Translate

Tuesday, August 28, 2012

ኃይለማሪያም ሆይ ቶሎ ና!


Abe Tokchaw
ኢትዮጵያን ላለፉት ሃያ አንድ አመታት የገዙት መለስ ዜናዊ አሁን በሞት የተነሳ ከስልጣናቸው ገለል ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሀዘን የሚገልፁ አንዳንድ ግለሰቦች ሲናገሩ “አንድ ቀን እንኳ ሳያርፉ… እንዲሁ እንደለፉ… አለፉ” በማለት ሲቆጩ ተመልክቻለሁ። ይሄ ነገር ነቀፌታ ነው ወይስ ውዳሴ ነው የሚለውን ለማወቅ ገና ጥናት እያደረግሁ ነው።
ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ 21 ዓመታት “ሀገሪቷን ከኔ በቀር የሚመራት የለም” በማለት በስልጣን ላይ ቁጭ ብለው መክረማቸው እኔ እንዳመላከተኝ ከሆነ ትልቅ ስህተት ነው። (ምንም ማድረግ አይቻልም ካመላከተኝ እንግዲህ መናገር ነው…) ከእርሳቸው ውጪ የሆኑ ሰዎችም ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን እንደሚችሉ ስልጣኑን ለቀው ቢያሳዩን ኖሮ ዛሬ ሲሞቱ ሰማይ የተከደነብንን ያኽል ባልተሰማን ነበር።  (እሺ ይሄንን እንተወው ሙት መውቀስ አግባብ አይደለም!)

አሁን በቅርቡ የጋናው ፕሬዘዳንት ሚልስ መሞታቸውን ሰምተናል። እኒህ ሰውዬ በጣም ዴሞክራት የሚባሉ ተወዳጅ መሪ ነበሩ። ልክ እርሳቸው እንደሞቱ ምክትላቸው ስልጣኑን ተረክበው ቃለ ማህላ ፈፅመዋል። ከዛም ህይወት እንደቀድሞዋ ቀጥላለች።
እኛም ዘንድ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት በይፋ ከተነገረ በኋላ አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ስልጣኑን ተረክበው ፓርላማው ተሰብስቦ ቃለ መሀላ ይፈፅሙ እና ይቀጥላሉ። ሲሉ አቶ በረከት ነግረውን ፤ ኢህአዴግን “ጎሽ የኔ አንበሳ” ብለነው ነበር። ነገር ግን አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ እስካሁንም ድረስ ቃለ መሃላ አልፈፀሙም።
ቃል አቀባዩ አቶ በረከት ስምዖንም ቃላቸውን አጥፈው “አሁን አስቸኳዩ ጉዳይ አቶ መለስን መሸኘት እንጂ መተካቱ አይደለም። አቶ መለስን ሰማኒያ ሚሊዮን ህዝብ ተክቶታል” ብለው ነግረውናል። (አደናግረውናል ከማለት ብዬ ነው)  ይሄንን በነገሩን ማግስትም “ተተኪ እንዳለው ባወቀ ሞት እንዲህ ባልተጨነቀ” የሚል የሀዘን እንጉርጉሮ በዜማ አሰርተውልን አየኮመኮምነው ነው። (በቅንፍም የግጥሙ ደራሲ እርሳቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠርጥረናል።)
የሆነው ሆኖ በአሁኑ ሰዓት ሀገሪቷ እየተመራች ያለችው በጠቅላይ ሚኒስትር ሳይሆን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ለቅሶ ነው። ይሄ ነገር እስከዚህ ሳምንት መጨረሻ ይቀጥላል። በዚህ መሀል የተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች እና የተለያዩ የመንግስት ስራዎች ይቀዛቀዛሉ። ይህም በሀገሪቷ ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም። እናም ብዙዎች ወደ መደበኛ ኑሯቸው መመለስ ሳይናፍቃቸው አይቀርም ብዬ እገምታለሁ። (መገመት መብቴ ነው!)
ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መደበኛ ፕሮግራሞቹን ከተወ አምስት ቀናት ተቆጥረዋል። “ልማታዊ” ዘገባዎቹን ርግፍ አድርጎ ትቶ ቅልጥ ያለ ለቅሶ ቤት ሆኗል። እንደውም አንዳንዶች ኢቲቪ ክፈት በማለት ፈንታ “ለቅሶቤቱን ክፈተው” ሲሉ ተደምጧል።
ይሄንን ጉድ አቶ መለስ ራሳቸው ቢሰሙ በጣም እንደሚያዝኑብን ምንም ጥርጥር የለውም። አሁን ሳስበው ይሄ ሁሉ የሆነው “ተዉ” ባይ በማጣታችን ይመስለኛል። ሁልጊዜም ሀዘን ላይ ሁሉም ሰው “አዛኝ” ከሆነ የሚፈጠረው ይሄው ነው። “ተዉ” ብሎ የሚቆጣ አንድ አካል ያስፈልጋል። ወይ ንስሀ አባት ወይ የሚፈራ አንድ ትልቅ ሰው፤ “አይ ምነው እቴ በቃ… የሞተ እንግዲህ አይመለስም እግዜሩም ሀዘን ማብዛታችንን አይወደውም” ብሎ የሚገስፅ የሆነ ሰው ያስፈልገናል። አቡነ ጳውሎስ ይህንን ስራ እንዳይሰሩ እርሳቸውም ማን ሞቶ ማን ይቀራል ብለው ሞቱ… የሙስሊሙ ኢማምም የሚያስጨንቃቸው የራሳቸው ቀጣይ ምርጫ እንጂ ይሄ አይደለም መሰል፤ ይሄንን ለማድረግ ሲተጉ አልታዩም። የሀገር ሽማግሌዎቹም ዋና “ሀዘንተኛ” ሆነዋል። ታድያ ማን ሃይ ይበለን? ማን ሀዘኑን በቅጡ አድርጉት ይበለን!? ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝም ተተክተው አልተተኩም!
ለዚህ ነው እንግዲህ ዛሬ ኃይለማሪያም ሆይ ቶሎ ና! ማለቴ። ለነገሩ ለዚህ ብቻ አይደለም። እውነቱን ለመናገር አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍቆኛል። በዚህ መልኩ ባይሆን ደስ ይለኝ ነበር። ግን እግዜር ካደረገው ደግሞ ከእግዜር ጋ አልከራከርም እናም አሜን ብዬ አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስቴር እየናፈቅሁ እገኛለሁ።
አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ መጥተው አቶ መለስ የጀመሩትን ሲያስቀጥሉ የተሳሳቱትን ሲያርሙ ለማየት ጓጉቻለሁ! ይችላሉ ብዬም አምናለሁ። ስለዚህም እላለሁ ኃይለማሪያም ሆይ ቶሎ ና!
ለህዝቤም እመክራለሁ!
“ምጡን እርሺው ልጁን አንሺው!”

No comments:

Post a Comment