Translate

Tuesday, February 21, 2017

ምዝበራ በየፈርጁ (ተሻለ መንግሥቱ)

ተሻለ መንግሥቱ 
ይህ የፍዳና የሰቆቃ ዘመን እስኪያልፍና የማይቀረው ወርቃማ የነፃነት ዘመን እስኪመጣ በሰመመን የምቆይበትን ብልኃት ባገኝ ወደድኩ፡፡ እንዲያ ዓይነት ጥበብ ተገኝቶ እንደእሥራኤሉ ፕሬዝደንት (ኤርየል ሻሮል) በሞትና በሕይወት መካከል አሸልቦ ሳይሰሙ ሳይለሙ ብዙ ጊዜ መቆየት ለእንደኔ ያለው ሰው ተፈልጎ አይገኝም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የምንኖር ጥቂት የማንባል ዜጎች አብዛኛው የምንሰማውና የምናየው ነገር ግራ እያጋባን በዚህ ሁኔታ ውስጥ ከመኖር ይልቅ አለመኖርን እንመርጣለን፡፡ አስደንጋጭ ወቅታዊ ሁኔታ ውስጥ ተዘፍቀናል፡፡ ራሳችንን እየታመምን የምንኖር አለን – በበኩሌ በጣም እያመመኝ እንደምኖር ብደብቅ ዋሸሁ፡፡
Kinfe Dagnew (B. Gen.), the chief executive officer (CEO) of the Metal & Engineering Corporation (MetEC)
Kinfe Dagnew (B. Gen.), the chief executive officer (CEO) of the Metal & Engineering Corporation (MetEC)
ዛሬ ጧት ነው፡፡ ከአንድ ወዳጄ ጋር እንጫወታለን – ስለወያኔዎች ሁለንተናዊ የምዝበራ ሥልትና የሙስናው ቅጥአልባነት ነበር በንዴት እየተንጨረጨርን የምናወጋው፡፡ የቀራቸው እኮ የለም፤ ሁሉንም እነሱ ተቆጣጥረውታል፡፡ በአንዲት ቀን አዳር መክበር የሚቻለው ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ መሆኑን ባለፉት 25 ዓመታት ውስጥ በተደጋጋሚ አስመስክረዋል፡፡ በአንዲት ቀን አዳር መክበር ብቻም ሳይሆን በአንዲት ቀን አዳር ማደኽየትም ሆነ አላንዳች በቂ ምክንያትና ፍትሃዊ ፍርድ አንድን ዜጋ መቅ ማውረድም እንደሚችሉ አስተዋይ ልቦና ላለው የዓለማችን ዜጋ አሳይተዋል፡፡ ላኪዎቻቸው ግን በወያኔዎች ዕኩይ ድርጊት ቢደሰቱ እንጂ አይገረሙም፡፡ እነዚህ የስቃያችን አበጋዞች ውጤቱን አስቀድመው የማያውቁትና ሲቻላቸው ደግሞ በርቀትም በቅርበትም የማይቆጣጠሩት አንድም ድርጊት በዓለም እንደሌለ የሚገነዘቡ  የፕላኔታችን ገዢዎች ናቸው፡፡

ሜቴክ የሚባለው የወያኔ ድርጅት ሀገሪቱን ራቁቷን እያስቀራት ነው፤ በላም አለኝ በሰማዩ የስኳር ፋብሪካ የውሸት ግንባታ ሂደት የሚያግበሰብሰው ገንዘብ አልበቃ ብሎ በሌሎች የመንግሥት ተብዬ ተቋማትም እጁን እየላከ የሀገሪቱን አንጡራ ሀብት እያሟጠጠው ነው – ኢትዮጵያን ማን ይድረስላት! እኛስ ምን እንሁን? ለማንስ ነው እግዚኦ የሚባለው – ለማን ነው የሚጮኸው? በዚህ ድርጅት የተሰገሰጉት ጡረታ የወጡ የወያኔ ኮሎኔሎችና ጄኔራሎች ዐይናቸውን በጨው አጥበው የምሥኪኑን ሕዝብ ሀብትና ንብረት ካላንዳች ይሉኝታ እየቦጠቦጡ ለግላቸው እያዋሉት ነው፡፡ ሥራ ላይ እያሉ ጎደልብን የሚሉትን አሁን እያካካሱ ናቸው፡፡
ልብ አድርጉ ለምሣሌ፡፡ ኤልፓ ውስጥ ነበረ የተባለውን ሙስና ለማስቀረት በሚል የማስመሰያ ሥልት የኤልፓን ዕቃዎች ሜቴክ እንዲያስገባ ይደረጋል፡፡ የሚገባው ዕቃ ግን ከበፊቱ የባሰ መናኛና እንደተቀየረ የሚቃጠል ወይ የሚፈነዳ ነው – ይህን የአደባባይ ምሥጢር ሁሉም የመሥሪያ ቤቱ ሠራተኛ ያውቃል፡፡ ሙስናው ግን ከዱሮው በዕጥፍ ድርብ በልጧል፡፡ ለአብነት ሜቴክ ለኤልፓ አንድ ትራንስፎርመር በ180 ሺ የኢትዮጵያ ብር ገቢ ያደርጋል – ያለምንም ጨረታ ለርሱ ብቻ በተፈቀደ ችሮታ (በየቦታው እንዲህ ነው የሚደረገው፤ አንተ በነፃ እሰጣለሁ የምትለውን ዕቃ ሳይቀር “ምን አገባህ?” ተብለህ በሚሊዮኖች እንዲገዛ ሊደረግ ይችላል፤ ወያኔና ገንዘብ እስከለተሞታቸው ላይፋቱ ተማምለው የትዝብትን ጫፍ አልፈዋል!)፡፡ ከዚህ ትራንስፎርመር በጥራትም በደረጃም እጅግ የሚበልጥ ትራንስፎርመር በ65 ሺህ ብር ከግል አቅራቢዎች ማግኘት እየተቻለ ባለቤት የሌላትን ሀገር ተረባርበው ለማለብ ሲሉ ሦስትና አራት ትራንስፎርመር በሚገዛበት ገንዘብ አንድ አልባሌ ምናልባትም ያገለገለና ያረጀ ያፈጀ ትራንስፎርመር ይገዛሉ፡፡ ለዚያውም በአነስተኛ ዋጋ የሚገኘው ጥሩ ዕቃ በድርጅቶቹ መኪና ተጭኖ የተፈለገው የኤልፓ ግቢ መግባት ሲችል የሜቴክ ውዳቂ ዕቃ ግን በኤልፓ ወጪ ከሥጋ ሜዳ (ታጠቅ አካባቢ) እንዲመጣ ይደረጋል፡፡ በአንድ ስብሰባ ይህ ዓይነት ግፍ በሀገር ላይ ለምን እንደሚፈጸም ቢጠየቅ ደብረ ጽዮን የተባለው የወያኔ ጭራቅ “እናንተን ምን አገባችሁ?” በሚል የጥጋብ አነጋገር ጠያቂዎቹን አሣፍሮና ከሥራ ደረጃም አወርዶ ከኃላፊነት አንስቷቸዋል፡፡ ዛሬ ስለሀገር ማሰብና መጨነቅ ጥያቄና አወንታዊ አስተያየትም ማቅረብ የሞትና የእሥራት ቀለል ሲል ደግሞ ከኃላፊነት ቦታ ወርዶ ተራ ሠራተኛ የመሆንና ከናካቴው ከሥራ በመባረር የበረንዳ አዳሪነትን ክፉ ዕጣ ያሰጣል፤ ዘመነ ግርምቢጥ፡፡ አፍህን ዘግተህ እነሱ እንደሚሉትና እንደሚያደርጉት እንደሚሆኑትም ካልሆንክ ጠንቁ ከባድ ነው፡፡ የነዚህ ወያኔዎች ልጆች በነገይቷ ኢትዮጵያ የሚገጥማቸውን የአንገትና የኅሊና ስብራት ከአሁኑ ሳስበው የልጆቼን ያህል እጨነቅላቸዋለሁ፡፡ በአንድ ሜትር ርቀት ውስጥ ከሚገኝ ፉርሽካ ባለፈ  ሌላ ምንም ነገር እንደማይታያት አህያ የሚመሰሉት አባቶቻቸው ግን ኅሊናቸው የታወረ በመሆኑ አሁንም ሆነ ትናንት ምናልባትም የመትረፍ ዕድሉን ካገኙት ነገም ቢሆን በአሁኑ ሰይጣናዊ ድርጊቶቻቸው የሚያፍሩ አይመስሉም፡፡ እነሱም ያሳዝናሉ እኮ፡፡
ኤልፓ ውስጥ የሚሠራ አንድ ትግሬ ኢትዮጵያዊ ከትልቅ ኃላፊነት ወደ ተራ ሠራተኝነት መውረዱን ሰማሁ፡፡ ምክንያት – በየስብሰባዎች እውነቱን እያጋለጠ ሀገሪቱን ከብዝበዛና ከሙስና እናድናት ብሎ በመጮሁ፡፡ ይህ ሰው ትግሬ በመሆኑ – ምናባልት – ሊገድሉት አንጀታቸው አልጨክን ብሎ ሊሆን ይችላል – “የኛ” የሚሏቸውን ግን የሁላችንም የሆኑትን ወገኖችም ላለማስኮረፍ ጭምር፡፡ ሌላ ቢሆን ኖሮ ግን በመኪና ተድጦ ወይም በአንዳች ሌላ ሰበብ (ሰበብም ሳያስፈልግ ኧረ!) እስካሁን ደብዛው ይጠፋ ነበር፡፡ ለማንኛውም ይህ ምርጥ ኢትዮጵያዊ ለሆዱ ሳያድር እየታገላቸውና ቢገድሉትም ግድ እንደሌለው በግልጽ እየነገራቸው ይገኛል – በነገራችን ላይ ቁጥራቸው ለመኩራሪያነት ባይደርስም እንዲህ ያሉ ለሆዳቸው ሳይሆን ለኅሊናቸው ያደሩ ቆራጥ ትግሬዎች እንዳሉ መረዳት ተገቢ ነው፡፡ እንግዲህ ይህን መሰል ዕንቁ ዜጋ፣ እንዲህም ያሉ  ያልተዘመረላቸው ጀግኖች አሉና ሕጻኑን ከነታጠበበት ውኃ ላለመድፋት እንጠንቀቅ – የእግረ መንገድ ማሳሰቢያ ነው፡፡
በተረፈ ወያኔ ያሳለፈላቸው ትግሬዎች ብዛታቸው ቀላል ነው ባይባልም – ማይምነት በሚበዛባቸው የኛን መሰል ሀገራት እንዲህ ያለ ዘውጋዊ ጭፍን ጭፍራነት የማይጠበቅ ባለመሆኑ – በተለይ በአሁኑ ወቅት ብዙ ተጋሩ ወደ ልመና እየተሠማሩ መሆናቸውን አዲስ አበባን በማየት መረዳት ይቻላል፤ ሕጻን ዐዋቂው ከማንም ወገኑ ባልተናነሰ እየለመነ የሚገኘው ለሥለላ ሥራ – አንዳንዶቹን መጠርጠር ተገቢ ቢሆንም – ወይም የልመናን “ሙያ” ለማየት ሲባል ለድሎትና ለቅንጦት እንዳይመስለን – እንደኛው ከእውነት ተቸግሮ ነው፡፡ ሁሉም በየሆዱ ይዞ “እህህ” እያለ እንጂ የወያኔ ልምጭ ያልሸነቆጠው በዘመኑ ቋንቋ አንድም  ክልል የለም፡፡ አንዱን ከሌላው እየለዩ በሀብት ማክበር ወይም ማደኽየት ደግሞ ትልቁ የወያኔ የአገዛዝ ሥልት መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ እውነቱን ለመናገር አጋንንት ለሥልት ካልሆነ በስተቀር በዘርና በጎሣ አያምንም፡፡ የሊቀ ሣጥናኤል ልጆች ወያኔዎች ደግሞ እንኳንስ ለመላው ትግሬ ለእናታቸውም ልጅ የማይራሩ ልዩ ጭራቆች ናቸው – እነኚህ የእፉኝት ልጆች ለአንዳንዶቻችን የክፋት ሥራ ተመጥነው በልካችን የተሠፉ የመርገምት ልብሶቻችን መሆናቸውን ደግሞ በእግረ መንገድ መጠቆምና ይህ መለኮታዊ ቅጣት ገብቶን ከልብ እንድንጸልይበትም ማሳሰብ እፈልጋለሁ፡፡ ልብ አድርጉ – ስብሃት ነጋ አንዳች መንፈሣዊ ኃይል በአካል ተከስቶ “ልጅህን ብትገብርልኝ አሥር ዓመት ዕድሜ እጨምርልሃለሁ” ቢለው እንዲያውም “ሌላም ልጨምርልህ እችላለሁ!” ከማለት የሚመለስ አይመስለኝም – የቆረበው በክፋት ሥራ ነውና፡፡ የወያኔዎች ብቸኛ ዘመድ ሆዳቸው ነው፡፡ ለሆዳቸውና ለሥልጣናቸው ሲሉ የማያደርጉት ነገር – የማይፈነቅሉት ድንጋይ – የማይቧጥጡት ሰማይ የለም፤ ለነሱ ያልሆነች ዓለም ብታልፍም ደንታ የላቸውም፡፡ ለነሱ ሚስትና ልጅ ብርቃቸው አይደለም – ብቸኛ ብርቃቸው ሰይጣናዊ ፌሽታና ዳንኪራ ነው – እንደሚባለውም ከሆነ ለዚህ ነው በሰይጣናዊ ምች የአልጋ ላይ ደዌ ተመትተው ብዙዎቹ በመድኃኒት እገዛ የሚኖሩት፡፡
ይህ ሥርዓት ከራስ ዱሜራ እስከራስ  ካሳር ሕዝበ ኢትዮጵያን እያደኸየና ለርሀብም ለሞትም ለስደትም እየዳረገ ነው፡፡ ተባብረን ካላስወገድነው እገሌ ከእገሌ ሳይባል ሁላችንም በቀጣዮቹ ጥቂት ዓመታት ውስጥ እናልቃለን፡፡ የፋሲካው በግ በገናው በግ መሣቁን ከቀጠለ አሣራችንም በዚያው ልክ ይቀጥላል፡፡
በአንዲት ሰሞነኛ ቀልድ የምትመስል እውነተኛ ገጠመኝ እንለያይ፡፡ ብሔራዊ ትያትር አካባቢ አንድ ትግሬ ወደ አንድ መኪና ጠጋ ብሎ ይለምናል፡፡ የሚለምንባት መኪና ሹፌር – ከምን ነገድ እንደሆነ አልሰማሁም – መስኮቱን ወረድ ያደርግና “ይቺን ‹ሥራ› እንኳን ለኛ አትተውልንም?” በማለት ስሙ ብቻ ያከበረውን ምሥኪኑን ትግሬ ቀልቡን በመግፈፍ ያስኮርፍና ካጠገቡ ያርቀዋል፡፡ … የኔ ቢጤው ድሃ ሰላይ ቢሆን ኖሮ የዚያችን መኪና ታርጋ በመያዝ ወዲያውኑ ይደውልና አምባሳደርን ወይም ጥቁር አንበሣ ሆስፒታልን ሳያልፍ ያ ቀልደኛ ሹፌር ሸቤ በተባለና ከዚያም የከፋ እርምጃ በተወሰደበት ነበር – ስለዚህ ምንም እንኳን ብሶት የማያደርገው ነገር ባይኖርም ከስሜት ይልቅ እውነትና ምክንያት ይበልጥ አዋጭ ናቸውና ወገናችንን የሚያስከፋ ነገር ላለማድረግ እንጠንቀቅ፤ ሁሉም ለሚያልፍ ነገር የማያልፍ ጠባሳ እንዳናስቀምጥ አማራና ትግሬ፣ ኦሮሞና ጉራጌ ሳንል ሁላችንም ወደየኅሊናችን እንመለስ፤ ያኔ ከኛ የራቀ የሚመስለን ፈጣሪም ፊቱን ወደኛ ያዞራል – The moral of the Story. ግን ግን ፈጣሪ ፊቱን ከኛ አላራቀ ይሆን እንዴ? ዘፋኙ “ዋሸሁ እንዴ” ያለው ትዝ አለኝ – አሁን፡፡ ለነገሩ ቢያርቅስ ማን ይፈርድበታል? ያንዳንዶቻችን ዕኩይ ሥራ እኮ ወደርየለሽ ነው!

No comments:

Post a Comment