Translate

Sunday, February 18, 2018

የትግላችን መጨረሻ ነፃነታችን ብቻ ነው! (የዲሲ የጋራ ግብረ ሃይል)

የዲሲ የጋራ ግብረ ሃይል
Ethiopians demonstration against the Amhara eviction
የዋሽንግተን ዲሲ የጋራ ግብረ ሃይል ከፈጣሪ በታች የምንመካበት የኢትዮጵያ ህዝብ ክንዱን አስተባብሮ ስለነፃነቱ በጋራ በመቆም ለነፃነቱ ገፋፊዎች ባሳየው ማንነቱ አንገታችንን እንድናቀና ስላደረገን ምስጋናችን ከልብ የመነጨ ነው።

ድል የመስዋዕትነት ውጤት ነውና ባለፉት ሃይ ሰባት አመታት ውድ ህይወታቸውን ሰለነፃነት ለገበሩ በእስርና እንግልት ከፍተኛ ዋጋ ለከፈሉ እንቁ ወገኖቻችን ከበሬታችን ወደር የለውም፤ በተለይ ከደቡብ እስከ ሰሜኑ ጫፍ ከምስራቅ እስከ ምእራብ እየተናነቁ ያሉ ወጣቶችን እንዲሁም በተለያየ የትግል ስልት ተሰልፈው የአቅማቸውን ላደረጉና እያደረጉ ላሉ ሁሉ ግብረ ሃይሉ አድናቆቱን ይገልፃል።
እኛ በግብረ ሃይሉ የተሰባሰብን ኢትዮጵያዊያን መነሻና መድረሻችንን ኢትዮጵያን አድርገን የድርጅትና የሃይማኖት አጥርን ሰብረን በአንድነት እየተጓዝን ያለን አባላት የህዝባችንን የአንድነት ውጤት እያጣጣምን ነገር ግን ወያኔ ካለው ባህሪ በመነሳት ሳንዘናጋ ትግላችንን ለመቀጠል መነሳታችንን ደማቸው እየፈሰሰ ባሉት ወገኖቻችን ስም እየገለፅን አገራችንን ቀስፎ ከያዛት ዘረኛ አገዛዝ ነፃ እስክትወጣ ድረስ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ለማድረግ ቃል እየገባንና ሁሉን አቀፍ የሆነ ስብስብ ለመፍጠር የሚደረጉ ጥረቶችን እያደነቅን ለተግባራዊነቱ ራሳችንን ማዘጋጀታችንን እንገልፃለን።
በድጋሚ በወገኖቻችን ደም ለተገኘው ድል ባለፉት አመታት ድምፅ ለሌለው ወገናችን ድምፅ ለሆናችሁ ሁሉ እንኳን ደስ አለን እያልን በተጨማሪም ከወያኔ የግፍ እስራት ለተፈቱትና ለቤተሰቦቻቸው የተሰማንን ደስታ እየገለፅን ያልተፈቱትም ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በኢትዮጵያውያን ህዝብ ትግል እንደሚፈቱ እምነታችን የፀና ነው።
በመጨረሻም በአሁኑ ወቅት የተገኙት ውጤቶች ሁሉ የትግላችን የመጨረሻ ምእራፍ መጀመሪያ እንጂ በራሱ ግባችን ስላልሆኑ አሁንም እንደ በፊቱ የተገኙት ድሎች ሳያዘናጉን የመጨረሻ ግባችን ለሆነው ውድ አገራችንንና ህዝባችንን ከዘረኛውና ግፈኛው የወያኔ ስርአት ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ የምንገላገልበትንና ፍትህ፣ ዲሞክራሲና እኩልነት የሰፈነባት ነፃ አገር ለመመስረት የምንችልበትን ሁኔታ እንፈጥር ዘንድ በአገር ቤት ይሁን በውጭ የምንገኝ ነፃነት አፍቃሪዎች አሁንም ዘር ሃይማኖት ሳይለያየን ለማይቀረው ድል የተጋረጠብንን ሁሉ በጋራ እንድናስውግድና በተገኙትም ጥቃቅን ድሎች እንዳንዘናጋ አበክረን እየገለፅን የተፋፋመውን ትግል ከዳር እንድናደርስ በመከራ ውስጥ ባሉት ወገኖቻችን ስም እንጠይቃለን።
ሞት ለዘረኛው ወያኔ!
አንድነት ሃይል ነው!
የዲሲ የጋራ ግብረ ሃይል dcjointtaskforce@gmail.com

No comments:

Post a Comment