Translate

Friday, August 31, 2012

በመለስ ሞት ምክንያት… ሰርግ ተሰረዘ፣ የቴዲ አፍሮ ኮንሰርት ተዛወረ፣ የምሽት ክለቦች ተዘጉ… ሌላስ?


(ኢ.ኤም.ኤፍ) የቀድሞውን ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊን ሞት ተከትሎ ከአዲስ አበባ አካባቢ የሚደርሱን ዘገባዎች በየ እለቱ የሚያስደምሙ ሆነዋል። ከደረሱን ዘገባዎች መካከል… ቴዲ አፍሮ ለአዲስ አመት በጊዮን ሆቴል ሊያደርገው የነበረው የሙዚቃ ዝግጅት ተሰርዟል፤ ላልታወቀ ጊዜ ተዛውሯል። በምሽት አዲስ አበባን ያዳምቁ የነበሩ ክለቦች ሙዚቃ ማጫወት ስለተከለከሉ፤ ደንበኞችም ስለሌሉ በራቸውን ለመዝጋት ተገደዋል። በአዲስ አበባ በየትኛውም ስፍራ የሚገኙ ሙዚቃ ቤቶች መሸጥ እንጂ ሙዚቃ ማጫወት ተከልክለዋል። ታክሲዎች እንደድሮው አዲስ የወጣ ዘፈን መክፈት አይችሉም። ዝርዝሩ በዚህ አይነት ይቀጥላል።
አንድ ነገር እንጨምር። አዲስ አበባ የሚገኘው ዘጋቢያችን የሰርገኞቹን ስም እንዳናወጣ ነግሮናል። ባለፈው እሁድ ስለሆነው ነገር እንዲህ አጫውቶናል። “ሰርገኞች እና ቤተሰብ ለሰርጋቸው ከአመት በላይ ሲዘጋጅ ቆይቷል። ለሰርጉ ስርዓት ማከናወኛም ጦር ኃይሎች ጋር የሚገኘውን የመኮንኖች ክለብ አዳራሽ በ13ሺህ ብር ተከራይተዋል። እናም የሰርጉ ቀን ከመድረሱ በፊት ቦታውን ለማዘጋጀት ሲሄዱ ሰርግ ማድረግ እንደማይችሉ ተነገራቸው።
ሰርግ ማድረግ አለመቻል ብቻ ሳይሆን፤ ገንዘባቸውም እንደማይመለስ መርዶ አረዷቸው። እንግዳ እንደጠሩና ምግብ እንዳዘጋጁ ቢናገሩም፤ ‘ድንኳን ጥላችሁ የምታደርጉትን ማድረግ ትችላላችሁ’ ተባሉ። አማራጭ ስለሌላቸው ሳይወዱ በግድ ሰርጋቸውን ድንኳን ጥለው አድርገዋል። በአንድ በኩል ሰፈራቸው እዚያው ጦር ኃይሎች አካባቢ መሆኑ ቢበጃቸውም፤ የሰርጉ እለት ግን የበለጠ አስገራሚ ነገር ተፈጠረ። ሰርጉ ከመደረጉ በፊት ካድሬዎች መጥተው የሰርግ ዘፈን እንዳይደረግ አስጠነቀቋቸው። ፖሊስም ድንኳኑን ከብቦ የሚሆነውን መከታተል ጀመረ። በመጨረሻ ከብዙ ልመና እና ልምምጥ በኋላ ሰርገኞቹ ብቻ ሲገቡ፤ ሰዉ “ሙሽራዬ የሚለውን ዘፈን ዘፈነ” ከዚያ በኋላ ከመብላት እና ከመጠጣት ውጪ ሰርጉ የሃዘን ቤት መስሎ ተጠናቀቀ።”

እንግዲህ የሰሞኑ የአዲስ አበባ ውሎ ይሄን ይመስላል። እራሳችንን ዝቅ ማድረጋችን የት እያደረሰን መሆኑን እናንተ ግምት ስጡበት። በዜናችን መጨረሻ ላይ አንድ ነገር እናክል። የቴዲ አፍሮ እና የአምለሰት የሰርግ ዝግጅት እንደቀጠለ ነው። በመጪው የኢትዮጵያ መስቀል ላይ፤ መስከረም 17፣ 2004 ዓ.ም. በሂልተን ሆቴል ሊደረግ ነው የታቀደው። ፓትሪያኩን ተከትሎ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ከመዝገብ ላይ ተሰርዘዋል። የሚሰረዙ ነገሮች እየበዙ ነው። የአዜብ መስፍን እህት ሰርግ በመስከረም ወር ላይ ነበር ሊደረግ የታቀደው። የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር በሚስጥር ሲሞቱ ሰርጉም በሚስጥር ተሰረዘ እና ለሰርጉ የተዘጋጀው ምግብና መጠጥ ሰሞኑን ሃዘነተኞች እየተሸኙበት መሆኑ ታውቋል። ከዚህ ሁሉ መሰረዞች በኋላ ግን፤ ለመስከረም 17 የታቀደው የቴዲ አፍሮ እና የአምለሰት ሰርግ እንዳይሰረዝባቸው በጸሎታችን እናስባቸው።

No comments:

Post a Comment