ክፍል 1
ሰሞነኛ
አዲሱን አመት ተቀብለን ሁለት ወራት ሳንሻገር ጥቅምት 11 ቀን የኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ እና ሥራ አሥኪያጁ ጋዜጠኛ ሚሊዮን ደግነው ክስ ተመስርቶባቸው ፍርድ ቤት ቀረቡ፤ በዳግም ቀጠሮ ዕረቡ ጥቅምት 20 ቀን በሐዋሳ ከተማ ጋዜጠኞቹ ለፍርድ ቤት ቀጠሮ ሄደው በስልት የተቀናበረ በሚመስል ሆኔታ ለመኪና አደጋ ተዳርገው ጋዜጠኛ ኤፍሬም የከፋ አደጋ ሲደርስበት ዋና አዘጋጁ ጌታቸው እና ሥራ አስኪያጁ ጋዜጠኛ ሚሊዮን በመለስተኛ ጉዳት መትረፋቸው ተሰማ፤ ጥቅምት 13 ቀን እኔን ጨምሮ ሌሎች ሦስት ጓዶቼ አንድ አመት በተጓተተ ክስ ፍርድ ቤት ቀርበን ክሱ ለህዳር 24 ተቀጠረ፡፡
ጥቅምት 15 ቀን የኢትዮጵያ ህዝብ አብዝቶ የሚሳሳለት ጋዜጣኛ ተመስገን ደዳለኝ ፍርድ ቤት ቀርቦ አንደ ገና በድጋሚ ቀጠሮ ጠቅምት 21 ውሎው ፍርድ ቤት ሆነ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስተር ኃይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው መንግስታዊ ስልጣናቸውን በመጠቀም በሀሣብና በአመለካከት ጎራ ለይተው በሚታገሏቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ፍረጃ አና ዛቻ ሲሰነዝሩ ከረሙ፤ ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ቤተ መንግስቱን ለቅቀው በየወሩ ግማሽ ሚሊዮን ወደ እሚከፈልበት ቤታቸው ሲያመሩ ዶ/ር ሙላቱ ፕሬዘዳንት የሚል ስያሜ በመያዝ ሰተት ብለው ወደ ቤተ መንግስቱ መግባታቸው ተሰማ፡፡