ጊዜ የማያሳየን ነገር የለም፤ ትግስት ካለና አምላክ ከፈቀደ ደሞ የማይሆን ነገር የለም። እስኪ ራሳችንን ወደሗላ መለስ ብለን ሥድስት ወራት በምናባችን እንመለስና ጊዜን የሗልዮሽ እንቃኘዉ። በዚያን ግዜ እኔ ለዉጥ በምን ያክል ቅበጽነትና ሁኔታ ሊመጣ እንደሚችል አናዉቅም፤ ሰርገኛ መጣ ብለን ከምንሯሯጥ ተሰባስበን ለማናቸዉም አጋጣሚ እንዘጋጅ ብዬ ስናገር በርካቶች ሰዉዬዉ አበደ እንዴ ሲሉ ነበር። አንዳንዶቹ አስጠንቁሏል ሲሉ፤ ሌሎቹ ደሞ የሚያዉቀዉ ነገር አለ እያሉ በትንታኔ ዉድ ጊዜን አሳለፍን። ወደፊት ሄደን ዛሬ ላይ ቆም ብለን ያለፉትን ስድስት ወራት ስንመለከት ለማመን የሚያስቸግሩ ስንት ታአምሮች አየን። እኛ ስንዳክር አምላክ ግን ስራዉን ሰራና ታምራቱን አሳየን። እስኪ ስንቶቻችን ነን መለስ ለዚህ ይበቃል ብለን ቅንጣት እንኳን ጥርጣሬ የነበረን? የአቡነ ጳዉሎስና አጠቃላይ የሃገሪቱ ጉዳይስ? ሁሉም ነገር ፈጽሞ የማይታመንና እምነት ካለ የማይሆን ነገር እንደሌለ በተጨባጭ ያየንበት የበረከት ወቅትን አሳልፈናል። የዚህ ጽሁፌ አላማ ስለህልፈተ መለስ ወይንም አሁን እየታየ ስላለዉ ቴያትር ግለሰባዊ ትንተና ለመስጠት አይደለም። በአንጻሩ ግን ከጊዜዉ ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት ስለመጪዉ ሁኔታ እንደ አንድ ዜጋ ሚሰማኝን ለወገኖቼ ለማካፈል ነዉ።
ሁላችንም ሰሞኑን እየተከሰተ ካለዉ ሁኔታ በዉስጣችን እጅግ ብዙ የምናብሰለስላቸዉ ጥያቄዎች እንደሚኖሩ አያጠራጥርም። ለኔ ግን ወሳኙ ነገር ሰሞኑን እየተከሰተ ያለዉ ድራማ አይደለም። ወሳኙና ዋናዉ የሚያሳስበኝ እንዲያዉም የሚያንገበግበኝ ጥያቄ ግን የወደፊቱ ጥያቄ ነዉ። በዚሁ አጋጣሚ አንድ የፈረንጆች አባባል ታወሰኝ ይህም፡ ትንንሽ ሰዎች ስሌሌሎች ሰዎች ያስባሉ፤ መካከለኛ ሰዎች ስለ ክስተቶች ያወራሉ፤ ታላላቅ ሰዎች ግን ስለ ሃሳቦችና መርሆች፡ብሎም ስለወደፊቱ ያስባሉ ይላል። ስለራሴ ለመናገር ሳይሆን ሁላችንም በዚህ ግዜ ታላቅ ሆነን ስለወደፊቱ በማሰብና በመዘጋጀት በዚህ አምላክ በፈጠረልን ታላቅ አጋጣሚ እንድንጠቀምና ከዚህ በፊት እንዳደረኩት ሁሉ በድጋሚ ወገኖቼን ለመማጸን ወይም ለመለመን ነዉ። ከዚህ አንጻር በኔ እምነት በዚህ ግዜ ሁላችንም ከዚህ አለም ስለተለዩት ግለሰብ ወይም እየተሰራ ስላለዉ ቲያትራዊ ክስተት ሳይሆን ዋናዉ ጭንቀታችን የወደፊቱ መሆን እንዳለበት በአጽንኦት ማስረገጥ እሻለሁኝ። በኔ በእምነት አሁኑ ወቅት ሀገራችንና ሁላችንም በታላቅ መስቀለኛ መንገድ ላይ እንገኛለን። የአንድ ታሪካዊ ምእራፍ ተዘግቶ የሌላ ታሪካዊ ምእራፍ ተከፍቷል። አበዉ የፈሰሰ ዉሃ አይታፈስም እንዳሉት ስላለፈዉ ታሪክ ብናወራ ምንም ማድረግ አንችልም። ፋይዳም አይኖረዉም። በጥሩነቱም ሆነ በመጥፎነቱ የራሱን እንደምታ ትቶ አልፏል።
አሁን ቢበዛም ቢያንስም ጨዋታዉ አዲስ ሆኗል። ለምን እንደሆን ወይም ከየት እንደመጣ ባላዉቀዉም እኔ በዉስጤ የሚሰማኝ በጣም ብዙ መልካም ነገሮች በሀገራችን እንደሚከሰቱ ነዉ። በኔ እምነት እንዲሁም በተለያዩ ሁኔታዎች የተተነበየዉ ኢትዮጵያ እጆትዋን ወደ አምላኳ ትዘረጋለች የሚባለዉ ግዜ እዉን እንደሚሁን ቅንጣት ታህል ጥርጣሬ የለኝም። የሀገራችን ቅን ልጆች የሚነሱበት ግዜ ደርሷል። ክፋት፤ ምቀኝነት፤ ተንኮልና፤ ራስ ወዳድነት፤ በእዉነተኛ ሀገርወዳድ፤ ቅን ልጆችዋ ትግል የማይቀረዉ ታላቅ ሀገር የምንገነባበት ለዉጥ መምጣቱ አይቀሬ ነዉ። እመኑኝ በኢትዮጵያ የክፉዎች ዘመን እየጨለመ ነዉ። ለዉጥም የማይቀር ተፈጥሯዊ ሂደት ነዉ። እኛ ባንፈልገዉም አምላክ ምን ሊሰራ እንደሚችል በተጨባጭ አይተነዋል። ተሰጥቶ የማያልቀዉም ታምራቱና በረከቱ ወደፊትም ያለገደብ ይፈስልናል።
ይህንን እዉነታ በጭፍን አለመኖሩን ለማያምኑ፤ አምላክን ለማይፈሩ የዚህ ስርአት አራማጆች ግን አንድ መልክት አለኝ። ምንም ስርአት ዘላለማዊ አይደለም፤ ዘላለማዊ መንግስት የአምላክ ብቻ መሆኑንና ከዚያ በታች ግን ሁሉም ስርአት ለህይወታዊ ኡደት ህግ ተገዢ እንደሆነ ነዉ። ይህም ተፈጥሯዊ ሂደት ነዉ። ከዚህ አኳያ በኔ እምነት አሁን ያለዉ ስርአት በአራት ስነ ልቦናዊ ደረጃዎች ዉስጥ እንደሚያልፍ እጠብቃለሁኝ። እነዚህም በዝርዝር ሲቀመጡ፡
1. የሃዘን ጊዜ (grief phase)
2. የግርግር ግዜ (confusion phase)
3. የማጠናከርያ ጊዜ (consolidation phase)
4. የመምከኛ ጊዜ (decay phase) ናቸዉ።
የሀዘን ግዜን በተመለከተ ባሁኑ ሰአት ስርአቱ ምንም እንኳን አቶ መለስን ከድርጅት አኳያ ተለይተዉ አይታዩም እያለ ቢገዘትም ተወደደም ተጠላም ለአንድ ድርጅት፤ ሃያ አመትን ያስቆጠረ መሪ (figurehead) ለስርአቱ አይኑ፤ እፍንጫዉ፤ ጆሮዉ፡ ስሙ፤ ሀልዉናዉ፤ ባጠቃላይ ሁሉም ነገሩ፤ ከዚህም በላይ ለድርጅቱ ጭንቅላቱ በአጭሩ እናቱ፤ አባቱ፤ እንዲያዉም አሳነስኩት እንጂ አምላኩ ነበሩ። እንደማንኛዉም አባቱንና እናቱን የህልዉናዉን፤ ምልክት ብሎም የሚያመልከዉን እንዳጣ ስርአት ያዝናል፤ በተለይም ከታች ላሉ የስርአቱ አቀንቃኞች ሀዘኑ ታላቅ ነዉ የሚሆነዉ። ምክንያቱም የሁለንተናቸዉ መሰረት ተናግቷልና። አምላካቸዉና ጣኦታቸዉን አጥተዋልና። እንዲያዉ ስገምተዉ የሚያለቅሱት፤ በሲቃ የሚያነቡትም ስላለፉት መሪያቸዉ ሳይሆን ስለራሳቸዉ፤ ስለሰሩት ሃጢያታቸዉ፤ ብቻቸዉን በመቅረታቸዉ፤ ቀኑ ስለጨለመባቸዉ ይመስለኛል። ይህም ተፈጠሯዊ ስለቦናዊ ሂደት ስለሆነ ሊደንቀን የማይገባ ጉዳይ ነዉ። ከታች ያሉት ተራ ጀሌዎቻቸዉ በዚህ ሁኔታ ሲያሳልፉ መሪዎቻቸዉ ደሞ አንድ እንደሆኑ፤ ተሰፋ እንዳለ፤ አመራሩ በሁኔታዎች ላይ ቁጥጥር እንዳለዉ ለማሳየት የሚቻለዉን ሁሉ ድራማዊ ትወና እያከናወኑ የገኛሉ። ለህልዉናቸዉ ሲሉ ይህንን ቲያትር ማሳየት ይጠበቅባቸዋል።
መቼም ግዜ ባለበት ቆሞ አይቀርምና ቀብሩም ያልፋል ታላቁም ድራማ ያበቃል። አለባብሰዉ ቢያርሱ እንደተባለዉም ጊዜያዊዉ ድራማ ሲያበቃ ሁሉም ስለወደፊቱ ማሰብ መጨነቅ መጀመሩ የሰዉ ጥቅማዊና ተፈጥሮያዊ ባህሪ ኑዉና ይህንኑ መጠየቁ አይቀሬ ይሆናል። ማንም ጨቋኝ መሪ ሁሌም እንደሚያደርገዉ ተቀናቃኝ ባጠገቡ እንዲኖር አይፈልግምና እኒሁ መሪም ግልጽ የሆነ ተተኪ ባለማዘጋጀታቸዉ በመሪ ነኝ ባዮች መካከል ሽኩቻዉ መጀመሩ አይቀሬ ነዉ። በእርግጥ አሁን የድራማዉ አካል በሆነ ሁኔታ ም/ጠቅላይ ሚንስትሩ ስልጣን ተሰጥቷቸዋል። ግን ይህ ሂደት ተፈጥሯዊ ብሎም ህገ ማንግስታዊ ባለመሆኑ፤ እንደ ኢህአዴግ ላለ በአንድ ወገን ፈላጭ ቆራጭነት ሲመራ ለነበረ ድርጅት ህልዉናችዉን፤ ማንነትቸዉና ሚስጥራቸዉን፤ አሳልፈዉ፤ ለማያምኑት ግለሰብ፤ ብሎም ሌላ ብሄረሰብ፡ ሲብስ ደሞ ከነሱ ጋር መከራና ፍዳ ሳይቀምስ፡ ለመጣ ሰዉ በመስጠት እየተመሩ ይቀጥላሉ ብዬ ለማሰብ እጅግ ይከብደኛል። እርሳቸዉም እንደ ሰዉነታቸዉ ከዚያም እንደምሁርነታቸዉ ብሎም አማኝ ነኝ ባይነታቸዉ፤ ወንበር አሟሟቂ፤ ትእዛዝ ተቀባይ፤ ተላላኪ፤ ሆነዉ የመቀጠላቸዉ አዝማሚያ እጅግ የራቀ ይመሰለኛል።
ይህ ይሆናል ተብሎ ቢገመት እንኳን ሌላዉ ጥያቄ ማነዉ ከጀርባስ ሆኖ ትዛዙን ሚሰጠዉ? መቼም ጠ/ሚኒስትርነት እጅግ ዉስብስብ ስራ ይመስለኛል። እንኳን ሀገር ይቅርና ድርጅት መርተን የምናዉቅ ሰዎች የአመራር ሃላፊነት ምን ያክል ከባድ እንደሆነ እናዉቀዋለን። በእያንዳንዷ ደቂቃ ዉሳኔ መስጠት በሚያስፈልግበት ሁኔታና በተለይም እንደሀገራችን በሀገር ዉስጥ፤ በአካባቢያዊና፤ አለማቀፋዊ ዉጥንቅጥ ዉስጥ ላለች ሀገር በዚህ ግዜ አጣብቂኝ ዉስጥ መሆናቸዉ እኔ መቼም መጥኔ ለሳቸዉ እላለሁኝ። ከዚህ አንጻር በኔ ግምት በሚፈጠረዉ ዉጥረት አንዱ ጉልበተኛ ከበታች ያለዉን ሀይል በማንቀሳቀስ ያሸንፍና እርሳቸዉን በመጠምዘዝ በፈቃዳቸዉ አልያም በሃይል እንዲወገዱ ያደርጋል። ሌላዉ አማራጭ ደሞ ምንም እኔ ባይመስለኝም፤ እርሳቸዉ የደቡብ ፕሬዝዳንት በነበሩነት ግዜ ያካበቱትን ልምዳቸዉን ተጠቅመዉና ባለፉት ሁለት አመታት ወደ ስልጣን ጠጋ ጠጋ በማለታቸዉ የአቶ መለስን ያክል የስልጣን ጥማት ተፈጥሮባቸዉ ከሆነና በዚህ ግዜ ጎጠኛ የሆኑትን አንዳንዶቹን የህወሀት ተበዳይ መሪዎች ማማለል ከቻሉ፤ ለተወሰነም ጊዜ በስልጣን ሊቆዩ ይችላሉ። በኔ እምነት ግን ይህ ጉዞ ግፋ ቢል በፊታችን ካለዉ ምርጫ ሊያልፍ የሚችል አይመስለኝም። ምክንያቱም ህወሀት ስልጣን ልጓሙን አሳልፎ ለሌሎች አምኖ ይሰጣል ብዬ ለመቀበል በጣም ያዳግተኛልና።
ሌላዉ መገንዘብ ያለብን መቼም መለስ ብልጥ እንደሆኑና በሽታቸዉም ለሁለት አመታት ያዉቁት ስለነበር ምንም ዝግጅት ሳያደርጉ አልፈዋል ብሎ ማሰብ የዋህነት ይመስለኛል። ቁልፉ ግን የዚህ የዝግጅት ሂደት ባለመጠናቀቁ በሂደቱ ዉስጥ ቅሬታ የነበራቸዉ ወገኖችም የሚጫወቱት ሚና ወሳኝ ነዉ የሚሆነዉ። ነገሩን ለማጠቃለል ያክል ስርአቱ ከለቅሶ ጊዜ በሗላ የግርግር የትርምስ የዉድድር ጊዜ ዉስጥ መግባቱ ሳይታለም ተፈታ ጉዳይ ነዉ። ፈረንጆቹ እንደሚሉት በፖለቲካ ቀመሩ (equation) ላይ በርካታ ዉስብስብ ግብአቶች (variables) ጭንቅላታቸዉ መዞሩ አይቀሬ ነዉ። ለዚህም የመስለኛል አንዳንዶች ምእረብያዉአን ሳይቀሩ አሁን ማንግስት የለም ብለዉ እየተጨነቁና ከጥቅማቸዉ አንጻር ሁኔታዎችን በቁጥጥራቸዉ ስር ለማዋል ሚፍጨረጨሩት። ይህም ጊዜ ላገራችን እጅግ ወሳኝና ፈታኝ በተለይም አጋጣሚዉን መጠቀም ለሚሹት ተቃዋሚ ሀይሎች ወሳኝ ጊዜ የሚሆነዉ። በዚህ የፖለቲካ ጡዘት ዉስጥም ህዝቡና ተቃዋሚዎች መግለጫ ከማዉጣት ያለፈ ቁልፍ ሚና መጫወት ይጠበቅብናል። የሃይል ሚዛኑንና የፖለቲካ ጨዋታዉን ወደ ሚፈለገዉ አቅጣጫ ለመቀየር በሳል ሆን የመሪነት (proactive) ድርሻ መወጣት አለብን።
ይህ ከላይ ተዘረዘሩት ሂደቶች ፈረንጆቹ እንደሚሉት አቧራዉ ከረገበ በሗላ (after the dust settles down) የመረጋጊያ ዘመን ይመጣል። የዚህም ዘመን ባህርይ ባሸናፊዉ ወገን ማንነት ይወሰናል። አምላክ የጀመረልንን እኛ መጨረስ ካቃተን ጽንፈኛዉና ጨቋኙ ወገን አሸንፎ ህዋት ከአሁኑ በበለጠ ሁኔታ ፋሽሽታዊ ሆኖ ለተወሰነም ጊዜ ቢሆን ተረጋግቶ ይወጣል - አምላክ ይህንን አያሳየን። በአንጻሩ ግን ህዝቡና ተቃዋሚዋች ነጻነትን ከልባችን የምንፈልጋት ከሆነና ይህንን አምላካችን የከፈተልንን ለመጨረስ ቆርጠን ከተነሳን ዉጤቱ ዉብ ይሆናል። የታላቅ ሀገር የታላቅ ዘመን ምእራፍ ይከፈታል።
አንድ ነገር በእርግጠኝነት የምናገረዉ ግን ህወሀት ከዚህ በሗላ በፍጹም የቀድሞ ህወሀት እንደማይሆን ነዉ። ጽንፈኛዉ ቡድን አሸናፊ ሆኖ ቢወጣ እንኳን በዉስጡ በሚፈጠረዉ የአንጃዎች ሽኩቻ እንዲሁም ከህዝቡና ከተቃዋሚዎች በሚደርስበት እንግልት ብዙም መዝለቅ እንደማይችል አልጠራጠርም። መለስ ምስጋና ይግባቸዉና የስልጣን ገብጋባነታቸዉ ከፍተኛ ክፍተትን ፈጥሮልናል። ለዘመናት የገነቡትን የጭቆና ድርጅታቸዉን በስስታምነታቸዉና በሞታቸዉ እንዳይሆን አድርገዉ በትነዉታል። ህወሀትም በዚህ ሂደት ያረጃል፤ ይጃጃል የማይቀረዉን ተፈጥሮአዊ ሞት ይሞታል። አልያም የብልህነትንና የአርቆ አስተዋይነትን መንገድ መርጦ እራሱን ቀይሮ ከጊዜዉ ተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር አመሳስሎ (adapt አድግጎ) የቀጥላል። እኔ እናንተን ብሆን የሁለተኛዉን መንገድ መርጬ ራሴን አስተካክዬ ለአምላክና ለህዝብ ፍላጎት ተገዝቼ የድርጅቴንና የአባሎቼን ህልዉና አረጋግጩ እቀጥላለሁኝ። ይህንንም መንገድ ለመምረጥ ኳሷ በሜዳቸሁ ነች። በአንፃሩ አማራጩን አይታችሁታል፤ ህዝብ አቅም ቢያንሰዉ፤ አምላክ ከጎኑ ነዉ። እርሱ ምን ሊያመጣ እንደሚችል በተግባር አሳይቷችሗል፤ ከእርሱ ጋር መዋጋቱን ከመረጣችሁ ግፉበት መንገዱን ጨርቅ ያርግላችሁ። እኔ ግን እንደ ፀሃይ ብርሃን ፈክቶ የሚታየኝን ሃቅ ልንገራችሁ፤ የቅኖችና፤ አምላክን የሚፈሩ፤ ኢትዮጵያዉያን ዘመን ቀርቧል፤ ይፈቀማልም፤ በትንቢቱም መረሰት ኢትዮጵያ ሀገራችን እጆችዋን ወደ አምላኳ ትዘረጋለች፤ ታላቅም ሀገር ትሆናለች። እኛም በሱ ተስፋ አለን። እንደሚሆንም ስለምንተማመን ሁሌም አሸናፊዋች ነን። አሜን።
No comments:
Post a Comment