ታደለ መኩሪያ
እነደዛሬው ለሙ መሬታችን በወያኔ ለባዕዳን ከመሸጡ በፊት ግንቦት የበሽበሽ ወር ነበር ። ሣር እንደልብ ስለሚበቅል ላሞች በገፍ ወተት ይሰጣሉ፣ሕፃናት ይጠግባሉ፣ ዕቦሳ ጥጆች ወተት የጠገቡ ያለገደብ ይቧርቃሉ፤ጨሌ የጠገቡ ወደል አህዮች ያናፋሉ፣ኮርማ በሬዎች ያገሣሉ፤ ሁሉም የጠገቡ ናቸውና ሃይ የሚላቸው የለም። ቦረትቻው፣ ቡና ቀላው፣ ዛፉን ሙዳው፣ አድባሩን አውጋሩን ልመናው፣በዚሁ በግንቦት ወር ነው። እንደነጮቹ (Thanksgiving day) የምስጋና ቀን ልለው ይዳዳኛል። የጥጋብ ወር ብዬ ልለፈው።
ያለንበት ወር እንኳን የግንቦት ወር እይደለም ታዲያንስ ‘የግንቦት ዕቦሶችን’ ምን አመጣው ትሉኝ ይሆናል። የወያኔ ዕቦሳዎችን ለማለት ነው።አቶ ሰባት ነጋና አቶ በረከት ስመዖን እንደ ግንቦት ዕቦሳ ጥጆች ወተት እንደጠገቡት ያለገደብ ሲቧርቁ ስለአየኋቸው ትንሽ ልበል ብዬ ነው።
ወተት የጠገቡት ሃይ ባይ ያጡት ዕቦሶች አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስተር አቶ ኃይለማሪያም ደሣለኝን ከቁብም አልቆጠሯቸው። እነዚህ ሁለት ግለሰቦች በዓለሙ መድረክ ላይ በኢትዮጵያ ስም ሲፏልሉ ቁሙ ባአንደኛ ያላቸውም የለም። እንዳሻቸው ወጥ ይረግጣሉ። ኤርትራዊያን ወይስ ኢትዮጵያውያን ናቸው የሚል ጥያቄም አስነስቷል። ጠቅላይ ሚኒስተር ኃይለማርያም ደሣለኝን ያው ከፓርቲያቸው የተመረጡትን እንደመሪያቸው ያለመቀበል የንቀት ምልክት ነው። በዚያም አላበቃም፣ አቶ ስባት ነጋ እንጣጥ ብለው እንደጉሬዛ በድፍረት ‘አማራውንና የኦርቶዶክ ሃይማኖት ተከታዮችን በማያሰራሩበት ሁኔታ መተናቸዋል’ አሉን።
አቶ በረከት ስምዖን በበኩሉ ደግሞ ከመቶ ሺ ያላነሱ ኢትዮጵያዊያን የተሰውበትን የባድሜ ጦርነት በጥቂት የትግራይ ተወላጅ ጦር ናፋቂዎች የወያኔ አባላት ግፊት እንደተፈጸመ አድርጎ አቅርቦታል። ሌላው የሚገርመው በፓል ቶክ ለኤርትራ ወጣቶች ስለ አሰብ ወደብ ተጠይቆ የሰጠው መልስ ነው። የአሰብን ወደብ ጉዳይ የሚያጠነጥነው የትውልድ ክፍል እያረጀ በመሄዱ ወጣቱ ስለአስብ ጉዳይ የማያውቀውና አገብጋቢውም አንደልሆነም ነው ማረጋገጫ የሰጣቸው። ከዘጠና ሚሊዮን ከሚገመተው የሕዝባችን ቁጥር ስልሳው በመቶ ወጣት በሆነበት ሕብረተሰብ ውስጥ ስለሃገሩ አገብጋቢ ጉዳይ አያውቅም ማለት ትልቅ ንቀት ነው። በተዘዋዋሪ የኢትዮጵያ ወጣት ዳም ደደብ የሃገሩን ታሪክ የማያውቅ በአልባሌ ተግባር ላይ የተሰማራ ለሃገሩ የኤርትራውን ወጣት ያህል የማይሰማው ግድ የለሽ ኖሮ የሚያልፍ ማለቱ ይሆን? መልሱን ከበረከት ስምዖን እንደ ኤርትራ ወጣቶች ጠይቀው እንዲረዱ ለኢትዮጵያ ወጣቶች እተውላቸዋለሁ።
ያም ሆነ ይህ የአቶ ስባት ነጋንና የአቶ በረከት ስምዖን ለኤርትራ መቆማቸውን ታዋቂውን ጠንቋይ ታምራት ገለታን ወይም ስለወያኔ ጉዳይ ኤክስፐርት ነኝ ባዩን ተሰፋዬ ገብረአብን መጠየቅ አይሻንም።
መዘንጋት የሌለብን ይህ ሁሉ አርቲ ሙርቲ ወሬ የሚነዛው በአቶ ኃይለማሪያ ደሣለኝ በጠቅላይ ሚኒስትርነት በምትመራው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። ይህ ደርጊት ‘የሹም ልል በጥፊ ያወላውል’ የሚለውን ተረት ያስተርታል። አቶ ኃይለማሪያ ደሣለኝ ጥሩ ሰው ሊሆኑ ይችላሉ። ሆኖም ግን በወያኔ ኮር ቡዱኖች ፍላጎት ወደሥልጣን የመጡ ስላልሆኑ በተገኘው ቀዳዳ ሁሉ ደካማ ሆነው እንዲታዩ መደረጉ ለሳቸውም ስውር አይደለም። በወያኔዎች ቁጥጥር ሥር ባሉ መገናኛ ብዙሃን የሆነ ያልሆነው ጥያቄዎች እያቀረቡላቸው ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር እያራራቋቸው መሆኑን ከራሳቸው በላይ ሌላ ሰው ሊነግራቸው አይገባም። ‘ከአያይዝ ይቀደዳል ከአንጋገር ይፈረዳል’ እንደተባለው የኢትዮጵያ ሕዝብ የእኝህ ሰው አቅጣጫ ወዴት ነው? ማለቱ አልቀረም። ሰዎች በጠራራ ፀሐይ ይገደላሉ፤ በወሎ ውስጥ በሙስሊም ወገኖቻችን ላይ የተፈጸመው ግድያ እንደምሳሌ የሚጠቀስ ነው። ለግድያው ለአፈናው ለዘረፋው ተጠያቂው ማነው? በመድረኩ ላይ ተዋናይ የሆኑት አቶ ስባት ነጋና አቶ በረከት ሰምዖን እንደሆኑ ሃገሪቷን የሚመሯት ግልጽ አልሆነም። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሣለኝ ከሁለት ያጡ እየተደረጉ መሆናቸው በተግባር ይታያል። የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ርዝራዦች እነርሱ የፈለጉት እንጂ እንዳለፈው ጠቅላይ ሚኒስትር በሙሉ ነፃነት እንዲሰሩ አይፈቅዱላቸውም። የአጋዚ ጦርን፣ የፈደራሉን ፖሊስ፣ እንደሸለምጥማጥ ሰዎችን በመኝታቸው ላይ የሚያንቀው ጋቢ ለባሹን የስለላን ቡድን ለመቋቋም የሚችሉት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ሲቆሙ ብቻ ነው። ይህ ‘አግብቶ ላያገባሽ ከባልሽ ሆድ አትባባሽ’ እንደሚባለው ወያኔን አምኖ የማያምኑበትን ማድረግ መጨረሻው ውርደት ነው።
የሰባት ነጋና የበረከት ስምዖን ቡረቃ ኃይለማሪያ ደሣለኝን የአመራር ችሎታ የሌላቸው አስመስለው የጉግ ማንጉጉን ጥርቅምን ወደሥልጣን ለማምጣት ነው። አቶ ኃይለማሪያምም ተቃዋሚዎችን በመሳደብና በእስር የሚማቅቁትን ለነፃነታው የሚዋጉትን ዜጎችን እንደወጀለኛ መፈረጁ ከሕዝብ ያርቅ እንደሆን እንጂ ወዳጅ አያፈሩበትም።
መፍትሔው ያለቅድመ ሁኔታ እስረኞችን መፍታት፤ ከተቃዋሚዎች ጋር ስለሃገር ውይይት መክፈት፤ የዳኝነቱ ሥራ ፍጹም በአስደንጋጭ ሁኔታ ላይ ስለሆነ በገለልተኛነት እንዲሰራ ማድረግ። ይህን ቢያደርጉ ከወያኔ እስር ቤት የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊያወጣዎት ይችላል። ለዘለቄተውም በሕዝብ ድምፅ በነፃነት ተመርጠው ሃገሮን ሊመሩ ይችላሉ። ስለኢትዮጵያ ጉዳያቸው ካልሆኑ ቡድኖች ጋር ብዙም አይጓዙም።
tadele@shaw.ca
No comments:
Post a Comment