ባለፉት ሦስት ቀናት የአርበኞች ግንቦት 7 ታጋዮች ትግራይ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች የወያኔን ሃይል ገጥመው የወያኔ መኮንኖችን ጨምሮ በርካታ የወያኔ ሰራዊት አባላትን እንደገደሉ በቃል-አቀባያቸው አማካኝነት ለኢሳት ቴሌቪዥን ገልጸዋል። ለጥቀውም እስከ ትላንት ድረስ ውጊያው ቀጥሎ እንደሚገኝ በድጋሜ ዜናውን አብስረዋል።

በወያኔ ዘረኛና ግፈኛ አገዛዝ የተንገፈገፈው የኢትዮጵያ ህዝብም ጆሮውን አቅንቶ ሁኔታውን በመከታተል ላይ ነው። ቀድሞውንም የወያኔ ሥርዓት ያለ ሃይል ትግል አይንበረከክም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካም ሆነ የሥርዓት ለውጥ ሊመጣ የሚችለው በተቃውሞው ጎራ የተሰለፉት ተባብረው በወያኔ ላይ ክንዳቸውን ሲያሳርፉ ብቻ ነው ብለው የሚያምኑት ኢትዮጵያውያን አርበኞች ግንቦት 7 በወያኔ ላይ የከፈተውን ማጥቃት በከፍተኛ ደስታ ነው የተቀበሉት።
አንዳንዶች አርበኛውን በገንዘብ ለመደገፍ እና ለማጠናከር ከወዲሁ እንቅስቃሴ ጀምረዋል።
ይህ በዚህ እንዳለ በወያኔ ጎራ በኩል ይህን ጉዳይ በተመለከተ ምንም የተሰማ ነገር የለም። ጥያቄው… ለወትሮው ትንሽ ትልቁን “የግንቦት 7” አባል ነው ብሎ በመፈረጅ ንጹሃንን እስርቤት የሚወረውረው ወያኔ በይፋ ስለተከፈተበት ጦርነት ለምን ዝምታን መረጠ? ነው።