ከዳኮታ ጥናት መአከል
የኛ ነግር መልሶ መላልሶ ሆኗል። በገራችን አቆጣጠር በ1960ዎቹ የተማሩና የነቁ ወጣቶች አቢዮት ማካሄድ በጀመሩ ጊዜ የተነሱ ልዩነቶች አንዳንዴ ቅርጻቸውን በመጠኑ ይቀይሩ ይሆናል እንጂ ዛሬም ድረስ ባንድ ወይ በሌላ በኩል የልዩነትና የፍዳችን ምንጭ ሆነው ቀጥለዋል። እነዚህ ልዩነቶች መረቀቂያዎች፤ መጣያያዎች ቢያመች መገዳዳያዎቻችን ናቸው። ችግር የሆነው ጎራ ለይተው በነበሩ ፖለቲከኛች የሀሳብ ልዩነቶቹ መፈጠራቸው ወይ መኖራቸው አልነበረም። ወይ ልዩነት የተፈጠሩባቸው አገራዊ ቁም ነገሮች ስህተተኛነትና ወይ አላስፈላጊነት ኖራቸው አይደለም። ትናንትናም ሆነ ዛሬ ምንአልባትም ነገም ችግር የሚሆነው ምንም አይነት ልዩነት ላይ በረጋ ሁኔታ መነጋገር፤ ልዩነትን ማቻቻል፤ አብሮ የሚያሰራና በጋራ የሚያታግል ማድረግ አለመቻሉ ነው። በሚያሳዝን ሁኔታ ይህ ችግር ከአርባ አመታት በሗላም ያሳየው መሻሻል እዚህ ግባ የማይባል ነው። ዛሬም ድረስ ቡድንም ሆነ ግለሰብ ልዩነት ታየበት ማለት አለቀ ጠላት አድርገው የሚፈርጁ ፖለቲከኞችና ድርጅቶች በገፍ አሉን። ያኔ ትግሉን በዋናናት የመሩትና ፖለቲካውን የተወኑት ዛሬም ወሳኔ ሰጪዎች በሆኑበት እዚህ ችግር ውስጥ መዳከራችን ብዙም አይገርምም።