣ በክልሎች ሁሉ መረብን በመዘርጋት ፣ አቅማችንን፣ ገንዘባችንን በሙሉ አንድ ላይ በማሰባሰብ፣ የሚደረግ ሕዝባዊ ፣ ሰላማዊ የእምቢተኝነት ዘምቻ በርግጥ ዉጤት ያመጣል።

ሸንጎ፣ የብሄራዊ ሽግግር ምክር ቤት፣ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር፣ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ሶሊዳሪቲ የመሳሰሉ በርካታ ደርጅቶች ፣ በኢትዮጵያ ሕዝብ ተማምነዉ፣ አገር ቤት ለሚደረገዉ ሰላማዊ ትግል አጋርነታቸውን እየገለጹ ነዉ። የእናንተ ድርጅት፣ ግንቦት ሰባት፣ ከሻእቢያ ጋር ያለዉን ግንኙነት በአስቸኳይ በጥሶ፣ ከነዚህ ድርጅትች ጋር አብሮ ለመስራት ይሞክር። እዚህ ላይ አበቃለሁ። የሚሰማ ጆሮ ካለ እንግዲህ ይሰማል።
Muziky68@yahoo.com

No comments:

Post a Comment