Translate

Sunday, August 26, 2012

በኢትዮጵያችን የጨለማው ዘመን አብቅቶ የብርሃን ጎህ እንዲቀድ


አንዱ አምባገነን አልፎ በሌላው እየተተካ የመከራውና የችግሩ ዘመን ሳያቋርጥ ሕዝብ ፍዳውን ሲያይ የኖረባት ሀገራችንን የሚገዛው የዘመናችን አገዛዝ፣ በመለስ ዜናዊ ቁንጮነት የጨለማETHIOPIAN FLAGዕድሜውን ከጀመረ ሃያ አንድ ዓመት አለፈው። ይህ አምባገነን ቡድን በሥልጣን ላይ ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲን ተቀብያለሁ፣ እንዲሁም የሰብዓዊ መብትን አከብራለሁ እያለ ቢመጻደቅም፣ ይህ ሁሉ ከተፃፈበት ወረቀት በላይ የማያልፍ ለመሆኑ የአገዛዙ የሃያ አንድ ዓመታት እኩይ ተግባራት ምስክሮች ናቸው። የዛሬይቱ ኢትዮጵያችን በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብት መከበር ምትክ፤ የመሰብሰብ፣ የመጻፍ፣ የመናገር፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ፣ በአጠቃላይም ዜጎች ሃሳባቸውን በነጻነት የመግለጽና የመደራጀት መብቶቻቸው የታፈኑባትና የአንድ ፓርቲ አምባገነንነት የሠፈነባት፤ የፍትህ አካላት የዜጎችን ደህንነት ከመጠበቅ ይልቅ የመጨቆኛና የማፈኛ መሣርያ በሆኑበት ሁኔታ ላይ ትገኛለች።
አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ይህ የግፍ አገዛዝ ማብቃት አለበት፤ በሁሉ አቀፍ ዴሞክራስያዊ ሥርዓት መተካት አለበት ካለ ቆይቷል። ኢትዮጵያ በዚህ አስከፊ ሁኔታ ከቀጠለች፤ለግዛታዊ አንድነቷና ለሕዝቧ ሰላም፤ አብሮ መኖር፤ ዘላቂና ፍትሃዊ እድገት ያሰጋታል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህ አይነት አምባገነንነት እንዲቀጥል አይፈልግም፤ አይፈቅድምም የሚል እምነት አለን። የሕወሓት/ኢሕአዴግ አስከፊ አገዛዝ ቅንቅን እንደበላው ዛፍ በውስጥ ቅራኔና በሕዝብ ትግል ተገዝግዞ እንደሚገረሰስ አያጠራጥርም። ይህ መውደቂያው የተቃረበ አምባገነናዊ አገዛዝ ሌላው ቢቀር ለራሱ ሲል እንኳ የያዘውን አካሄድ መለወጥ እንዳለበት ሊገነዘብ ይገባዋል እንልላለን። የአገዛዙ ቁንጮ አቶ መለስ ዜናዊ ከዚህ ዓለም በሞት ከመለየታቸው ጋር ተያይዞ፤ ቀጣዩን የኢትዮጵያን ሕዝብ ተስፋ ብሩህ ለማድረግ አሁን በሥልጣን ላይ ላለው ፓርቲም ሆነ በጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ለተተኩት ለአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ልዩ አጋጣሚ ተፈጥሮላቸዋል። ይህ ለሁሉም ክፍሎች ሊጠቅም የሚችል እድል እንዳያመልጥ ያለውን ጨቋኝና ከፋፋይ የሆነ የአገዛዝ ሥርዓት ለመለወጥ ፈቃደኛና ቁርጠኛ መሆን አለባቸው እንላለን። ስለሆነም፤ አገራችንን ከአደጋ ለማዳንና እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመመስረት፤ ሁሉን ባካተተ ብሄራዊ ውይይት፤ የሥልጣን ምንጭ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ መሆኑ የሚረጋገጥበት ሥርዓት እንዲፈጠር የሚያስችል ሂደት እንዲጀመር እንጠይቃለን።
ለዚህ ለተቀደሰ ዓላማ አመቻች እንዲሆንና የኢትዮጵያ ሕዝብ በገዥው ፓርቲ ላይ እምነት እንዲኖረው ከተፈለገ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣኖች የሚከተሉትን እርምጃዎች ባስቸኳይ እንዲወሰዱ እንጠይቃለን።
1ኛ/ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን መፈናፈኛ ለማሳጣትና ማንም ዜጋ ሊኖረው የሚገባውን ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቱን ለመግፈፍ እንዲያመች ‘ሽብርተኛን ለመቆጣጠርያ’ በሚል የወጣው አዋጅ ባስቸኳይ እንዲነሳ፤
2ኛ/ ኢትዮጵያ በፖለቲካ ምክንያት ዜጎች የሚታሰሩባት ሀገር መሆኗ ባስቸኳይ እንዲያከትም ሁሉም የፖለቲካና የኅሊና እስረኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ፤
3ኛ/ የዴሞክራሲያዊ መብቶች ያለምንም ገደብ እውን መሆን አለባቸው። ዜጎች ሃሳባቸውን በነፃ የመግለጽ፣ የመደራጀት፣ ስብሰባ የማድረግ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የመውጣት ነፃነቶችን የሚገድቡ እንደ “የነጻው ፕሬስ መተዳደሪያ ሕግ” ያሉ ሕግጋት ባስቸኳይ እንዲነሱ፤
4ኛ/ ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ያለምንም ገደብ በነፃ የመንቀሳቀስ መብታቸው መከበር አለበት፤
5ኛ/ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርቲያን አባቶች፤ በቤተክርስቲያን አመራር፤ በፓትሪያርክ አመራረጥ ላይ የገዥው ፓርቲ የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት በሙሉ ማቆም አለበት፤
6ኛ/ የኢትዮጵያ ጥንታዊ የታሪክ ቅርስና የእምነታችን መገለጫ በሆነው በተቀደሰው የዋልድባ ገዳም ላይ በልማት ስም የሚካሄደው እምነትንና ታሪክን የማጥፋት ዘመቻ በአስቸኳይ እንዲቆም። ይህኑን የግፍ ድርጊት በመቃወም የታሰሩ አባቶችና ምዕመናን በአስቸኳይ እንዲፈቱ፤
7ኛ/ የእምነት ነጻነትን በመጻረር በእስልምና ኃይማኖት ላይ እየተደረገ ያለው ጣልቃ ገብነትና አፈና መቆም አለበት፤ በእስር ላይ የሚገኙት የምእመናኑ ተወካዮችም በአስቸኳይ እንዲፈቱ፤
8ኛ/ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳያውቀው አምባገነኑ አገዛዝ የሀገራችንን መሬት ቆርሶ ለሱዳን መንግስት ያስረከበበት ውል መሻር አለበት፤ አባቶቻችን ያስረከቡን የሀገራችን ድንበር እንዲከበር ይደረግ፤
9ኛ/ በልማት ስም ዜጎችን እያፈናቀሉ በነፃ ተሰጠ ሊባል በሚችል ደረጃ ለባዕዳን ከበርቴዎች የተቸበቸበው የሀገራችን ለም መሬት የኪራይ ውል እንዲሰርዝ፤ ከቀያቸው በግፍ የተፍናቀሉት ወገኖቻችን ድጋፍ ተደርጎላቸው በአስቸኳይ ወደ ትውልድ ቦታቸው እንዲመለሱ፤
10ኛ/ ከኢትዮጵያ ድሃ ሕዝብ ከህግ ውጭ እየተሰረቀ ወደ ውጭ አገሮች የሚላከው፤ በአመት በብዙ ቢልዮን ዶላር የሚገመተው ዘርፋ መቆም አለበት። የተዘረፈው የሕዝብ ሃብት እንዲመልስ፤ ዘራፊዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ፤
ውድ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ!
በስምህ እየተነሱ የራሳቸውን የግፍ አገዛዝ የሚጭኑብህን እምቢ በላቸው! በሀገርህ እንደ ዜጋና እንደ ሰው የሚገባህን መብትና ነጻነት የሚነፍጉህን እንደማትገዛ አሳውቃቸው! የአገዛዝና የጭቆና ዘመን መብቃት አለበት ብለህ በአንድነት ተነስ። በሃይማኖትህና በቋንቋህ ሊከፋፍሉህና የግዛት ዘመናቸውን ሊያራዝሙ የሚፈልጉትን ሁሉ ይበቃኛል፣ አትከፋፍሉኝ በላቸው! “ሀገር የጋራ ነው ፣ ኃይማኖት የግል ነው” የሚለውን ብሂል አትርሳ። ለመብትህና ለነፃነትህ ተነስ! እንደ አባቶችህ ሁሉ ለሀገርህ ድንበር ቁም። አጋጣሚ ተጠቅመው ሊያለያዩህና አገርህን ሊከፋፍሉ ለሚነሱ መሠሪዎች አትበገር።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት ሆይ!
ኢትዮጵያና ሕዝቧ በእናንተ ጥበቃ ሥር መሆናቸውን አትርሱ! ለሕዝብ ደህንነትና ለሀገርህ ድንበር መጠበቅ ቀናዒ መሆን ብሔራዊ ግዳጅህ ነው። የሕይወት መስዋእትነትን በመክፈል፣ የሀገሪቱ ድንበር እንዳይደፈር በቁርጠኝነት በመነሳት መዋደቅ ያንተ ግዳጅ እንደሆነ ሁሉ የሕዝብን ነጻነት፣ ደህንነትና ክብር የመጠበቅ የታሪክ ኃላፊነት እንዳለብህ አትርሳ። እንደ ሕዝብ አካልነትህ የሕዝብን እሮሮ አድምጥ። ለተጎዳውና ለተጎሳቆለው ወገንህ ደጀን ሁን። ሰብዓዊ መብቱ የተገፈፈው የኢትዮጵያ ሕዝብ በወገንተኛነት ከጎኑ እንደምትቆም እምነቱ መሆኑን አትርሳ። ጠብመንጃህ በሕዝብ ላይ እንዳይነጣጥር ለራስህና ለወገንህ ቃል ግባ፤ ይህን ባታደርግ ግን በታሪክና በመጭው ፍርድ ተጠያቂ ትሆናለህና። እኛም በጋራ ለፍትህ፤ ለነጻነትና፤ ለእኩልነት ትግል የቆምን ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች፤ የጊዜዉን አሳሳቢነት ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ጨቋኙ ስርዓት ከላይ በዝርዝር ያስቀመጥናቸውን የጭቆናና የግፍ ተግባሮች ባስቸኳያ እንዲያቆምና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እራሱን ለለውጥ ክፍት እንዲያደርግ እንጠያቃለን። በአንፃሩም በሀገራችን የሁሉም ዜጋ መብት፤ ፍትህ፤ እኩልነት፤ ነጻነትና ዴሞክራሲ የሚከበርበት ሁኔታ እስኪፈጠር ድረስ የጀመርነውን የጋራ ትግል በከፍተኛ ሁኔታ አጠናክረን የምንቀጥል መሆኑን እናሳውቃለን። ሕብረተሰቡም ጅምር የትግል ውጥናችን እንዲሳካ ከጎናችን በመቆም አስፈላጊዉን ድጋፍ ሁሉ እንዲያደርግልን እንጠይቃለን። እንዲሁም በውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ የተቃዋሚ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ከምንጊዜውም በላይ ኃይላቸውን ለጋራ ትግሉ አስተባብረው እንዲቆሙ በአጽንዖት እናሳስባለን።
ኢትዮጵያ ከወደቀችበት አረንቋ በልጆቿ መስዋዕትነት ትወጣለች!
ድል ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዝብ!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
ብሩህ ኢትዮጵያ ሕዝባዊ ንቅናቄ
የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ)
የኢትዮጵያ ብሄራዊ የሽግግር ምክር ቤት
የኢትዮጵያ አበይት ጉዳዮች መወያያ ሂደት
የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር (በጄ/ል ከማል ገልቹ የሚመራው)
የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ
ዓለም አቀፍ ሕዝባዊ ንቅናቄ ለለውጥ በኢትዮጵያ / በቃ
ጥምረት ለነፃነት ለእኩልነት ለፍትህ በኢትዮጵያ
Advocay for Ethiopia
Aug. 24, 2012

No comments:

Post a Comment