Translate

Saturday, August 25, 2012

የዘመነ መለስና የዘመነ ዘረኝነት ፍጻሜ


ከሳሙኤል ሽፈራው/ዳላስ
ላለፉት ሁለት ወራት በዚህ በውጭ ለምንኖር ኢትዮጵያውያን መነጋገሪያ ሆኖ የቆየው የመለስ መኖር አለመኖር ነበር። ኢትዮጵያውያን እንኳን ለሟች ቋሚን አክባሪ፣ የየትኛውምMeles Zenawi Ethiopian long time ruler died  ሀይማኖት አማኝ እንሁን ፈርሀ እግዚያብሔር ያለን ነን። እንደሌሎች አገር ባህሎች ከዚህ ጥፋትም ይሁን ልማት ለኔ ምን ይደርሰኛል የምንል ሳንሆን። ያለንን አመስግነን የምንኖር ነን። በእርግጥም ነጻነታችንን ጠብቀን የኖርን በመሆናችን የማንንም ባህል አልቀላቀልንም። እናም ለመጀመሪያ ለሚያየንም ሆነ ለሚገናኘን ሰው አክባሪነታችን፣ ከልስላሳ አንደበት ተቀላቅሎ አይነአፋር ያስመስለናል እንጅ ጨካኝ፣ ቂመኛና በቀልተኛ ናቸው ተብለን አንታማም።

ያም ሆኖ ሰሞኑን ለ21 አመታት በጉልበት አገራችንን ይዘው ያስተዳደሩን (የገዙን ይስማማል) ሰው አቶ መለስ መዳረሻቸው ከጠፋን ከሁለት ወራት በኋላ እለተ ሰኞ (ነሐሴ 14/2004 ዓ.ም) ህልፈታቸውን ያበሰረው ዜና ተሰማ። አከታትሎ ምናልባትም በሰው አገር ለሁለት ወራት የቆየው ግብናቸው አዲስ አበባ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ መድረሱን በተዘጋጀና ውብ ሆኖ ግዜ ተወስዶበት በተቀነባበረ ትያትራዊ አቀባበል በምስል አየን።
የምእራብ የዜና አገልግሎቶች BBC CNN NPR ሌሎችም በተቀነባበረ ዜና ድርሳን አቀረቡ። መንግስታትም ከያቅጣጫው የሐዘን መግለጫወቻቸውን መላካቸውን ሰማን። ነገርን ነገር ያነሳዋል። ለፕሬዜዳን ኦባማ ጥብቅ ተከራካሪ ነኝ (ከጓደኞቸ ጋር ስሆን ማለቴ ነው።) ባለፈው ምርጫ የኔንና የቤተሰቤን ድምጽ ከመስጠት ባለፈ አንዳቅሚቲ አንድ ሁለት ብየ በሁለት ጊዜ የምችላትን ያክል አድርጌ ነበር። ለነገሩ በዚህኛው ምርጫ እስካሁን ድምጼን እለግሳለሁ ከሚለው ያለፈ ባላግረግም፣ እስከዚህች ቀን የነበረኝና ያለኝ ውሳኔ የአንድ የስደተኛ ቤተሰብ ድምጽ ለመለገስ ዝግጁ ነብበርሁ። ታዲያ ይህ በዚህ እንዳለ። ፕሬዜዳንቱና የዜና አውታሮቻቸው አንድ በአንድ አፍ የሚናገሩ ይመስል አቀራረቦች ሁሉ ያሳጡባቸው ነበር። የዴሞክራሲ ተምሳሌ ነኝ የምትለው አገር መሪም ሆኑ ዜና ተንታኞች፣ ሟቹን አቶ መለስ ዜናዊን አገሩን ከችጋር አውጥቶ ነው ያለፈው፣ መልካምና ብሩህ መሪ ነበር አሉን። ለማን እንደሚናገሩ ባላውቅም። ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ያላቸውን ንቃቻ ግን አልሸሸጉንም። ቁጭ ብየ አሰብሁ። የአንደኛው ዜና ተንታኝ አባባል ከልክ ያለፈ ከንክኖኝ ከዚያ ሳላገግም የምወዳቸውና ምርጫየን የለገስኳቸው ፕሬዜዳንት፤ ያውም ግማሽ አፍሪካዊ ብሎም የጎረቤታችን የጆሞ ኬኒያታ አገር ልጅ እንዲህ እኛን ንቀው ለሚሰሟቸው የምእራብ ዜጎቻቸው ሲናገሩና የመለስ ማለፍ ለዩኤስ አሜሪካ ከባድ ጉዳት እንደሆነ ስሰማ ሀዘኔ ዲያቆን ዳነኤል ክብረት እንዳለው ለሟቹ ሳይሆን ለወገኖቸ፤ በፍርድ ሊጠየቁባቸው ለሚገባው ለነሽብሬ ደሳለኛ ሌሎች ወጣቶች፣ እንዲሁም ለዘመናት አንባገነንነትን ሲታገሉ በእኒሁ ሰው (መለስ) ተይዘው መዳረችሻቸው ለጠፋው ነበር። ያነን ባደረጉበት አገር። ሰንደቅ አላማ ጨርቅ ነው ባሉበት ( ለነገሩ አይገባም ከልክ እላፊ የሆነ ንግግር ነው ብለን ነበር። አነሰም በዛ ከሬሳ ሳጥናቸው ላይ ተላብሰውት የነበረው አገር ሲይዙ ያንቋሸሹት ጨርቅ ነበር) የመሀሉን ሰማያዊ አንባሻ ሳይጨምር ማለት ነው። እናም እሳቸውም ፍርድ ቤት እንዳመላለሷቸው ጋዜጠኞች። ከልጆቻቸው ነጥለው ወህኒ እንዲማቅቁ እንደሆኑት ወገኖች ሁሉ ተፈረድ ሊባሉ ሲገባ ሞት ቀደማቸው።
በምእራብ መንግስታትና ሚዲያወች የተሰጡ አስተያየቶች
እስቲ ላፍታ ወደ ምእራባውያኑ የሀዘን መግለጫወች ልመለስ። የሌላውን ኢትዮጵያዊ አስተሳሰብ ማወቅ አልችልም ግን እኔን ከልክ ያለፈ ያስደመመኝ ምን ያህል እኛን እንደሕዝብ እንደሚንቁን ነው። እናም እንዲወጣልኝ ልናገረው። የዩኤስ አሜሪካ የተባበሩት መንግስታት ማህበር ወኪል የሆኑት፤ ቀደም ብለውም ለአፍሪካ ምክትል እንደራሴ አንባሳደር ሆነው ያገለገሉት ሱዛን ራይስ “አቶ ዜናዊ ከበድ ያለ ውለታና የመልካም ስራ ውጤት ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለመላው የአፊካ ዜጋ ትተው አልፈዋል” ብለው ሲሳለቁ። የቀድሞው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጎርደን ብራውን “የዜናዊ ህልፈት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ቅስፈት ነው” ብለውናል። በስልጣን ላይ ያሉት የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስቴር በበኩላቸው “የአፍሪካ ልዩ የሆኑ አፈጉባኤ ነበሩ” ሲሉን። በቀጣይ የአለም ከፍተኛው ባለንብረት ቢል ጌት በበኩላቸው “ለኢትዮጵ ድሀ ጸጋን ያጎናጸፉ” ብለዋቸዋል።
ይህ ከላይ ያሰፈርሁት የሀዘን መግለጫና ጥቅሶች ያመላከተኝ ጉርሻ በሚሸጥበት ሐገርና የሚኖርን ታሪካዊ ሕዝብን ያንቋሸ። ብሎም ለጥቁር ሕዝቦች ሁሉ እኒህ ሐያላኑ ያላቸውን አስተሳሰብ የሚያሳጣ ፌዝ ነበር።  ይህን የአናሳ መንግስት በስልጣን መቆየት ምክንያቶቹ ምእራባውያኑ ከምንም ተነስተው ሳይሆን። ኢትዮፕያ ለአፍሪካውያን ነጻነት ስትል የእያን ስሚዝ ዘረኛ መንግስት የፒተር ቦታንና ቀዳሚ የሆኑ የደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ መንግስታትን የታገለች። በአለም አደባባይ ብቸኛ የጥቁር አፍሪካን ወክላ ቅኝ ግዛትን ከአሕጉራችን ለማስለቀቅ ያለመታከት የተዋጋች። ከፍ ሲልም በ1884 በበርሊን የተበየነውን አፍሪካን የመቀራመቱን ብይን በተግባር አድዋላይ በአራት ሰአታት ፍልሚያ አፈር ያለበሰች በመሆኗ። ከትውልድ ትውልድ ሲቀጣጠል የኖረን የዘረኝነት ቂም በቀል የተወጡበት ጊዜና ግለሰብ ከነድርጅቱ አንድ አቶ መለሰ ዜናዊ በመሆኑ። በእርግጥም ከፍ ያለ ክብር ሊለግሱት የሚገባ ነበር። አቶ መለስና ዘረኛው የፖለቲካ ድርጅታቸው የ84 ሚሊዮኖች አገርን የባሕር በር ያሳጣት አስተዳደርና፤ ለ21 አመታት ለዘመናት የታገልንለትን የመብት ጥያቄ አፍኖ፤ በግድያና በእስር ዜጎችን የሚያማቅቅ ስርአት ነውም ነበርም።
አንዳንድ የምእራብ አይነደረቅ ጋዜጦችና መሪወቻቸው ለደቡባዊው የአለም ሕዝብ ያላቸውን ንቃቻ ከመቸውም የመለስን ሞት ተንተርሶ በሰጡት አስተያየትና፣ በዘገቡት የዜና ዘገባ ማየት ችለናል። ከሁሉም እኔን መሰል ናቸው ለግፏን ይቆማሉ ያልናቸው ኦባማ የተናገሩት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ስድብ ነበር።
ጋዜጠኛ የደካሞች አቅምና ጉልበቱ ለሌላቸው አፍና ጆሮ ሆኖ የሚሰራ ሙያተኛ ነው። የጋዜጠኝነት ሙያ ግፈኞችን፣ ወንጀለኞችን ማጋለጥ ለተበዳዮችና ለግፏን አፈጉባኤ መሆን ነው። በመሰረቱ በዚህ ባሳለፍነው ሳምንት። ከሙያው ጋር ጨርሶ የማይገናኙ የውሸት ደላሎችን እንዳየንና እንደሰማን ሁሉ፤ እውነተኛ ጋዜጠኞችንም ተመልክተናል። ሚስተር ኦባማ አፍሪካ አንድ ታላቅ ሰው አጣች ባሉበት የዲፕሎማሲ አነጋገር።የአሜሪካ ድምጽ የእንግሊዘኛ ጣቢያ ሪፖርተር አኒታ ፖል ለአመታት ወደ ኢትዮጵያ ተመላልሳ ያየችውንና ከራሳቸው ከአንባገነኑ አንደበት ያገኘችውን ሙሉ የስራ ሪፖርት አቅርባለች። በዚህ ሪፖርት አኒታ ለ21 አመታት የምታውቃቸው አንባ ገነንና የዘር ድርጅታቸውን ስራና ተግባር፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ የከፈለውን የመከራ እዳና የ84 ሚሊዮኖች አገር ወደአለመኖር እድትሄድ የተዘየደውን መለስ/ወያኔአዊ ግፍ በሚገባ አስፍራለች።
ኤሪ በርነት የCNN አንከር በበኩሏ አዲስ አበባ ድረስ በመሄድ የዘገበችውን ሙሉውንhttp://www.youtube.com/watch?v=frNPQ-Sx8so&feature=youtu.be  ከዚህ ማየት ይቻላል። በትክክልም እንደዘገበችው ኢትዮጵያውያን በራሳቸው አገር እቀባ የተደረገባቸውና፤ መለስ ምንም ያህል የምእራብ ዳርሊንግ ይሁን እንጅ በሕዝቡ ላይ የጠነከረ አንባ ገነን እንደነበር ለአዳማጯ አቅርባለች። የቢቢሲው ማርቲን ፕላውት እንዴውም የወያኔ ስርአት በዘር የተመረኮዘ የከፋፍለህ አባላው መንግስት መሆኑንና መለስ የዚህ ስርአት ዲዛይነርነቱን በሚገባ አስነብቦናል። http://www.bbc.co.uk/news/world-africa-19332646
ኢትዮጵያ ከመልስ ሞት ማግስት
ሁለት ወራት የፈጀው ግርግር (በሐሳብ) ማለት ነው ተዘጋ። ወያኔወቹ ቁጭ ብለው መከሩ። ለሁለት ወራት ኳሷ የት ትወድቅ ይሆን ብሎ ይጠባበቅ የነበረው ተቃዋሚ ትናንት የነጠረችበትን ቦታ ተረዳው። ሁሉም አይኑ ወደተለይያየ አቅጣጫ ነበር። አሁን ግን ያው ተመልሶ ወደአንድ አቅጣቻ ሆነ። ሁኔታን ለመለወጥ ሳይሆን፤ ሁኔታው እንዲለውጠው የሚጠብቀው የኢትዮጵያ ተቃዋሚ፤ ከዚህ ምንም ሊያገኝ አይችልም። አንድ “ልጅ ተክሌ የሚባሉ ወጣት” በጻፉት ማሳሰቢያ የተቃዋሚ መሪወቻችን አቅጣጫ ሊያሳዩንና ግፉ ይሉናል ብለን ስንጠብቅ ነገርን ፈችና ትንቢት ተንታኝ ሆነው አገኘኋቸው ያሉት ተገቢ አነጋገር ነበር። የመለስ ዜናዊን ሞት መደበቅ የፈለጉት የሕወሐት አባላት፣ በተለየም አንድ የተወሰነ ክፍል ሐይል ሆኖ እየወጣ ሲሆን። የመገንጠልን ማኒፌስቶ ካወጡበት ጊዜ ጀምሮ የድርጅቱ አባት ይባል የነበሩትን አቶ ስብሐት ነጋን እና ሁነኛ መስራች አባላቱን ያላካተተ ጠበብ ያለ ስብስብ መንግስት መፍጠራቸው፤ ለዚያም አለሳልሰውና ከውስጥም ከውጭም ሊመጣ ይችላል ያሉትን ግፊት ቦታ ቦታ ካስያዙ በኋላ መሆኑ ነው። ይፋዊ በሆነ መልኩ የከንባታ ተወላጅ የሆነው አቶ ሐይለማሪያም ደሳለኝ የመለስን ቦታ የሚረከብ መሆኑን ሲያስታውቁ። በስውር መንግስታቸው ማለትም ሐይልና እውነተኛ ስልጣን በእጃቸው የገባው አምስት የሕወሐት (ወያኔ) አመራር አባላትና በኤርትራዊነቱና ላለፉት አመታት የዘር ፖለቲካን በማራመድ ብሎም ለብዙ ኢትዮጵያውያን ነፍስ መጥፋት፣ መታሰርና ዳብዛ መጥፋት ምክንያት ነው ተብሎ የሚነገርለት አቶ በረከት ስምኦን፣ እንዲሁም ታዬ ተክለሐይማኖት (በአሳሳች ስሙ ኩማ ደመቅሳ) እና አቶ ሐይለማሪያምን የጠቀለለ ነው።
ለሕዝብ ቀረበ በሚባለው መልእክት የአቶ መለስን የአምስት አመት ዘመን ለመጨረስ ምክትሉን አስቀምጠናል ቢባልም። ለሁለት ወራት ሬሳን ዲፕ ፍሪዘር አስቀምጦ ተቦክቶ ያለቀው ግን የሕወሐትን የበላይነት ለማስቀጠል የተዘየደ የሽግግር መንግስት (ሽግግሩ በትግራይ ስም የትቂት ዘረኛ ወያኔወችን የስልጣን የበላይነት ማስቀጠያ ሽግግር መሆኑ ነው።)
የተቃዋሚው ሚና ምን ይሆን?
ከላይ እንደአንድ ኢትዮጵያዊ ለማስተዋል የሞከርሁት ነገር ቢኖር፤ አሁንም እንደ 21 አመታቱ ሁሉ ሕወሐት የመንግስት ስልጣን ይዞ ለመቀጠል ማሰቡን ነው። የመለስን ሞት መደበቅና ወር አልፎ ሳምንታትን ማስቆጠር ሌላ ነገር ሳይሆን ጊዜ ወስዶ ያው ሕዝብና አገር ገዳዩን ዘረኛ ስርአት ለማስቀጠል የተሞከረ ነው።፡ይህ በቃ ሊባል ይገባል። ተቃዋሚ የሆነና የተደራጀ ሁሉ ይህን ስርአት ማስገደድ ይኖርበታል። ትግል መስዋእትነት ጠያቂ ነው። አያሌ የነጻነት ትግሎች መጠው ሄደዋል። አንዳቸውም አልጋ ባልጋ አልነበሩም።፡ደም ያፈሰሱ አጥንት የከሰከሱ ናቸው። እስካሁን ያልተቋጨው የሰሜን አፍሪካና የአረቡ አለም የዴሞክራሲ አብዮት ዳግም ያስገነዘበን የትግልን መራርነት ነው። በአገር ውስጥ ተደራጅተው ምርጫን መጠበቅ አግባብነት የለውም። የተነሳሳውን የሕዝብ ጥያቄወች ሲሆን መምራት አለያም ማገዝ ይጠበቅባቸው ነበር። ግን አላደረጉም።፡የሰላም ታጋይነት ወይንስ የስርአቱ አካልነት ነው?
በውጭ የተደራጁ የፖለቲካ ድርጅቶች ሊገነዘቡት የሚገባው አንድ ጉዳይ ትግሉም፤ ነጻነትና እኩልነት የሚፈልገውም ሕዝብ ያለው እዚያው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው።እናምንበታለን በሚሉት የትግል አሰላለፍ እዚያው፣ የሕዝብን ችግር ተቸግሮ። ሞቱን ሞቶ። በታጋይ ሊደርስ የሚችለውን መከራና ስቃይ ካልተቀበሉ እንዴት ነው ታገልን የሚሉት? ሕዝቡስ እንዴት ይመንና ይከተላቸው? አየር ባየር በሆነ ፖለቲካ ወረቀትና፤ የአጭር ሞገድ የራዲዮ ስርጭት ሊሆን ይችላል ብለው ካሰቡ ትልቅ ስህተት ነው። እዚህ ላይ እንዳይተረጎምብኝ ያስፈልጋል። የዛሬ አርባ አመት ገደማ በቦሌና በባሌ የሚል አበባል ነበር። እናም በቦሌ የገቡትም የሳት እራት ከመሆን ያመለጡ ትቂቶች ናቸው። በባሌ ያሉት በለስ ባይቀናቸው እና የጸረ ኢትዮፕያው ሐይል በደጋፊወቹ ብዛትና መጠን የበላይነት ባይወስድ ኖሮ፣ ድል አድራጊነታቸው እርግጥ ነበር። አንዳንድ ወገኖች ዛሬ ትናንት አይደለም ይሉናል። ሌሎቹ ደግሞ የነ እከሌን ድጋፍ ካላገኘን የማይሞከር ነው ብለው ተፈጽመዋል። እናም ሌት ከቀን አንጋጠው የሚመለከቱት ያገራቸውን ጫካና ዱር ሳይሆን የሌሎችን ደጀንነት ነው። ግን አንድ የኢትዮጵያ ታጋዮች ማወቅ የሚኖርባቸው ከተሞችም ወደጫካነት መቀየራቸውን ነው። ሕዝብ ጫካ ነው። በተለይ የተበደለ ሕዝብ ሊያታግለው የሚችል ካለ ዝግጁነቱን ካሳየ አመታት ተቆጥረዋል። ደግሞም በሊቢያ፣ በግብጽ፣ በየመን፣ ያየነው ትግል እንደነሆችሚንና ቸጎቬራ ተራራ ደብቀኝ የሚል አይደለም። ዛሬም በሶሪያ እያየነው ያለው ትንንቅ፣ ያመረሩ ታጋዮች እየሞቱ የጀመሩት ትግል አድጎና ተመንድጎ ስርአቱ በሜካናይዝድ ጦር እንዲዘምትበት ተገዶ ነው። የሰሜን አፍሪካው ትግል ጫካና ዱር በሌለባቸው የሰሐራ ምድረበዳ ከተሞች ተጀምሮ የተጠናቀቀ ነው።፡አዎ በአካባቢው ጥቅም ያላቸው ሐያላኑ ታጋይ ተነስቶ ካልጎረበጣቸው በጀ ሊሉን አይችሉም። አንዴውም አመለኞች ብለው እንዳይመዘግቡን እሰጋለሁ። መጎርበጥ ሲጀመር በነሱ ይብሳል። የዲፕሎማቶቻቸው እሩጫ ያኔ ነው። ልመናውና ማግባባቱ የሚታየው። የሕዝብ ጥያቄወችን ልብ ብለው የሚያዳምጡና ለእውነተኛ ምላሽ የሚገደዱት ማለቴ ነው።
ጎበዝ መታገል ከተባለ ለነገ ተብሎ ቀጠሮ የለም። ከዛሬ የተሻለ ጊዜ ስለሌለ መነሳት አሁን ነውና ተነሱ እንነሳ። መሪ ይምራ ተከታይም ይከተል። እኔ ለመከተል ዝግጁ ነኝ። እልፍ አእላፍ ዜጎች እንደኔው ይመስሉኛል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

No comments:

Post a Comment