Translate

Monday, August 20, 2012

ማነህ ባለ ሣምንት ያስጠምድህ ባሥራ ስምንት


ነጻነት ዘገዬ
“የጸሎት ጦር ሲወጋ እንጂ ሲወረወር አይታይም!”
“እስመአልቦ ነገር ዘይሰኣኖ ለእግዚአብሔር፡፡”
እንዴት ነው ነገሩ! ይሄ ነገር እውነትም ትንቢቱ ደረሰ ማለት ይሆን? “የምን ትንቢት?” ብሎ የሚጠይቅ መቼም አይጠፋም፡፡ በነገራችን ላይ ዛሬ ዕለቱ ነሐሴ ሚካኤል ነው፡፡ በኦርቶዶክሳውያን ዘንድ የንግሥ በዓል ባይሆንም  በወርኃዊ የሚካኤል በዓልነቱ ከአዘቦቱ ለየት ባለ መልክ ይከበራል፤ የጥዋ ማኅበር ያላቸውም በፍልሰታ ምክንያት ካላዘዋወሩት በስተቀር ዛሬ ጥዋቸውን ሊጠጡ ይችላሉ፡፡… በጥዋ ማኅበር ሥርዓት ታዲያ  በመጨረሻው አካባቢ ሙሤው ይነሳና “ዳቦው  ባረረ፣ ጠላው በቀጠነ … በቅዱስ እገሌ ስም ባለቤቱ ማሩኝ ይላችኋል” ይልና ጋቢውን መስቀልኛ አጣፍቶ በመልበስ ማኅበርተኛውን በትህትና ይጠይቃል፡፡
ከዚያም “ዳቦውም አላረረ፤ ጠላውም አልቀጠነ…” ተብሎ በኅብረት ከተመለሰ በኋላ ሌላው ሥርዓት ይለጥቅና ቀጣዩን ዘካሪ ወይም የጥዋ ተረኛ – ባለአንድ – ባለሁለት – ባለሦስት -(ባለአራት ድረስ ይሄዳል ልበል?) በማነህ ባለሣምንት ያስጠምድህ ባሥራ ስምንት ሃይማኖታዊ ትውፊት እያስነሳ በጥዋውና በዘካሪ ካህኑ ፊት እንዲወድቁ ያደርጋል – ሣርም ይነሰነስባቸዋል፡፡ … የወደቁት ይነሱና  እየበሉና እየጠጡ ጨዋታቸውን ይቀጥሉ፡፡ እኔ ግን ወደተነሳሁበት ጉዳይ እንድገባ ይፍቀዱልኝ፡፡ የርዕሴን ምንነት አብራራሁ – አሁን  ለማንም ግር አይልም፡፡
የሰሞኑ የሀገራችን ሁኔታ አጃኢብ የሚያሰኝ ነገር ሆኗል፡፡ እኔ ስተኛም ስነሳም ቤተስኪያንም ስሄድ ጉድ ጉድ እያልኩ አንዳች ነገር እንደነካው ሰው ብቻየን በማውራት በፈጣሪ ሥራ መደነቅን አብዝቻለሁ፤ መልስ እንደሚሰጠኝ ሁሉ “የት ተደብቀህ ኖረህ ነው?” እያልኩም በመጠየቅ ላይ ነኝ፡፡ በወያኔ ሠፈር ፈንግል ገብቶ በሁለት ወር ውስጥ ብቻ ሦስት አንዲስ አንዲስ እሚያካክሉ ፖለቲካዊ ተፅዕኗቸውም የትዬለሌ የሆነ ጠረንገሎ ባለሥልጣናትን ሲያጋድም ማየት ትንግርት እንጂ እውን አይመስልም፡፡ አሁን ቅርብ ሰዓት እንደሰማሁት ደግሞ በአንጻራዊ ሁኔታ በአዲስ አበቤዎች ልብ ውስጥ በተወሰነ ደረጃ በጥሩ ጎኑ የሚወሳው አርከበ ዕቁባይም ለአልጋ እንደተሸነፈ ሰማሁ፡፡ ይህ የደም ካንሰር የሚባል ወያኔያዊ ልክፍት  ያላጥለቀለቀው ወያኔ የለም እየተባለ ነው – ከአሁን በፊት አሰፋ ማሞንና ሌሎች በርካታ ቱባ ወያኔዎችን የገደለ መጥፎ በሽታ ነው፤ ተፈራም፣ ሥዩምም፣ አዲሱም፣ በረከትም ሌሎቹም በቅርብ ርቀት የሚከታተሉ ወረፍተኞች መሆናቸውን እየሰማን ነው – ክርስቶስን የከዳ የወፍጮ መጅ ባንገቱ ታስሮ ወደ ጥልቁ ባሕር ቢወረወር እንደሚሻለው በክርስቶስ በራሱ አንደበት የተነገረው አጽናኝ ቃል ለክፉዎች በሚሰጥ ፍርድ ብዙም እንዳናዝንና እንዳይሰማን ለመርዳት ይመስላል፡፡ በሰው ሞትና ህመም መደሰት በመሠረቱ አግባብ ባይሆንም ይሄ የሰሞኑ ሁኔታ እኮ ሰው በጥሞና ከተረዳው በሃያ ዓመት ጸሎት ብቻ የሚገኝ ድል አይመስልም – የሶቪየት ኅብረት ሕዝብ ያ ሃይማኖትን አጥፊና ድህነትን አስፋፊ የኮሚኒስት ሥርዓት ከሥሩ ተገንድሶ የወደቀላቸው እኮ በሰባ ዓመት ጸሎት ነው፡፡  እንደዚህ ዓይነት አጋጣሚ ባለፈው የፖላንድ ፕሬዚደንት እንደሞተበት ዓይነት የአውሮፕላን ወይንም የመኪና አደጋ ካልሆነ በስተቀር በህመም ይገኛል ተብሎ የሚታሰብ አይደለም፡፡ ጨካኝና ልበ ደንዳና የሀገር መሪ፣ የበግ ለምድ የለበሰ ተኩላና ቀበሮ የሃይማኖት መሪ፣ በተለይ የአመራር ቦታው ከአንድ  የትውልድ ሐረግ በተሰባሰበ ዘረኛ የጦር ኃይል የተዋቀረ የመከላከያ ሠራዊት አዛዥ በጥቂት ሣምንታት ውስጥ የአልጋ ቁራኛና የአፈር ሲሳይ ማድረግ ለሰው የሚቻል አይደለም፡፡ ለእግዚአብሔር ግን ተቻለ – ለዚህ ነው ከመግቢያ ጥቅሶቼ መካከል “ለእግዚአብሔር የሚሣነው ነገር የለም” የሚለውን የጨመርኩት፡፡ ከዚህ ምን መማር እንችላለን ብሎ መጠየቅ ብልኅነት ነው፡፡ መማር የምንችለው ትልቅ ነገር “ከእንግዲህ ወዲያ አዳሜ ይህን ሰይጣናዊ የሀገር አገዛዝ ከወያኔ ተምረሽ በዘርና በሃይማኖት እየተሳሳብሽ ቤተ መንግሥት ገብተሽ ሕዝብ ጫንቃ ላይ እንጎማለላለሁ፤ ያሻኝን አደርጋለሁ፤ ‹ቀጣዩ ወርተራ የኔ ነው› ብትይ ውርድ ከራስ! ከዚህ ተማሪ” የሚል አንዳች ኃይል ወደ መድረክ ብቅ ማለቱን ነው፡፡ እውነት ነው፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበልና ከዚህ ሁኔታ ዱዲ ሳያወጣ በነጻ ይማር – እንደወያኔዎች የነፍስም ይሁን የሥጋ ግብር ሳይከፍል፡፡
“ሕዝቡ ምን ይላል” የምትል ቀስቃሽ ዘፈን አለችው ሻምበል በላይነህ – ሻምበል የራሱ ስም በላይነህ ያባቱ፡፡ ሕዝቡ እንዲህ ይላል፡- ዘረኝነት በቃን፡፡ የሃይማኖት ክፍፍል በቃን፡፡ ጎሰኝነት በቃን፡፡ ጎጠኝነት በቃን፡፡ ወንዘኝነትና በጎጥ በሸንተረር መወተፍ በቃን፡፡ ባገር ልጅነት ለሥልጣን መጠራራት ገለማን፡፡ ድህነት አንገሸገሸን፡፡ ጦርነትና ርሀብ መታወቂያችን ሆነ፡፡ ባልፈለግነውና ባልመረጥነው የፖለቲካ ሥርዓት መገዛት ቋቅ አለን፡፡ በሆዳምና በአጋሰስ ማይማን መሪዎች መመራት አንገፈገፈን፡፡ የድህነታችን ዋነኛ መንስዔ መጥፎ አገዛዝና ሙሰኛ የመንግሥት ተቋም በመሆናቸው ለአንዴና ለመጨረሻው ይወገዱልን፡፡ አንድነታችንን እየቦረቦሩ ያሉት በሥልጣን ጥምና በሀብት ማጋበስ ዘመቻ ተጠምደው አራት ኪሎን በጉልበት ሙጥኝ ያሉ ግለሰቦች እንጂ እኛ አልተለያየንም፤አንለያይምም፡፡ እያለን የሌለን ሆንን፡- በአካልም፣ በመንፈስም፣ በሰው ኃይልና በተፈጥሮ ሀብትም፣ በታሪክም… በሁሉም ሳናጣ በብልሹ አስተዳደር ምክንያት ግን በሁሉም  የደኸየን ሆንን፡፡ ወልደን፣ አሳድገንና አስተምረን ለወግ ለማዕረግ የምናደርሳቸውን ልጆቻችነን ለባዳ መገበር የማናመልጠው ዕጣ ፋንታችን ሆነ፡፡ የሀብታም ድሆች ሆነን የዓለም መዘባበቻ ሆነን ቀረን፡፡ ተናቅን፣ እስከመፈጠራችንም ተረሳን… ይህን ሁሉ መገፋትና መበደል ያዬ አንዳች  ኃይል  “ከእንግዲህ ይህ ሁሉ ታሪካችሁ መለወጥ አለበት፤ ሀገራዊ የዕድገትና ብልጽግና ሕይወትንም ‹ሀ› ብላችሁ ከእንደገና ማጣጣም አለባችሁ”- እያለን ነው አሁን በመካከላችን ገብቶ፡፡ አንድ በድረ ገፅ የሚጽፍ ሰው ቀደም ባሉ ወራት ውስጥ እስከሚቀጥለው ዓመት ማገባደጃ አንዳች ለውጥ እናያለን፤ የኢትዮጵያ ነጻነት ዳር ዳር እያለ ነው ብሎ እንዳስነበበን አሁን ትዝ አለኝ፡፡ ትንቢቱ ሊይዝለት ይሆን እንዴ? በመግቢያየ ላይ የጠቀስኩት ትንቢት ግን የዚህን ሰው አይደለም፡፡ ወደዚያ ልግባና ባጭሩ የምለውን ብዬ ሃሳቤን ልቋጭ፡፡
ዱሮ ነው፡፡ መነሻው ምናልባት የሼህ ሁሴን ጅብሪል ሳይሆን እንደማይቀር እገምታለሁ፡፡ ነገር ግን በዚያ የቆዬ ትንቢት መሠረት ወያኔ የሚባል ገዢ ኃይል ኢትዮጵያን እንደሚቆጣጠር፣ ብዙ ጥፋትም እንደሚያደርስ፣ ከእግዚአብሄር እንደተላከ ቀጪ ሆኖም የሕዝቡን ኃጢያት እንደሚያወራርድና በመጨረሻው ግን ሕዝቡ አምርሮ ካለቀሰና ከጸለየ በየት እንደወጣ እንኳን ሳይታወቅ እንደጢስ በንኖ እንደሚጠፋ  የሰማን ሰዎች አለን፤ ጊዜው ከመራቁ አንጻር አንዳንዶቻችን ልንረሳ እንችል ይሆናል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ያለው ሌላም ትንቢት አለ፡፡ ያ እንዲቀርልን በርትቶ መጸለይ ነው፡፡ ይሄ ራሱም ከበቂያችን በላይ ነው፡፡ ያልሰማችሁ ምንም እንኳን በማብቂያው ላይና በትንቢቱ ፍጻሜ ገደማ ብንሆንም አሁን ዘግይቶም ቢሆን መስማቱ የሚገድ አይመስለኝም፡፡ በመሠረቱ አንድ ትንቢት ከተፈጸመ በኋላ ቢነገር ትንቢት አይደለም፡፡ ትንቢት ከተነሣ አይቀር ደሴ ላይ “ነገ ቤት ይቃጠላል!” ስትል ቆይታ በማግሥቱ ራሷ አንዱን ቤት በማጋየት ትንቢቱን በራሷ እንደፈጸመች ስለሚነገርላት አንዲት ዕብድ ሴት አንብባችኋል? ወያኔም ገና በረሃ  ውስጥ ሳለ ‹ኢትዮጵያ ልትበታተን ነው፤ ከመበታተን የሚያድናት የኢሕአዴግ አመራር ብቻ ነው› እያለ ሲያስፈራራን ቆይቶ ራሱ መጥቶ በታተናትና ትንቢትን በራሱ በመፈጸም አንዱ ሟርተኛ ዕብድ ሆኖ ተመዝግቧል – ከደሴዋ ዕብድ ቀጥሎ መሆኑ ነው፡፡
የሆነስ ሆነና ቀጣዩ ባለሣምንት ማን ይሆን? ከእግዚአብሔርስ ጋር ታግሎ ማን ሊያሸንፍ  ይችላል? ከሃይማኖት ሰባኪ አትቁጠሩኝና የጠፋችሁ ወያኔ ልጆቻችን ለምን በሩ ሳይዘጋ አትመለሱልንም? የእናንተን የአጥፊዎቻችንንና የእኛን የምታጠፉንን ኃይል አንድ አድርገን በአወንታዊ የልማት ጎዳና ብንጠቀምበት እኮ ምናልባት በጥቂት የአምስት ዓመት መሪ ዕቅዶች ውስጥ አሁን የምንቀናባቸው ሀገሮች የደረሱበት ደረጃ ላይ እንደርሳለን፡፡ ለመጠፋፋት የምንጠቀምበትን ሀብትና ንብረት (resource) ለግንባታ ብናውለው የት ልንደርስ እንደምንችል እስኪ አስቡት፡፡ ዛሬ በደረሰኝ አንድ ጽሑፍ በሲያትል ለሚኖሩ ትግራውያን ማስታወቂያ ወጥቶ በሁለት ሞኞች የወያኔ ሰዎች ዘረኛ ዝግ የትግርኛ ተናጋሪዎች ስብሰባ ሊደረግ ነው – ይህን ዓይነቱን ዝግ ወያኔያዊ ስብስባ በርግጥ ላለፉት ሃያ አንድ ዓመታት – ከዚያም በፊት ከወያኔ የመሀል ሀገር ካባ ከቁጩው የኢሕአዴግ ምሥረታ በኋላ ከበረሃም ጀምሮ – በሀገር ውስጥም ለምደነዋል፤ ጠጠር ያለች ነገር ብቅ ባለች ቁጥር እነሱው ብቻ በቀንም ሆነ በደረቅ ሌሊት በዝግ ይሰበሰቡና አብዚ አብዚ ብለው የሚሆነውን ያደርጋሉ እንጂ ሌሎችን አምነው ምሥጢር አያካፍሏቸውም፤ መረገም ነው፡- የሁላችንም መረገም! ከአሁን ወዲያ ግን ያ የሚቀጥል አይመስለኝም፡፡
አንዱ ፍቅረኛውን “እያጫወትኩሽ ታንቀላፊያለሽ?” አላት የተባለው ለካንስ ወዶ አይደለም! አሁንም በዚህ የሞተ ጉዳይ መጓዝ የሚፈልግ አለ? ምን ዓይነት ቂልነት ነው? በወያኔው ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ‹የሰካው መርፌ›(ባህላዊውን የመሰቃቀል ባዕድ አምልኮታዊ መጥፎ ልማድ ያስቧል – ‹አፉ› ካልተባለ እስከ ሰባት ትውልድ የሚረፈርፈውን!) ሥራውን መሥራት ከጀመረ በኋላ ይህን ዓይነት አስቀያሚና የነፈሰበት   የዐመፃ ትውልድ ጎጠኛ ሤራ ማካሄድ ይገባል? ሦስት ልጆቹን ትቶ ያገኛትን አህያ ብቻውን ቅርጥፍ አድርጎ ከበላ በኋላ ችግር ሲደርስበት ልጆቹ እንዲረዱት የተማፀነውን የጅቡን ታሪክ አስታውሱና ወያኔን “ዕዳህን እዚያው በጠበልህ ቻል” በሉት፡፡ ብቻህን እንደበላህ ብቻህን ተወጣት በሉትማ ግዴላችሁም፡፡ ደግሞም ሌሎች በዚህ ወያኔ በጀመረው መንገድ ለመሄድ ያቀዳችሁ ዜጎች ካላችሁ በፍጹም አያዋጣችሁምና በጊዜ ተመለሱ – በወቅት አመጣሽ የዕድል ብርብራ መስከርና የሚሠሩትን ማጣትንም ተውት፡፡ ጊዜ የሚሰጥን መልካም አጋጣሚ በወጉ መጠቀም ከአስተዋይ ሰው ይጠበቃልና የወያኔ በሰማያዊ ዱላ መመታት ለሌሎች ጠማማ አስተሳሰቦች መነሳት ዋስትና ስለማይሰጥ እባካችሁ ወገኖቻችን ቁጭ ብላቸሁ በርጋታ አስቡና ለሁሉም ሕዝብ የሚጠቅም ነገር ለመሥራት ቆርጣችሁ ተነሱ፡፡ ከእንግዲህ ወዲያ በየመንግሥት ምሥረታው ማግሥት  እየተረጋገምን በከንቱ አንጨራረስ፡፡ አትሞኙ ወንድሞቼና እህቶቼ፤ ይህን ቃሌን ማስፈራራት እንዳትሉት ፍርዱን እያያችሁት ነው፡- ሲወጋ እንጂ ሲወረወር የማይታየውን የጸሎትና የዕንባ ጦር እያዬ መቼም ወደዚህ የተበላ ዕቁብ የሚገባ የሚኖር ካለ በርግጥም ንክር ነው፡፡ “የአበራሽን ጠባሳ ያዬ በእሳት አይጫወትም፡፡”አንገት የተፈጠረው ለምንድነው? ጥቂት እናስብ እንጂ፡፡
ውድ ወገኖቼ! የሰው ዘር በሙሉ አንድ ነው፡፡ መሳሳት ግን ያለ ነው – ጥንትም አሁንም፡፡ የተሳሳተን ማረምና ማስተካከል ተገቢና የሚጠበቅም ሆኖ ሳለ የጥፋትን መንገድ ተከትሎ መንጎድ ከሰውነት ተራ ያወጣል እንጂ ለማንም ለምንም አይጠቅምም፡፡ የመለስ ስህተት ለግደይ የጽድቅ መንገድ ሊሆን አይችልም፡፡ የአምባቸው ስህተት ለጌታቸው በማስተማሪያነት ካልጠቀመውና ይባስ ብሎም ስህተትን ከስህተት ተምሮ የቀደመን ስህተት አሻሽሎ በጥፋት መንገድ የሚጓዝ ከሆነ ሰው አንለውም፡፡ ገመቹ በፈይሣ ላይ ያየውን ስህተት አርሞና አስተካክሎ ካልተጓዘ በግብርም በፍጥረትም የግደይና የጌታቸው አባሪ ተባባሪ ነውና  መጨረሻ ላይ ከሚጠብቀው የቅጣት ግርፋት አያመልጥም፡፡ አንዱ ካንዱ በአወንታዊ መልክ ካልተማረ ሕይወት አሰልቺና የመጠፋፋታችን መንስዔ ትሆናለች፡፡ አንዳችን ከአንዳችን ካልተማርንና የአንዳችንን ጥፋት ሌላኛችን አርመን ካልተጓዝን የሰው መሆን ትርጉም የት ላይ ነው? ከአውሬ በምን ተለየን?
ሰው እንዴት የራሱን አእምሮ አይጠቀምም? ሲሸኑ እሚሸና፣ሲሮጡ እሚሮጥ፣ሲቆሙ እሚቆም… እንስሳ ነው፡፡ የራስን አእምሮ በመጠቀም ከሌሎች ጠንካራና ደካማ ጎን ተምሮ የራሱን ሕይወት እሚያስተካክል ግን ሰው ብቻ ነው፡፡ በሰው ስህተት ላይ የራሱን መርህ አጽድቆ የሚጃጃል ሰው ካጋጠመ ግን ሰው ሳይሆን እንስሳ ነው፡፡ ከቀሪዎቹ እንስሳት እንደምንሻል ማሳየት አለብን፡፡ እንደነዱሽ መሆን የለብንም፤ አያዋጠምም፡፡ ሰውን በዘውጋዊ ቀረቤታም ይሁን በፍቅርና በውዴታ በጭፍን ብንከተለው ዥው ወዳለ ገደል ሊከተን ይችላል፡፡
በጦሩ ውስጥ ያሉ የአመራር መኮንኖች በአሁኑ ሰዓት መልእክታቸውን ሌሎች ወገኖች እንዳይረዱት በትግርኛ ብቻ እንዳደረጉ በዜና እየተከታተልን ነው፡፡ ይህም ነገር የኛ ሁኔታ የሦርያን እየመሰለ መምጣቱን የሚጠቁም ነው፡፡ የሦርያውያን አላዊቶች ምንም እንኳን ከሌሎች ወንድምና እህቶቻቸው በቋንቋ ባይለያዩም በሰው ሠራሹ የሃይማኖት  ልዩነት ሳቢያ በተፈጠረው ችግርና ችግሩም በፈጠረው በኢኮኖሚና በፖለቲካ የበላይነትን የመሻማት ውድድር ጥቂቶች በብዙዎች ላይ ከሥርዓት ውጪ መፈንጨታቸው በቀላሉ ለማይወጡት ቀውስ ዳርጓቸዋል – ያን በሩቅ ያድርግልን፡፡ ጥቂቶች ሥልጣንንና ያን ሥልጣን ተከትሎ የሚገኝን ጥቅም በብዙኃን እንቀማለን ብለው ስለሚሰጉ ሁሉንም ነገር በራሳቸው ቁጥጥር የማድረግ ፍላጎት ያላቸው መሆናቸውን በሦርያና በኢትዮጵያ ወቅታዊ ተጨባጭ ሁኔተ ጠንቅቀን የምነረዳወ ነው፡፡ በዚያም ምክንያት ነው የሦርያና የኢትዮጵያ የጦርና አጠቃላይ የኢኮኖሚ አወቃቀር ከገዢው የአናሳ ብሔር ወይም ነገድ እንዳይወጣ ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ የምናየው፡፡ በዚህም ምክንያት ነው በሰሜነኞች የተሞላው የኢትዮጵያ ጦር ቋንቋ እስከመቀየር በሚደርስ ሥጋት ተወጥሮ ሌት ከቀን ሌሎች ወንድምና እህቶቹን የጦር አባላት በመሰለል እራሱንም እነሱንም እንቅልፍ በማሳጣት ላይ የሚገኘው፡፡ በጋራ ሀገር አንዱ ሰላይ ሌላው ተሰላይ፣ በጋራ ሀገር አንዱ እውነተኛ ልጅ ሌላው የእንጀራ ልጅ፤ በጋራ ሀገር አንዱ ባዕድ ሌላው ምሥጢረኛ የቤት ልጅ(እንኳን በተግባር እያየነው ሲያስቡት ራሱ እንዴት ይቀፋል ወንድሞቼ? …. የሆነበት ሁኔታ ከተፈጠረ በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት እውነተኛ ኢትዮጵያውያን ከጠቅላላው ሕዝብ ከስድስት በመቶ ላይበልጡ ነው ማለት ነው፡፡ ይህን አስከፊ ስዕል ለሁሉም ወደሚጠቅም በጎ አቅጣጫ  መለወጥ የሚቻለው ሁሉም ዜጋ ከሰማይ እየወረደ ካለው መብረቅ ጋር ሲተባበር ብቻ ነው፡፡ መብረቁ ቀጣይ ነው፡፡ ባለሣምንቶች እነማን ሊሆኑ እንደሚችሉም እንገምታለን፡፡ ዋናው ግን ቱባ ባለሥልጣናትም ይሁኑ ጩጬዎቹ ተራቸውን ጠብቀው የሥራቸውን ዋጋ የሚያገኙበት ጊዜ ላይ መድረሳቸውን ሁላችንም አጢነን ከተመሳሳይ ጥፋት ራሳችንን ለመታደግ ቆርጠን መነሳት ይኖርብናል፡፡ ትግርኛ ተናጋሪ ወገኖቻችንም እነዚህ የጥፋት ተልዕኮዎችን በቃችሁ ልንላቸው ይገባል፡፡ በስማችን እየነገዱና እያተረፉ እንዲኖሩ ልንፈቅድላቸው አይገባም፡፡ በርግጥ በቃ የምንልበት ጊዜ ካለፈ ብዙ ቆይቷል፤ ቢሆንም አሁንም አልመሸም፡፡ በጥፋት መንገድ የሚጓዙ እህትና ወንድሞችን በጋራ ሃይ እንበላቸው፡፡ በወንጀል ሥራቸው ቅጣት ከሞቱት ይልቅ ገና ወረፋቸውን እየጠበቁ ያሉት ይበልጣሉ፡፡ እስካሁንም እኮ እንደነአብዱል መጂድና ክፍሌ ወዳጆ በበሽታ ብቻ ሳይሆን ራሳቸውን በወገብ ሽጉጣቸውና በገመድ ሳይቀር አንገታቸውን ሲጥ እያደረጉ ያለቁ የወያኔ ባለሥልጣናት አሉ (ማን ነበር ቀደም ሲል ራሱን ሰቅሎ የገደለ ወያኔ የመገናኛና ትራንስፖርት ሚኒስትር? አየናቸው?)
አጫጭር ወቅታዊ መረጃዎች (አንዳንዶቹ ወሬዎች ተጨማሪ ማጣራት ያሻቸዋል፤ ነገር ግን እሳት በሌለበት ጭስ የለም ይባላልና ከእውነቱ ብዙም እንደማይርቁ መጠርጠር አይከፋም)
  1. ከ27 ዓመታት በፊት በ2ብር የገዛሁት መጽሐፍ ቅዱስ አርጅቶብኝ በቀደም ዕለት ልገዛ ብጠይቅ 180 ብር ተባልኩ
  2. ሰሞኑን የአንድ ኩንታል ነጭ ጤፍ ዋጋ 1900ብር ደረሰ – የመጨረሻው ቀይ/ጥቁር ጤፍ 1400 ብር (በየቀኑም ይለዋወጣል)
  3. የፈረንጁ ቀይ ሽንኩርት በኪሎ 13 ብር የሀበሻው 17 ብር ይሸጣል (የካ ሚካኤል አጠገብ ባለው የሾላ ገበያ)
  4.  አዜብ መስፍን ከጂ8 ስብሰባ ትንሽ ቀደም ሲል በባሏ በመለስ ላይ ሽጉጥ ተኩሳ ልትገድለው እንደሳተችውና ከዚያን ጊዜ ወዲህ ግንኙነታቸው እስከዚህም መሆኑን ሰማሁ
  5. በረከት ስምዖን  ከሀገር ሊወጣ ሲል ሰሞኑን በደኅንነት ሠራተኞች መከልከሉን ሰማሁ
  6. አምባሳደር ሥዩም መስፍን የመለስን ቦታ ለመተካት ከቻይና መምጣጡን ሰማሁ
  7. አዜብ መለስን እንዳላስታመመች፣ አሁን ከብዙዎች ባለሥልጣናት ጋር ሌባና ፖሊስ የድብብቆሽ ጨዋታ ላይ እንዳለች ሰማሁ
  8. በወያኔ ውስጥ ሁከትና ከፍተኛ ውዥንብር መኖሩን፣ ተለጣፊዎችም ነፍስ ለማወቅ ዳር ዳር እያሉ መሆናቸውን ሰማሁ
  9. ነጭ ሽንኩርት ከ90 እና 100 ብር ወርዶ 20 ብር መግባቱን፣ ድንችም ወደ 2ብር ከሃምሳ መውረዷንና የድሆችን ወስፋት ለጊዜውም ቢሆን  እየሸነገለች መሆንዋን ሰማሁ(ለምን መጥፎ ዜና ብቻ!) ቡና ግን እንደተሰቀለ ነው በኪሎ ከ80ብር በላይ – እኔ ኪሎውን በአንድ ብር የገዛሁበት ዘመን ነበር፡፡ የ3 ብሩ አንድ ግራም 18ካ. ወርቅም አሁን 700 ብር ገደማ ነው
  10. ከወያኔ ባለሥልጣናት ልጆች አብዛኞቹ – ገና ከሰባተኛና ስምንተኛ ክፍል ጀምሮ ያሉቱ -  ሀሺሻም፣ ጫት ቃሚዎችና  ሰካራም ሆነው የወላጆቻቸውን የደም ገንዘብ በከንቱ እንደሚጫወቱበት ሰማሁ (ከየሚማሩበት ምንጭ አለኝ)
  11. ብዙዎቹ የወያኔ ባለሥልጣናት ትዳራቸው የተበጠበጠና የትም … እንደሚያመሹና እንደሚያድሩ ሰማሁ
  12. የኤርትራው ፕሬዚደንትና ከፍተኛ ባለሥልጣናትም እንደኛዎቹ ሁሉ ትዳራቸውና ጤናቸው የተናጋ ክልፍልፍና ያልተረጋጋ  ሕይወት እንደሚመሩ – እንዲያውም የኢሳይያስ አፈወርቂ ባለቤት ሕጋዊ ፍቺ እንደጠየቀች  ከጌታቸው ረዳ ድረገፅ አነበብኩ (ሕዝብ/ሰው ጠላ እግዜር ጠላ – ወጣ ወጣና እንደሸምበቆ … ነው ነገሩ)፡፡ የሁሉም የቁልቁለት መንገድ ተጀምሯል፡፡
  13. ቤተ ክህነት በፓትርያርኩ ሞት ምክንያት እየታመሰች መሆንዋን በተለይም እጅጋየሁ የተባለችው የቀድሞዋ የማህሙድ አህመድ ሚስት የአባቷን መሞት ለማመን ባለመፈለግ ‹ውለዱልኝ፤ አልሞቱብኝም፤ እዬዬው› እያለች እያመሰቻቸው መሆንዋን ሰማሁ፤አነበብኩም፡፡ “አለዚያ ከግብጽ የገዛሁትን ቆብ ቀድጄ እጥላለሁ” በማለት ለያዥ ለገራዥ ማስቸገሯ ተያይዞ የደረሰኝ ዜና ያስረዳል – ‹ዱሮውን ያልቀደደችው ይመስል› የሚሉ አቃቂረኞችም አሉ ተብሏል – እዚያው አካባቢ፡፡
  14. የኢትዮጵያ ኦርቶደክስ ሃይማኖት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት አብዛኞቹ በፓትርያርኩ ዘመዶችና አጎንባሽ የጥቅም ተካፋዮች መያዟን፣ በአሁኑ ወቅትም በፓትርያርኩ ኅልፈት ሳቢያ መድረሻ ማጣታቸውን ሰማሁ
  15. በወያኔ ሥርዓት ብልሹነት ምክንያት አዲስ አበባና ሌሎች ከተሞች በተስፋ መቁረጥና በድህነት እንዲሁም የወር ገቢያቸው በቂ ካለመሆኑ የተነሳ  ዕብድና ሰካራም እንዲሁም ለማኝ፣ በረንዳ ተዳዳሪነትና ግልጽ ሽርሙጥና(ከ10 ዓመት ዕድሜ አካባቢ የሚጀምር ሴተኛ አዳሪነት) ከምን ጊዜውም በበለጠ  እየተስፋፋ መምጣቱን ታዘብኩ
  16. አጠቃላይ የሕዝቡ ኢኮኖሚያዊ ኑሮ ክፉኛ ተናግቶ አብዛኛው ከደላቸው ጥቂቶች በስተቀር አብዛኛው ሕዝብ ከጤፍ፣ ከሥጋ፣ ከማርና ከቅቤ … ምግቦች ተቆራርጧል፡፡ ሥጋ በኪሎ ሉካንዳ ቤት ከ100ብር ጀምሮ፣ ቅቤ ሊያውም ጥራቱ የተጓደለ ከ150 ጀምሮ፣ ማር ከ100ብር ጀምሮ፡፡ የዛሬ መቶ ብር በብዙ ገበያዎች የቀ. ኃይለ ሥላሤን አንድ ብር መሆን ካቃተው ሰነበትን፡፡ ስለሆነም ብዙው ዜጋ የቅቤ ቅሉንና የሥጋ ሞረዱን አርቆ አስቀምጧል እያሉ የሚናገሩ ወገኖች ትክክል ናቸው፡፡
ዝምዝማት
መንፈስ ቅዱስና ሙሽራይቱ  “ና” ይላሉ፤ የሚሰማም “ና” ይበል፤ የተጠማም ይምጣ፤ የፈለገም የሕይወትን ውኃ ያለምንም ዋጋ በነጻ ይውሰድ፡፡ …
      የእነዚህ ነገሮች ምሥክር የሆነው “አዎ፣ በቶሎ እመጣለሁ” ይላል፡፡
አሜን፣ ጌታ ኢየሱስ ሆይ ና!
የጌታ የኢየሱስ [ክርስቶስ]ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን፡፡
                                   የዮሐንስ ራዕይ፣ ከቁ. 17 እስከ 21

አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ! የዚህን ከሞራል፣ ከሃይማኖትና ከአስተዋይነት ጎዳና የወጣንበትን ዕኩይ ዘመን ዕድሜ አሳጥርልን! ሀገራችን ኢትዮጵያን ባርክ፡፡

No comments:

Post a Comment