Translate

Monday, August 27, 2012

ወ/ሮ አዜብ በለቅሶ ላይ በሚወረውሯቸው ድንገተኛ ቃላቶች የተበሳጨው ኢህአዴግ ፣ ከካሜራ ቀረጻ ውጭ እንዲሆኑ አዘዘ::


ኢሳት ዜና:- (Aug. 28) የአቶ መለስ ዜናዊን እረፍት ተከትሎ ከፍተኛ የሆነ ድራማ እየሰራ ያለው ኢህአዴግ፣ ወ/ሮ አዜብ ከካሜራ ቀረጻ ውጭ እንዲሆኑ ለጋዜጠኞች ትእዛዝ ማስተላለፉ ታውቋል።
በተወሰነ ጊዜ ሰው በሚሰባሰብበት ሰአት ላይ ብቅ እያሉ የሚያለቅሱት ወ/ሮ አዜብ መስፍን፣ በድንገት በሚወረውሩት ቃላት ያልተደሰተው ኢህአዴግ ከካሜራ ቀረጻ ውጭ እንዲሆኑ ማድረጉን ታማኝ ምንጮቻችን ገልጠዋል።
ወ/ሮ አዜብ መስፍን በለቅሶአቸው ጊዜ የሚያወጡዋቸው ቃላቶች የኢህአዴግ ባለስልጣናትን ክፉኛ እያበሳጨ፣ በመካከላቸውም ጥርጣሬ እንዲፈጠር እያደረገ መሆኑን ነው ምንጫችን የገለጡት።
የአቶ መለስ ሁለተኛ ልጅ የሆነችው ማርዳ መለስ በበኩሏ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና የግል ሚዲያ ጋዜጠኞች እናቱዋን በሚቀርጹበት ሰአት የግል ጠባቂዎቿን ጠርታ ከቤተመንግስት ተገፍትረው እንዲወጡ ማስደረጉዋን የአይን እማኞች ለኢሳት ዘገባ ገልጠዋል።

የኢህአዴግ መንግስት የጠቅላይ ሚኒሰትሩን መሞት ለህዝብ ከገለጠ በሁዋላ በመላ አገሪቱ በእየቀበሌው ፣ የወረዳ መስተዳዳሮች እና መንግስታዊ ተቋሟት ሀዘናቸውን ጥቁር ልብስ እየለበሱ እንዲገለጡ የሚያንቀሰቅሷቸው የህብረተሰብ አባላት አሁንም በእየቀበሌው ከተተከለላቸው ድንኳን ባሻገር ቤተመንግስት ጎራ እያሉ እንዲያለቅሱ እወተወቱ ነው።
የመንግስት የመንግሥት ኮሚኒከሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የኮሙኒኬሽንና ሚዲያ ዘርፍ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞት በጋራ ሐዘናቸውን የሚገልጹበት ቀን ማዘጋጀቱም ታውቋል።  ከየሚዲያችው መሳተፍ የሚፈልጉ ሐላፊዎችና ጋዘጠኞች በጋራ ጠቁር ትሸርት በማሳተም እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቦላቸውዋል።
በማህበራዊ ድረገጾች ላይ የተበተኑ ደብዳቤዎች እና ኢሳት በእየአካባቢው የነጋገራቸው ሰዎች እንደሚያረጋግጡት ህዝቡ አሁንም የግዳጅ ለቅሶ እየወጣ ነው። በወላይታ ዞን ደረጃ የሚደረገውን የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ለቅሶ ይመለከታል በሚል ርእስ የተጻፈው ደብዳቤ ሲዘረዝር ” የኢትዮጵያ ብርሀን የሆኑት ክቡር ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ ከዚህ አለም በሞት በመለየታቸው ምክንያት በዞን ደረጃ ህዝባችን የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን መግለጽ እንድችል በሶዶ ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤት ፊት ለፊት በተዘጋጀው አደባባይ በተደራጀ ሁኔታ በመምጣት ሀዘናችሁን እንድትገልጹ እና እሁድ ከጧቱ 2፡30 ጀምሮ በዋላይታ ባህል ለንጉስ በሚደረግ ለቅሶ ስርአት በሶዶ ስታዲየም በሚዘጋጀው የውሎ ለቅሶ ስርአት ላይ መላውን የተቋማችሁን ማህበረሰብ በማስተባባር በተደራጀ ሁኔታ በተባለው ሰአትና ስፍራ በመገኘት የስርአቱ ተካፋይ እንድተሆኑ እናሳስባለን።” ብሎአል።
ኢሳት ያነጋጋራቸው እጅግ በርካታ ሰዎች በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሚታየው የአቶ መለስ ዜናዊ ለቅሶ ድራማ ነው ሲሉ አጣጥለውታል።
የህዝቡን አስተያየት በነገው ዝግጅት እናቀርባለን።
አዲስ አበባ በአሁኑ ጊዜ በንግድ ፣ በአገልግሎት ዘርፍ እና በተቋማት ስራ የተቀዛቀዘ ሲሆን የመንግስት ተቋማት ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት እየሰጡ አለመሆናቸውም ታውቋል።

No comments:

Post a Comment